በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን ሙስና አሳሳቢነት «ሌብነቱ ቅጥ የለውም» ሲሉ ገልጸውታል።
እውነታቸውን ነው። ነፍስ ዘርቶ ተንቀሳቅሶ መንግሥትን ጠልፎ የጣለው ሌብነት ዛሬም ፈተና ሆኗል። ይህ ለምን ሆነ? አንዱ መልስ የተከተልነው የኢኮኖሚ መስመር ይመስለኛል።
የኢኮኖሚ ሊቃውንት ሌሎች የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ሕዝብን አደኽይተዋል ብለው የፈጠሩት ካፒታሊዝም በተለይ እንደ አገር በሀብት ፈጠራ ረገድ ያስመዘገባቸው ስኬቶች ቢኖሩም፣ ጥቂቶችን ፍጹም የማይደረስበት የሀብት ማማ ላይ የሚሰቅል፣ ብዙኃንን ደግሞ ከድህነት ወለል በታች የሚጥል ሥርዓት ነው።
ይህ በመላው ዓለም የታየ ነው። ለዚህ ቀላል ምሳሌ ለማቅረብ ያህል በፈረንጆቹ 2020 በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስብሰባ ላይ ኦክስፋም ባቀረበው ሪፖርት በዓለም ላይ ያሉ 2ሺ153 ባለሀብቶች ያላቸው የሀብት መጠን ከዓለም ሕዝብ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮኑ ካለው ድምር ሀብት መብለጡ ነው።
ከሶቪየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ ካፒታሊዝም ብቸኛው ዓለምአቀፍ የኢኮኖሚ መስመር ሆኖ ቀጥሏል፤ ኢትዮጵያም ለግሉ ዘርፍ በሯን በመክፈት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ቀስ በቀስ ወደ ግል በማዞር በዚህ የኢኮኖሚ መስመር ውስጥ ገብታለች። ይህ ችግር የለውም።
የኢኮኖሚ መስመር በርካታ ባለሀብቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፤ ባለሀብቶቹ የተፈጠሩበት መንገድ ግን በአብዛኛው ጤነኛ አይደለም።
የአብዛኛው የሀብት ምንጭ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው። ይህ አላግባብ የተጀመረ የባለሀብትነት ጉዞ ጥቂቶች በአንድ ጀንበር ከድህነት ወደ ፍጹማዊ ሀብታምነት እንዲመነጠቁ አደረገ፤ በእነሱና በተራው ሕዝብ መካከል ያለው ልዩነት ሰፋ። ይህ ሁኔታ በዘመነ ኢህአዴግ በእጅጉ ተንሰራፍቶ ሀብታምነት አገራዊም ቡድናዊም ግለሰባዊም ራእይ ሆነ።
ተሰርቶ ከሆነ ችግር የለውም። በዘረፋ ለእዚያውም በተቋማዊ ዘረፋ የሚገኝ መሆኑ ነው የሚያሳስበው። ኢትዮጵያ በ30 አመት 30 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ አግኝታ 30 ቢሊዮን ዶላር የተዘረፈባት ጉደኛ አገር የሆነችውም በእዚሁ የኢህአዴግ ዘመን ነው።
ባለሥልጣናት እና ከነሱ ጋር የተዛመዱ፣ በእከከኝ ልከከልህ የተሳሰሩ ሁሉ ከመቅጽበት ሚሊየነር ሆኑ። በአገራዊው ለውጥ መጀመሪያ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የተደራጀ ዘረፋ ሲሉት የነበረውን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል።
ዘረፋው የተካሄደው ደግሞ ግዙፍ የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ተቋም ተቋቁሞ ባለበት ዘመን መሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያጎላዋል። ይህ ሌብነት ቀስ በቀስ አድጎና በልጽጎ ገዢው ፓርቲ ራሱ የፈጠራቸው እና «ልማታዊ ባለሀብት» እያለ ሲያሞካሻቸው የነበሩ ባለሀብት ወሮበሎች መልሰው ራሱን ይውጡት ያዙ።
መንግሥት አንድ እጄን ታስሬ ነው ከነሱ ጋር የምጫወተው በማለት ከአቅም በላይ እንደሆኑበት እስከ መግለጽ ደረሰ።
ከለውጥ በፊት ኢህአዴግ አካሄድኳቸው ይላቸው በነበሩ «ጥልቅ ተሀድሶዎች» በሙሉ የችግሩ ምንጭ የመንግሥት በኪራይ ሰብሳቢ በባለሀብቶች መጠለፍ (state capture) እንደሆነ ይነገር ነበር። ማንም ግን እነ እገሌ ሌቦች ናቸው ለማለት አልደፈረም።
ለኢህአዴግ መውደቅ ከዋነኛ ምክንያቾች አንዱ የሆነው ሌብነት የኢህአዴግ ችግር ብቻ ሆኖ አልቀረም። ከአገራዊው ለውጥ በኋላም ብልጽግና ስልጣኑን ይዞም ሌብነት አይሏል፤ ሌቦች የሚያቆማቸው አጥተዋል።
በቅርቡም የፓርላማ አባላት ሙስና በአገሪቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስገንዝበዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህን አምነዋል። «ቂምና ሌብነት የቁልቁለት ጉዞአችን መነሻ ነው።» ብለዋል። እውነት ነው፤ ሌብነት ኢትዮጵያን ቁልቁል እየነዳት ነው። ሆኖም ብልጽግናም ቢሆን ኢህአዴግን ከገደለው በሽታ የሚታደገውን ክትባት አልወሰደም። ሙስናን ለመታገል ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ውስጥ ካልገባ ማለት የሚቻለውም ይህንን ነው። ሙስናው ይበልጥ ስለታም ሆኖ መገኘቱም ይህንኑ ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ «ባለስልጣንን ሌባ ማድረግ የሚፈልጉ ባለሀብቶች አሉ» ብለዋል። ይህም ማለት መንግሥት የመጠለፍ እና የሕዝብ ሳይሆን የባለሀብቶች ጉዳይ አስፈጻሚ የመሆን አደጋ አለበት ማለት ነው። በእዚህ ላይ እኔ የማክለው አለ። ባለሀብቶችን ሌባ የሚያደርጉ ባለስልጣናትም በርካታ መሆናቸውን ነው። ለተራ ጉዳይ ጭምር ጉቦ ይጠይቃል እኮ፤ በሙስና የተጠረጠረ ባለስልጣን ወይም ሠራተኛ ማረሚያ ቤት ሲጠበቅ ሌላ የተሻለ መስሪያ ቤት እና ክፍል ተቀይሮለት ይገኛል።
