የ2010ሩን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ “ባለቤት አልባ” ሕንጻዎች በርከት ብለው መገኘታቸው ሲነገር ነበር:: በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በአንድ ሰሞን የማጣራት ሥራ ብቻ ከ100 በላይ ባለቤት አልባ መገኘታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በሂደት በርከት ያሉ ባለቤታቸው ያልታወቁ ሕንጻዎች ስለመገኘታቸውም ነው የተነገረው:: እነዚህ ሕንጻዎች ባለቤት አልባ ሲባሉ በእርግጥ ባለቤት ስለሌላቸው አልነበረም:: ምክንያቱም ሲገነቡ ያስገነባቸው አካል፤ የገነባቸውም ተቋራጭ አለና ነው::
ይሁን እንጂ እነዚህን ሕንጻዎች ያስገነባቸው አካል በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መሪ ይዞ እንዳሻው ሲዘውር የነበረ ቡድን አባላት፣ አገልጋዮች እና አጋፋሪዎች ስለነበሩ፤ በማንአለብኝነት በየቦታው አስገንብተው እና አከራይተው እንደ ጥገት ላም በየወሩ አልያም በየዓመቱ (እንደ ኪራይ ውላቸው ሁኔታ) ገንዘብ የሚያልቧቸው ሰነድ አልባ ሕንጻዎች ነበሩ::
እነዚህ ሰነድ አልባ ሕንጻዎች ታዲያ ለውጡን ተከትሎ የሃብት ማጣራት ሲደረግ የእገሌ ነኝ የሚሉበት አንደበት ስለሌላቸው መጠሪያ አልባ ባለቤት የለሽ ሆነው “ባለቤት አልባ ሕንጻዎች” ለመባል በቁ:: ሆኖም ባለቤታቸው አንድም በአካባቢያቸው ሆኖ የሚጎበኛቸው፣ የእኔ ነው ቢሉ ከምን አምጥታችሁ ሰራችኋቸው ሊባሉ ሆኖ ዝም ያሉ ሆነው፤ ካልሆነም ራሳቸውን ወደ አንድ ጥግ ካስቀመጡት ጉምቱ የዘረፉ ሃብት አካባቾች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል:: እነሱ እገሌ ነው ባይሉ፤ እኛም የእገሌ ናቸው ማለት ቢሳነን ያለግብራቸው ስም ሰጥተን “ባለቤት አልባ” አልናቸው::
ዛሬም ባለቤት አልባ ሕንጻዎችን ያሳየን ለውጥ፤ ሌላ ባለቤት አልባ ጉዳይ እንድንመለከት የግድ ብሎናል፤ ከባለቤት አልባ ቤቶች ወደ ባለቤት አልባ የዋጋ ንረት ተሸጋግረናልና:: ምናልባት የዋጋ ጉዳይ ሲነሳ “ምነው ዋጋን የሚቆጣጠር፣ ገበያን የሚመራ ተቋም ባለበት አገር እንዴት ‘ባለቤት አልባ የዋጋ ንረት’ ይባላል”? ትሉ ይሆናል::
እርግጥ ነው መንግስት እንደ መንግስት የግብይት ሥርዓቱን የሚቆጣጠርና የሚመራ ተቋም አቋቁሞ፤ ሹመኞች መድቦና ባለሙያዎችም በየደረጃው ቀጥሮ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ በየወሩ ከሕዝብ የተሰበሰበውን ሃብት ምንዳ ይከፍላል:: ምንደኞቹም ከቢሮ ውለው መግባትን፤ ወር ጠብቀው ምንዳ መቀበልን ሳይዘነጉም፣ ሳይዘገዩም ይከውናሉ:: ዋናው ጉዳይ ታዲያ እነዚህ የንግዱ ዘርፍ ምንደኞች ንግዱን ስለምን በወጉ መምራት፤ ዋጋውንስ ስለምን መግራት አቃታቸው? የሚለው ነው::
ይህ ጉዳይ በትንሹም በትልቁም የሚጠየቅ፤ በተራው ዜጋም፣ በመንግስት አካሉም የሚወገዝ፤ የዜጎችን በልቶ የማደር አቅምን እየተፈታተነ ያለ፤ የሕዝብን ብሶት እና ምሬትን የመቋቋም ትዕግስት እስከማላሸቅ የደረሰ ሆኗል:: በዚህ መልኩ የሚገለጸው የዋጋ ንረት በተለይም የሸቀጦች ዋጋ ላይ የሚታየው ከእለት እለት መቆሚያ ያጣ የዋጋ ጭማሪ መቼ የት ቦታ ይገታ ይሆን? የሚለው የሁሉም ዜጋ በተለይም በወር ደመወዝ የሚተዳደረው ሰራተኛ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ደጋግሞ የሚነሳ ጥያቄ ነው::
ምናልባት ያልደረሰበት ሆኖ፤ ምንም ችግሩ ቢከፋ የችግሩን ገጽ ሊገነዘብ የማይችል ጥቂት የኅብረተሰብ ክፍል ሊኖር ቢችልም፤ የሸቀጦች ዋጋ በጥቅሉም የምርቶችና አገልግሎቶች የገበያ ዋጋ ለአንድ ቀን እንኳን ረግቶ ያለመገኘት ነዋሪዎች ይዘው በወጡት ብር ያሰቡትን ገዝተው መግባት ያልቻሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል::
እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው መሰረታዊ ጉዳይ የዋጋ ንረቱ ምክንያት ምንድን ነው? የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ እያደረገ ያለው አካል(ባለቤቱ) ማን ነው? ይሄን የዋጋ ንረት ከመከላከል አኳያ የዘርፉ ተቋም ምን እየሰራ ነው? ከሰራስ ምን ውጤት አስገኘ? ውጤት ካላስገኘስ ውጤት ያላስገኘበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚሉት እና በመጨረሻም የዋጋ ንረቱ ባለቤት ኖሮት ከሽቅብ ሽምጡ ፋታ የሚያገኘው መቼ ነው? የሚሉት ጉዳዮች ናቸው። እኔም እነዚህን ይዤ የሰማሁትንም፤ የታዘብኩትንም ለማለት እሞክራለሁ::
የዋጋ ንረቱ ምክንያት ተብለው ከሚነሱ ቀዳሚ ጉዳዮች መካከል የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ:: ይሁን እንጂ እነዚህ በምክንያትነት የሚቀርቡ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሁሉም ቅቡልነት ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም:: ለምሳሌ፣ አንዱ ምክንያት የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ነው። በዚህ ረገድ የሸቀጦችን ዋጋ ማየት ቢቻል፤ በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል አርሶአደሩ ምርት አምርቶ በዝቅተኛ ዋጋ ሲሸጥ፤ አንዳንዴም ያመረተው ምርት ገዥ አጥቶ በማሳ ላይ ተበላሽቶ ማየት የተለመደ ነው::
ይሁን እንጂ በክልል ዋና ዋና ከተሞችም ሆነ በአዲስ አበባ ያለው ዋጋ አምራቹ ከሚሸጥበት በእጥፍ እና ከዚያም በላይ ከፍ ያለ፤ ምርቱም ኖሮ ዋጋው የማይቀመስ የሆነበት ነው:: ይህ ምናልባት ከአርሶ አደሩ የመጣው ምርት እሴት ተጨምሮበት የተፈጠረ የዋጋ ልዩነት ቢሆን የተወሰነ ሊያሳምን የሚችልበት እድል ነበር፤ ነገር ግን ከማሳ ተሰብስቦ በቀጥታ ወደከተሞች የሚሄድ የግብርና ውጤት ላይ (ያውም ምርቱ ሳይጠፋና እጥረት ሳይኖር) የሚታይ የዋጋ መጋነን ገበያውን በወጉ ካለመምራት የሚመነጭ ካልሆነ በስተቀር ከፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ጋር የሚያያዝ ሊሆን አይችልም::
