(ክፍል አንድ)
የዘንድሮው የዓድዋ የድል በዓል በሁለት አበይት ምክንያቶች ይለያል ። አሸባሪውና ከሃዲው ሕወሓት ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ ተማምሎና ለ47 ዓመታት ተዘጋጅቶ በሕዝባዊ ማዕበል ደብረ ብርሃን ተቃርቦ የነበረበትን ወራሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደ አባቶቻችን ወደ ጦር ግንባር በመዝመት በሰጡት ቆራጥ አመራር ፤ በጀግናው መከላከያ ሠራዊት ፤ በልዩ ኃይሎች፣ በሚሊሻዎችና ፋኖ የተቀናጀ ተጋድሎና መስዋዕት ፤ በደጀኑ ሕዝብ አለኝታነት በአገራችን ህልውና ላይ ተደቅኖ የነበረው አደጋ ተቀልብሶ የምናከብረው የድል በዓል ስለሆነ ከሌላው ጊዜ ይለያል ።
ከ45 ዓመታት በፊት ታላቋን ሶማሊያ እመሠርታለሁ በሚል የቀን ቅዠት የዚያድባሬ ጦር አገራችንን በወረረ ጊዜ እንዲህ እንደ ዛሬው ጀግኖች ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ነጻነቷና የግዛት አንድነቷ ተከብሮ ቆይቶናል ። በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ፤ “ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ መሆን አለበት ።” ያለውን እዚህ ልብ ይሏል ። ነጻነታችንን ከየትኛውም አቅጣጫ ከሚሰነዘር ጥቃት ለመከላከል እንደ አባቶቻችንና አያት ቅድመ አያቶቻችን ሁል ጊዜ ዝግጁ በመሆን በተጠንቀቅ መጠበቅ አለብን ።
የዓድዋ ድል ሉዓላዊነታችንና ነጻነታችን ከማስከበር በላይ በነጮች ላይ የተቀዳጀነው ታላቅና አኩሪ ድል ቢሆንም ከተመጽዋችነትና ከተረጅነት አለመላቀቃችን ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎት ኖሯል ። ድህነታችን አንገታችንን አስደፍቶናል ። ዓድዋን አኮስምኖብናል ። ግርማውና ሞገሱ እንዲገፈፍ አድርጎታል ። አገራችን ከዓድዋ ይልቅ ደጋግሞ በሚጎስማት ድርቅና ረሀብ ሆኗል የምትታወቀው ። ለረሀብ የመዝገበ ቃላት ምሳሌ እስከመሆን ደርሳለች ። አሁን ግን ይህ የታሪካችንና የማንነታችን ለምጽ ሊነጻ የተቃረበ ይመስላል ።
የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቆ በአንድ ተርባይን 375 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት ለመላቀቅ በዋዜማው ላይ እንደምንገኝ ያበስራል ። 13 ተርባይኖች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ5000 ሜጋዋት በላይ ኃይል ያመነጫል ። ይህ ኢኮኖሚውን ፣ ዲፕሎማሲውንና ስነ ልቦናን ይዞ ከመነሳቱ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ተጨማሪ ፋይዳ አለው ። የዓድዋን ድል በኢኮኖሚውና በብልጽግናው ደግመን እስከ ዛሬ ሙሉዕ ያልነበረውን ድል ሙሉዕ እንድናደርገው ስለሚያግዘን የዘንድሮውን የዓድዋ 126ኛ የድል በዓልን ልዩ ያደርገዋል።
በዓድዋ ድል ላይ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ምሑራን የተደረጉ ጥናቶች ፣ ምርምሮች ፣ ድርሳናት ፣ የኪነ ጥበብ ስራዎች ፣ ተረኮች እና አካዳሚያዊ ሙግቶች ፤ ዓድዋ ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአፍሪካውያን ከፍ ሲልም የጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን የሚተርኩ ናቸው ። የዓድዋን ድል ከዚህ አንፃር ብቻ መመልከት የአሸናፊዎች ታሪክ ብቻ እንዳያደርገው እሰጋለሁ ።
