ኖህ ከመንበሩ ነኝ፤ ይድረስ ለሰፈራችን መራዥ ሐኪሞች።ከሠላሳ ዓመታት በላይ ያላማቋረጥ ደብዳቤ ጽፌላችሁ ነበር።አንዳችሁም ለደብዳቤዎቼ ምላሽ አልሰጣችሁም ።ፖስታ ቤቶች ደብዳቤዎችን ለሠፈራችን ሰዎች ማድረሱን ተውት እንዴ? ወይስ መራዥ ሐኪሞች ደብዳቤው ደርሷችሁ ካነበባችሁ በኋላ መልስ ልትሰጡኝ አልፈለጋችሁም? የሆነው ሆኖ ደብዳቤዬን አንብባችሁ መልስ እስከምትሰጡኝ ድረስ መጻፌን አላቆምም።ደብዳቤዬ ቢደርሳችሁም ባይደርሳችሁም ለማንኛውም በማለት ሁሉም የሠፈራችን ሰዎች በሚያዩት ዋርካው ላይ ለ29ኝ ጊዜ ለጥፌዋለሁ።
እሁድ የጊዮርጊስ ዕለት በሠፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ኖህ መንበሩ የጻፈውን ደብዳቤ ያነባሉ።ታዲያ እንደዛሬው ዓይናቸው ሳይደክም ለሠፈሩ ሰው ሁሉ ደብዳቤ በማንበብ የሚታወቁት መሪጌታ ተስፋ ከእርጅና ጋር በመጣ የጤና መታወክ እንዲሁም በሰፈራችን ሰዎች ላይ በሚደርስ ተደጋጋሚ በደል ብዙ ጊዜ በማልቀሳቸው የተነሳ ዓይናቸው አላይላቸው ስላለ ዋርካው ስር ከተሰበሰቡት አንዱን ጎረምሳ እንዲያነብላቸው ጠየቁት።አይ ቀን ሲጥል!
ድሮ ድሮ በሠፈራችን ፊደል የቆጠረ ባልነበረበት ጊዜ መሪጌታ ተስፋ ደብዳቤ ለማንበብ ምን ከመሰለ የበግ ቀይ ወጥና ናላ ከሚያዞር ጠላ ጋር ተሰጥተው እና ተለምነው ደብዳቤ ያነቡ ነበር።እናቴ ስታወጋኝ በዚህ ዘመን ተምሮ ሥራ አጥቶ ከሚንገላጀጀው ሰው ምነው ግማሽ የሚሆነው በዚያ ዘመን በተፈጠረ ብዬ ተመኘሁ።«የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም» እንዲሉ በድሮ ጊዜ ከበግ ቀይ ወጥ ጋር ናላ የሚያዞር ጠላ ጠጥተው ለማንበብ ይጀነኑ የነበሩት መሪጌታ ተስፋ ዛሬ ጊዜ ከድቷቸው ፤ ቀን አልፎባቸው እርሳቸውም ለማንበብ ሰው ሲለምኑ ተመለከትን።ወይ ጊዜ !
መሪጌታ ተስፋ ዋርካው ላይ የተለጠፈውን ደብዳቤ እንዲያነብላቸው የጠየቁት ልጅ ለመሪጌታ ተስፋ ሊያነብ ጉሮሮውን ጠረግ ጠረግ እያደረገ ማንበቡን ጀመረ።ዋርካው ላይ የተለጠፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፤ ይድረስ ለሰፈራችን መራዥ ሐኪሞች ኖህ ከመንበሩ ነኝ ።ከ30 ዓመት በፊት የአድዋን ድል አስመልከቶ በየዓመቱ በእኛ በሰፈር በሚገኘው ትልቅ ዋርካ ስር ይከበር ነበር። በዓሉን ለማክበር ሁሉም የሠፈራችን ሰዎች በሠፈራችን በነበሩ በርካታ ትልልቅ እድሮች አማካኝነት እየተሰለፉ እና ትርኢት እያሳዩ ወደ ትልቁ ዋርካም ይመጣሉ።የአባቶቻቸውን ታሪክ እና ገድል በቦታው የነበሩ እስኪመስል ድረስ ያወጋሉ።ልጆችም የአያቶቻቸው ገድል ለዛ ባለው በአባቶቻቸው አተራረክ ሲሰሙ እጅጉን ስለሚደመሙ የአፋቸው አከፋፈት ለጉድ ነው ።ከቀፎው የተሰደደ ንብ እንኳን ቢመጣ ከእነድንጉላው ጭምር የሚያስተናግድ ይመስላል።
