በውልደትና እድገቱ ኢትዮጵያም የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፡፡ ይህ ሊለወጥ የማይችል የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ስሪት ነው፡፡ “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይለውጥምና!” የብሔር ብሔረሰብ አገር መሆንም ችግር ሆኖብን አያውቅም፤ ብሔር ብሔረሰብ ሆነን ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ኖረናልና፡፡
ሊክዱት፣ ሊሸሹት የማይችሉት ፍጹም ተፈጥሯዊ የራስ ማንነት ስለሆነ ይህንን እውነታ ማንም ሊክደው አይችልም፡፡ ይሄንን እውነታ ሸሽቶና ማንነቱን ክዶ፣ ከራሱ ተጣልቶ የተወለደው “የትግራይ ሕዝብ” ነጻ አውጭ ግንባር/ ትሕነግ/ ብቻ ነው፡፡
እፉኝቱ ትሕነግ ገና ሲወለድ ዥንጉርጉር መልካቸውን ይዘው በዥንጉርጉርነታቸው ውስጥ ደግሞ በሥጋና በደም የተሳሰረ፤ ፍጹማዊ በሆነ ፍቅርና መቻቻል የማያረጅ ኅብረትና አንድነት ፈጥረው፤ በአንድነታቸውና በኅብረታቸው ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ጠብቀው፣ የተከበረና አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር መስርተው በፍቅርና ክብር ፀንተው የኖሩ ኢትዮጵያውያን አባቶቹንና እናቶቹን ማንነት ክዶ ነው የተወለደው፡፡
በዘረኝነት ልክፍትና በእኔ ብቻ የበላይ ልሁን የኢምፔሪያሊዝም ሾተላይ የእርግዝና ዘመኑን ሳይጨርስና ገና የሰውነት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ያለጊዜው ከኢትዮጵያ ምድር የተወለደው ጭንጋፉ ትሕነግ፤ ከራሱ ማንነትና ከዓለም አቀፋዊው የዘመኑ እውነታ በተቃራኒው እየዳኸ የእምቦቆቅላ ዘመኑን ጨርሶ በሁለት እግሩ ቆመ፡፡
እናም “አገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል” እንዲሉ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ተወልዶ ማደግ የጀመረው የዘመን መርገምቱ ትሕነግ ዓለም ከምን ጊዜውም በላይ ወደ አንድነት እየመጣች በነበረችበትና በሰው ልጆች መካከል ድንበር ተሻጋሪ አንድነትና ትብብር እየተፈጠረ በመጣበት በሃያኛው ክፍለ ዘመን በአንድ ሕዝብ መካከል ጥላቻንና መከፋፈልን የሚፈጥር ድንበር ለማበጀት አልሞ ተነሳ፡፡
አልሞም አልቀረ፤ ከራሱ ማንነትና ከዘመኑ የዓለም እውነት በተቃራኒው የቆመ ይህንን እኩይና ከፋፋይ ዓላማውን ለማሳካት፤ ራሱን ክዶ ሌላውን ለማስካድ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለመነጣጠል ከሕዝብ ተነጥሎ አገር ጥሎ በረሃ ገባ፡፡
ራሱ የተገኘበትንና በዥንጉርጉርነት ውስጥም ሆኖም ፍጹም የሚያስቀና አንድነትና ኅብረትን መሥርቶ፣ በፍቅሩና በሕብረቱ አንድነትን ብቻ ሳይሆን እንደ አለት የማይሸረሸር፣ እንደተራራ የማይገፋ ኃይልና ኃያልነትንም ገንብቶ በዚህም ታላላቅ የአሸናፊነትና የድል ታሪክን ሠርቶ፣ በአኩሪ ማንነትና ስም ታውቆ የኖረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ለማፍረስ ጫካ ለብሶ መከረ፡፡
በአንድነቱና በኅብረቱ ታፍሮና ተከብሮ በኖረ ኃያልና ታላቅ ሕዝብ ፋንታ በመለያየትና በመነጣጠል ተከፋፍሎ፣ ኃይሉን አጥቶና ተዳክሞ በሃፍረትና በውርደት የሚኖር ሕዝብ ለመፍጠር የሚያስችል ይፋዊ የጥፋት ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገባ፡፡
