የአስተማሪ ሕይወት መነሻው ልጅነት ነው ይባላል። አስተዳደግ ትልቅ ሆነው ለሌሎች አርአያ መሆንን እንደሚያላብስ ብዙዎች ይስማማሉ። የእውቀትና የችሎታም ምንጭ ይኸው እንደሆነ ያምናሉ። እናም የሕይወት መምህር ቤተሰብ በመሆኑ ሁሉም በቤተሰቡ ተሰርቶ ዛሬን እንዲያይ ይሆናል።
ይህ ደግሞ አሳዳጊዎች አለያም እናትና አባት የሰጡን ነገር መጥፎ ወይም ጥሮ አድርጎ ያቆየናል። ሕይወታችንንም ይመረዋል። ዘሩ በመልካም መሬትና በንጹህ ልብ ላይ ከተዘራ ፍሬውም ያማረ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ከዚያ በተቃራኒው ከሆነም እንዲሁ መራራ ፍሬን እናገኝበታለን። ይህ ደግሞ ለራስም ለአገርም ሸክም መሆኑ አያጠራጥርም።
ለዚህም ነው ቤተሰብ ልጁን ሲያሳድግ መሰረቱን ያስተካክል የሚባለው። ይህ ከገጠማቸው መካከል ለዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ ይዘንላችሁ ብቅ ብለናል። እንግዳችን ወይዘሮ አለሚቱ አበበ ይባላሉ። ከገጠር ቀበሌ ጀምሮ እስከ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድረስ አገልግሎት ለመስጠት የታደሉ ናቸው። በዚህ ጉዟቸውም በተለይ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ሰፊ ለውጥ ያመጡ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።
አሁንም እንደ ሕዝብ ተወካዮች አባልነታቸው ለተመረጡበት ሥራ የበኩላቸውን ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው። እናም ከሕይወታቸው ብዙ ትማራላችሁና አንብቧቸው ስንል ጋበዝናችሁ። አስተዋይዋ ልጅ ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ክልል ውስጥ ቡና ጣዋባ ቀበሌ በ1968 ዓ.ም ነው። ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ ሲሆኑ፤ በቤት ውስጥ ያለ ሥራ ተቀምጠው አያውቁም።
ሁሉንም በቻሉት ልክ ያከናውናሉ። ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ጭምር በጠዋት ተነስተው እበት ይጠርጋሉ፤ ቆጮ ይጨምቃሉም። ለዚህ ደግሞ ያነሳሳቸው እናታቸውን አብልጠው መውደዳቸውና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የሥራ ጫና ስለሚያስተውሉት ነው።
እርሳቸው ላይም ወደፊት እንደሚሆን ስለሚያሳስባቸው ከአሁኑ መለማመዱ ይገባል ብለውም ያደርጉታል። በእርግጥ የአባታቸው ነጻነት ሰጪነት ይህንን እንደሚቋቋሙት አሳምኗቸዋል። እናታቸውም ሥራ ይልመዱ ብለው ዝም ይሏቸዋል እንጂ ብዙ እንዲደክሙ አይፈልጉም።
እርሳቸውም ይህንን ያምናሉ። እናም እገዛቸው ‹‹50 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ›› እንደሚባለው በመረዳዳት ውስጥ ሥራ ይቃለላል ብለው ማመናቸው እንደሆነ ያስረዳሉ። ባለታሪካችን በተጨማሪ የውጭ ሥራውም ቢሆን በተለይ ከብት መጠበቁ አይቀርላቸውም።
እንደውም ደስተኛ የሚሆኑበት ተግባራቸው ነው። ምክንያቱም ከጓደኞቻቸው ጋር በግላጭ ተገናኝተው የሚጫወቱበት ጊዜ ነው። ብዙ ልምዶችና የጨዋታ አይነቶችን የሚማሩበት በመሆኑ ሥራውን ማከናወን ያስደስታቸዋል። ሌላው በልጅነታቸው የሚሠሩት ነገር የጓሮ አትክልትን መንከባከብ ሲሆን፤ ኃላፊነት ወስደው ጭምር ይተጉበታል። ለዚህም ምክንያት አላቸው።