ይሁን እንጂ የዓድዋ ድል ከ95ኛ ዓመት ወዲህ የበዓሉ አከባበር ድሮ ከምናውቀው የተለየ እየሆነ መጣ። በእድሮች አማካኝነት ይሰበሰብ የነበረው ሕዝብም፤ ሰፈራችን በሚገኙ ዘጠኝ ቀጣናዎች እና ሁለቱ እድሮች አማካኝነት እየተሰበሰበ እንዲከበር ተደረገ።እንደድሮው በሠፈራችን በሚገኘው ዋርካ ስር ማክበርም ቀረ።ሁሉም ቀጠናዎች የእየራሳቸው መሰብሰቢያ ሥፋራ አበጁ ።ሁለቱ እድሮችም ለዓመታት በተጠቀሙበት እና ቀያሪ ባጣው የተቀዳደደ ድንኳን ስር እስከዛሬ ድረስ እየተሰበሰቡ ይገኛሉ። ዋርካው ብቻውን ቀረ።እዚያ ዋርካ ስር ሄጄ የዓድዋን ድል የማከብረው እኔ ብቻ ነኝ ።
ይህ ሁሉ የሆነው በእናንተ የፈረንጅ አፍ ተምራችሁ በመጣችሁ በመርዝ መርፌ በሽተኛ አክመን እናድናለን ባላችሁ በምትደሰኩሩ አባዮች ፣ ዓይናችንን ጨፍነን ፎቶ እናነሳልን ብላችሁ በምትደሰኩሩ አስመሳዮች፣ ሳይኖራት ያስተማረቻችሁን አገራችሁን የንዋይ ሴሰኝነት አስክሯችሁ በጥቅም አሳልፋችሁ የሸጣችሁ ሐኪም ነኝ ባይ መርዝ ወጊዎች ነው ! ብሎ ማንበቡን ሳይጨርስ መሪጌታ ተስፋ ደብዳቤውን እንዲያነብላቸው የለመኑትን ወጣት አስቆሙ።ሰማህ ልጄ! ይህን ደብዳቤ የጻፈው ሰው ቀለም የዘለቀው ነው። ስለምን ብለህ አጠይቅም? ልጄ! አሉት፡፡ወጣቱም ስለምን ቀለም የዘለቀው ሊሉ እንደቻሉ ጠየቃቸው ።
መሪጌታ ተስፋ የዛሬን አይሁን እንጂ ደብዳቤን ከማንብብ በተጨማሪ የዓለማዊ መጽሐፍትን ያነቡ ስለነበር ትንሽ የፖለቲካ (ክፋት) እውቀት የዘለቃቸው ሰው ነበሩ። «ለውሀቤ ዝናም ማየ ከልእዎ ( ለዝናብ ጌታ ውሃ ነሱት )ወይም አባት ላም ይሰጣል ልጅ አጓት ይነሳል» እንዲሉ ፈረንጅ አገር እንዲማሩ የተላኩ የሠፈራችን ልጆች ከፈረንጅ አገር ጥበብን ተምረው ለአገራችው መኪና ፣ ወፍጮ ፣ባቡር ፣ ጠብ መንጃ፣ ትራክትር ፣ ኮምባይነር ፣ በአጠቃላይ የተለያዩ ማሽኖችን አሰራር እና ቴክኖሎጂዎችን ተምረው መጥተው ሳይኖራት የአስተማረቻቸውን አገር መጥቀም ሲገባቸው፤ ፈረንጆች አፍሪካን በተለይም ደግሞ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል የሆነችውን አገራችንን ለማጥፋት የሸረቡትን ሴራ በአንድ ትንፋሽ ጨልጠው ጠጥተው ራሳቸውን የሠፈራችን ችግር ፈች ሐኪም አደረጉ።ፈረንጆች የጋቷቸውን እንዳለ በመቀበል ግርዱን ከዘሩ ሳያጣሩ መርዛቸውን በሠፈራችንም ላይ ለመዝራት ደፋ ቀና አሉ።
