ታሪካዊ ዳራ – አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ፤
የወቅቱ የጀርመን ቻንስለር የነበረው ኦቶ ቫን ቢስማርክ እ.ኤአ. ከ1884-1885 አስራ አራት አገራትን ያሳተፈ ጉባዔ በመጥራት አፍሪካን ለመቀራመት የሚያስችል ድርድር እንዲያደርጉ ግብዣ አቀረበላቸው። “ለመስዋዕት በግነት – Scapegoat” እንድትሆን የተፈረደባትን የአፍሪካ ካርታ በስብሰባው ጠረጴዛ ላይ ዧ ተደርጎ ተዘርግቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የአህጉሪቱ ካርታ በወርድና በርዝመቱ ሰፋ ተደርጎ በአዳራሹ ግድግዳዎች ዙሪያ ከዳር ዳር ተሰቅሏል።
ቻንስለር ቢስማርክ ወደ ካርታው እየጠቆመ እንዲህ በማለት ንግግሩን ጀመረ። “የተከበራችሁ የዓለማችን ታላላቅ መንግሥታት ሆይ! አፍሪካ ይሏት አህጉር በትልቅ የኋላ ቀርነት ጨለማ የተዋጠች ዕድለ ቢስ ምድር ነች። ዜጎቿ ኋላቀር ብቻ ሳይሆኑ ሰብዓዊ ክብር እንኳን ሊቸራቸው የማይገቡ ፍጡራን ናቸው። አኗኗራቸውም ከዱር እንስሳት የተለየ አይደለም። ፈጣሪ የለገሳቸውን ሀብት እንኳን በአግባቡ አልምተው ራሳቸውን ከጨለማ ሊያወጡ የሚያስችል አቅም የላቸውም።
የአህጉሪቱ ሰሜናዊና ምዕራባዊ ክፍል በአብዛኛው በተፈጥሮ ዘይት፣ በብረት ማዕድን፣ በዩራኒዬም፣ በጥጥ፣ በካካዋና በተለያዩ ሀብቶች የታጨቀ ነው። የመካከለኛውና የደቡቡ ክፍልም እንዲሁ ከላይ ከተዘረዘሩት ሀብቶች በተጨማሪ በአልማዝ፣ በወርቅ፣ በፕላቲኒዬምና በነሐስ የበለፀገ ነው። ምሥራቁ ክፍል ደግሞ በተለየ ሁኔታ በዱር እንስሳት፣ በቀንድ ከብቶች፣ በቡናና በሻይ እና በልዩ ልዩ የሰብል ፀጋዎች ሊሸፈን የሚችል የሀብት ክምችት አለው።
ይህንን ሁሉ እምቅ ፀጋ በማህጸኑ የታቀፈው የአፍሪካ ምድር ለሺህ ዘመናት የኖረው ዳፍንት በወረሰው ጨለማ ውስጥ ነው። ስለዚህ እኛ ታላላቆቹና ሥልጡኖች አገራት የአፍሪካን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድህነት አሽቀንጥረን በመጣል ነፃ ልናወጣቸው ግድ ይለናል። ለዚህ ታላቅ ተልዕኮ የፈጣሪ እገዛ አይለየንም። በፈቃዳቸው እጃቸውን የሰጡ አገራትን በሰላም ተቀብለን እንታደጋቸዋለን። የአመጽ ሙከራ የሚያደርጉትን ደግሞ አስገብረን የባርነት ቀንበር እናሸክማቸዋለን። ስለዚህም የጋራ ውሳኔያችን መደምደሚያና የግባችን መዳረሻ ይህ እንዲሆን በአንድ ልብ ተስማምተን አፍሪካን ልንቃረጥ ይገባል።”
ከተሰበሰቡት አስራ አራት አገራት ውስጥ ታሪካዊ ምክንያቱ ጥርት ብሎ ባልተገለጸና ባልተብራራ ምክንያት(?) ስዊድን-ኖርዌይ፣ አውስትራሊያ-ሀንጋሪ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሩሲያ፣ ዴንማርክና አሜሪካ ራሳቸውን ከቅርጫው ውስጥ ባለማሳተፍ ጉባዔተኛውን ተሰነባብተው ተለዩ። በአንጻሩ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ስፔንና ጣሊያን “ዕልል በቅምጣችን” እያሉ በመዘመር የምስኪን አፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ሊቀራመቱ ካራቸውን መዘው ፊታቸው በተዘረጋው ካርታ ላይ የየድርሻቸውን ለመቃረጥ አሰፈሰፉ። እያዳሸቃቸው የነበረውን የወቅቱን የኢኮኖሚ ግሽበት ለመቋቋምም ጥሩ መፍትሔ እንደሆነ ከልባቸው አመኑ። ፖለቲካዊ ተጽዕኗቸውን (በወረራ) እና ሃይማኖታዊ ተልዕኳቸውን (በሚሽነሪዎች) በኩል ለማስፈጸም በመቋመጥም በቀን ቅዠት ውስጥ ተዘፈቁ።