ችግኝ መትከልና አረንጓዴ ነገር መውደዳቸው እንዲሁም በቀላሉ ገበያ ሳይኬድ የፈለጉትን መመገብ እንደሚቻል ማመናቸው ይህንን ተግባራቸውን አጥብቀው እንዲወዱትና እንዲሠሩበት ሆነዋል።
ወደ ግል ባህሪያቸው ስንገባ ደግሞ በቤተክርስቲያን የሕጻናት ትምህርት ስለሚከታተሉ ትሁትና አስተዋይ ናቸው። በመዝሙርም አገልጋይ ሲሆኑ፤ ልዩ ተሰጥኦዋቸው መዘመር እንደሆነ የተረዱት በዚህ አገልግሎታቸው ወቅት እንደሆነ ያነሳሉ።
በዚያው ልክ ተጨዋችና ሲነኳቸው የማይታገሱም ናቸው። እንደውም ስለተሰደቡ ብቻ ሕጻን ፈንክተው የሚገቡና ለራሳቸው የሚከራከሩ አይነት ልጅ እንደነበሩም ያስታውሳሉ። በእርግጥ በዚህ ውስጥ የተለየ ባህሪም አላቸው። ይህም አስታራቂ መሆናቸውና ቶሎ ይቅርታ የሚጠይቁ ልጅ መሆናቸው ነው። ጸብን አጥብቀው ይጠላሉ። ከራሳቸው አልፈው ልጆች እንዳይጣሉ ያደርጋሉ። ከተጣሉም ያስታርቃሉ። በዚህም ብዙ ልጆች ስሞታ ተነግሮባቸው አይገረፉም፤ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ጸብ ውስጥም አይገቡም።
ይህ ለምዶባቸው ዛሬም ድረስ አይደለም ከሌላ ሰው ጋር ከባለቤታቸው ጋር እንኳን አለፍ ያለ ንግግር አያደርጉም። መንግስት ሰራተኛ መሆን የልጅነት ህልማቸው ነው። ምክንያቱም ሙያውን የሚያስቡት ተጣጥቦ መብላት፤ ጸዳ ብሎ መሥራት ያለበት አድርገው ነው። ግን ከገቡበት በኋላ ያ እንዳልሆነ አይተዋል። ብዙ የሚለፋበትና ከተሠራበት አገርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጭምር የሚለወጥበት እንደሆነ ተረድተዋል።
በዚህም በተለይ ለሴት ልጅ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት ለመቀየር ይህንን ህልማቸውን እውን ማድረግ እንዳለባቸው ያስቡ ነበር፤ አድርገውታልም። ሴት ነጻ ሆና እንድትኖር ምን ያስፈልጋታል የሚለውን ከእናታቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብ እያዩ ማደጋቸው ደግሞ ለዚህ እንዳገዛቸው ያምናሉ። ለሴቶች ታጋይ የመሆናቸው ምስጢርም ይህ መሰረታዊ ጉዟቸው እንደነበር ያነሳሉ።
ሰርተፍኬቱ ማስተር ደርሷል አባታቸውም ሆኑ እናታቸው የተማሩ ናቸው። በተለይ አባት ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የሚያምኑ ሲሆኑ፤ እርሳቸውን በሁሉም መልኩ ይደግፏቸዋል። ሥራ እንዳያበዙ ጭምር ይቆጧቸዋል። አጥኚ የመጀመሪያው መርሃቸው ነው። እናት ደግሞ ብዙም ስላልገፉበት ከስራቸው ሳይለዩ እንዲያገለግሏቸው ይፈልጋሉ።
ቀለም ብቻ ሳይሆን ሙያም ተማሪ የሚል አቋም አላቸው። በዚህም ቤት ውስጥ በሥራ እንዲጠመዱ ያደርጓቸዋል። ነገር ግን የአባወራን ትዕዛዝ ማክበር የግድ ነውና ለእርሳቸው አባታቸው ነጻነታቸው ሆነውላቸዋል።
ጥሩ ተማሪ ሆነው የገፉትም ለዚህ ነው። የመማራቸውና እዚህ የመድረሳቸው ምስጢር አባታቸው የሆኑላቸው እንግዳችን፤ ትምህርታቸው አሀዱ ያለው በዚያው በትውልድ ቀያቸው አቅራቢያ በሚገኘው መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ነው። ቅድመ መደበኛን ጨምሮ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተከታትለውበታል።
ከዚያ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ለመማር ወደ ተፈሪ ኬላ ከተማ አመሩ። በዚያም ተፈሪ ኬላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገቡና ሁለቱን ክፍሎች አጠናቀቁ። እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ደግሞ የተማሩት ዲላ ከተማ ላይ ነው። አባታቸው በሥራ ምክንያት እዚያው ስለሆኑ ምንም ቸግሯቸው አያውቅም። ነገር ግን ራሳቸውን ጭምት አድርገው ስለቆዩ በብዙ ነገር ተፈትነዋል።
የመጀመሪያው በትምህርታቸው የተሻለ ተማሪ አለመሆናቸው ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ አብረዋቸው የሚያጠኑ ልጆች ማጣታቸው ነው። ከማንም ጋር አይገጥሙም። ዳቦ ጭምር ወጥተው አይገዙም። ጓደኞቻቸው ቤትም ሄደው የማጥናት እድል የላቸውም። ስለዚህም የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው የተጠበቀውን ያህል አልሆነላቸውም።
ለዚህ ደግሞ ተወቃሹ አባታቸው ሳይሆኑ ራሳቸው መሆኑን ያነሳሉ። ምክንያቱንም ሲያብራሩ ጥናታቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ወደከተማ ወጣ ሲሉ ተጽዕኖ ይፈጠርባቸዋል ብለው አስበው ስለሚንከባከቧቸው ከትዕዛዙ መውጣት የለብኝም በሚል ከቤት ሳይወጡ በራሳቸው አጥር ውስጥ ሆነው ይቆያሉ።
ብቻቸውን ገባቸውም አልገባቸውም ያነባሉ። በዚያ ላይ የእናት ናፍቆት አለባቸው። ቅዳሜና እሁድ እንኳን አባት እናታቸው ጋር ሲሄዱ በዚያ ከሆኑ የሥራ ጫና ይበዛባቸዋል ከሚል ስጋት አንጻር እርሳቸውን አይፈቅዱላቸውም። በዚህም ብቻቸውን ያሳልፋሉ። እናም ብቻ ማጥናት፣ ብቻ መዋልና ማደሩ ውጤታማ ሊያደርጋቸው አልቻለም።
እንደ ማንኛውም ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የሚማሩበትንና የሚመረቁበትን እድል ማግኘትም አልሆነላቸውም። ማትሪክ ከወሰዱ በኋላ በውጤቱ አለመሳካት የተነሳ እንዲናደዱ መንስኤ የሆናቸውም ይህ ነገር ነው።
በዚህም ቤተሰቤን በትምህርት ካላስደሰትኩ በትዳሩ ደስተኛ ላድርጋቸው ብለው የዛሬውን የትዳር አጋራቸውንና የትምህርታቸው ዳግም ጀመሪን አገቡ። በእርግጥ ይህም ቢሆን ዝም ብለው የወሰኑት አልነበረም።
የጓደኛቸው ወንድም በመሆኑ በቅርበት አውቀውታል። በዚያ ላይ የእርሱ አባትና የእርሳቸው አባት በጣም የሚዋደዱና ቤተሰብ መሆናቸው የሚያስደስታቸው ነበሩ። ስለዚህም እርሳቸውንም ቤተሰባቸውንም ለማስደሰት ጋብቻ ፈጸሙ። ከ1983 እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ የቤት እመቤት ሆነውም ቆዩ። በእርግጥ በዚህ መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ባልትና ትምህርትን በአገረ ሰላም መካነ ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስና ባልትና ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በሰርተፍኬትም ተመርቀዋል።
መደበኛውን ትምህርት ለዓመታት አልቀጠሉትም። ይሁን እንጂ ዓመታት ቢያልፉም በጠንካራው ባለቤታቸው አማካኝነት ዳግም ከትምህርት ጋር ተገናኝተዋል። ‹‹እርሱ ጠንካራ ብቻ ሳይሆን የሚስቱን ስኬትና ደስታ የሚወድ ሰው ነው›› ብለው የሚመሰክሩለት እንግዳችን፤ ብርታት ሆኗቸው አራስ ቤት ሳሉ የተፈጠረውን እድል እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል። ይህም ቲትአዬ ተወዳድረው ያለፉበት ሲሆን፤ ሕጻኗን ጭምር ይዞ ነው ወደ ትምህርት ቤት የላካቸው። ለዚህ መንስኤው ደግሞ የቤተሰቦቹ አመለካከት ነበር። በሁነቱ ቤተሰቦቹ እጅግ ተበሳጭተውባቸው ነበር።
አልፈው ተርፈው ‹‹የሰባት ወር ሕጻን እንዴት ትታ ትሄዳለች፤ ልጅቷ አንድ ነገር ብትሆን በሕይወቱ እንጠይቃታለን፤ የእርሷንም ሕይወት ከአንተ እንጠብቃለን›› እስከማለትም ደርሰዋል። ግን አቋም ያለው ስለነበረ አይመለከታችሁም ራሴ አሳድገዋለሁ ብሎ ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል።
ትንሽ እህታቸው ቤት ውስጥ ስላለች የመማር ጉጉት ያደረባቸው ወይዘሮ አለሚቱ፤ የሆነው ይሁን ብለው ነው ጨክነው ወደ ትምህርት ቤት ያቀኑት። በእርግጥ እድል ቀንቷቸው ሁኔታውን እናታቸው ሰምተው ለተወሰነ ጊዜ ልጅቷን ተንከባክበውላቸዋል።
የገጠሩ ሁኔታ ቢመቻት ኖሮም እስከሚጨርሱ ያሳድጓት ነበር። ግን ብዙም አልተመቻትምና መልሳ አባቷ ጋር እንድትሆን ተደርጓል። ይህ ሆኖ ብዙ አልተከፉም። ምክንያቱም የባለቤታቸውን ጥንካሬና ቆራጥነት ያውቁታል። እርሱም ቢሆን ፍጻሜውን አሳምሯል። ትምህርታቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ ተንከባከባት። በዚህም ዳግመኛ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ያስቻላቸውን ባለቤታቸውን እጅግ አድርገው ያመሰግኑታል።
የእናታቸውን ድጋፍ እንዲሁ ምስጋና የሚችሩት ጉዳይ ነው። የቲትአዬው ትምህርት ተጀምሮ የተጠናቀቀው በሐዋሳ መምህራን ኮሌጅ ውስጥ ሲሆን፤ በሁለገብ ትምህርት መስክ በመምህርነት ነው። ከዚያ በኋላም እንዲሁ ያለትምህርት ረጅም ዓመታት አልፈዋል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ልጆችን የማሳደጉና ሌሎች የሴቶች የሥራ ጫና ነው።
ትምህርት ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ማንነትንም የሚቀይር እንደሆነ የሚያምኑት ወይዘሮ አለሚቱ፤ መቼም ቢሆን በመማር ተስፋ ቆርጠው አያውቁም። እንደውም ቁጭታቸውን ድባቅ ለመምታት ይጣጣራሉ እንጂ። ስለዚህም ከሥራ ጋር መማር አይቻልም የሚለውን የመንግስት አመራር ሰብረው በድብቅ እንዲማሩ ሆነዋል። ይህም በ2003 ዓ.ም ዳግም ከትምህርት ጋር የተገናኙበት
ሲሆን፤ በአልፋ ዩኒቨርሲቲ በርቀት ትምህርት በፐብሊክ አድምኒስትሬሽን ትምህርት መስክ ዲፕሎማቸውን ይዘዋል። ሴቶች ጉዳይ ላይ እየሰሩ ባለበት ጊዜ ደግሞ ብዙ ሰዓታቸውን ሳይፈጁ ዲግሪያቸውን በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ትምህርት መስክ መማር ችለዋል። ይህም ቢሆን እንደቀደመው የመማር እድሉም ሆነ ፈቃዱ የላቸውምና በድብቅ ያደረጉት ነው።
ከዚያ አሁንም በይፋ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ማስተማራቸውን በቢዝነስ አድምኒስትሬሽን እንዲጀምሩ ሆነዋል። የመመረቂያ ጽሑፍ ብቻም ቀርቷቸዋል። ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ የክልል ተመራጭ ሆነው ሐዋሳ ላይ መከተማቸው ነው። እናም ደስተኛ ሆነው ትምህርቱን እየተከታተሉ ይገኛሉ። እንግዳችን ዶክትሬታቸውንም የመማር እቅድ አላቸው። በተለይ በአካል ተገኝተው የሚመረቁበት ቢሆን እጅግ ያስደስታቸዋል። ምክንያቱም በእነዚህ ጊዜያት አንድም ቀን ተመርቀው አያውቁም። ስለሆነም ያንን ቀን ለማየት ይጓጓሉ።
ሴትነትና ሥራው
የሥራ ‹‹ሀሁ›› የጀመረው በመምህርነት ሙያ ነው። ረጅም ዓመታትን በሁለገብ መምህርነት በቲትአዬ አገልግለዋል። ይህም ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ ነው። በዚሁ ሙያ እስከ 1999 ዓ.ም ድረስም ቦታ ቀይረው ሠርተዋል። በዚህ ጉዟቸው መምህር በመሆናቸው ብዙ የተጠቀሙት ነገር እንዳለ ያነሳሉ።
አንዱ ቤተሰብን አብሮ ማድረጉ ሲሆን፤ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ሳይለዩ የሚሠሩበትን አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ሌላው ሦስተኛ ልጃቸውን ቅሪት ስለነበሩ እንዳይርቁ አድርጓቸዋል። ስለዚህም ብዙ የእግር ጉዞ ሳይኖርባቸው ሴታሞ የሚባል ቀበሌ ላይ ከዚያም የበለጠ ቀርበው ዳራ ወረዳ ቀባዶ መለስተኛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሰሩ ሆነዋል።
ቀጣዩ የሥራ ምዕራፍ ሴቶች ላይ ለዓመታት የቆዩበት ሲሆን፤ መጀመሪያ የጀመሩትም ዳራ ወረዳ በሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና የሴቶች አቅም ማጎልበት የሥራ ሂደት ውስጥ በባለሙያነት ነው።
አንድ ዓመት ብቻ በመደቡ ላይ አገልግለዋል። ምክንያቱም ምክትል ሴቶች ቢሮ ኃላፊ ሆነው በመሾማቸው ቦታቸው ተቀየረ። አሁንም በዚህ መደብ አልቀጠሉም።
ዓመት ሳይሞላቸው ዋና ቢሮ ኃላፊ ሆኑና እንዲሠሩ ተደረጉ። ይህ ደግሞ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በሴቶች ዙሪያ የተለያዩ ለውጥ ያመጡ ተግባራትን እንዲፈጽሙ አገዛቸው። በተለይም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ አመርቂ ውጤት እንዲያመጡ እድል ሰጥቷቸዋል።
እንግዳችን ጥንካሬያቸውና ሥራቸው ለክልል ምክር ቤት አባልነት ያስመረጣቸው ሲሆን፤ ከወረዳው ወጥተው በቀጥታ በቀድሞ ደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሐዋሳ ላይ ከትመዋል። በዚህም የሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ዋና ሰብሳቢ ሆነው አምስት ዓመታትን አሳልፈዋል።
ከዚያ ሲዳማ ክልልነቷን ስትረከብ እርሷን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እንዲቀላቀሉት ሆኑ። የአዲሱ ምክር ቤት አባል ሆነውም ሥራቸውን ጀምረዋል።
በዋናነት በኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው እያገለገሉም ናቸው። ከ1999ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በነበራቸው ቆይታ በሴቶች ላይ የሠሯቸው ተግባራት ሁሌም እንደሚያስደስታቸው የሚገልጹት ወይዘሮ አለሚቱ፤ በተለይ ገጠሪቱን የኢትዮጵያ ክፍል በሚገባ በማየትና የሴቶችን ችግር ፈልፍሎ በማውጣት በሚቻላቸው ሁሉ ለውጥ ያመጣ ሥራን ማከናወናቸው ያረካቸዋል።
ለአገሬም ለሴቶችም አበረከትኩ የሚሉት ነገር እንዲኖራቸውም አድርጓቸዋል። በተለይም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ በሲዳማና አካባቢው እንዲሁም ሀመር ያለውን የሴት ልጅ ግርዛት፤ ሚኒጊን የመሳሰሉት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቆም የሰሩት ተግባር እጅግ የሚደሰቱበት እንደነበርም አጫውተውናል።
ሚኒጊ እየተባሉ የሚጣሉና እንዳያድጉ የሚደረጉ ሕጻናትን ማህበረሰቡን ታችኛው ክፍል ድረስ በመሄድ እርሳቸው ብቻ ባይሆኑም ከእነዚያ መካከል ሆነው አስተምረው ተስፋቸውን እንዲያለመልሙ ማድረጋቸው ሁሌም የሚኮሩበት ተግባራቸው እንደሆነም ይናገራሉ።
ከዚህ ትይዩ የሴቶች የሥራ ጫና ላይ የሠሩትም ተግባር ያስደስታቸዋል። በጥቃትና መሰማት አለመቻል ላይ ያሉ ክፍተቶችንም በትንሹም ቢሆን መድፈን በመቻላቸው ይደሰታሉ። ገጠሩ አካባቢ ብዙውን ሀብት ንብረት ወንድ ከመያዙም በላይ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ እድሉ ለራሱ ያደርጋል። በዚያ ላይ ከቤት እንድትወጣም አይፈቀድላትም።
ይህ ደግሞ በችግሯ ዙሪያ እንኳን እንዳትወያይ ትሆናለች። በዚህም ዝም ብላ የምትቀመጥ እንጂ የምትማርና ራሷን የምትለውጥ አትሆንም። ሌሎችን እያየችም እንድትማር አያደርጋትም። እናም ይህንን ለመፍታት ታችያው ክፍል ድረስ ደርሶ ማስተማሩ በብዙ መልኩ ያስፈልጋልና የቻሉትን በማድረጋቸውም ይኮራሉ።
ሴቶች ለውጥ እንዲያመጡና አርአያ እንዲሆኑ ሁሉም አካል ድርሻ አለበት። ይሁን እንጂ ያንን አስቦ የሚንቀሳቀስ እምብዛም ነው የሚሉት ባለታሪካችን፤ ብዙ ያልተሳካላቸው ነገሮችም እንደነበሩ ያነሳሉ። ለአብነት የጠቀሱትም ሕግ ፊት ሴቶቹ ሲቀርቡ ወድጄ ነው የሚሉትን ነው።
ለዓመታት በተደጋጋሚም ተፈትነውበታል፤ እዚህ ላይ አልሰራም ያሏቸው ባለሙያዎችም እንደነበሩ ያስታውሳሉ። እርሳቸው ግን እስከ መጨረሻው ገፍተውበት ጥቂቶችን ማትረፋቸው ደስታን እንደፈጠረላቸውም ያስረዳሉ። ሴቶችን በተመለከተ ብዙ ቢለፉም ‹‹ማህበረሰቡ ጋር ብዙ ያልተፈቱ ነገሮች አሉና ገና ዳዴ ላይ ነኝ፤ ብዙ መሥራት ያለብኝ ጉዳዮች ከጎኔ አሉ።
ሥራዬ ያለቀ ሳይሆን የተጀመረ ነው›› ይላሉ። ለዚህም የመጀመሪያ ተግባራቸውን ከአሁኑ ጋር እያዳመሩ እንደሚቀጥሉበትም አውግተውናል። በተለይ ሴት የምትጎላው ሴቶች ሲወጡና ሲታዩ፤ ማንነታቸውን በተግባር ሲያስመሰክሩ ነው ብለው ያምናሉና አሁን በተቀመጡበት አግባብ ሥራቸውን ተግባራዊ ለማድረግና የወከላቸውን ሕዝብ ለማስደሰት ሳይተኙ እንደሚሰሩ ይናገራሉ።
በተለይ ለአገር ፈተና የሆነው የውሸት ሪፖርቶችን ሥራን ለማክሸፍ ምክር ቤቱ በሰጣቸው ኃላፊነት ታችኛው ክፍል ድረስ ወርደው እንደሚሠሩና ሥራና ወሬው እንዲገናኝ እንደሚያደርጉ አጫውተውናል።
ወቅታዊ ሁኔታው ለሴቶች
ስለ አገርና ሴቶች ለማንሳት መጀመሪያ ሰላምን ማንሳት አስፈላጊ ነው። ሰው የሚባል ፍጡር በምድር ላይ የሚኖረው ሰላም ካለና አገር በደስታ ዜጎቿን መምራት ስትችል ብቻ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል። ስለዚህም ሰላም የሁሉም ፈጣሪና አኗሪ መሆኗን ማመን ይገባል የሚሉት ወይዘሮ አለሚቱ፤ ሰላምን ካጣን ምንም ሊኖረን አይችልም። አገር እንኳ አይኖረንም።
ምክንያቱም ሰው እንጂ መሬቱ አገር አይደለም። እናም ለሁሉም ደህንነት የሰላም መኖር ግድ እንደሆነ ማሳየት እንዳለበት ይመክራሉ። አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታም የሚተነትኑት ከዚህ አንጻር ነው። እንደርሳቸው አባባል አገርና ሴት የተነጣጠሉ አይደሉም።
