ግራ በመጋባት በጥያቄ ብዛት ዞር ዞር ቢያደርገኝ ብእሬን ከወረቀት ላገናኝ ተነሳሁ። እንደው እንደ አቅሚቲ ከፃፉቱ እኩል ልታይ ባይዳዳኝም እሞካክራለሁ። እስኪ ልነሳና ልጀመር ጨዋታ፤ በየመንገዱ ላይ የጥያቄ ብዛት የወሬ ጋጋታ የማን ነሽ? ምንድነሽ? ከየት ነሽ?” ይለኛል ከየትስ ብመጣ? ምን ያስጨንቀዋል። የሰውነት ክብር ሰው የመሆን ልኬን ፈጣሪ ሳይነፈገኝ የምን ጥያቄ ነው ከየት ነሽ ? ወዴት ነሽ? ምንድ ነሽ? ቆይ ማነሽ? ብሎ መጠያየቅ። ባለቅኔው፣ አዝማሪው፣ ዘፋኙ… ሁሉ ይሄንን ነው የሚለው ከየት ነህ ከየትነሽ የሰውን ልጅ አትበሉ። ለዚህ መሰሎኝ ቅሉ የአድዋው አርበኞች ሄደው የወደቁ።
አንድ ለመሆን ሚስጥር የአረንጓዴ ቢጫ የቀይ ቀለም ገመድ የመተሳሰሪያው የአንድ መሆን ሚስጥር ዛሬ ለቆምኩበት ለአንገቴ መቀናት ሰው ተከፍሎበታል ከደምና ከአጥንት። ገድዬ አልፎከርኩኝ ሞቶብኝ ነው እንጂ ግራ የተጋባሁት የደም ጎርፍ እንደ ውሃ ሲፈስ እያየሁት የማነህ ከየት ነህ በሚል አልባሌ ውሃ አይቋጥር ወሬ ኧረተው ነቃ በል ርካሽ አይደለህም የተከፈለልህ ከሁሉ ይልቃል። በወርቅ በብር በአልማዝ በቁስ አይለካም የደም ዋጋ ክብሩ ከሁሉ ይበልጣል። ዋጋው ይግባህና ከተኛህበት ንቃ ሰው አይርገፍ ንቃ የሰው ቅጠል ይብቃ።
ገዳይ ንፁህ ፈጅቶ በኮራበት ሀገር ባጠፋው ሳይቆጭ እየተጎማለለ እያቅራራ ሲኖር ለተገፋ ማልቀስ ለምነው ‘ሚያስወግር? ለምነው የሚያስነቅፍ እኮ ለምን ብሎ የድሃው እንባ ይታበስ ሲባል ጦርነት ያበቃል አቅላችሁን ሰብስቡ ራሳችሁን እዩ ይበቃል ይበቃል ያለው ይኑርበት ቀሪው ይረፍበት ለምን ይጠየቃል? ለምን ይወቀሳል የፈጣሪን መንገድ መመሪያው አድርጎ ሰላም ይሻላል፣ ምክክር ይበጃል ያለው ሰው ለምንስ ይጠላል።
ገዳይ እንደው ክፉ ገድሎም አይበቃውም “እሰይ” ብሎ አይረካ ሬሳን በሬሳ ላይ ደምን በደም እየቀላቀለ እያጣጠበው ከሰው አቅም በላይ ከህሊናም በላይ ከሰው ሀሳብ በላይ ሰቅሎ ከቅጠል በታች እንዳልባሌ እቃ እንደ ቆሻሻ ጨርቅ እንደተራ ወድቆ ልብ ከደነደነ የወገኔ ማለቅ የኀዘኔን መብዛት የእንባዬን መፍሰስ ከክፋት ከታየ እንባዬን አድርቆ ኀዘኔን መቀማት አዲስ ወሬ ሆኖ ዝም ብሎ ከጣለ ያኔ…..ያን ግዜ ማለፉ መተውም እጅግ ይከብዳል። እናም እጮህለታለሁ በማንነቱ አይሰቃይ አይገደል ብዬ ።
እዚህ ጋ ልወለድ ከእገሌ ዘር አርጉኝ ብሎ ያለ አለ? ዘሩን የመረጠ? አንድም ሰው እኮ የለም ማንም አልፈልግም እኔን ከኦሮሞ ፣ ከወላይታ ወይ ከአማራ ደግሞ ከትግሬ አድርጉኝ ያለ። ንፁሁ ሲጎዳ ባልመረጠው ደሙ ባልመረጠው መልኩ እሱ ባለሰራው ሥራ፤ መዳኛዬ ብሎ ከሞት ኋላ ህይወት ቢኖርልኝ ብሎ በእምነት ለተገዛው መንዙማ መዝሙሩን ቆሞ የዘመረው ክርስቲያንም ሙስሊም ጥፋት ከሆነበት በምርጫ ማምለኩ ወንጀል ከሆነበት እንባዬ አይቆምም ዛሬም አነባለሁ ፤ዝም ብዬ እጮሃለሁ……. ሰሚ እስካገኝ ድረስ።
ለህዝቤ አለቅሳለሁ ደረቴን እየደቃሁ እሪታዬ በዝቶ ፊቴን እየነጨሁ አሁንም እጮሃለሁ….. በጅምላ ለሚያልቀው ለሚፈሰው ደሙ አንጀቴ ይላወሳል እንባዬ ግድብ የለው ዝንብሎ ይፈሳል። ሰቀቀን ለበላው ለድሃው ወገኔ ጦርነት ሲጎሰም በልቶት ሰቀቀኑ፣ ስደት ለመረጠው ከገዛ ሀገሩ ፣ ከገዛ ወገኑ።