ምኞታቸው በቅዠት ብቻ አላበቃም። የበርሊን ኮንፍረንስ አዘጋጇና ሰብሳቢዋ ጀርመን ተሸቀዳድማ በማዕድን በበለፀጉት የዛሬዋ ታንዛኒያና ናሚቢያ ላይ ዐይኗን በማጉረጥረጥ ድርሻዋን ገምሳ አነሳች። “ታላቅ ነኝ” ባዩዋ እንግሊዝ ቀዳሚውን “ፀሐይ አትጠልቅብኝም” የወረራ ታሪኮቿን በዋቢነት እያቀረበች በመከራከር ከግብጽ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ ጎልድ ኮስት በመባል እስከሚታወቀው የአህጉሪቱ ምዕራባዊ አካባቢዎች ድረስ ልቧ የፈቀደውን ሁሉ እየመረጠች የቅኝ ግዛቷ ምርኮዎች ለማስገበር እየፈነደቀች ወሰነች። ፈረንሳይ በአብዛኛው የምዕራብ አፍሪካ አገራትን (ሞሪታንያ፣ ሴኔጋል፣ ማሊ፣ ጉያና አይቮሪ ኮስት፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቤኒን እና ኒጀርን) ጥርሷ ውስጥ አግብታ ለማላመጥ ቃሏን ሰጠች። ፖርቹጋል በአንጎላና በሞዛምቢክ ላይ የሙጥኝ አለች።
የቅርጫ ተጋሪዎቹን የአውሮፓ ቅኝ ገዢ “ኃያላን” ግራ ያጋባችውና በእሳት አሎሎ መስለው ሊዳፈሯት ወኔ ያጡት አንዲት ብቸኛ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች። ኢትዮጵያን በተመለከተ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ፈራ ተባ እያሉ “እኔ ልሞክራት ወይ?” በማለት እርስ በእርስ እየተፎካከሩ በሹክሹክታ የተወያዩት የታሪኳን ግዝፈትና የሕዝቧን የጀግንነት ታሪክ በሚገባ ስለሚያውቁት ነበር። እንግሊዝ ሰላሣ ከመቶ ያህል አፍሪካን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ጨክና ስለነበር (ግብጽ፣ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ ሰሜን ምዕራብ ሱማሊያ፣ ዛምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ናይጄሪያ፣ ጋናና ማላዊ) ኢትዮጵያንም ለመዋጥ ብትጎመዥ አይፈረድባትም።
ፈረንሳይም በበኩሏ የኢትዮጵያን የቅርብ ጎረቤት ጅቡቲን በቁጥጥሯ ስር ስለምታደርግ ወደ ኢትዮጵያም እጆቿን ብትዘረጋ ሊያዋጣት እንደሚችል መመኘቷ አልቀረም። ጣሊያን ከተመደበላት የቅርጫ ድርሻዋ መካከል (ሊቢያ፣ ኤርትራና ሱማሌ) እንደተጠበቁ ሆነው ኢትዮጵያም መካተት እንዳለባት በተለያዩ ምክንያቶች ስለተከራከረችና “የራሷን ጎረቤት ኤርትራን አስታክኬ እጆቼን በቀላሉ መዘርጋት እችላለሁ” ብላ ስለሞገተች “ሥራሽ ያውጣሽ ብለው” እንደ ምኞቷ ኢትዮጵያን “ቅኝ እንድትገዛ” በተከፈለ ልብም ቢሆን እጃቸውን ዘረጉላት።
በርካታ ዝርዝር ምክንያቶች የሚጠቀሱለት ስምምነታቸው በዚሁ የተጠናቀቀ ይምሰል እንጂ በተቃራጮቹ አገራት መካከል ትልቅ ያለመተማመን መፈጠሩ አልቀረም። ይህንን ፖለቲካዊ ውስብስብ ሴራ በሚገባ የተገነዘቡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ “እኛም ቤት እሳት አለ” እንዲል የአገራቸው ብሂል በቅኝ ገዢዎቹ መካከል የእርስ በእርስ አለመተማመን እንዲፈጠርና የፖለቲካ ሽንፈት እንዲገጥማቸው ዘዴ ማውጠንጠናቸው አልቀረም። ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ሩሲያ ለኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲያደርጉ በማግባባት ወዳጅነታቸውን ለማጠናከር ሞከሩ። ይህንን በማድረጋቸውም እንዳቀዱት በዋና ዋና ቅኝ ገዢዎች መካከል ነፋስ የሚያስገባ የፖለቲካ ድማሚት በማፈንዳት ግራ አጋቧቸው።
ከኢትዮጵያ እኩል “ነፃ ሀገር” ተብላ ያለ አግባብ የምትጠቀሰው ላይቤሪያ እ.ኤ.አ በ1822 አሜሪካ አርነት የወጡ “ባሪያዎችን” ከአገሯ አጓጉዛ ያሰፈረቻቸውና በ1847 እንደ ነፃ ሀገር በችሮታ የተቋቋመች ስለሆነች እንዲህ ነው የሚል ክርክር ውስጥ ገብቶ አላግባብ ታሪኳን ማግዘፍ አስፈላጊ ስላይደለ “በቅኝ ግዛት ያልተያዘች” የሚለው አገላለጽ በዚህ ጸሐፊ እምነት እጅግም ተቀባይነት የለውም።
