አበው «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» እንዲሉ፤ ኢትዮጵያውያን በየታሪክ ምዕራፎቻቸው በፈጠሩት ሕብረትና አንድነት እልፍ ፈተናዎችን አልፈው፤ ያልተቆራረጠ ታሪክን ከትበው ኖረዋል፤ እየከተቡም ናቸው።
ከእነዚህ የታሪክ ምዕራፎች መካከል ደግሞ ወደ ዓድዋ ተራሮች በአንድነት ተምመው የፈጸሙት ዘመን አይሽሬው ገድላቸው አንዱ ሲሆን፤ ይህ ገድላቸው ከራሳቸው አልፎ ለብዙዎች የትብብር መንፈስን የፈጠረ፤ ተደጋግፎ በአሸናፊነት መሻገር እንደሚቻል ያስተማረ ሕያው የድል ምዕራፍ ሆኖ ዘመናትን ሲዘከር ኖሯል፤ እየተዘከረም ይኖራል።
ዓድዋ – ከዛሬ 126 ዓመት በፊት የቅኝ ግዛት እሳቤ ውስጥ ሰጥመው የሚቅበዘበዙ አውሮፓውያን ወደተለያዩ አህጉራትና አገራት የወረራ መረባቸውን የዘረጉበት ነበር።
መረቡ በስፋት ካረፈባቸው አህጉራት መካከል ደግሞ አፍሪካ ቀዳሚዋ ስትሆን፤ ሁሉም የአፍሪካ አገራት በዚህ መረብ የመጠመድ ዕድሉ ደርሶባቸዋል። በዚህም ከኢትዮጵያ በስተቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ በመረቡ ተጠልፈው ለቅኝ ግዛታቸው መደላደያ ሆነው ዓመታት ዘልቀዋል።
ታዲያ ኢትዮጵያ እንዴት መረቡ ጠልፎ ሳያስቀራት እና የቅኝ ግዛት ሕልማቸውን ሳያሳኩባት ቀሩ? ሊባል ካስፈለገም፤ ኢትዮጵያውያን ለክብርና ሉዓላዊነታቸው ግንባራቸውን የሚሰጡ፤ ራሳቸውን ለወራሪ ለማስገዛት በጅ የማይሉ ሕዝቦቿ ስለ አገራቸው ነፃነትን ስለእነሱም ክብር ሲሉ በመዋደቃቸው ቅኝ ገዢዎችን አንኮታኩተው በውርደት በመሸኘታቸው ምክንያት መሆኑን ይገነዘባሉ።
እንዴት ቢሉ፤ የፋሺስት ጣሊያን ወራሪ ጦር በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ የተቀዳጀውን የቅኝ ገዢነት ድል በኢትዮጵያም ለመድገም በ1888 ዓ.ም የኢትዮጵያን በር ማንኳኳት ጀመረ። የቤቱ ባለቤት ኢትዮጵያውያንም እንግዳን እንጂ ወራሪን የማስተናገድ ባህሉም፣ ልምዱም የላቸውምና «ማን ነህ? ከየት ነህ? ጉዳይህስ ምንድን ነው?…» የሚሉ ጥያቄዎችን አጥርተው ሲያበቁ፤ አመጣጡ ለወግ ባህላቸው የማይመጥን መሆኑን ሲገነዘቡ ከድንበራቸው እንዳያልፍ ይነግሩታል።
ይህ በእብሪት የተወጠረ ወራሪ ጦር ግን አንኳኩቶ ቢያቅተው ገንጥሎ ለመግባት ሞከረ፤ እናም በሩን መነቅነቅ ጀመረ። በዚህ ጊዜ በር ላይ ያሉ ሕዝቦች በሩን ለብቻቸው አጥብቀው ለመያዝ ተፈተኑ።
ለንጉሣቸውም አሳወቁ። ንጉሣቸውም ለእርስታቸው መደፈር እንቅልፍ የሚይዛቸው አልነበረምና፡- «ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፤ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ።
ከእንግዲህም ብሞት ሞት የሁሉ ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ ልዑል እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት ልዑል እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል።
እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በልዑል እግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።
የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም። አሁንም ጉልበት ካለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅ፣ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በኀዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፤ እግዝዕትነ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።
ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።» ሲሉ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም ለሕዝባቸው አዋጅ አወጡ።
