በአጼ ምኒሊክ መሪነት አድዋ ላይ ያገኘነው ድል ብዘሃነታችን ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ህልውናችንንም ጭምር ያስከበረ ድል ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን የጣሊያንን የነጭ ሰራዊት ዓድዋ ላይ በማሸነፋችን በጥቁር ዘር ላይ ነጮች የደገሱትን የጥፋት ድግስ በማቆም የአለም ታሪክ ይሄድ የነበረበትን አደገኛ አቅጣጫ አስቀይረናል ። መልካም 126ኛው የዓድዋ ድል በዓል። ዋንጫችንን ለምኒሊክ ከፍ እናድርግ!
የዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ሶማሌነት፣ ጉራጌነትና ወዘተ የተረፈው ዓድዋ ምድር ላይ ኦሮሞ፣ አማራውም፣ ጉራጌው፣ ትግሬውና ወዘተ ደሙን በጋራ አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ ነው።
የእምነት የቋንቋ የባህል ልዩነታችን የድክመታችን ምንጭ ሆኖ፣ ዓድዋ ላይ በጋራ ተሰባስበን ጣሊያንን ማሸነፍ ባንችል ኖሮ፣ ዛሬ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግራዋይነት፣ ሲዳማነትና ወዘተ የሚባል ነገር አይኖርም ነበር።
ክርስትና፣ እስልምና፣ ዋቄ ፈታ፣ አክሲዮን ጽዮን፣ ላሊበላ፣ አልነጃሺ፣ እሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ገዳ፣ ቡሄ፣ አሽንዳ፣ አተቴ፣ ሌሎችም በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጥ የሚገኙ ድንቅ የእምነት የባህል እሴቶቻችን አይኖሩም ነበር። የሺ ዘመናት እድሜ ያላቸው የተዋህዶ ክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት መትረፍ የቻሉት ክርስቲያኑ ከሙስሊሙ ጎን ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ጎን ዓድዋ ላይ ወድቆ ነው።
እሬቻ የተረፈው፣ እሬቻ ዛሬ በአል ሆኖ የሚከበረው ኦሮሞና አማራ አንድ ላይ ከሌሎች የሃገሪቱ ሕዝቦች ጋር በጋራ ጣሊያንን ዓድዋ ስለሰበሩት ብቻ ነው። የዘመኑ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን እንደሚሉን ኦሮሞው አማራውን ወይም አማራው ኦሮሞውን ሰብሮት ቢሆን ኖሮ እንኳን እሬቻ ሁላችንም አንኖርም ነበር። አማራና ትግሬ ብቻቸውን ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ገጥመው ተሸነፈው ቢሆን ኦሮሞነት አይኖርም ነበር።
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በመቶ ሚሊዮኖች ተከታዮች ያሏቸው፣ ታሪክ የራሱን የዘመናት አሻራ ያሳረፋባቸው፣ ከማንነታችን ጋር የተጋመዱ የክርስትና እና የእስልምና ልዩ እምነቶች አሉን። ዓድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ እምነቶቻችንም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ወይም እስልምና ወይም ዋቄ ፈታ ወይም ሌላም ሃገራዊ እምነት መሆኑ ቀርቶ ጣሊያኖች የሚጭኑብን የጣሊያኖች እምነት ብቻ ይሆን ነበር። ከዛም በታች ተዋርደን ሁሉም ቀርቶ “ደግሞ ለባሪያ የምን እምነት” ተብለን እንደ ውሻ በቤተእምነት ደጃፍ ላይ እንዳንደርስ እንደረግ ነበር።
