የሕወሓት አጀንዳን ላለማመንዠክ ጆሮም አይንም ነፍጌ ነበር። ሁሉም እንዲህ ሊያደርግ ይገባል ብዬም አምናለሁ። ለእያንዳንዱ የሕወሓት ቅርሻ ማህረብ ወይም ናፕኪን ለማቀበል መሞከር ከጥቅሙ ይልቅ አሉታዊ ተጽዕኖው ስለሚያመዝን ። ግፉ፣ ሰቆቃውና ነውሩ የሚረሳ ባይሆን እሱ በሚሰጠው አጀንዳ ላለመወሰድ ምዬና ተገዝቼ ነበር ።
ሰሞኑን ቴዎድሮስ አድሀኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ሳለ በአሸባሪነት የተፈረጀን ፤ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ፣ ውድመትና ዘረፋ የፈጸመን፤ ለዛውም በአመነስቲ ኢንተርናሽናል የፈጸመው ግፍ ለዓለም በተጋለጠ እና የአሜሪካ መንግስት በገደምዳሜ ባስጠነቀቀው ማግስት፤ በእብሪትና በግብዝነት ተነስቶ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ብቅ ብሎ እንኳን ለ47ኛ ዓመት አደረሳችሁ ሲል በመመልከቴ ግዝቴንና መሐላዬን ለማፍረስ ተገደድሁ። ባይሆን ለሃጢአቴ ንስሐ እቀበልበታለሁ።
ሕወሓት በግድ አልረሳም። አለሁ። ለማለት ከደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል እስከ ቴዎድሮስ አድሀኖም፤ ከትግራይ ቴሌቪዥን እስከ ድምጺ ወያኔና ዲጅታል ወያኔ ድረስ እንኳን ለ47ኛ የሕወሓት ምስረታ አደረሰን እየተባባሉ ነው። የደረሱ ይመስል። የአራዳ ልጆች እንደሚሉት የእድሩ ድክመት ነው እንጂ ከሞቱ እኮ ቆዩ።
የኢሳቱ መሳይ ደግሞ የምን 47ኛ፣ እንኳን ለ4ኛው ተስካር አደረሳችሁ በማለት የጣሉትን ከል እንዲያነሱ፤ በራሳቸው ላይ ለ4ኛ ጊዜ ትቢያ እንዲነሰንሱ አስታውሷቸዋል።
ያው እንዳሻቸው ሲፋንኑበት ከነበረው አገዛዝ ተከርብተው በልካችሁ ሁኑ ከተባሉና ወደ መማጸኛ ከተማቸው ከመሸጉ አራት አመት እንደሆናቸው ለማስታወስ ። እኔም ትንሽ አስተካክዬ እንኳን ለ4ኛው የሕወሓት ሙት ዓመት አደረሳችሁ ብዬ ነበር ። ሳስበው ሕወሓት ልደቱንም ሆነ ሞቱን እኩል በአንድ ላይ ነውና የጀመረው እንኳን ለ47ኛው ሙት ዓመት አደረሳችሁ ማለትን መረጥሁ ።
በ1967 ማኒፌስቶው አማራንና ኦርቶዶክስን በጠላትነት የፈረጀ ጊዜ፤ ትግራይን እገነጥላለሁ ያለ ዕለት፤ የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ ናቸው ያለ ዕለት ፤ የማንነት ፣ የልዩነትና የጥላቻን ፖለቲካን ለመከተል፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳለት ፤ ወዘተረፈ ሞቱን ከልደቱ ጋር መሳለመሳ ጀምሯልና።
አማራን ከኦሮሞ እያናከስሁ፤ ኦርቶዶክስን ከእስልምና እያባላሁና እየከፋፈልሁ፤ እየገደልሁ፣ እየገረፍሁ፣ እያሰቃየሁ፣ እያጎርሁ፣ እያሰርሁ፣ እየጨቆንሁ፣ እያፈንሁና እየዘረፍሁ ዘላለም ስልጣን ላይ እቆያለሁ ያለ ጊዜ የቁም ሞቱን ጀምሯል።
ቁሞ ቀሯ፣ ተቸካይዋ፣ ወሬሳዋ፣ ሴረኛዋ ና ግፈኛዋ የትህነግ/ሕወሓት ቡድን የምስረታዋ 47ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሊቀ መንበሯ በኩል ባወረደችው ሙሾ፤ እያንዳንዷ የትግራይ መሬት እስክትመለስ ፤ ከበባው እስኪሰበር ፤ ለደረሰብን ጉዳት ካሳ እስኪከፈለን ትግሉን እንቀጥላለን አይደለም ትጥቅ መፍታት የሕወሓት ሰራዊት ይበልጥ ይጠናክራል ስትል የተለመደውን ድንፋታዋን አሰምታለች። ጭፍን ደጋፊዎቿን ለማጽናናትም በከፍተኛ መስዋዕትነት በአፋር አምስት ወረዳዎችን ወራለች።
በሕዝቧ እርሀብ ፖለቲካዊ ትርፍ ለመቀላወጥ ብቸኛውን የእርዳታ ማጓጓዣ መንገድ ዘግታለች። ሆኖም ጀምበሯ እየጠለቀባት ነው። አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያንና አለማቀፍ ተቋማት ሸፍጧን እየተገነዘበ ነው። የአመነስቲ ኢንተርናሽናልና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞነኛ መግለጫ ለዚህ እማኝ ነው። የእሷን አጀንዳ ከምሰልቅ የእኔን አጀንዳ ላቀብል።
ለመሆኑ ሕወሓት ማን ናት !? ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው እንደሚሉት የመርሳት አባዜ ስላለብን ስለ እፉኝቷ ሕወሓት አመሰራረትና ስለአገራችን ዘመናዊ ፖለቲካ ትንሽ ልበል። የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ በርካታ ሺህ ዓመታትን ወደኋላ ቢመልሰንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን ብዙ ፈቀቅ ያላለ ነው።
ይሁንና በሰራተኛ ማህበር፣ በሙያ ማህበራት፣ በተማሪዎች ማህበራት፣ በመረዳጃ ማህበር፣ በልማት ማህበር፣ በተወላጆች ማህበር፣ ወዘተረፈ ስም የፍትሐዊነት፣ የተጠቃሚነት፣ የውክልና፣ የእኩልነት፣ የነጻነት፣ የመብት ጥያቄዎች ላይ መምከርና መወያየት የተለመደ ነው። በነጻነት የመሰብሰብና የመደራጀት መብት ስላልነበር እነዚህ ማህበራዊ አደረጃጀቶች ለፖለቲካዊ ትግል ሽፋን በመሆን አገልግለዋል።