ተማሪዎች ገና አሜሪካ እና አውሮፓ እያሉ በረባው ባረባው ይነታረኩ ነበር።ለምሳሌ የተማሪዎች ኅብረት በአሜሪካ እና የተማሪዎች ኅብረት በአውሮፓ ፍጹም አይስማሙም ነበር።ከዚያም ባለፈ የተማሪዎች ኅብረት በአውሮፓ ደብዳቤ ሲጻጻፉ በአማርኛ ከሆነ ደብዳቤ የተጻጻፉት ከሠፈራችን ማህጻን የተፈጠሩ ነገር ግን የሠፈራችንን እንደሠፈር መኖር የማይፈልጉ የምዕራባውያን የጥፋት ዛር ውላጅ የሰፈረባቸው ገንጣይ እና አስገንጣይ ድርጅቶች በቅኝ ገዥ ቋንቋ የተጻፈን ደብዳቤ አንቀበልም ይላሉ።ታዲያ በምን ቋንቋ እንዲጻፍላችሁ ትፈልጋላችሁ ? ሲባሉ በፈረንሳይኛ ወይም በእንግሊዘኛ ይላሉ።ከአውሮፓ እና ከአገራችን ቋንቋ ቅኝ ገዥ የትኛው ነው? ሲባሉም ለመመለስም ፈቃደኛ አልነበሩም።
ሠፈራችን ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተፋልማ ድል እስከምታደርግ ድረስ የምትጻጻፍበትን የራሳችሁን ቋንቋ ስለምን ተጸየፋችሁት? የሆነው ሆኖ በቋንቋ እና መሰል ተልካሻ ነገሮች እንዲነታረኩ አልነበረም።እናት አገራችሁ ትቀምሰው ሳይኖራት ድሃ እና ረሃብተኛ እየተባለች የውጭ ዕድል ሰጥታ ያስተማረቻቸው።የአውሮፓን የእድገት መነሻ ጥበቦችን ተምረው እንዲመጡ እንጂ! ከተላኩበት ተልዕኮ ውጭ ወጥተው ፖለቲካ ሳይገባቸው የፖለቲካ መርዝ እየፈረፈሩ ራሳቸውን በድንቁርና አስይዘው በማይገባቸው ቁማር ናወዙ።ሳያውቁም ያወቁ መሰላቸው።
የሠፈራችን ቀንደኛ ጠላቶች የወጓቸውን የጥፋት መርዝ በመቶ ሺህ አባዝተው በሰፈራችን ላይ ደፉት ብለው እንደመተከዝ አሉ።ቀጠል አድርገው በል ልጄ ማንበብ የጀመርከውን ደብዳቤ ጨርስልኝ ሲሉ ጠየቁ። ልጁም ማንበቡን ቀጥሎ ፤ በመርዝ መድፊያችሁ እናክማለን እያላችሁ ዓለም የሚቀናበትን አንድነታችንን ለማላላት ከተሰካለችሁም ደግሞ ለመበታተን በማይገባበት ጉራንጉር ሁሉ ገባችሁ።
ምንአልባት በዓድዋ ጦርነት ገድል የሠሩ አባቶቻችን ፎቶ በየአደባባዩ ባትሰቅሉ ፣ ሐውልት ባታቆሙላቸው፣ ቤተ መጽሐፍት እና ዩኒቨርሲቲዎችን በስማቸው ባትገነቡላቸው እንኳን ምኒሊክ ፣ አሉላ፣ ዮሐንስ ፣ ባልቻ፣ ጎበና ዳጨ ፣ ፊታውራሪ ገብረየስ፣ ራስ መኮንን ፣ ቴዎድሮስ ፣ ኧረ ስንቱ ጀግኖች ለአንድነታችን በጀግንነት እንደተዋደቁ እያወቃችሁ ስለምን እነሱን እና ሥራቸውን ለማኮሰስ ተጋጋጣችሁ? እናንተ የምታንኳስሷቸውን ስንት አፍሪካዊ የነጻነት ምሳሌ አድርጎ እንደሚወስዳቸው ለማሰብ ስለምን ተሳናችሁ? የሠፋራችን ብሎም የዓለም ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት የሚላቸውን አባቶቻችንን እናንተ ግን ትንሽም ሰውነታችሁን ሳይሰቀጥጣችሁ ባንዳ ስትሉም ተደመጣችሁ።ለመሆኑ ባንዳ ማን ነው? አባቶቻችሁ ያስረከቧችሁን ነጻነት በፈረንጅ ፍርፋሪ የሚሸጥ ወይስ በታሪክ ላለመወቀስ ሲል ውድ ሕይወቱን የገበረ?