ሌላው ሊነሳ የሚገባው በዚህ መልኩ የምርት እጥረት በሌለበት ሁኔታ የዋጋ ንረቱ ከእለት እለት ማሻቀቡ፤ ግስጋሴውን የሚወስነው ጣራ መጥፋቱ ለምን ይሆን? የዚህ ተግባር ተዋናዩ ማን ነው? የሚለው ነው:: በዚህ በኩል ገበያውን የሚመራው የመንግስት አካል የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ልልነትን ማየት ይቻላል:: ምክንያቱም አንድ ምርት እጥረት ሳይኖርበት (ለምሳሌ፣ ከአርሶአደሩ ማሳ የሚመጡ የግብርና ውጤቶች) ከእለት እለት ዋጋ ሲያሻቅብ ዝም ብሎ መመልከት የአሰራር ችግር፤ የክትትልና ቁጥጥር ልምሻነት እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም::
ከዚህ ባለፈ ሃይ ባይ ያጣውና በገበያው ውስጥ እንዳሻው የሚንፈላሰሰው ደላላ ለችግሩ መፈጠር አንዱ ብቻ ሳይሆን ቀንደኛው ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል:: ከአርሶአደሩ በወደቀ ዋጋ የሚገዛው ምርት ተጠቃሚው ጋ ሲደርስ የማይቀመስ ዋጋ ወጥቶለት እንዲሸጥ በማድረጉ በኩል ደላላው በቅቤ ጠባሽ ምላሱ የሚፈጥራቸው አሳሳች መረጃዎች እና የገበያ ሰንሰለቶች ነጋዴውን ዋጋ እንዲጨምር፤ ሸማቹም ባልተገባ ዋጋ እንዲሸምት የሚያስገድዱ ናቸው::
የንግዱን ሥርዓት እንዲመራ በተሰየመው ተቋም የአሰራር ልምሻነትም ሆነ በባለ ቅቤ ጠባሽ ምላስ ደላላዎች ያልተገቡ አካሄዶች የሚፈጠረውን አርቴፊሻል (ተፈጥሯዊ ያልሆነ ሰው ሰራሽ) የገበያ ዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ከማቃለል አኳያ የተሞካከሩ ስራዎች መኖራቸው ባይካድም፤ ምን ያህል ውጤት አመጡ? የሚለውን ጠይቆና ዳስሶ ማለፉ ተገቢ ነው:: በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር በአርሶአደሮች ማሳ ተገኝተው የምርት እጥረት አለመኖሩን፤ በዋጋ ደረጃም ቢሆን አርሷደሩ በርካሽ እንደሚሸጥ፤ ነገር ግን በመሃል ባለው ደላላ በኩል የምርት እጥረት እንዳለ በማስወራት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ ስለመሆኑ አረጋግጠው፤ የእሁድ ገበያዎች እንዲጀመሩ ተደርጓል::