ለተደፈረችው ፣አንገቷ አቅርቅሮ ቀና ማለት ላቃታት ለተሰበረችው እንግልት እህቴ፣ ለከርታታይቱ መማር ማደግ መሮጥ በሚለው እድሜዋ የሰቀቀን እንባ ከፊቷ ለሚፈሰው፤ አብሬ አለቅሳለሁ ላዘነች እናቴ፤ ለአማራ እጮሃሁ፤ ለትግሬ እጮሀለሁ፤ ለኦሮሞ ወንድሜ፣ ለደቡብ አባቴ፣ ለሀረሪ፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋር፣ ድሬዳዋ ላለው ወገኔ ፤ ለሁሉም እጮሃለሁ ሁሉም የአባቴ ልጅ ሁሉም ወንድሞቼ ሁሉም እህቶቼ ወገኖቼ እላለሁ።
ለተበዳይ ህዝቤ፣ ለሞተ ወገኔ…ለተራበው ለሱ በጠኔ ላለቀው ለእናቴ ለአባቴ ለእህት ለወንድሜ እጮህለታለሁ! ሰሚ ጆሮ ባገኝ በቃችሁ ስላቸው የሚያበቃ ቢኖር ገዳይም ሟችም የኔው ወንድም እህት ኀዘኔ ቅጥ አጥቶ ከቤቴ ሳይወጣ በግራ መጋባት ዓይኔን እያንከራተትኩ እንባዬን አፍስሼ እጮህለታለሁ።
የመከፋፈሉን፤ በጎጥ ማሰለፉን፤ ቡድኑን አንተ አብጀው ወገኔ መሆኑን የአንድ ማህፀን ብቃይ ስጋዬ መሆኑ ንፁህ መሆኑ ነው የሚያገባኝ እኔ፤ በመከፋፈል ውስጥ በመቆራረሱ በመመራረጥ ውስጥ አለማለፉ ነው የሚታየው ዓይኔ። ትናንት ጮኼያለሁ፣ እጮሃለሁ ዛሬ፣ እጮሃለሁ ነገ ሁሉም ወገኔ ነው ድምፅ የተነፈገ።
እጮህለታለሁ! ድምፄን ከፍ አድርጌ ሰሚ ጆሮ ባገኝ ጩኸቴ ተሰምቶት አንተም ተው አንተም ተው የሚል ትልቅ አባት አስታራቂን ባገኝ።ምክክሩ ሰምሮ እንባ ደርቆ እስከማይ።
በዝያ ሞት በዚህ ሞት ሰቆቃ ማዳመጥ አየሩን አጣቦት እዚህም ቤት እዛም ቤት ትኩስ ንፍሮ ቀርቦ ነጠላ ተዘቅዝቁ ድንኳኑም ተጠሎ ኀዘን በኀዘን ላይ እየተደራረበ በግራ ገባኝ ደራሽ እስኪጠፋ ባዶ ድንኳን ብቻ ብቻ እንባ መጭመቀ ዓይን እስኪጠፋ። አባቴ ተሰቅሎ፣ ወንድሜ ተቃጥሎ፤ እህቴ ታግታ፣ እናቴ ተደፍራ። አያቴ ተሰ’ዶ ህፃን ልጄ ታርዶ… አሞኛል… አሞኛል ! ወገን ሞቶብኛል! ሰው ተገ’ሎብኛል በማያውቀው ጉዳይ ባልገባው ጨዋታ ዋጋ ከፍሎብኛል።
በሌለበት ግንባር ባልዋለበት ሜዳ ቀድሞ እየተመታ፣ቀድሞ እየወደቀ፤ አንሺ በሌለበት አፈር አልባሽ ወገን የአሞራው ሆድ ጠገቦ ጅብ ቁንጣን እስኪይዘው ቀድሞ እየተሰዋ፤ ተጨምቆ ተጨምቆ ጠብ ላይልለት የድላቸው ፋይዳ፣ ለዜሮ ድምር ውጤት መከራ የሚገፋው እየወደቀበት በማያውቀው እዳ…።
በሰቀቀን በስጋት ልጆችን ሊሸሽግ ቢያጣ ጉድጓድ ውስጥ መክተቻ። ሞት እያንዣበበ… ደክሞት ካረፈበት ከደሳሳ ቤቱ፣ ለማይሞላ ኑሮው ለማይነጋው ሌቱ። ወትሮም ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ማጀቱ ሚላስ የሚቀመስ በታጣበቱ፤ ምን ልቁረስ ምን ላቅምስ በሚለው አንጀቷ በእንባ ለታጀበው ኀዘን ባኮሰሰው በሚያሳዝን ፊቷ፤ ይበቃል በቃችሁ የሰይጣን ፈረሶች ሰላም የጠላችሁ ይበቃል እላለሁ እጮህላታለሁ ላንቃዬ እስኪበጠስ ሰሚ ጆሮ ባገኝ ብዬ ለከፋው ወገኔ እንባ አባሽ እንዲኖር እጣራለታለሁ። ክፋት ፣ጠበኝነት፣ጠላት ብሎ መፈራረጅ ጥንትም ነበር እኮ ሆኖ ነው መፍትሄው ይቅርታ ማድረጉ። አሁንም እላለሁ ሁሉም ክፋት ይብቃ ! ምክክር ንግግር ደግሞ ይቅር ባዩ ዳር እስከዳር ይሙላ።
ብስለት
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም