የሰው ልጅ ክቡር
ሰው መሆን ክቡር
ሰው ሞቷል – ሰው ሊያድን፣— ሰውን ሲያከብር
በደግነት፣ በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፣
በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር — ሰው ሞቶ፤”
ዓድዋ ሲነሳ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባውን መዘንጋት ይከብዳል። በትክክል የዓድዋን ድል ዋጋ ተረድታ በግሩም ዜማዋ በድንቅ ቅላፄ አዚማልናለች። ለዚህም ነው የፅሁፌን መግቢያ ከእርሷ ዘፈን ግጥም ጥቂት ስንኞችን መዘዝ ያደረኩት። የሰውነት ክብር የተገለጠበት፣ ሰው ሊያኖር ሰው የተሰዋበት፣ ሰው ለማዳን ዋጋ የተከፈለበት የእምዬ ኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ምሳሌ የአፍሪካውያን ኩራት ታላቅ ድል – ዓድዋ።
ይህ ታላቅ ድል ሲነሳ ‹ሴት ወንዱ፤ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፤ እገሊት እገሌ ሳይባል አቅም ያለህ በጉልበትህ አቅም የሌለህ በፀሎትህ የሀገሬ ልጅ ሆይ ናና ጠላትን እንመልስ› ከሚል ጥሪ በቀር ዘር፣ ብሄር፣ ጎጥ ያልተጠራበት፤ ኢትዮጵያዊነት ከፍ ያለበት፤ አንድነት የጎላበት ታላቅ እና አንጸባራቂ ድል የተመዘገበበት ነው የትናንቱ ዓደዋ። ደግሞም ዓድዋ ዛሬ ናት ዛሬ የዋጋውን ልክ ሳይገባን የአንድነት ምስጢሩ ሳይገለጥልን እኛነት አንሶ እኔነት ብቻ የገነነበት ዓድዋ ዛሬ ናት።
ዋጋው ወርዶ ሲታየን የደምና የአጥንት ልናስብ ይገባል፤ ትናንት ስለተሰውት መቼ ተነሱና የወዳደቁት፣ መች አፅማቸው ፈርሶ መች ትዝታቸው ደብዝዞ፤ መቼስ ነው ታሪክ ቀለሙን አጥቶ የሀገርን የታላቂቷን እናት ታሪክ የተጀመረ መመልከት አሳንሶ።
ይልቅ ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ፤ ምስጋና ለእነርሱ ለዓድዋ ጀግኖች፣ ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፣ ምስጋና ለታላቆቹ አባቶች እምነታቸውን ከፊት አስቀድመው በፍፁም ወኔና ጀግንነት የጥቁር ድል አምባ፣ ዓድዋ ለሰጡን ወገኖች። ዓድዋ፤ አፍሪካ፣ እምዬ ኢትዮጵያ ተናገሪ… የልጆችሽን ታላቅ ገድል አውሪ፤ አያቶቻችን ምን እንደሰሩ መስክሪ ፤ ከምድርሽ እስከ አፅናፍ የናኘውን የድል ታሪክሽን አውሪ።
እምዬ ስለ ታላቁ ድልሽ፤ ስለ የዓድዋን ተራሮች፤ ተናገሪ፤ ገና የድልሽ ዋጋ ገና የመስዋዕቱ ከፍታ ላልገባቸው አብራሪ፤ የአምባላጌን ተዓምር፤ የሰው መሆን ትግሉን፤ የኔነቴን ቀመር ፤ስፍርና ልኩን የኢትዮጵያዊነቴን፤ የእምዬ ዘር ያንቺ ምርጥ ቀመር፤ የእውነት መመዘኛ ስፍር አልደፈርም እምቢኝ ያልኩበትን ንግግር እምዬ ተናገሪ ካንቺ ወዲያ ማን ሊመጣ ምስክር።
እማማ ኢትዮጵያ አዲሱ ትውልድሽ እንደምን ዘነጋው፤ እንደምንስ ረሳው፤ ዥንጉርጉሩን ቀለም ልዩነት ውበትሽን የመልኬን ማሰሪያ፤ የወገብሽን ስፍር ድርብ መቀነሽን፤ እምዬ ኢትዮጵያ በጦርነት መሀል የተረሳው ረሃብ የጠማሽ ውሃ ጥም፤ የልጆችሽ ጭንቀት እንደምን ይረሳል። እንደምን ተረሳን፤ የህብረ ቀለሙ የአንድነት ማሰሪያው አረንጋዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ማሰሪያው፤ የአንድነት ምስጢር የከፈሉት ዋጋ፤ የልጆችሽስ ደም እንደምን ይዘንጋ።