ይህ በተወሰነ ደረጃ የኅብረተሰቡን ችግር ለማቃለል አግዟል:: ይሁን እንጂ ይህ ተግባር በሚፈለገው ልክ የኅብረተሰቡን ችግር ፈትቷል ማለት አያስችልም። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ደረጃ የተጀመሩት የእሁድ ገበያዎች በተወሰኑ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ናቸው:: እነዚህን ገበያዎች የሚፈልጋቸው ደግሞ በአመዛኙ ድሃው የኅብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ፤ ወደገበያዎቹ ለመድረስ ረዘም ያሉ የታክሲ ጉዞዎችን ማድረግ ስለሚጠበቅበት ለተጨማሪ ወጪ እንዲዳረግ እያደረገው ይገኛል:: በመሆኑም ይህ መልካም እሳቤ የበለጠ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ገበያዎቹን ማስፋት፤ ረዣዥም የደላሎች እጅ እንዳይበክለውም መከላከልም ያስፈልጋል::
በዚህ ላይ የታየው መልካም ጅምር እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ የመንግስት የገበያውን ሥርዓት የመምራት ጉድለት በጉልህ ያሳዩ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው:: በተለይ መንግስት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገላቸው ወደ አገር የሚገቡ እንዲሁም በአገር ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረጉ ያሉ እንደ ዘይት፣ ስኳር እና የስንዴ (የፊኖ ዱቄት)ን ማንሳት ይቻላል:: እነዚህ ምርቶች የኅብረተሰቡን ጫና ለመቀነስ ሲባል ከፍተኛ ድጎማ የሚደረግባቸው እንደሆነ ይታወቃል::
ለምሳሌ፣ የዘይት ምርት ከውጪ ሲገባም ሆነ በአገር ውስጥ ሲመረት ከሚደረገው ድጎማ ባሻገር፤ በቅርቡ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲነሳለት ተደርጓል:: ይህ ደግሞ ቢቻል ከነበረበት ዋጋ ዝቅ እንዲል፤ ካልተቻለ ደግሞ ባለበት እንዲቆይ ሊያደርግ ግድ ነበር:: ነገር ግን የተጨማሪ እሴት ታክስ በተነሳ ማግስት ነው የዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ የተደረገው፤ ዛሬም ድረስ ልጓም አጥቶ በ360 ሲሸጥ የነበረ አምስት ሊትር ዘይት ዛሬ ላይ ከ700 ብር በላይ ዋጋ ወጥቶለት ነው በአደባባይ እየተቸበቸበ ያለው።
እዚህ ላይ፣ ነጋዴው ሃሳቡም ዘመዱም ገንዘብ ሆኖ የእለት ገቢውን እያሰበ ዋጋ ቢጨምር የሞራል ዝቅታውን እንጂ ሌላ ላያሳይ ይችላል:: ነገር ግን ይሄንን ነጋዴ እንዲመራ የተቀመጠው አካል ጉዳዩን በዝምታ ለምን ይመለከተዋል፤ በተደጋጋሚ የሚያስቀምጣቸው ገደቦችና አሰራሮች ሲጣሱስ በቸልታ ማለፉ ለምን ይሆን፤ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ነው:: ምክንያቱም ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ ዘይትን ከዚህን ያህል ዋጋ በላይ አትሽጡ ይላል፤ በዚህ ጊዜ ዘይት ከገበያው እንዲጠፋ ይደረጋል፤ አንድ ሰሞን ሱቅ ለመፈተሽ ሙከራ ይደረግና ውሃ የሚቋጥር ውጤት ሳይገኝ ይታለፋል::