ትሕነግ የጥፋትና የርኩሰት ዓላማውን ለማስፈጸም በማኒፌስቶው በዋነኝነት አንግቦት የተነሳውና መጀመሪያ ያደረገው ደግሞ የራሱንና የአገሩን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ማንነት ለመካድና ለማስካድ ብሎም ኢትዮጵያውያን እርስበእርሳቸው እንዲጠላሉና ኢትዮጵያን እንዲጠሉ የሚያስችል በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ሌላ አዲስ የሐሰት ማንነትን ለራሱና ለኢትዮጵያውያን መፍጠር ነበር፡፡
ይህም “ኢትዮጵያን የአማራ ገዥዎች ሌላውን ብሔርና ብሔረሰብ በኃይል አስገድደው የፈጠሯት አገር ናት፤ ትግራይም የኢትዮጵያ አካል ሳትሆን ራሷን የቻለች አገር ናት፣ እናም ትግራይም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ማንነታቸውን ለማስከበርና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በጨቋኙ አማራ ላይ በጋራ መነሳትና መታገል አለባቸው” የሚለው እጅግ አደገኛ የጥፋት መርዝን የተሸከመው የጥላቻና የሐሰት ትርክቱ ነው፡፡
ምክንያቱም ትርክቱ፡- 1ኛ) ከላይ ሲያዩት ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተቆረቆረ መስሎ ግን ደግሞ ኢትዮጵያን ለአንድ ብሔር ብቻ ጠቅልሎ በመስጠት በተቃራኒው የብሔር በሔረሰቦችን ማንነትና የአገር ባለቤትነት መብት የሚነጥቅና እንኳንስ መብታቸውን ህልውናቸውን የሚክድ፤ 2ኛ) እውነተኛውንና ትክክለኛውን የኢትዮጵያን ዥንጉርጉርነትና ተፈጥሯዊ ማንነትን ክዶ የሚያስክድ፤ 3ኛ) አንድን ሕዝብ የሁሉም ጠላት አድርጎ ፈርጆ ሌላ በእርሱ ላይ በጠላትነት እንዲነሳ የሚያደርግ እጅግ አደገኛ የክህደት፣ የውሸትና የጥፋት ትርክት በመሆኑ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ የተወለደው መርገምተ ሰብኡ ትሕነግ ለግማሽ ክፍለ ዘመናት ዕድሜ ልኩን የኖረው እንግዲህ ለማንነቱ እታገልለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን በማስካድና ከኢትዮጵያ በመነጠል፣ ብሎም ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ በማበላላትና በመነጣጠል ይህንን እኩይና አስጸያፊ የጥፋትና ርኩሰት አጀንዳውን ያለእረፍት እየፈጸመና እያስፈጸመ ነው፡፡
ትህነግ በስልጣን ዘመኑ
ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር “መብት” በሚል ሽፋን የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደምና እነርሱ ብቻ የበላይ ሆነው ለመኖር የጥላቻና የልዩነት ፖለቲካን አምጠው ወልደው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ በትጋት ሲተገብሩ የቆዩት ትህነግና ትህነጋውያን የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰባዊ ማንነት አጥፍተው አገርና ሕዝብ ክፉኛ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ማድረጋቸው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡
በዚህም በትሕነግ የሴራ ፖለቲካ የተነሳ በገዥነት በቆዩባቸው ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ለጆሮ የሚከብዱ፣ ለሰሚ የሚያርዱ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥኑ፣ በጥቅሉ እጅግ በጣም የሚዘግኑና የሚያሳፍሩ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችንና ተዘርዝረው የማያልቁ ሌሎች ታህተ ሰብዕ ክንዋኔዎችንም በየፈርጁ ለማስተናገድና የታሪካችን አካል ለማድረግ ተገድደናል፡፡
ከማዕከላዊ የስልጣን መንበሩ ከተባረረ በኋላ
