እንኳን ለዓድዋ ድል 126ኛ በዓል በደህና አደረሰን፤ በደህና አደረሳችሁ!
በየዓመቱ እንደማደርገው ሁሉ በመንግሥት (ጉዳዩን በባለቤትነት በያዘው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት) በኩል በሚደርሰኝ ግብዣ መሠረት ነው ዛሬ በመካከላችሁ የተገኘሁት። በዚህም መሠረት ሁለት ጊዜ በዓድዋ ከተማ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ፣ ዛሬ ደግሞ በዓድዋ ድልድይ እንድገኝ በቀረበልኝ ጥሪ መሠረት በመካከላችሁ በመገኘቴ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ። ብሔራዊ በዓል ላይ መገኘት ደግሞ ግዴታዬ ነው፤ ርዕሰ ብሔር የሕዝብ አንድነት ምልክት ስለሆነ እዚህ ካልተገኘሁስ የትስ እገኛለሁ?
የዓድዋ በዓል በአገራችን ታሪክ ከፍተኛ ቦታ የያዘ በዓል ነው። ዛሬ ነፃ በሆነች አገራችን ለማክበር የቻልነው አያቶቻችን፣ ቅድመ አያቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን ባፈሰሱት ደም እና በከፈሉት ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት ነው። አዲስ ነገር ባይሆንም በየዓመቱ የምንሰማው ቢሆንም፤ ይሄንኑ መንገሩ በጣም አስፈላጊ ነው። ከቅኝ አገዛዝነት ሞት ይሻላል ብለው የሕይወት ዋጋ በከፈሉ የአገራችን ጀግኖች መስዋዕትነት ላይ ቆመን መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም።
የነፃነት ዋጋ የሚለካው ነፃነት የተነፈጋቸውን አገሮች ታሪክ ስንመረምር ነው። እንደ አገር እንደ ሕዝብ ኮርተን ደረታችንን ሞልተን የምንቀርበው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለተጨቆኑ ሕዝቦች ሁሉ «ወራሪን፣ ቅኝ ገዢነትን ማሸነፍ ይቻላል» የሚለውን ለማስተላለፍ በመቻላችን ነው። ወደድንም ጠላንም የዓድዋ በዓል የሌላው ሕዝቦችም አኩሪ ታሪካችን፤ ለእኛ ደግሞ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ነው።
ይህንን የፈጸመው ከ126 ዓመት በፊት የነበረው ትውልድ ነው። ይህ እንዲፈጸም ያደረገው በማንኛውም የውጊያ ታሪክ እንደሚታየው ሁሉ በወቅቱ በነበረው መንግሥት እና በነበሩት መሪ አስተባባሪነት ነው። ይሄንን ጉዳይ በዓሉን በማስመልከት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የወጣው ሰነድ ላይ «የዓድዋ ድል ፋይዳ» በሚለው ላይ በግልጽ ማስቀመጡን ለማየት ችያለሁ። በዚህም መሠረት በሰነዱ ላይ «አፄ ምኒልክ የሚመሩት ማዕከላዊ መንግሥት ለጦርነቱ የክተት አዋጅ ሲያወጣ ለጋራ አገራቸው ቀናኢ የነበሩ ሕዝቦች ለአገራቸው ነፃነት ጥሪውን ተቀብለው በመስዋዕትነታቸው ያረጋገጡት ድል ነው፤» ይላል።
ዛሬም አገራችን ያለችበት ወቅት ወሳኝ ወቅት ነው። እንደ አገር ለማደግ፣ ለመዳበር የምንችለው መሠረታችንን ስናጠናክር ነው። ታሪካችን ላይ የጋራ መግባባት ሲኖረን ነው፤ ታሪክን ለታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች ስንተው ነው፤ ታሪክን ለጊዜያዊ ጉዳይ ብቻ የምንጠቀምበት ሳይሆን ሲቀር ነው። ታሪኩን በታሪክ እንዳየነው፤ ታሪኩን ያልተጋፈጠ ሕዝብ፣ ፊት ለፊት ቆሞ ያላየው ሕዝብ የወደፊት አገሩን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የዘንድሮ በዓል አከባበር ዙሪያም ብዙ አስተያየቶች ሲሰሙ ሰምተናል፤ አይተናልም። ማወቅ ያለብን አንድ ነገር እንደዚህ ዓይነት ግዙፍ የሆነ የዓድዋ በዓል በመላው አገር የሚከበር በዓል ነው። አሁንም በደመቀ ሁኔታ በየቦታው ይከበራል። በዓል ደግሞ (ብሔራዊ በዓል) ይፋዊ በሆነ ደረጃ የሚከበረው አንድ ቦታ ላይ ነው። ያን ቦታ ደግሞ የሚወስነው መንግሥት ነው። ይሄንን ግልጽ አድርገን፣ ለሌላ ውዝግብ ቀዳዳ ሳንተው ይሄንን ግዙፍ በዓል በእውነቱ መጠበቅ አለብን። በየቦታው ለሌላ መከራከሪያ፤ ለሌላ ውዝግብ መክፈቻ እንዳይሆን ሁላችንም ጠንቅቀን መሥራት አለብን ብዬ አምናለሁ። እናም ይሄንን አደራ ለማለት ነው።