ከዛም እንዲቀንስ የተባለው ዋጋ ባለበት እንኳን መቆየት አቅቶት ከፍ ብሎ ይተመንና ሱቁ ሁሉ በዘይት ይጥለቀለቃል:: ተቸግሮ የከረመው ሕዝብም የሚከራከርለት ተቋም ባለመኖሩ እያዘነ ከሌለው ላይ አብቃቅቶ ለመሸመት ይሰማራል:: ይሄን አይነት ተደጋጋሚ ትዕይንት የዘመናችን ገበያ መገለጫ ሆኗል። የሚገርመው ችግሩን ማን ፈጠረው ሲባል፤ ነጋዴውም የመንግስት አካልም አብሮ ጠያቂ መሆኑ ነው::
በዚህ መልኩ ምርቱ ሳይጠፋ በሰው ሰራሽ ደባ በሚፈጸም አሻጥር፤ ያዝ ለቀቅ እያሉ ዘላቂነት በሌላቸው፣ ቢኖሩም አሉ ለማለት ያህል በሚፈጠሩ የማረጋጊያ አሰራሮች፤ አስገዳጅ የሚመስሉ ነገር ግን ከቃል ያለፈ ተፈጻሚነት በሌላቸው የእርምት እርምጃዎች እና አሰራሮች የፈጠረው የማን አለብኝነት ስሜት፤ በመንግስት ተቆጣጣሪ አካልም ሆነ በነጋዴው ላይ በሚታይ የአሰራር ግድፈትና የሕግ ጥሰት የሕግ ተጠያቂነቱ ልል መሆን፤ በገበያው ላይ የተንሰራፋው የጋራ ተጠቃሚነት ሸፍጥ፤… በጥቅሉ ባለቤት የለሽ በሚመስለው የገበያው መድረክ ሕዝቦች ለከፋ ችግር፤ ለመረረ ቅሬታ ተዳርገዋል::
በዚህ መልኩ ገበያው በማን እንደሚመራ፤ ዋጋውም በማን እንደሚተመን በማይታወቅበት መልኩ የሚፈጠር የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት ደግሞ፤ ዋነኛ ተጎጂ ሕዝቡ ነው:: ሕዝቡ ደግሞ ዛሬ ቅድሚያ ለአገሬ እና ለሕልውናዬ ብሎ አንጀቱን አስሮ በየጓዳው እያነባ ያለ ነው:: ይህ እንባ ያበረ እለት፤ ረሃብ በየቤቱ ከፍቶ የተገለጠ እለት ታዲያ ምላሹ ምን ሊሆን ይችላል:: ትናትን በእነ ሱዳን የዳቦ ዋጋ ላይ አምስት ሳንቲም ተጨመረች በሚል ምክንያት የታየው አብዮት ተምሮ ለገበያው ሁነኛ ባለቤት መስጠት እና የህዝብ እንባን ማበስ ረሃቡንም ማስታገስ ተገቢ ይሆናል::
ሕግና መንግስት ባለባት አገር፤ ሕገ ወጦች በዝተው በተዛባ ጉዟቸው፤ በአልጠግብ ባይ ሕልማቸው ድሃውን መበዝበዝና ጾም ማሳደር የሆነ ቦታ በቃ ሊባል የተገባ ነውና ይሄው ሊሆን ያስፈልጋል:: ገበያው ባለቤት ኖሮት በሕግ ሊመራ፤ ሸማቹም ተቆርቋሪና ሰሚ አግኝቶ ሸምቶ ማደር የሚችልበት ምህዳር ሊፈጠርለት ያስፈልጋል:: ባለቤት ላጡ ተግባራት መዳረሻ አልባ ጥያቄን እየሰነዘረ፤ ሰሚ አልባ ሮሮውን እያሰማ፤ አባሽ አልባ እንባን እያፈሰሰ ሊኖርም አይገባውም::
ከህዝቡ የሆነ ነገር ሲፈልግ በየቤቱ እያንኳኳ የሚጠይቅ አካል፤ ሕዝቡ ወደ ቢሮው ሄዶ ሲጠይቀው ጥያቄውን አድምጦ መፍትሄ መስጠትን መለማመድ ይኖርበታል:: ከዚህ ባለፈ እሱ ሕዝቡን ሲፈልግ በአድራሻው ሄዶ የሚያፋጥጥ፤ ሕዝቡ እሱን ሲፈልግ አድራሻው ላይ ተገኝቶ ምላሽ የማይሰጥ ተቋምም፤ ኃላፊና ባለሙያ ጉዳዩ የሕዝብ አይደለምና ሚናውን ለይቶ በማልያው ሊጫወት ይገባል:: የሕዝብን ምሬት ልክ ያሳጣው የዋጋ ንረት ጉዳይ ባለቤት ኖሮት ከሽቅብ ሽምጡ ፋታ የሚያገኝበት አሰራር ሊዘረጋ፤ አሰራሩም በጥብቅ ሊፈጸም ይገባል እላለሁ:: አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ፤ ሰላም!
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም