የአንድ አገር የሳይንስና ቴክኖሎጂ መዘመን ለስልጣኔ መላቅና ለኃያልነት ቁልፍ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። እያንዳንዱ ተግባርና ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በዲጂታል ሥርዓት በሚከወንበት ዘመን ዘርፉን በውጤታማነት ማዘመን ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይታወቃል።
ይህ ደግሞ ለጠንካራ ተወዳዳሪነትና ለቀልጣፋ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በዚህ ምክንያት መንግሥታት የቴክኖሎጂውን ዘርፍ ለማዘመን ልዩ ትኩረት ከማድረጋቸውም በላይ የእርስ በእርስ የትብብር ማዕቀፍ መዘርጋት ብሎም የትምህርት ሥርዓቱን ለዘርፉ ውጤታማነት አበርክቶ እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎች አሁን አሁን ትኩረት እየተሰጠው የመጣ ይመስላል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ ለተቀላጠፈ እድገት የድርሻውን እንዲወጣ ከማስቻል በዘለለ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች በራስ አቅም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የማበልፀጉ ሂደት መስመር እየያዘ መምጣቱ ይታመናል።
ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በመንግሥት አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂ በመሠረተ ልማት፣በዲጂታል ኢኮኖሚ እና ሌሎችም ማዕቀፎች ላይ የምንሰማቸው መረጃዎችም ኢትዮጵያ በቀጣይ ልትሠራቸው የሚገባት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም እንኳን ጅማሬው የሚያሳየን መልካም መሠረትና መደላድል እየተፈጠረ መሆኑን ነው።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዓምድ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ዘርፉን ለማላቅ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ መረጃዎችን ይመለከታል። በተለይ ከትብብር ማዕቀፍ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ሌሎች መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የደረሱንን መረጃዎች እንደሚከተለው በስፋት ለማንሳት ይሞክራል።
“ፀሐይ ለቤተሰቦቿ” ዘላቂ የዲጂታል፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትን ለማምጣት ታዳጊዎች ላይ መሥራት በእጅጉ ወሳኝ ነው። ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀጣዩ ትውልድ የዘርፉን መሠረት እንዲያፀና ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።
ከዚህ ውስጥ ደግሞ በኦንላይን የመማሪያ ዘርፍ በቅርቡ ይፋ የሆነው “የዊዝ ኪድስ” መርሐ ግብር ተጠቃሽ ነው። “ፀሐይ ለቤተሰቦቿ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መተግበሪያ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የኦንላይን መማሪያ ሥርዓት ሲሆን የመማሪያ ሥርዓቱ ለቤተሰቦች፣ ለወላጆች እና ለአሳዳጊዎች በወላጅነት እና ሁለንተናዊ የሕፃናት እድገት ላይ አጫጭር ትምህርቶች የሚሰጥበት ነው፡፡
የዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ መስራች ወይዘሮ ብሩክታዊት ጥጋቡ የልጆችን ሁለንተናዊ እድገት ለማዳበር የሚጠቅሙ የተዘጋጁ ትምህርቶች የሚገኙበት ሥርዓት መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
እነዚህን ትምህርቶች በሰባት ቋንቋዎች ለማዘጋጀት እየተሠራም ነው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ጉዳዩን በማስመልከት በሰጠት አስተያየት፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ውስጥ የሚገባና እንደ ቅንጦት ሳይሆን ግዴታ እየሆነ የመጣ ነው። የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለመተግበር አስቻይ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው ።
እንዲህ ያሉ ሥርዓቶች የዲጂታል እውቀት ያለው ዜጋ ለመፍጠር ትልቅ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል። ወላጆች እና አሳዳጊዎች የልጆቻቸውን እውቀት ለማሳደግ በ “www.t4f.et” ላይ በመግባት እንዲጠቀሙ ያሳስባሉ። ትምህርቶቹ የተቀረፁት በልጆች ጤና፣ በትምህርት፣ በሥነ ልቦናና በሕፃናት ትምህርት ዘርፍ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነው።
የትብብር ማዕቀፍ
የኢትዮጵያን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለማዘመን ውጤታማ ከሆኑ አገራትና ታላላቅ ተቋማት ጋር መተባበር በእጅጉ ጠቃሚ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ኢትዮጵያ እና ራሺያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የነበሯቸውን ትብብሮች እና ውሎች በአዲስ የትግበራ ምዕራፍ ለማስቀጠል መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።
ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ከራሺያ ፌዴሬሽን ፓርላማ ሴናተር ኢጎር መሮዞቭ ጋር ውይይት አድርገው ነበር። እንደ እርሳቸው ገለፃ ከአንድ ምዕተ ዓመት ተኩል በላይ የዘለቀውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሁለትዮሽ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ማስቀጠል ይገባል።
የራሺያ ፌዴሬሽን ሴናተር ኢጎር መሮዞቭ ራሺያ በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ኒውክለርን ለሰላም በመጠቀም ረገድ፣ በፋርማሲ ቴክኖሎጂ፣ በንግድ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የሁለትዮሽ አገራዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ጉዳዮች ያላትን አቅም ለማካፈልና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት መንግሥታቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ይናገራሉ ።
በተለይም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በራሺያ ከተሞች ሁሉ ለማዳረስ የግሎናስ ዓለም አቀፍ ጂፒኤስ ያስገኘውን ፋይዳ አካፍለዋል። በኢትዮጵያ የራሺያ ፌደሬሽን አምባሳደር ኢቭኒ ተርኪያን እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያና ራሺያ በስማርት ሲቲ ፕሮጀክት፣ በጸጥታና ደህንነት እንዲሁም በትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ ተግባራትን በአጭር ጊዜ አስቀምጠው ወደ ሥራ ይገባሉ።
ሚኒስትሩም ራሺያን እንዲጎበኙ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረሙን ለመካፈል የተደረገላቸውን ግብዣ አድንቀዋል። የራሺያ ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በገጠማት ችግር ሁሉ በወሳኝ ግዜያት ከጎኗ መቆሟን ያመሰገኑት ዶክተር በለጠ፤ የራሺያ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን በስፋት እንዲያፈሱና ያልተነካውን የኢትዮጵያ እምቅ አቅም በማውጣት የሁለቱን አገራት ሕዝቦች ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በውይይታቸውም ካሁን ቀደም ያሉ ስምምነቶችን በማጠናከር ቀጣይ ግንኙነቶችን እና የትብብር ማዕቀፍን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን በመለየት ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ለመግባት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የቡራዩ ተሰጥዖ ትምህርት ቤት
በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የመሠረተ ልማት ግንባታ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የቡራዩ የልዩ ተሰጥዖ ትምህርት ቤት መገንባቱንም እናስታውሳለን።
አሁን ደግሞ የቤተ ሙከራ እቃዎችን የማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ሰምተናል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና “ስቴም ፓወር” (STEMpower) ለቡራዩ ልዩ ተሰጥዖና ተውህቦ ትምህርት ቤት ግንባታ የቤተ-ሙከራ እቃዎችን ለማሟላት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡
ስምምነቱ የቡራዩ የልዩ ተሰጥዖና ተውህቦ ትምህርት ቤትን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በሂሳብ እና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት እና እነዚህን የቤተ ሙከራ እቃዎችን የሚገጥም የባለሙያ እቅርቦትን ያካተተ ነው፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ ለሁሉም ልዩ ችሎታ ያላቸው ኢትዮጵያውያን መፍለቂያ ታስቦ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክቱ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ነው ያስታወቁት ፡፡ ከግንባታው መጠናቀቅ ጎን ለጎን የቤተ ሙከራ መሳሪያዎችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው ።
ለዚህም ስቴም ፓወር እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ ለቡራዩ የልዩ ተሰጥዖ ትምህርት ቤት የቤተ ሙከራ መሳሪያዎችን እያቀረበ መሆኑን ይናገራሉ ፡፡
በቀጣይም የቤተ ሙከራ እቃዎችን ብቻ ሳይሆን መሣሪያዎቹን የሚገጥም የባለሙያ ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ይጠቅሳሉ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒ ኤች ዲ) እና የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ (ፒ ኤች ዲ) ፈርመውታል፡፡ “STEMpower” ሁለት የቤተ-ሙከራ ክፍሎችን ሙሉ ወጪያቸውን በመሸፈን የማደራጀት ሥራ ለመሥራት ነው ከስምምነት የተደረሰው፡፡
የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለማቸው ሥርዓቶች ውስጥ የሚተገበሩ 222 አገልግሎቶች በኦንላይን እንደሚሰጡ ይፋ ሆኗል። ይህን መረጃ ይፋ የሆነው 45 የመንግሥት አገልግሎቶች ኦንላይን ለመስጠት የሚያስችሉ ሥርዓቶች ለምተው በተመረቁበት ወቅት ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጋር አገልግሎቶቹ ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲተገበሩ ለማድረግ በጋራ እንደሚሠሩም ታውቋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የመንግስት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ በትኩረት እየተሠራ ነው ።
በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ 2 ሺህ 500 አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት እቅድ መያዙን፣ 222 አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ መሆናቸውንና ከ100ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ በሥርዓቱ ውስጥ ተመዝግበዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ መረጃ በያዝነው ዓመት 400 የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይን ለመስጠት እየተሠራ መሆኑ ታውቋል ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተመረጡ የመንግሥት አገልግሎቶችን በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችል ስልጠና ለሁሉም ክፍለ ከተማ ባለሙያዎች ሰጥቷል።
ባለሙያዎቹ በኦንላይን የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ሳይቆራረጡ ለዜጎች እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው። በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በለሙ መተግበሪያዎች ላይ የሚሰጡ 168 አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ ይገኛሉ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ሁሪያ አሊ የኦንላይን አገልግሎት ዜጎች በወረዳና ቀበሌ ጭምር ቅሬታ የሚያነሱባቸውን የመንግሥት አገልግሎቶች በተቀላጠፈና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
የዲጂታል ክህሎት በአንድ አገር ላይ የዲጂታል ሥርዓት በላቀ ደረጃ መዘርጋት ብቻውን በዘርፉ ውጤታማ አያደርግም። ይልቁኑ ዜጎች ስለ ዲጂታል እውቀት ያላቸው ክህሎትን በተመሳሳይ ማሳደግ የተቀናጀና ሙሉ ስኬት ላይ ያደርሳል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል ሥርዓት ግንባታ መሠረቶች እየተጣለ ነው። ይሁን እንጂ የአገሪቱ ዜጎችን በተመሳሳይ መንገድ የተሟላ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚሠራ ሥራ በቂ ነው ተብሎ አይታመንም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነት ማድረጉን ገልጿል። ስምምነቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የካፒታል ልማት ፈንድ (UNCDF) እና የዓለም አቀፉ የቢዝነስ ማሽን ኮርፖሬሽን (IBM) የሴቶችና ወጣቶችን የዲጂታል እውቀት ለማሳደግ በኦንላይን ትምህርት መስክ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ነው ያደረጉት።
ዋነኛ ዓላማውም ሴቶችና ወጣቶች የራሳቸውን የቴክኖሎጂ መፍትሄ እንዲያፈልቁ፣ እንዲያሳድጉና ወደ ቢዝነስ እንዲቀይሩት ለማስቻል ነው። ጉዳዩን አስመልክተው ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ የዜጎችን የዲጂታል እውቀት ማሳደግ ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።
የዜጎችን የዲጂታል እውቀት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝነት አለው ብለዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዓለም አቀፉ የቢዝነስ ማሽን ኮርፖሬሽን የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የዲጂታል እውቀት ተነሳሽነት መሪ ኦሪየት ናየል በአፍሪካ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ለኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ምሩቃን እንዲሁም ለቴክኖሎጂ አልሚዎች ስልጠናዎች እየሰጡ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የካፒታል ልማት ፈንድ የፕሮጀክት መሪ አቶ እንዳሻው ተስፋየ “የዲጂታል ኔሽን አፍሪካ” የሚል ተነሳሽነት በመመሥረት የአፍሪካውያንን የዲጂታል እውቀት ለማሳደግ እየተሠራ እንደሆነ ነው የገለፁት።
ትምህርቱ በክላውድ አገልግሎት፣ በአዲሱ ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በዴታ ሳይንስ እና በኢንተርኔት ቁሶች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሲሆን የኢንዱስትሪ ተኮር ስልጠናዎችንም ያካትታል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014