ከዚህ ሁሉ የቁልቁለት ዘመን በኋላ ደግሞ በርካታ ዓመታትን በፈጀና አያሌ መስዋዕትነትን ባስከፈለ የሕዝብ ትግል ከሦስት ዓመታት በፊት በተደረገ ጥገናዊ ለውጥ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመ ታሪካዊ ሊባል የሚችል አገራዊ ለውጥ በማምጣት ዕውን ማድረግ ተቻለ፡፡
ሆኖም የጥቅም ጀንበራቸው ያዘቀዘቀችባቸው የመሰላቸው ትሕነጎች ከለውጡ ማግስት ጀምሮ “ጨቋኝተጨቋኝ” የሐሰት ፍረጃ ፖለቲካቸውን እንደ አዲስ አድሰው በለመዱት የጠላትነትና የፍረጃ ትርክታቸው ሕዝብን አለያይተው፣ በጠላትነት አቧድነው ዳግም ከፋፍሎ በማዳከም ሕዝብን በበላይነት ቀጥቅጦ ለመግዛት በብሔር ብሔረሰብ መብት ሽፋን ዳግም ሕዝብን ለጦርነት ቀሰቀሱ፡፡
ለዚህ እኩይ ዓላማቸው መሳካት ያመቻቸው ዘንድም አንድ ጊዜ ለአገራዊ አንድነት ሌላ ስም በመስጠትና ከእውነታው በተቃራኒ ለቃሉ አሉታዊ ትርጉም በመፈብረክ፣ የራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የሚነፍግ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚንድ፣ ፌዴራላዊ ሥርዓቱን የሚያጠፋ፣ ወደ አህዳዊ ሥርዓት የሚመልስ፣ ብሔር ብሔረሰቦችንም የሚውጥ…ወዘተ የሚሉ የሐሰት ውንጀላዎችን በስፋት በለውጡ መሪዎች ላይ ሲያሰራጩ ከረሙ፡፡
ሃያ ሰባት ዓመት ሕዝብን በግፍ እየገደለ አገርን በገፍ እየዘረፈ ተንደላቆ ከኖረበት የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በሕዝብ ትግል ተባርሮ መቀሌ የመሸገው ትሕነግ፤ ለሕዝብና ለአገር ሰላም ሲባል በርካታ ማባባያዎች ቢደረግለትም ሰነፍ ሲያከብሩት የፈሩት ይመስለዋልና ጭራሽ እብሪቱ እየባሰበት ሄደ፡፡
በግለሰቦች ምርጫ ሳይሆን በተፈጥሮ አስገዳጅነት ሰዎች ላይ በተጫነ መንጋ አቧድኖ ጎራ ለይቶ ሕዝብን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለማስገባት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በስፋት ሲሠራ የቆየው ዓለም ባወቀው ፀሐይ በሞቀው ከባድ የህልውና ችግር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሕዝብ በሕይወትና በሞት መካከል ሆኖ እየተጨነቀ ባለበት ሁኔታ በሕዝብ ላይ ጥፋትን ሊያስከትል በሚችል አኳኋን ምርጫ ካልተደረገ በሚል አገር ይያዝልኝ አለ፡፡
ቀጥሎም ራሱ የጻፈውን ሕገ መንግስት ሽሮ “በራሴ ክልል ላይ ምርጫ ካላካሄድኩ አገር ትፈርሳለች” በሚል ለውጡ ያመጣውን ነጻነት ተጠቅሞ ያለ ምንም ሃፍረት አገርን ለማፍረስ ፎከረ፡፡
ሁኔታው ያሳሰባቸው ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እብሪተኛውን ለመሸምገል በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ መቀሌ ቢሄዱም “በፍጹም በመብታችን (በግል ጥቅማችን ማለታቸው ነው)፣ ይህ ቀይ መስመር ነው አንደራደርም” በማለት ታላቁን የኢትዮጵያውያን እሴት አሳንሰው ሽማግሌዎችን አዋርደው መለሱ፡፡
በዚያም እንደፎከሩት ባደረጉት ሕጋዊ ያልሆነ የጨረባ ክልላዊ ምርጫቸው ከአምስት ሚሊዮን የክልሉ ሕዝብ ሁለት ሚሊዮን መራጭ ተመዝግቦላቸው እነርሱ ግን በአስር ሚሊዮን ሕዝብ ተመርጠን ብለው በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የተመዝገበ “ታሪካዊ” ምርጫ አካሂደው ሕዝባቸውን የስልጣን ባለቤት አድርገው ምርጫው በድል ተጠናቀቀ¡
እንደገና ወደስልጣን ለመመለስ
ዳግም ወደ ስልጣን ተመልሼ ኢትዮጵያን እያፈረስኩ ካልገዛሁ በሚል ከማዕከላዊው ስልጣን ተባርሮ መቀሌ ከመሸገ በኋላ ኢትዮጵያን እንዴት ማፍረስ እንዳለበት ለሦስት ዓመታት ሲያሴር የቆየው ከሃዲው ትሕነግ በመጨረሻም ዕኩይ ዓላማውን እውን ለማድረግ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊትና በኢትዮጵያ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው አሳፋሪ ክህደት ፈጸመ፡፡