ይሄንን ስናደርግ በዓድዋ ላይ የምናደርገው ሁሉ ለእኛ ብቻ፣ ለእኛ ጥቅም ብቻ አይደለም። ይሄንን በጥንቃቄ መያዝ አለብን። ይሄ ታሪካዊ ጀብዱ ስንዘክር ይሄንን ተከትሎ ለተነሳሳው የዓለም ሕዝብም ኃላፊነት ስላለብን ነው። የምናደርገውም የሚያሳየው ይሄንን ነው። ስለዚህ «ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም» እንዳይሆን፤ ሁላችንም ይሄንን በዓል በሥነሥርዓት ተግባብተን በተገቢው ትኩረት ማክበር ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ። እናም ይሄንንም አደራ ለማለት ነው።
ዛሬ የሚገኘው የእኛ ትውልድ ብዙ ከፍሏል። ባለፉት ወራት ያየነውም ይሄንኑ ነው የሚያሳየው። ከእርስ በእርስ ጦርነት አሸናፊ የለምና ያሳለፍነው ጊዜ ብዙ የሚያኮራን አይደለም። የዚህች አገር ልጆች ደም ፈስሷል፤ አጥንት ተከስክሷል፤ አንዳችን አንዳችንን ነው የጎዳነው። መሆን የሌለበት ነው የተከሰተው። ከዚህ የምንወጣው ደግሞ ከዚሁ ጥሩ ትምህርት ወስደን ነው። እንዳይደገም በማድረግም ነው። ግድግዳው ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ በቅጡ በማንበብ ነው። በመተባበር ነው፤ በመግባባት ነው፤ በመናበብ ነው።
ከሁሉ በላይ የዓድዋ መንፈስ እና የዓድዋ ቅርስን፣ ከዓድዋ የምንወርሰውን በየዕለት ተዕለት ሥራችን ተግባራዊ ስናደርገው ነው። ለዚህም ለረዥም ጊዜ እይታ ይዘን ስንነሳ ነው። ኢትዮጵያን ለዓለም ማሳየት ያለብን ከዚህ ከዓድዋ ከያዝነው እሴት ጋር አያይዘን ነው። በመከፋፈል አይደለም። እርስ በእርስ በመዋጋት አይደለም። ይሄ በጥንቃቄ ይዘን መሄድ ያለብን ነው። ምክንያቱም እኛ ብንወድም ባንወድም ይሄን ሁሉ ታሪክ ይመዘግበዋልና ነው።
ስለዚህ አሁንም የዓድዋ መንፈስ እና የዓድዋ ቅርስ በሁላችን ውስጥ ማደር አለበት። ይሄንን ይዘንም ነው ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለው። ዓድዋ ላይ እንደታየው በአንድነት፣ የሚከፋፍለንን ሁሉ ወደ ጎን ትቶ ለአንድ ዓላማ በመተባበር ነው። በዚህም የታየው ጀብዱም ከፍተኛ ነው። ስለዚህ እኛ የምንሠራው ከመፈክር እና ከመዘከር በላይ በተግባር በየዕለቱ ስናሳየው ነው። ወደፊት ሁኔታዎች ተመቻችተው ባለፉት ወራት የቆሰልንበትን ቁስሎች ጠግነን፤ የተቸገሩትን፣ የተጎዱትን ደግፈን፤ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ የተጎዱትን ደርሰንላቸው፤ የሚከተለውን በዓል እንደገና በዓድዋ ለማክበር ፈጣሪ ይርዳን።
በተደጋጋሚ የዓድዋ በዓል ላይ እንደገለጽኩት፤ ቀጣዩ ክተት መሆን ያለበት ኋላ ቀርነት ላይ ነው። ድህነት ላይ ነው። ይሄንን ሁላችንም መተባበር አለብን። የክተት ትርጉሙ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የደረስንበት ደረጃ ምስክርነት ነው። ሕዝቡ የከተተው ለአንድ ዓላማ፤ ለአንድ ግብ ነው። በዚህም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የምናደርገው ጥረት ላይ ሁላችንም ከተባበርን የሚበግረን ነገር እንደሌለ አሳይተናል። እናም በድጋሜ ዓድዋ ላይ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ እንዳሳየነው ገድል፤ ዛሬም አገራችንን ከኋላ ቀርነት፣ ከችግር እንድናወጣ ሁላችንም እንድንተባበር በዚህ ቀን ጥሪዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያ አገራችን ለዘለዓለም ትኑር፤ የምትኖረው ደግሞ ሁላችንም ስንተባበር፣ ስንደማመጥ፣ ለአንድ ዓላማ ስንሰለፍ ነው። ፈጣሪ ይሄንን እንድናደርግ ይርዳን!
አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2014