የሆነው ሆኖ ግን አንዳንድ ቅኝ ተገዢ የአፍሪካ አገራት ቀዬአቸው ድረስ የመጡባቸውን የአውሮፓ ወረራዎችንና ተስፋፊዎችን በአሜንታ አልተቀበሏቸውም። ኬኒያውያንና ዚምባቤያውያን ለእንግሊዝ፣ ናሚቢያውያንና ታንዛኒያውያን ለጀርመን፣ ጉያናውያን ለፈረንሳይ በተለያዩ የአርነት ንቅናቄዎቻቸው አማካይነት አንገዛም ብለው ለጊዜው የአመጽ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጥረታቸው በሙሉ የተጠናቀቀው በሽንፈት ነበር።
ኢትዮጵያን ለማስገበር የቋመጠችው ጣሊያን በወረራ ዕቅዷ ላይ አጥብቃ መሥራትና ወጥመዷን መዘርጋት የጀመረችው ቢያንስ ከስድስትና ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር። ይህንን ሴራ በሚገባ የተገነዘቡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አንዳች ክፉ ችግር በአገራቸው ላይ ሊመጣ እንደሚችል ስለተገነዘቡ በራስ መኮንን የሚመራ የእንደራሴዎቻቸውን ልዑክ ወደ ራሷ ወደ ኢጣሊያ ሳይቀር በመላክ የዲፕሎማሲ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም።
ምዕራባውያን የጠረጠሩት ቅሌት በተግባር ተረጋገጠ፤
ከአፄ ዮሐንስ ህልፈት በኋላ በትግራይ ሹማምንት መካከል የክህደትና የትዕቢት ስሜትና ክህደት በመስተዋሉ አፄ ምኒልክ በ1882 ዓ.ም ወደ ትግራይ በመጓዝ በሹማምንቱ መካከል ሹም ሽር በማድረግ ችግሮችን አስተካክለው ወደ ሸዋ ከተመለሱ በኋላ የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በኢጣሊያዊው ኮንት አንቶኒሌ እና በራሳቸው በምኒልክ መካከል የተፈረመው የውጫሌ ውል ስህተት እንዲታረም ማድረግ ነበር።
የውሉ 17ኛው አንቀጽ ስህተት የሆነበት ምክንያት በኢጣሊያንኛ ቋንቋ በተጻፈው ሰነድ ውስጥ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከሌሎች መንግሥታት ጋር የሚፈልጉትን ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ለመላላክ ፈቅደዋል” የሚለው ግዙፍ ስህተት የአገሪቱን ሉዓላዊ ክብር የሚዳፈር መሆኑ ስለተደረሰበት ነበር።
ለጦርነቱ ሰበብ ሆኖ የኢትዮጵያውያንን ቁጣ ያነሳሳው ይህ አንቀጽ እንዲታረም አንቶኒሌ ተደጋግሞ በንጉሡ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሊሆን ባለመቻሉ ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑ ተረጋገጠ። ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ነበር አፄ ምኒልክ “…ከእንግዲህ ወዲህ ስለ አገሬ ስለ ኢትዮጵያ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና አላዝንም። ደግሞም እግዚአብሔር እስካሁን በጠላት ፊት አሳፍሮኝ አያውቅምና ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። ስለዚህ የአገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ …ለአገርህ፣ ለሚስትህ ለልጅህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ገንዘብ ያለህ በገንዘብህ፣ ጉልበትም ገንዘብም የሌለህ ግን በኀዘንህ እርዳኝ። ይህን አዋጅ ከሰማህ በኋላ ወስልተህ ከዘመቻው ብትቀር ትቀጣለህ።” የሚለውን አዋጅ አስነግረው ፍልሚያው እንዲጀመር ትዕዛዝ የሰጡት።