ዳሩ ግን ታሪኩ የተሸናፊዎች ፣ የቅኝ ገዥዎች ፣ የተስፋፊዎች ፣ የወራሪዎች ፣ የነጮች ጭምር አድርገን ስናየው የዓድዋ ድል ከጥቁር ሕዝቦች ድል አልፎ የሰው ልጆች ታሪክ ፣ ገድል ይሆናል ። ጸሐፍት የዓድዋ ዘመቻ ከወሰደው ጊዜና ከሚያካልለው የቦታ ስፋት እንዲሁም በድል ከመደምደሙ አንፃር ሲታይ የ19ኛው መ.ክ.ዘ ታላቁ ጦርነት እንደሆነ ያወሳሉ ። ዓድዋን አንድ እርከን ከፍ በማድረጉ ላይ ከተግባባን ፤ ይሄን የሰው ልጅ ታላቅ ታሪክ ያነበሩትን መግፍኤዎች ፣ መነሻዎች ፣ ውጤቶችን አክለን ትምህርቱን የዘመናዊ ኢትዮጵያ እርሾነቱንም ለጋዜጣው እንዲመጥን ቀንጨብ አርገን እንመለከታለን ፤
የፈረንሳይ ቱኒዚያን የመያዝ ፣ የናፒየር ዘመቻ ፣ የቤልጅየሙ ንጉሥ ኮንጎን የመቆጣጠር ፣ የአውሮፓውያን የተስፋፊነት ሕልም ፣ የስዊዝ ካናል መገንባትን ተከትሎ የቀይ ባሕር ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ከፍ ማለቱና በወቅቱ የነበረው የዘውድ ሽኩቻ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ ለመቋመጧ በመግፍኤነት ከሚጠቀሱት ሰበቦች ዋነኞቹ ናቸው ። በጊዜው የንጉሥ ምኒልክ ወደዙፋኑ መቃረብ ያስደሰተው የጣሊያን ወኪል ፔትሮ ኢንቶኔል ግንኙነቱን በፊርማ ለማረጋገጥ ሚያዚያ መገባደጃ ላይ በ1881 ዓ.ም ውጫሌ ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም በቃ ። ስምምነቱ ስውር ደባ ያለው ቢሆንም ዋና ዓላማ አድርጎ የተነሳው የባሪያ ንግድን ለማስቀረትና ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ላሰበችው የንግድ ልውውጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያገለግል ነበር ።
ዳሩ ግን ውሎ ሳያድር የስምምነቱ አንቀፅ 17 ውዝግብ አስነሳ ። በዚህ አንቀጽ የጣሊያንኛ ቅጅ መሠረት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን የምታደርገው በጣሊያን በኩል እንደሆነ የሚያስገድድ መሆኑ በተዘዋዋሪ አገሪቱን በጣሊያን ሞግዚትነት የምትተዳደር ያደርጋታል ። የአማርኛው ቅጅ ግን የውጭ ግንኙነት ማረግ ትችላለች ይላል። በስምምነቱ አንቀጽ 19 ላይ የአማርኛና የጣሊያንኛ ቅጅዎች እኩል ተቀባይነት እንዳላቸው መደንገጉ አለመግባባቱን አካረረው ።
በ1887 ዓ.ም በወርሐ መስከረም በገበያ ቀን ቅዳሜ አፄ ምኒሊክ ታሪካዊውን የ” ወረኢሉን “ ክተት አዋጅ አስነገሩ ። “ …አገርንና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባሕር ተሻግሮ መጥቷል ። እኔም የአገሬ ሰው መድከሙን አይቼ ብታገሰውም ፤ እያለፍ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር ፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር እርዳታ አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም ። ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ ፤ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ ፤ …” አዋጁን ተከትሎ በአፄ ምኒልክ አዝማችነት ፣ ከመላው አገሪቱ በከተቱት መኳንንትና መሳፍንት ባለሟልነት ከ100ሺህ በላይ ወዶ ገብ የገበሬ ጦር እና 29ሺ ፈረሰኞች በኢትዮጵያዊ አንድነት ፣ ጀግንነት ፣ ቆራጥነት ፣ አልበገር ባይነት ፤ ዳርድንበሩን ፣ ሉዓላዊነቱን ሊያስከብር ቀፎው እንደተነካ ንብ ወደ ሰሜን ተመመ። ጄነራል ባራቲየሪም ሰራዊቱን ወደ መሀል ትግሬ እንዲንቀሳቀስ ትዕዛዝ ሰጠ ።
አፄ ምኒሊክ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ፋሽስታዊውና ወራሪው የጣሊያን ጦር ከግዛታቸው ለቆ እንዲወጣ ቢጠይቁም ፤ ጄኔራሉ አሻፈረኝ ከማለቱ ባሻገር በዕብሪት የማይሆን ቅድመ ሁኔታ ይደረድር ጀመር ፤ የአፄው ጦር ትጥቅ እንዲፈታ ፣ ራስ መንገሻ እንዲታሰሩ ፣ መላውን ትግሬን እንዲያስረክብ እና የጣሊያንን የበላይነት እንዲቀበል ጠየቀ ። በዚህም ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ እርግጥ ሆነ ።
ወራሪው ጣሊያን የመጀመሪያውን የሽንፈት ኩታውን በሁለት ሰዓት ውጊያ አምባላጌ ላይ ተከናነበ ። የአምባላጌው አኩሪ ድል ኢትዮጵያውያን በጣሊያን ላይ የተቀዳጁት የመጀመሪያው ታላቅ ፋና ወጊ ድል ቢሆንም፤ ከወታደራዊ ስኬቱ በላይ ስነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነበር ። ኢትዮጵያውያን የአውሮፓን ጦር ድል መንሳት እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ፤ የአፄ ምኒሊክን ጦር የውጊያ ሞራል ያነቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭም የንጉሡን ክብር ፣ ተቀባይነት ከፍ አደረገ ። የአፄ ምኒሊክ ጦር ግስጋሴውን ቀጥሎ መቀሌን ተቆጣጠረ ። ይሄን ተከትሎ ስብሐትና ሐጎስ የተባሉ ለጣሊያን ያደሩ
ባንዳዎች ከድተው ለንጉሡ መግባታቸው ለወራሪው አስደንጋጭ መርዶ ነበር ። የንጉሡ ጦር በወርሐ የካቲት እኩሌታ ለዓድዋ ጥቃት ዝግጁ ሆነ ። የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦር ወዲና ወዲያ ማዶ ተፋጠጠ። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በተካሄደ ጦርነት የጀኔራል ባራቲየርና የሌሎች ጄኔራሎች ጦር ተሸነፈ። ሸሸ። ተፈታ። ወደ 10ሺህ የሚጠጋ የጣሊያን ጦር ሙት ፣ ቁስለኛ ፣ ምርኮኛ መሆኑን አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ሲያትቱ ፤ ሌሎች ደግሞ የሟቹን ቁጥር 11ሺህ፣ የተማረከውን 4ሺህ ያደርሱታል ።
ከጄኔራሎች አርሞንዲና ዳቦርሚዳ ሲሞቱ ፤ በ1850ዎቹ የአገራቸውን ነፃነትና አንድነት በማስከበሩ ብሔራዊ ጀግና ከነበረው ጁሴፔ ጋሪባልዲ ጋር ይነፃፀር የነበረው የጄኔራል አርቤርቶኔ መማረክ ለጣሊያናውያን ሌላው አስደንጋጭና በሀፍረት አንገት ያስደፋ መርዶ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ ። ከጦር መሣሪያም መድፍ ፣ 11ሺህ ጠመንጃ ፣ በርከት ያለ ጥይትና ቁሳቁስ ተማርኳል ። ከኢትዮጵያ የጦር አበጋዞችና የንጉሡ የቅርብ ባለሟሎች ጀግናውን ፊታውራሪ ገበየሁ ፣ ልዑል ዳምጠው ፣ ደጃዝማች መሸሻ ፣ ደጃዝማች ጫጫ ፣ ቀኛዝማች ገነሜና ሌሎች ለአገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት መውደቃቸውን ፤ በተጨማሪም 4ሺህ ሲሞቱ 6ሺህ ኢትዮጵያውያን መቁሰላቸውን የተለያዩ የታሪክ ሰነዶች ቢያትቱም ቁጥሮ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገምታል ።
ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስካፍንጫው የታጠቀው የጣሊያን ጦር አፍሪካዊና ኋላቀር በሆነ የገበሬ ጦር የኢትዮጵያ ሕዝብ መረታቱ ለማመን የሚቸገር መነጋገሪያ ሆነ ። አንዳንድ ምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች የኢትዮጵያውያንን ጥቁርነት እስከ መካድ ደርሰው ነበር ። የታላቁ የዓድዋ ድል የአፄ ምኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱ ( ብርሃን ዘኢትዮጵያ ) ዝና በመላው ዓለም እንዲናኝ ከማድረጉ ባሻጋር አገሪቱን በዓለማቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ መነጋገሪያ አደረጋት ። ከአፅናፍ አፅናፍ የዓለምን ትኩረት እንድትሰብ አደረጋት ።