በአባቶቻችሁ ልክ ጀግናችሁ እንደራሽያ ፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቻይና ወዘተ ጅምላ ጨራሽ የሆነ መሣሪያ ሰርታችሁ ሰፈራችንን ማስከበር ሲገባችሁ የፍርፋሪ ፍርፋሪ ፤ የእንጥፍተጣፊ እንጥፍጣፊ እየቃረማቸሁ ከርሳችሁን ስትሞሉ ድሃ እየተባለች የምትጠራውን ሠፈራችሁን ረሳችሁ።ይባሱኑ ሠፈራችንን በቀጣና ከፋፍላችሁ ልታጫርሱን በጥፋት ባቡር እየሸመጠጣችሁ ነው። የፍርፋሪ ፍርፋሪ የለውም የእንጥፍተጣፊ እንጥፍጣፊ የለውም የሚለውን አባባል ውሸት መሆኑ ያየሁት በእናንተ እኩይ ሥራ ነው ።
በአውሮፓ እና በአሜሪካ የሚገኙ በነጮች ነጻነታቸውን የተቀሙ ጥቁሮች ሠፈራችንን በነጻነት በምሳሌ አንስተው ኢትዮጵያኒዝም ሲሉ ስለምን እናንተ የጥቁር ወንድሞቻችሁን ነጻነት የነፈጉ ኃይሎችን የፖለቲካ ሴራ እንደ እውቀት ቆጥራችሁ ሠፈራችሁን ልታፈርሱ ተነሳችሁ?
አሁን ላይ የሠፈራችን ነዋሪዎች በኑሮ ውድነት እና በሰላም እጦት ሲንገላቱ እስኪ የእውነት ሐኪም ከሆናችሁ ሕዝባችሁ ለገጠመው ችግር ሁነኛ መፍትሔ ሰጡ? ወይስ ለእናንተ ሐኪምነት ማለት ሕዝብን በችግር መዝፈቅ ነው?
የሚገርመው የሰፈራችን ጥሩንባ ነፊዎች ነገር ነው። የመርዝ መርፌ ሐኪሞች ነጋሪት በጎሰሙ ቁጥር የጥሩንባ ለፋፊዎች ነገር እጅጉን ይገርማል።አንድም ቀን የሠፈራችንን ሰዎች ችግር እና በደል ለመናገር ያልደፈሩ፤ ነገር ግን የመርዝ መርፌ ወጊዎች አንድ ትንሽ ነገር ትንፍሽ ካሉ የእነሱን ሃሳብ ለማስተጋባት የሚቀድማችሁ የለም ።ስለምን የሠፈራችሁን ሰዎች ዘነጋችሁ?
ይህን የጥሩምባ ነፊዎችን አሽከርነት ስመለከት እ.ህ.ህ እስከመቼ እ.ህ. ህ…… የሚለው ዘፍን ያስታውሰኛል።
በመጨረሻም በአሜሪካ እና በአውሮፓ ተምረው መጥተው ሠፈራችንን ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል በማበጣበጥ ሰላም የነሱ ኃይሎች የታሪክ ተወቃሽ እንደሆኑ ሁሉ አሁን ላይ ያላችሁ በሠፈራችን የምትገኙ ሐኪሞች ጥሩ ሥራዎችን ሠርታችሁ እንደ ዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችን በመልካም ታሪክ ስማችሁን እንድታስጠሩ አደራ ! አደራ !! የእናንተው ውድ ወንድማችሁ ኖህ ከመንበሩ።ብሎ አንብቦ ሲጨርስ….
መሪጌታ ተስፋ «ሕማማ ለዓይን ርዕየተ ጸላኢ ወይም የዓይን በሽታዋ ጠላቷን ማየቷ» እንዲሉ ኖህ ከመንበሩ በስህተት በአንዳንድ የሕክምና ሙያ ላይ የተሠማሩ ሰዎችን በኃላፊነት ተመልክቶ ቢበግን ነው ይህ የመሰለ ደብዳቤ መጻፉ ።ስለሆነም አሁን በሥራ ላይ ያላችሁ ስመ ጥር ሐኪሞች ከጎናችሁ በሕክምና ሙያ የተሰለፉ አንዳንድ ሐኪሞች ሰፈራችንን ለማፍረስ እየተንገታገቱ እያየን ነው። እነዚህን ሰዎች ሠፈር ሳያፈርሱ መላ እንድትሏቸው የበኩሌን ልነግራችሁ እወዳለሁ ብለው፤ ደብዳቤውን ያነበላቸውን ልጅ መርቀው ሸኙ ።እራሳቸውም የዓድዋን የድል በዓል ከኖህ ከመንበሩ ጋር ለማሳለፍ ኖህ መንበሩን እየተጠባበቁ ከዋርካው ጥላ ስር ተቀመጡ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014