ምርጥ ወታደራዊ ጄኔራሎችንና የዘመኑን የጦርነት ዝግጅት በሚገባ ያሟላው የኢጣሊያ ሠራዊት ምንም እንኳን የአቅሙ ግዝፈት ይህ ቀረሽ ባይባልም እጅግም ለዘመናዊ የጦርነት ፍልሚያ ዝግጁ ያልነበረውና በአብዛኛው በወዶ ዘማቾች የተዋቀረው የኢትዮጵያ ሠራዊት በአገር ፍቅር ወኔና በአልደፈርም ግለት ደሙን እያስቆጣ በጎራዴና በጋሻ በመፋለም ያንን በዕብሪትና በዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን ወራሪ ድል በመንሳት በዓድዋ ላይ ከራሱ ተርፎ ከዘመን ዘመን በዓለም ታሪክ ውስጥ ሲተረክ የሚኖረውን ድል ለማስመዝገብ እጅግም የተራዘመ ቀናት አላስፈለገውም ነበር። ስለሆነም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ለሰዓታት በቆየ ጦርነት ወራሪው የጣሊያን ሠራዊት የሽንፈቱን ዕንቆቆ እየመረረውም ቢሆን ሊጎነጭ ግድ ሆነ። አፍሪካን የተቃረጡት የአውሮፓ አገራት የፈሩት ደርሶ የውርደቱን ሸማ በጋራ እንዲከናነቡም እብሪታቸው ግድ አላቸው።
በርክሌይ የተባለው እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ ስለ ዓድዋ ጦርነት በጻፈው መጽሐፍ ውስጥ ከኢትዮጵያውያን ወገን የሞተውን ሰው ቁጥር የገመተው ሰባት ሺህ ያህል ሲሆን የቆሰለው ግን አስር ሺህ እንደሚገመት መዝግቧል። የኢጣሊያ ወራሪ ይዞት የመጣው 56 መድፎችና ቁጥር ስፍር የሌላቸው ጠብመንጃዎችም በምርኮ ተሰብስበዋል። ምርኮው የተጓጓዘውም በ500 ያህል አጋሰሶች እንደነበር የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ። በኢጣሊያኖች በኩል የሞቱት ሰዎች 6133 እንደሆኑና የተማረኩት ደግሞ ወደ ሁለት ሺህ እንደሚገመት በርክሌይ በመጽሐፉ ውስጥ ዝርዝሩን አስቀምጧል።
የዓለምን ታሪክ ከለወጡት ግዙፍ ክስተቶች መካከል እንደ አንዱ የሚቆጠረው የዓድዋ ድል በጭቆና ቀንበር ስር ወድቀው ለነበሩት አፍሪካውያን ትልቅ የተስፋ ጎህ የፈነጠቀና የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲቀጣጠልም ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ ዓለማት ለተበተኑ አፍሪካውያን የዲያስፖራ አባላትም ትልቅ የመነቃቂያ ምክንያት ለመሆን በቅቷል።
የትዝብታችን ዝክር፤
ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን ለመላው ጭቁን ሕዝቦች አርነት መውጣት እንደ ማነሳሻ ምክንያት የሚታመን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በእኛ የድሉ ባለቤቶች አንጻር የተሰጠው ክብር የሚገባውን ያህል ነበር ብሎ ለመደምደም ግን ያዳግታል። ወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ብቻም ሳይሆን የቅኝ ገዢ አውሮፓውያንን አንገት ያስደፋው ያ ታላቅ ድል የተመዘገበበት የትግራይ ክልል፤ የዘመናችንን አሸባሪዎች አቅፎ በመያዝ ወራሪ ጠላት እንኳን ያልፈጸመው ግፍ በመከላከያ ሠራዊታችን አባላትና በንጹሐን ዜጎች ላይ ተፈጽሞ ነበር ብሎ ለታሪክ ምስክርነት ማስተላለፉ የመጻኢውን ትውልድ ስሜት ማኮማተሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደር የለሽ የግፍ መገለጫ ተጨማሪ ታሪክ ሆኖ መመዝገቡ በራሱ በዚህ ጉልህ ታሪክ ላይ አመድ የመድፋት ያህል የሚያሸማቅቅ ነው።
“እያረርን ለመሳቅ” እና “ድል እየዘመርን ለመሸማቀቅ” ግድ የሆነብን ይህ የስሜታችን ዳፋ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ምን ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል ዛሬ መተንበዩ ቢያስቸግረንም “የእናንተ ዘመን አስከፊ መራራ ታሪክ የተፈጸመው በርግጡ በዚያ ክልል ውስጥ ነበርን?” እየተባልን መሞገታችን እንደማይቀር በማሰብ ከወዲሁ ብንዘጋጅበት አይከፋም። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014