አንዷ በአንዷ የሚተኩና የሚለሙ ናቸው። በምክንያትነት የሚያነሱትም መሰረቱን የያዘ ቤት የምትሰራው፤ ማህበረሰብ የምትፈጥረው ሴት ልጅ መሆኗን ነው። ልጇን ስታሳድግ አገር ወዳድ፤ ራሱን አክባሪና ማንነቱን ተቀብሎ የሚኖር ካደረገችው ሰላም ብቻ ሳይሆን አብሮት የሚመጣው ልማትም እውን ይሆናል።
በዚያው ልክ የሚጠበቅባትን ያልሰራች እናት ሰላም አደፍራሽና የሌላ አድናቂ ልጅ ትፈጥራለች። ይህ ደግሞ አገር ላይ ነውጠኞች እንዲበራከቱ ያደርጋል፤ ሰላምን ያደፈርሳል። በዚህም የመጀመሪያ ተጎጂዋ ራሷ ትሆናለች። እናም የሰላም ዋጋ በሴቶች ሰሪነት ልክ ይወሰናል ይላሉ። አሁን የገባንበት ጦርነት የግዳጅ ጦርነት ነው።
ብዙ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ እንደሆነ በብዙ መልኩ ተገልጧል። የመጀመሪያው ሴቶችን ማሰቃየት ላይ ያተኮረ ነው። የአገር ንብረትንም ማውደም ኢላማ አድርጓል። ንጹሃንን በማይታሰብ መልኩ ማሰቃየትና መጨፍጨፍም መለያው ነው። በዚህም መንግስት ትዕግስተኛ ሊሆን አልቻለም።
የሕዝቡ ጉዳይ ስላንገበገበው ገብቶበታል። ድልም በብዙ መልኩ ተቀናጅቶበታል። በተለይም ምንም ድርሻ የሌላቸውን ሕጻናትና እናቶችን መታደግ እንደቻለ ይሰማኛል። ሴራው ከሰው አልፎ እንስሳትን ጭምር ያካተተ እንደነበር አይተናል።
ግን ይህም በዝቶ እንዳይቀጥል መፍትሄ እንደተቸረውም ያነሳሉ። በጦርነቱ የጭካኔ ጥግ እንደታየ የሚናገሩት እንግዳችን፤ የአሸባሪው ተግባር አገርን ከመራና ካስተዳደረ ቀርቶ ምንም ካልተማረ ሰው እንኳን የሚጠበቅ አይደለም። ግን ሆኖ አይተነዋል፤ ለማመንም ስንቸገርበት ቆይተናል።
ይህንን አድራጊዎቹ ሰዋዊ ባህሪ እንደሌላቸውም እያደር እንድናምን ሆነናል። ምክንያቱም ከሰይጣን የተማሩት ካልሆነ በስተቀር ይህ በሰው ላይ መሆን የሌለበት ግፍ ነው። እናም እነርሱን አይደለም ኢትዮጵያዊ ሰው ናቸው ለማለት እቸገራለሁ ይላሉ። ምክንያቱንም ሲያነሱ ማንም ሰው ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት ጭምር ያዝናል። እነርሱ ግን ለሁለቱም ሲያዝኑ አይታይም። ስለሆነም ተግባራቸውም ምግባራቸውም ከዲያቢሎስ የወረሱት እንጂ ከሰውኛ ባህሪ አልመጣም እንዲሉ አድርጓቸዋል።
ይህ ተግባራቸው የትውልድ ቅብብሎሹን ያሻክረዋል። የእርስ በእርስ መተማመንም ይቀንሳል። ብዙዎች አገርኛ እሳቤን ለማምጣትም እንዲቸገሩ ያደርጋል። ስለዚህም ከዚህ ህመም እንዲፈወሱ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይኖርበታል። ህክምናው ደግሞ ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት በተለያየ መልኩ መምጣት መቻል አለበት።
መንግስትም ቢሆን በስነልቦና ሕክምናው ሊያግዛቸው ይገባል። በእርግጥም በቻለው ልክ እያደረገው እንዳለ ይሰማኛል። ብዙ ለውጦችም እየታዩ ናቸው። በቂ ነው ማለት ግን አልችልም። ምክንያቱም ይህ አካል ሌሎች ወንድምና እህት እንዳሉት ማወቅ አለበት።
ለዚህ ደግሞ በጦርነቱ ያልተነኩ አካላት ልዩ እገዛ አድርገውላቸው ከጎናችሁ ነን ማለት አለባቸው ባይም ናቸው። ከሁሉም በላይ አድራጊዎች በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው የሚያብራሩት እንግዳችን፤ እንደመንግስት ያዝ ለቀቁ መቆም አለበት። የዚያን ጊዜ ጥፋተኛው ተገቢውን ቅጣት አግኝቷልና መተው ይለመዳል። አድራጊውም ከዚህ በኋላ እንዳይደግመው ይሆናል። አገር ወደ መረጋጋቱ ትገባለች። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ከዚህጋር ተያይዞ የተነሳ ይመስለኛል። እናም የጠፋ ሕይወት ባይመለስም የሕዝቡ ህመም ግን በተወሰነ ደረጃ እየታከመ ነውና ጅማሮው ይቀጠል ይላሉ።