እናስ ሙሰና ለምን አይስፋፋ? የሙስናው ጉዳይ ያሳሰባቸው መንግሥት እየሠራ ካለው አመለካከትን የመግራት እና ሕግ የማስከበር ሥራ ባለፈ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያዎች የምርመራ ዘገባዎችን እንዲሠሩ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ እኔ በአመለካከት በኩል እየተሠራ ያለው በቂ ነው ብዬም አላምንም። መንግሥት ሠራሁት የሚለው የአመለካከት ለውጥ በመሬት ላይ አይታይም።
ሙስናውን በሕግ አግባብ የመቆጣጠሩ ሥራም ቢሆን የሚጨበጥ ለውጥ አልታየበትም። ሕግ የማስከበር ሥራው ተግባራዊ ሲሆን ይታይ የነበረው አንድም በፖለቲካ አካሄዳቸው መስመር በሳቱ ሰዎች ላይ ነው፤ ለመጥለፊያ።
ከዚያ ውጭ ሌቦችን አነፍንፎ ለሕግ በማቅረብ ላይ ተጨባጭ እርምጃ ታይቷል ለማለት ያስቸግራል። እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለመፍታት ኃላፊነቱ የተሰጣቸው እንደ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ (የአሁኑ ፍትህ ሚኒስቴር) ያሉ ተቋማት ከችግሩ ስፋት አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል እርምጃ ሲወስዱ አልታየም።
መንግሥት ሙስና አሁንም አብይ ችግሬ ነው እያለ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። በዘመነ ኢህአዴግ አንድ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ዋና ባለስልጣን በምርጫ 97 ማግስት ይመስለኛል ክልል ላይ የመንግሥት ሀብት ባክኗል ብለው ለፓርላማው ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በክልል በጀት ውስጥ ምን አገባው፤ ሲፈልጉ ሊያቃጥሉት ይችላሉ ብለው ነበር።
ኢህአዴግም እንዲህ ዓይነቱን የመሪ ንግግር ባይሰማ ኖሮ ውድቀቱ እንዲህ የከፋ አይሆንም ነበር። አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚዲያ በሚካሄድ የምርመራ ዘገባ ሙስኞችን ለማጋለጥ እና ለመታገል ውሳኔ ላይ መደረሳቸው አንድ ጥሩ እርምጃ ነው።
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱም ይህን የአገር እና ሕዝብ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ራሳቸውን ዝግጁ አደርገው ወደ ሥራው መግባት ይኖርባቸዋል። ሆኖም ሙስናው የገነገነ መሆኑ ስር ነቀል ሥራን የሚፈልግ ነው።
እዚያው ድረስ ግን የሚዲያው አማራጭ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከልና መቆጣጠር የሚሠሩ መንግሥታዊ ተቋማት ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ እንደ ማንቂያ ደወል ሊጠቀሙበት ይገባል። ከዚያ ባለፈ እኔ ለፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አድናቆቱ አለኝ።
አሁንም የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትም ይሁን በክልል ደረጃ ያሉ ተመሳሳይ ተቋማት ጠንካራ ክትትል በማድረግ እና ያልተሸፋፈነ ሪፖርት ለምክር ቤቱ እና ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጆሮዎቹን ወደ ሕዝቡ አድርጎ፣ በሩንም ከፍቶ መረጃዎችን በመሰብሰብ ድምጹን ማሰማት መጀመር ይኖርበታል።
ቀድሞ በፌዴራል ሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ይሠራ የነበረው ሙሰኞችን የመመርመርና የመክሰስ ኃላፊነት የተሰጠው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይጠበቅበታል። ትንንሾቹን ዓሣዎች ብቻ ሳይሆን ትልልቆቹን ዓሣ ነባሪዎችም መያዝ ይኖርበታል። የሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንና ሌሎችም እንደዚያው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን የካቲት 26 /2014