ስማችን ኦኬሎና አርዬት፣ ለሜሳና ጫልቱ፣ ሃጎስና ሃዳስ፣ሃሰንና ዘይነብ፣ ሃይለ ሚካኤልና ወለተማርያም፣ አንበርብርና ተዋበች፣ ዘበርጋና ኬርየዢ፣ ኤራቶና መፋያት፣ በርገኖና ጫኪሴ፣ ገቲሶና ሚሸሜ፣ ግሽና እና አቸም፣ ወዘተ የሚል ሆኖ የምናገኘው አያቶቻችን በጋራ ብዝሃነታችንን ሲከላከሉ ደማቸውን በማፍሰሳቸው አጥንታቸውን በመከስከሳቸው ነው።
ቅደመ አያቶቻችን በጋራ ጣሊያንን መመከት ተስኗቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሁሉም የዚህ ሃገር ወንድና ሴት በሙሉ ሰብአዊ ክብራችንን ገፎ በባርነት ሊገዛን ባህር አቋርጦ መጥቶ በነበረው በጣሊያን የባሪያ ገዥ ስም ነበር የምንጠራው። ወንዱን ከዚህ መለስ “ማሪዎ” ተብለሃል ሴቷን ደግሞ ከዚህ መለስ “ማርገሪታ” ተብለሻል እየተባለ የጅምላ ስም ይታደለን ነበር። ለባርነት በተዳረጉ በሌሎች ሃገሮች ይህ የስም አሰጣጥ ተግባራዊ መደረጉን አንርሳ! ልብሳችን፣ ምግባችን፣ ሙዚቃችን፣ ጭፈራችን፣ ቋንቋችንና ትውፊታችን እንደ ብዝሃነታችን የተዋበና ያማረ ሆኖ መትረፍ የቻለው በጋራ ዓድዋ ላይ የወደቁ የቅደመ አያቶቻችን የመስዋእትነት ልጆች ስለሆንን ብቻ ነው።
ዓድዋ ላይ ተሸንፈን ቢሆን አለባበሳችንም አመጋገ ባችንም አንድ ወጥ የጣሊያን አለባበስና አመጋገብ፣ መልካችንም የጣሊያን ዲቃላ፣ ነጫጭባ፣ ሙላቶ ይሆን ነበር።
ዓድዋ ላይ ተዋርደን ቢሆን ኖሮ ሁላችንም የምንና ገረውም ቋንቋ ጣሊያንኛ ይሆን ነበር። ወይም ከጣሊያን ጋር ተስማምተው ኢትዮጵያ ላይ የሰፈሩ አውሮፓውያን ጌቶቻችን ቋንቋ ይሆን ነበር።
ዛሬ የልዩነትና የመጋጫ ምክንያት አድርገን የምናቀርበው የዘውግ ማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የዘር ልዩነት ወድሞ፣ ተጨፍልቆ እንደሰው በኩራት ሳይሆን፣ ጣሊያን በፋብሪካው ከሚያመርተው ርካሽ የፋብሪካ እቃ ወይም በገመድ ጣሊያኖች አስረው በየፓርኩ ከሚጎትቷቸው ውሾች የተለየ ማንነት የማይኖረን፣ ከቢጫው ዘር በታች የተመደብን የመጨረሻው የተዋረድን የዓለም ፍጥረቶች ሆነን እናርፈው ነበር። ያም እድለኞች ከሆንን እንጂ፣ እንዲህ አይነቱ እድል ላይገጥመን ይችል ነበር።
ኢትዮጵያ በብዝሃነት ያሸበረቀችው፣ የኢትዮጵያ ልጆች በቅኝ ከተገዙ የአለም ህዝቦች የተለየን ሆነን የተረፍነው፣ ነጭ ከኛ የተለየና የተሻለ ፍጡር ነው ብለን የማናምነው፣ በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድ የቻልነው፣ የእምነት፣ የባህል፣ የቋንቋና ሌሎችም ብዝሃነታችን የሚያንጸባርቁ እሴቶቻችን ማትረፍ የቻልነው፣ በጋራ የቆሙ በጋራ የወደቁ ቅድመ አያቶቻችን ልጆች ስለሆንን ነው። አማራውን የኦሮሞው፤ ኦሮሞውን የአማራው፤ ትግሬውን የጉራጌው፤ ጉራጌውን የትግሬው፣ ሲዳማውን የሶማሌው፤ ሶማሌውን የሲዳማው ልጅ የሚያደርገው የኛ ቅድመ አያቶች አንዳቸው ለአንዳችን መትረፍ ተያይዘው በጋራ መስዋእትነት በመክፈላቸው ነው።