አንችማ እማማዬ! አንቺማ ባለ ብዙ ዘር ባለ ብዙ ቀለም የህብር ባለቤት የብዙዎች እናት፤ የተፃፈ ታሪክ በዓድዋ ብራና፤ በሰፊው ተራራ፤ በደማቅ ቀለም ደምቆ፤ በአጥንታቸው ብእር የተፃፈው ጠልቆ፤ የባለ ብዙ ታሪክ የማይጠፋ አሻራ ባለቤትስ ነበርሽ፤ ጎተራሽ የሞላ፤ እጅሽ የማይሰስት፤ መሶብሽ የማይነጠፍ፤ የምትሰጪው የምትቆረሺው ሳይጠፋ እልፍኝ ማጀትሽ ሞልቶ ምነዋስ ከቤትሽ ፍቅር ጠፋ።
መልካ መልክሽን ውበትሽ፤ የፊት ቀለም ንቅሳትሽ፤ ዝንጉርጉር ማንነትሽ፤ አንድ በሆነው አንቺነትሽን በማይጠፋ ቀለም በደማቁ ጽፈሽ፤ ታሪክ ሰሪም ታሪክ አኗሪም ካንቺ መሀፀን ሆኖ፤ ታሪክ ደላዥ ታሪክ አፍራሹም ካንቺው ጉያ ውስጥ ተሸጉጦ እምባ ደም የፈሰሰበት አጥንት የተከሰከሰበትን ዋጋ አሳዊቂው እስኪ በቋንቋሽ።
በለሆሳስ አንደበትሽ፤ በእናትነት ውብ ቃና፤ መልካም በሆነው ቅኔ፤ በመላእክት ቋንቋ፤ በማህሌታዊ ድምጽ፤ በየጎራው አናት የአርበኞቹን ቅኔ ወርቅና ሰሙን ዘርፈሽ፤ በእስትንፋስሽ ቃና፣ በምናብሽ ሽታ፣ ከዓድዋ ቁመት ላይ ዓድዋን ጨምረሽ፤ በሰገነቱ ላይ፤ ነጋሪት እያስጎሰምሸ የትናንት ታሪክሽ ላልገባው ግራ ለተጋባው ትውልድ ተናገሪ ማማ ኢትዮጵያ የታሪክሽን ዋጋ ምንነት ላልገባውም ግራ ለተጋባውም መስክሪ።
ዓድዋን ስትተርኪ፤ በንግስናው ቀሚስ ፤ በእጅ አምባርሽ ደምቀሽ፤ የእጅሽ እንሶስላ የፀጉርሽ ቁንዳላ ጣል ያለበት ኩታ ውበትሽን አጉልቶት፤ ድብልቅልቁ ቀለም ባለ ሰፊው ጥለት ከላይ እስከ ታች ቁመትሽን አልብሶት ሸብ ያለው ወገብሽ በባንዲራው ጥለት ባማረው መቀነት እስኪ ተናገሪ ድምፅሽም ይሰማ ታሪኩን የናቀ የተከፈለውን የአንድነትሽን አርማ እማ ተናገሪ የድል ታሪክሽን ለጠላት የማይበገር ክንድሽን የደም ዋጋ ክፍያሽን የልጆችሽን ጽናት የአንድነት ጉልበት አቅምሽን።
ባንቺው አደባባይ ይኸው ይህን ሰሞን፤ ስንቱን ሰው ጦረኛ፤ ስንቱን ሰው አርበኛ፤ ስንቱን ሰው ጀብራራ ባንቺው እልፍኝ ማጀት ጠላት ሳይመጣበት እርስ በእርሱ እየተፋጀበት የትናንቱን ገመድ የመተሳሰሪያው የአንድነት ሰንሰለት፤ የትናንቱን ዋጋ ሲታጣበት እናት አለም ጡትሽ ደም እያጎረፈ፤ ልጅሽ በልጅሽ ላይ ሰይፍ እየመዘዘ፤ አንድ ሆኖ ለመቆም ከእልፍ አመታት በፊት ተዘንግቶ ወድቆ የባንዲራሽ ክብር የባንዲራሽ ዋጋ ከልጆችሽ ልብ ጠፍቶ፤ የአንድነት ገመድ በህብር የታሰረው፤ እሱም እንኳን ላልቶ ግራ ለተጋባው፤ ለጨነቀው ትውልድ ውጪ ተናገሪ የድል ታሪክሽን አውሪ።
ሀገሬ ሰው ያጣሽበትን ልጅ፤ ያልወጣልሽን ምክንያት፤ አእላፍ ወንዞች ከማህፀንሽ እየወጡ፤ የውሃ ማማ የሆነው ስምሽ አንቺ ግን እየተጠማሽ፤ የዳቦ ቅርጫት መሆን ሲገባሽ በረሃብ እየተነሳሽ ፤ ጧሪ አስደሳች ልጅ ያጣሽበት የባንዲራሽ ክብር ያልገባንን ምክንያት እናት አለም እስኪ ጠይቂ ከመገፋፋት ከመጣጣል ከመጠላለፍ፤ ዘሎ በአንድ አንድ ዓድዋው ዘመን ለዳር ድንበርሽ ክብር ሰው የታጣበት ምክንያት።
ልጅ እያለሽ ያልተጦርሽው፤ ወንዝ እያለሽ ላልለማሽው ሀብትሽ ተትረፍርፎ ያልከበርሽ የራስን አስጥሎ ደጅ የሚያሳየንን አባዜ ታሪክ ጥሎ ሌላን በመመኘት መንፈዜ ትውልድ የሚባል ነገር ጠፍቶ ኢትዮጵያዊነት ከለር ለታጣበት፤ መሬት ባልነካ ወሬ ውሃ በማይቋጥር ትርክት መከፋፈል መበታተን የበዛበት እዚህ ዘመን ላይ ቆመሽ እማ ተናገሪ ተናገሪ ኢትዮጵያ የዓድዋን ዋጋ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014