ድሉ ጥቁሮች ነጮችን ድል መንሳት እንደሚችሉ በማሳየቱ ፤ በቅኝ ግዛት ፣ በጭቆና ለሚገኙ የዓለም ሕዝቦች በተለይ ለአሜሪካ ጥቁሮች መነቃቃትን ፈጥሯል። ለማርክስ ጋርቬ ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ፣ ለኔልሰን ማንዴላ ፣ ለኩዋሚ ንኩሩማህ ፣ ለስቲቭ ቢኮ ፣ ለማልኮም ኤክስ እና ሌሎች ንቅናቄዎች እርሾ በመሆን አገልግሏል ። ለደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት ሆኖ አገልግሏል ። የአረንጓዴ፣ ቢጫ ፣ ቀይ ባንዲራችን ከ20 በላይ የአፍሪካና የካሪቢያን አገራት ሰንደቅ በተለያየ ቅርፅ የመገኘቱ ሚስጥርም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ። የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ ተቀባይነትም የራሳቸው ጥረት እንዳለ ሆኖ መነሻው አንፀባራቂው የዓድዋ ድል ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ ። አንዳንድ የፖለቲካና የታሪክ ልሂቃን የትላንቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ( አአድ ) ሆነ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት ( አ.ኅ ) የምስረታ ሀሳብ የአድዋ መንፈስ የበኩር ልጅ የሆነው የፓን አፍሪካኒዝም የመንፈስ ክፋይ ነው ይሉታል።
የዓድዋ ትምህርት
በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆነው ሬይሞንድ ጆናስ የዓድዋን ድል ትምህርት ፣ አንድምታ ፣ ጥልቀት ፣ ከፍታ ፣ ንዑድነትና ትርጉም በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዲህ ይገልፀዋል ፦ “ …ምኒሊክ እና ጣይቱ ወደ ሰሜን የዘመቱት ስልጣናቸውን በፅኑ መሠረት ላይ ለመገንባት ብቻ አልነበረም ። …የትግራይ ፣ የሸዋ ፣ የኦሮሞ ፣ የወላይታ እና የሌሎች ሕዝቦችን ውስጣዊ አንድነት በደም አስተሳስረው በጋራ ጠላት ላይ በመዝመት የጋራ አገር ለመገንባት እንጂ ፤ የሕዝቦች ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው በእያንዳንዱ ሃይማኖት ፣ ማንነት ብሔር ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን የጋራ ነፃነትን ለመቀዳጀት በሚከፈል መስዋዕትነት ነው ።
ይህ አይነቱ መተሳሰር ብቻ ነው የኢትዮጵያ የነፃነት ከፍታ መገለጫ ፤ የዓድዋ ትምህርትም ይኸው ነው። ልንታደለው የሚገባን ነፃነት ልንከላከለው የሚገባ መሆን እንዳለበት ዓድዋ ያስታውሰናል ። የአድዋ ድል ያስገኘው ነፃነት ብቻ ሳይሆን የተገኘበትን መንገድ ብናጤነው የዘመናችንም ታላቅ ወታደራዊ ድል እንድሆነ እንረዳለን ።በጠመንጃ ብቻ በመታገዝ የተገኘ ድል አይደለም ። የበርካቶችን ልብ በማሸነፍ እንጅ ፤ …”
ይህ የሬይሞንድ ጥልቅ ፣ ምጡቅ የዓድዋ ትምህርት ፣ ፍልስፍና ዳጎስ ዳጎስ ያሉ መፅሐፍት የሚወጣው ከመሆኑ ባሻገር አዲስ አተያይን ንጻሬን የገላለጠ ነው ማለት ይቻላል ። የዓድዋን ትምህርት አገራችንና ሕዝባችን ከሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሊተረጎም ፣ ሊተነተን ፣ ሊመከርበት የሚገባ ከቡድ ሀሳብ ነው ። በአንድ በኩል የምንገኝበትን ዘመንና ትውልድ የዋጀ ፤ ከፍ ሲልም እኛን እንደ ዜጋ ተከሳሽ ሳጥን ላይ አቁሞ በመስቀለኛ ጥያቄዎች የሚሞግት ፣ የሚዳኝ ሆኖ ይሰማኛል ። በሌላ በኩል በአግባቡ ተንትን ከተረዳነው መሻገሪያ ይሆነናል። ለዛሬ በዚህ ላብቃ፤
አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሐቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014