ምንሊክ ከመላው ኢትዮጵያ ወረኢሉና በኋላም ዓድዋ ላይ እንዲሰባሰብ የጠራው ሕዝብ ሳይገኝ ቀርቶ ቢሆን፣ ተገኝቶም በወኔና በጀግንነት ሳይዋጋ ቀርቶ ቢሆን የዛሬው የየግላችን የማንነታችን መለያ አድርገን መናቆሪያ ያደረግነው ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ እምነታችን፣ የኔ ነው አትድረሱብኝ የምንለው አሰፋፈራችን ያበቃለት ነበር።
በ19ኛው ምእተ ዓመት መጨረሻ፣ ነጮች ለጥቁር ዘር የደገሱት ድግስ ምን እንደሆነ በደንብ ለሚረዳ፣ የእኛ ቅደመ አያቶች ዓድዋ ላይ ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ አገራችንን ባህር አቋርጦ ለመጣ ጠላት ማስረከብ ብቻ ሳይሆን እንደሰው በዚች ምድር ላይ መኖራችንም አጠራጣሪ ነበር። የነጮች ህልም በተፈጥሮ ሃብት፣ በመልካም አየር ጠባይና በመሬት ስፋት የታደለችውን አፍሪካ ከውስጧ ነባሩን የጥቁር ዘር አጥፍተው እንደ አውስትራሊያና እንደ ሰሜን አሜሪካ የነጮች መፈንጫ ለማድረግ ነበር። ዓላማቸውም ለአውሮፓ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ሃብት ከአፍሪካ መውሰድ አልነበረም። የቅኝ ግዛት አላማቸው ጥሬ እቃው ፍለጋ መሆኑ ቀርቶ ሰው ማስፈሪያ ፍለጋ ሆኖ ነበር።
ስለሆነም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል ስንኮራ የሚያይ የጥቁር ዘር በሙሉ እኛም የተረፍነው በእናንተ ቅድመ አያቶቻችን መስዋዕትነት ነው። ክብር ለዓድዋ ሰማእታት” የሚለን።
ዓድዋ ላይ ቀደምቶቻችን ጣሊያንን ድል በመንሳት ያተረፉት ከብዝሃነታችን ጋር የተያያዙ የየአካባቢያችን ትውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶችና ቋንቋዎች ብቻ አይደለም። እነዚህ የየአካባቢውን እምነቶች፣ ትውፊቶች፣ የታሪክ ቅርሶች፣ የሁሉም የሃገሪቱ ሕዝብ ሃብቶች እንዲሆኑ በማድረግ ጭምር ነው።
ለወላይታው ወጣት የአክሱም ሃውልት ትርጉም የሚሰጠው ያለ እሱ ቅድመ አያቶች የዓድዋ ምድር መስዋእትነት አክሱም የጣሊያን እንጂ የትግሬ ሃገር አለመሆኗን፣ ሃውልቱም የኢምፔሪያል ጣሊያን የድል አድራጊነት ምልክት እንጂ የአንድ አፍሪካዊ ሕዝብ የታላቅ ስልጣኔ ማስታወሻ እንደማይሆን ስለሚታወቅ ነው። ሌሎችም ከደቡብ እስከ ስሜን ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያሉ የታሪክ ቅርሶች በሙሉ የአካባቢው ሳይሆኑ የመላው የሃገሪቱ ዜጎች መኩሪያና መመኪያ ቅርሶች ተደርገው የሚታዩት በዚህ ሎጂክ ነው። ያለሁሉም መስዋእትነት አንዳቸውም አይተርፉም ነበርና ነው።
ደግሞ ደጋግሞ በታሪክ እንደታየው፣ የታሪክ ጸሃፊዎችም እንደሚያስገነዝቡን ሀገራትን ሃገር ከሚያደርጋቸው ትልቁና ጠንካራ ኩነት ዋናው የአንድ ሃገር ህዝቦች ራሳቸውን ከወራሪ ጠላት በመከላከል በጋራ የከፈሉት መስዋእትነት በጋራ የሚቀዳጁት ድል ነው። ዓድዋ የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሃገር መሰረት የሆነውም፣ ከመሆንም ውጭ አማራጭ እንዳይኖረን ያደረገው በዚህ ታሪካዊ ትርጉሙ የተነሳ ነው!
በአንዳርጋቸው ጽጌ
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2014