ሰብል እያጠፋ የነበረን የአንበጣ መንጋ ከሕዝብ ጋር ሲከላከል በዋለ የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በተኛበት ከውጭና ከውስጥ ከብቦ፣ በሰው ልጆች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ክህደት በግፍ ፈጸመበት፡፡
ከሃዲው ትሕነግ ይህን ያደረገው መካናይዝድ፣ መድፈኛ፣ ታንከኛና ሚሳኤልን ጨምሮ የአገሪቱን ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን ዋነኛ የጦር መሳሪያና የጦር ክፍሎች የያዘውን የሰሜን እዝ ሙሉ በሙሉ በመደምሰስና መሣሪያውን ዘርፎ በመታጠቅ የአገሪቱን የጦር ኃይል ለመቆጣጠርና ዳግም ኢትዮጵያን እያፈረሰ የመግዛት ዕኩይ ዓላማውን በኃይል ለማስፈጸም አስቦ ነበር፡፡
ሆኖም በታሪኩ ሽንፈትን የማያውቀው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብና መከላከያ ሠራዊቱ እጅ አልሰጥም ብለው፣ እጅግ በላቀ ወታደራዊ ጥበብና አስደናቂ ጀግንነት ታግሎ፣ ውድ መስዋዕትነትን ከፍሎ ከበባውን ሰብሮ የተፈጸመበትን ጥቃት በብቃት መክቶ የከሃዲውን የትሕነግ የኃይል ክንድ ሰብሮ መልሶታል፡፡
ከጥቃቱ በፊት ከእኛ በላይ ወታደራዊ ዕውቀት ያለው የለም፣ “ጦርነት ለእኛ ባህላዊ ጨዋታችን ነው”፣ ከእኛ በላይ ጀግና የለም እያለ ጉራውን ለዓለም ሲቸረችር የነበረው ልክ አያውቄው የትሕነግ እብሪተኛ ኃይል በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ገና በመጀመሪያው ቀን አከርካሪውን ተመትቶ መፍረክረክ ጀመረ፡፡
አስራ ሰባት ዓመት የታጠቀ ኃይል ጭቆና ካማረረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታግሎ ያስወገደውን የደርግ ሥርዓት የሕዝብን ታሪክ በመስረቅና ለራሱ ብቻ በመስጠት በአስራ ሰባት ዓመት ትግል ደርግን ገረሰስን እያለ፤ “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የሚል የሐሰት ታሪክ አስጽፎ ዕድሜ ልኩን በውሸት ጀብዱ ሲታበይ የኖረው ትሕነግ አስራ ሰባት ቀን ሳይዋጋ ተፍረከረክ፡፡ በሃሳብ ተሸንፎ ከማዕከላዊ መንግሥትነት ተባርሮ በ “ሕዝብ” ዋሻ ተከልሎ ከመሸገበት መቀሌም ተባረረ፡፡
ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ጦር ወግቼ ያዝኩ ቢልም “ባህላዊ ጨዋታዬ ነው” በሚለው ጦርነት መቶ ለዜሮ ተሸንፎ ፈርጥጦ ተንቤን የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ገባ፡፡ ከሩብ ክፍለ ዘመናት በላይ ግፍና በደልን ያሳለፈው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ አንድ ላይ ቆርጦ በመነሳቱና ጥቃቱን በመመከቱ ያሰበውን ማሳካት ያልቻለው ሕወሓት እንደ ውልደቱ ዘመን ተመልሶ ወደ ቀበሮ ጉድጓድ ገብቶ በምላስ ታንክና መድፍ እየማረከ፣ በወሬ ጀት እየጣለ፣ በፕሮፖጋንዳ መከላከያ ሠራዊትን እየደመሰሰ ስምንት ወራትን አሳልፏል፡፡
ሆኖም ጀግንነት መለያው የሆነው ጀግናው ሃገር መከላከያ ሰራዊት ጉምቱ የትሕነግ መሪወችን ከገቡበት እየገባ እንደ ተኩላ እየታደኑ፣ እንደ አይጥ ከየጉድጓዱ አንገታቸውን እየታነቁ ለሕግ እንዲቀርቡ አደረገ፡፡
ብዙ ተለምነው እጃቸውን በሰላም አልሰጥ ያሉ፣ እንዲያውም በሰላም እጃችሁን ስጡ የሚለውን የመከላከያ ሠራዊት የሰላም ጥሪና በጎነት እንደለመዱት ለጥቃትና ለጥፋት መፈጸሚያ ለመጠቀም የሞከሩ አንዳንድ የክፋት ውላጅ፣ የሕዝብ ጠላት የሆኑ ከሃዲ የትሕነግ መሪዎችን ደግሞ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ላይመለሱ ወደ መቃብር እንዲሸኙ አደረጋቸው፡፡