መልእክት
እንደአገር በብሔሮች መካከል መቃቃርና የእርስ በእርስ አለመተማመን እየታየ መትቷል። ለዚህ ደግሞ አገራዊ ምክክሩ ወሳኝነት አለው። አገርን ሰብሰብ አድርጎ በአንድነት ውስጥ ለማቆምም መፍትሄ ሰጪ ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ችግር ካለንግግርና ውይይት አይፈታም። በተለይ እኛ አገር ላይ እየተፈጠረ ያለው ችግር ከዚህ ውጭ የሚሆንበት ምንም ምክንያት አለ ተብሎ አይታሰብም።
እናም ሁነቱን ተቀብሎ ፈጥኖ ወደተግባር መግባቱ አሁን ካለንበት ችግር ያወጣናል ሲሉ ይመክራሉ። የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም የሚሉት ነገር አላቸው። ይህም አሁን አገራት እኛን የሚፈሩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ምክንያቱም በጦርነት፣ በማዕቀብና በማስፈራራት ሊያተራምሱን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ሁሉንም በዳግማዊ ድል አልፈነዋል።
ከዚህ በኋላም እንዳይሞክሩት አስተምረናቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአገራችንን የኑሮ ችግር የምንፈታበት መንገድን ጀምረናል። በኩራዝ የሚያነበው፣ በጭስ የምትሰቃየው፣ ርቀት ሄዶ የሚያስፈጨው ሰው እፎይታን የሚያገኝበት ጊዜ ላይ ደርሷል የሚለው ነው። ይህ የህዳሴ ጉዞ ዶላርን የምንመዠርጥበት ጊዜ ላይ ለመድረስ ሩቅ እንደማንጓዝ የሚጠቁመን ነው። እናም ለስኬታማነቱ አሁንም መቀነታችን፣ ኪሳችን መፈተሽ አለብን። በጉልበቱና በእውቀቱም የሚያግዘው ደከመኝ ማለት የለበትም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ብዙ የሚያለፋ ነገር የለም።
ስለሆነም ፍሬውን ለመልቀም ደስታውን ለማፈስና ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም መትጋት አለበት ሌላው መልእክታቸው ነው። ማንም አገር እንደኢትዮጵያ አይሆንም። በሁሉ ነገር ሀብታም ናት። ይሁን እንጂ ማየት ላይ ክፍተቶች አሉ።
በአለን ልክ መጠቀምም እንዲሁ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሰውን ቀድሞ መመልከት ነው። ስለሆነም መጀመሪያ ያለንን አይተን በዚያ ላይ ለመጨመር መነሳሳት ያስፈልገናልና እዚህ ላይ እንበርታም ሲሉ ይመክራሉ። በመጨረሻ ያስተላለፉት መልእክት ለትዳር አጋሮች ሲሆን፤ ከወንድ በስተጀርባ ሴቶች አሉ እንደሚባለው ከሴቶች ጀርባም ወንዶች አሉ መባል መጀመር አለበትና ወንዶች ይህንን ለሴቶች ማሳየት አለባቸው የሚለውን ነው። ይህንን ሲያደርጉ ደግሞ ባለቤታቸውን በሁሉም ዘርፍ አግዘዋት መሆን ይገባዋል።
በተለይ በትምህርት እንድትወጣና የሥራ ጫናው እንዲቀንስላት ሊያበረቷት ያስፈልጋል። በዚህም ተጠቃሚ የሚሆኑት እነርሱ መሆናቸውን በቅርብ ያዩታል ሲሉ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። እኛም ምክራቸው ይተግበር በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ በዚህ ቋጨን። ሰላም!::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014