ሕዝቡም ለንጉሡ ታዛዥ፤ ለአገሩ ጉዳይ ሟች፤ ለነፃነቱ ወደኋላ የማይል ነበርና ጥሪውን ተቀብሎ ዳር ድንበሩን ለማስጠበቅ ከአራቱም አቅጣጫ ተመመ። በሺ ኪሎ ሜትሮች በእግርና በፈረስ ተጉዞም፣ በር ገንጥሎ ወደ መሃል ሊገሰግስ ቋምጦ ጉበኑን በማለፍ ላይ ያለውን ጠላት ዘልቆ ሳይገባ ዓድዋ ላይ አገኘው። ዓድዋ ላይ የተገኘው ጠላት በእብሪት ሲደነፋ፣ በያዘው መሣሪያ ተመክቶ ሲያቅራራ፣ ጥቁርን ዝቅ አድርጎ ለራሱ በሰጠው ከፍ ያለ ግምት በባዶ ጉራ ሲወጠር፤ ከአራቱም አቅጣጫ በመደፈር ስሜት የተመመው ሐበሻ በጥበብ በታገዘ አመራሩ፣ በወኔ በተሞላ ጀብዱ የሐበሾቹን ምድር ከወራሪ እንዲጸዳ አደረገ።
ዓድዋ ላይ የጥቁሮችን የድል ጅቦ ለኩሶ፤ የነጮችን ተሸናፊነት አወጀ። አውሮፓውያን የቅኝ ግዛት የመረባቸውን ዕጣ ሲሰናዘሩ ዕድለቢሷ ጣሊያን ከደረሷት አገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በዓድዋ ተራሮች ላይ የተዘረጋውን የወራሪ ጦር እንዳልሆነ አድርጋ ስትበትነው፤ ብዙዎች ይሄን ማመን ተስኗቸው ነበር። ሆኖም እውነት ምን ጊዜም እውነት ነውና የሆነውን ለመዘገብ፤ በታሪክ ጽፎ ለማኖር ግድ ሆነባቸው።
የዚህ ሽንፈትና ውርደት ካባ ልኬ አይደለም ያለችው ጣሊያን ታዲያ፤ 40 ዓመታትን ቂም አርግዛ ቆይታ ለዳግም ወረራ ወደ ኢትዮጵያ አቅንታ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህም በለስ ሳይቀናት አምስት ፍሬ አልባ ዓመታት ስትዋትት ኖራ ተሸንፋ ለመውጣት ተገድዳለች።
ምክንያቱ ደግሞ የትናንት አባቶቻቸው ልጆች በወቅቱም ኢትዮጵያን ላለማስገዛት፤ በደም ተጽፎ የተሰጣቸውን ነፃነት አስደፍረው አንገታቸውን ዝቅ ላለማድረግ በያሉበት ተናብበውና ተባብረው ወራሪውን ፋታ በመንሳት ነበር የወራሪውን ተስፋ አጨልመው የመለሱት። ይህ ዳግም ውርደቱ ደግሞ በዓድዋ የተለኮሰው የነፃነት የድል ችቦ የበለጠ እንዲበራ እና ደምቆ እንዲታይ አደረገ።
የኢትዮጵያውያን ሕብረት እና አንድነት ለሌሎች የተስፋ ብርሃንን ፈንጥቆ፣ ለአሸናፊነት የመነሳት ስነልቡናን አላበሰ። በዚህም ዓድዋ የነፃነት ችቦ የተለኮሰበት፣ የኢትዮጵያውያን የድል ገድል የታተመበት፣ የኢትዮጵያውያን የአንድነታቸው ትስስር ማህተም ያረፈበት ታላቁ የታሪክ ምዕራፍ ብቻ ሳይሆን፤ ዓድዋ ጠንካራዋ ኢትዮጵያ የመፍጠሯ ምስጢርም ነው።
ይህ በሕብረት ተጋድሎ የተገኘ ድል፤ የጠንካራና አልደፈር ባይ አገርና ሕዝብ አሻራ ሆኖ የሚነበብ የአንድነትና ሕብረት ማህተም ያረፈበት ቀን ታዲያ፤ ዛሬም ድረስ ሰዎች ሲተባበሩ የማይፈቱት፣ የማይረቱትና የማይሻገሩት ምንም ነገር እንደማይኖር ሕያው ምሳሌ ሆኖ ይገለጻል።
ለዚህም ነው ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የመተባበር እና በአንድ ቆሞ የማሸነፍ የድል በዓል የሆነው። ይህ ሲባል የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ነው፤ ከፍ ሲል የአፍሪካውያን፤ ሲጠቃለልም የመላው የዓለም ጭቁን ሕዝቦች ነፃ የመውጣት ድልን ያጎናጸፈ በዓል ነው የሚባለው።
ይህ ደግሞ ብሂል ብቻ አይደለም፤ ተግባርም እንጂ። ምክንያቱም ድህረ ዓድዋ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው የዓለም ጭቁኖች «እንቢኝ አልገዛም» ብለው እንዲነሱ፤ ለነፃነታቸው ታግለው ነፃ እንዲወጡ የአሸናፊነት ስነልቡና አላብሷቸው ታይቷል።
እናም ዓድዋ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጭቁኖች በሕብረት ቆሞ የማሸነፍ አቅም የፈጠረንል፤ አንድ ዓይነት በደል የደረሰብን፣ ከአንድ አቅጣጫ የሚፈስስፍ የግፍ ጽዋ በአንድ መንገድ የተጎነጨን፤ አንድ ዓይነት ግፍና መከራ የደረሰብን፤ በብዙ መልክ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ያሉን ሕዝቦች በአንድ እሳቤ ቅኝ አገዛዝን ተዋግተን እንድናሸንፍ የአንድነት ስሜት የፈጠረልን የአንድነታችን ማህተም ነው የምንለው።
ዛሬም ይኸው ማህተም አብሮን ያለ፤ የሚኖርም ነው፤ ስለዚህ ይሄን ማህተም መጠበቅ፤ ማላቅ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል። አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ፤ ሰላም!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን የካቲት 22 /2014