በዚህም በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት አይበገሬ ክንድ ተደቁሶ ዳግም ስልጣን የመያዝና አገርን እርሱን ብቻ በሚጠቅም መንገድ የመግዛት አልያም የማፍረስ የትሕነግ እኩይ ዓላማ ሙሉ በሙሉ ከሸፈ፡፡
በመጨረሻም ለጥቂት ከሃዲ ሃገር ሻጭ የትሕነግ ወንበዴዎች ተብሎ ሕዝብ በረሃብ እንዳይቸገርና ክረምቱን ያለምንም ችግር የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን በማሰብ መንግሥት በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከትግራይ ክልል ወጣ፡፡
የትሕነግ የክህደትና የማስካድ ጉዞ ከባሕላዊ ጨዋታው በኋላ
ይሁን እንጅ የመከላከያን ከትግራይ መውጣት ተከትሎ ከነአካቴው ከምድረ ገጽ ካልጠፋ በቀር የማይጠፋው ትሕነግ ከጉድጓዱ ወጣ፤ የተወለደበት፣ ያደገበትና ያረጀበት ክህደቱ፣ ውሸቱና እብሪቱም ከበፊቱ ብሶ መጣ፡፡ በመከላከያ ወታደራዊ ስትራቴጂም ይሁን በሌላ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ከወንጀል መሸሸጊያ የብሔር ዋሻው ባሻገር ጥቂት የአፋርና የአማራ አዋሳኝ መሬቶችንም ያዘ፡፡ እናም እብሪቱና ውሸቱ አገር ምድር አልበቃው አለ፡፡
ያም ሆኖ በክልላዊ ኃይሎችና በአካባቢው አርሶ አደር ሚሊሻዎች ብቻ በየቀኑ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣል፣ ሕዝብ ለመቅበር እስኪቸገር ድረስ ታጣቂ ኃይሎቹን ያስጨርሳል፣ በየግንባሩ ይደመሰሳል፣ በገፍ ይማረካል፡፡ ጁንታው ግን በሽንፈቱ የሚፎክር፣ በሞቱ የሚደንስ፣ እንደ ሳጥናኤል ላይመለስ ወደ ጥልቁ እስኪወረወር ድረስ በስንፍናው የሚኮራ እብሪተኛ የማይድን ከንቱ ታህተ-ሰብዕ ቡድን በመሆኑ ዛሬም በውሸቱና በምናባዊ ጀብደኝነቱ ቀጥሏል፡፡
ሲደመሰስ ደመሰስናቸው፣ ሲማረክ ማረክናቸው፣ የያዘውን ሲነጠቅ ያዝንባቸው በሚል የቁም ቅዠቱ ሕዝብ ማደናገሩን ቀጥሎበታል፡ ፡ ይህ የመጨረሻው ለመድረሱ ምልክት ሆኖ ከአንድ ወር የጥሞና ጊዜ በኋላ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የማያዳግም ክንዱን አሳረፈበት፡፡
በርካታ ውድመቶችንና ዘግናኝ ሰብዓዊ ጥፋቶችን ቢፈጽምም ዳግም ተሸንፎ ትሕነግ በእብሪት ከወረረው የአፋርና የአማራ ክልል ተባርሮ ወደ መከረኛው የትግራይ ሕዝብ ተመልሶ ሄዶ ቢሸሸግም “ስልታዊ ማፈግፈግ አድርገን እንጅ ተሸንፈን አይደለም የወጣነው” የሚል የተለመደ ክህደቱንና ውሸቱን ቀጠለ፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ በቁሙ ሲኦል እስከመሄድ የቆረጠው ጁንታው ሲኦል የመግባት ሕልሙ እውን ካልሆነ በቀር ክህደቱንና ኢትዮጵያን የማፍረስ ሥራውን ስለማይተው እነሆ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ በእብሪት ሌላ ወረራን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያን ማዕከላዊ ስልጣን ከመቆናጠጡ በፊት ሲያራምድ የነበረውን “የትግራይ ቤተ ክህነት” እና “የትግራይ መጅሊስ”ን የማቋቋምና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በሚወዱት ሃይማኖታቸውም ለመነጣጠልና ለማጠፋፋት የመጨረሻ ክህደቱን እየፈጸመ ይገኛል፡፡
ዳሩ ምን ያደርጋል፤ ሰው እንኳን መሆን ያልቻለው ታህተ ሰብኡ ትሕነግ ፈጣሪ ሆኖ የኢትዮጵያውንን ዕምነትና ሃይማኖት እርሱ በፈለገው ልክ መክፈልና ማከፋፈል አይቻለውምና የክህደት ራዕዩ አይሳካም፡፡
ኢትዮጵያ በእውነተኛ ማንነቷ ለዘላለም ትኖራለች!
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014