በ1960ዎቹ እንደ እንጉዳይ የፈሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እርሾ በመሆንም አገልግለዋል። ሜጫና ቱለማ መረዳጃ ለኦነግ / ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር /፤ የአገር ቤትና የውጭ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለኢህአፓ/ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ/ ፤ ለመኢሶን/ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ/፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) ለሕወሓት/ለሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ መመስረት ጥንስስ ሆነው አገልግለዋል።
በተማሪዎች የ1960ዎች እንቅስቃሴ ከእነ ግርማቸው ለማ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስሙን የወረሰው)፣ ሰለሞን ዋዳ ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም ፣ በክፉም ስሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው ።
ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ / ኮርጆ/ ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ ተደጋግሞ ቢወቀስም፤ አንዳንዶቹ ዋለልኝ የተማሪዎች ማህበር መሪዎች ያሳለፉትን ውሳኔ አነበቦ፣ ጻፈ እንጂ የብሔር ጥያቄን ቀድሞም ሆነ ለብቻው አላነሳውም በማለት ጥያቄው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለደው ስለሆነ ከዋለልኝ ጫንቃ ውረዱ የሚሉ ወገኖች አሉ ።
ያም ሆነ ይህ በፈጠራ ትርክትና በግልብ ትንተና መታገያና ማታገያ ሆኖ የመጣው የብሔር ጥያቄ አገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል እና አጣብቂኝ መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር ፤ አገር ፣ ሕዝብና የባህር በር አሳጥቶናል።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያባላና እያጨቃጨቀ ይገኛል። በአገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች ተጠምዷል። የብሔር ጭቆናበተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል ።
እዚህ ላይ በሕወሓት ፣ በኦነግ እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ይስተዋሉ የነበሩ ልዩነቶችን በአብነት ማንሳት ይቻላል። ሆኖም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለትህነግ፣ ለኦነግና ለሌሎች የብሔር ድርጅቶች መፈጠር እርሾ ሆኖ ማገልገሉ አይካድም።
የጋራ አገር ፣ ታሪክና ጀግና እንዳይኖረን አድርጓል። ጥላቻ ፣ ልዩነትና ጎሰኝነት እንዲጎነቁል ለም አፈር ሆኗል። የሀብት ብሔርተኝነትን /resource nationalism /ተክሏል።
አገራዊ ምክክሩ ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት የማሪያም መንገድ ይሰጠናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም በ11 ሰዎች በምዕራብ ትግራይ በሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በተባለ ስፍራ የተመሰረተው እና የቀዳማይ ወያኔ ቅርሻ የሆነው “ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ” /ተሓህት/ ወደ አማርኛ ሲመለስ የትግራይ ሕዝብ አርነት ግንባር፤ የዛሬው ትህነግ/ሕወሓት ባልጠራ ርዕዮተ ዓለም የትግራይ ሕዝብ ጭቆና መደባዊና ብሔራዊ ነው በሚል ግልብና እንቶፈንቶ ትንታኔ እንዲሁም አንድን ሃይማኖትንና ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ የተጠነሰሰው በተማሪዎች እንቅስቃሴ እርሾነት ነው።
ደርግን ለ17 ዓመታት በነፍጥ ታግሎ በ1983ዓ.ም ለስልጣን ቢበቃም። የብሔር ጥያቄን ለከፋፍሎ መግዣነትና የስልጣን እድሜውን ለማራዘም፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ለማሳደድ ስላዋለው የብሔር ጥያቄን በሀቀኝነት ሙሉ በሙሉ አልመለሰውም።
የመደብ ቅራኔውንና ልዩነቱን ከመፍታት ይልቅ ዘራፊና ስግብግብ መደብ ፈጠረ። ቁጭት ፈጥሮ ድጋፍ ማሰባሰቢያ አደረገው እንጂ ታገልሁለት ያለውን የብሔር ጥያቄ በልኩ አልመለሰውም። ለዚህ ነው ጥያቄው የብሔሩ ልሒቃን በአቋራጭ ስልጣን መያዣ እንጂ የተራው ሕዝብ ጥያቄ ተደርጎ የማይወሰደው።
በድቡሽት ላይ በተመሰረተ ግልብ ትንተና የመደብ ጭቆናን ከብሔር ጥያቄ አፋልሰውና አጣርሰው የፈጠሩት ትህነግ መጨረሻውን እየተመለከትን ነው ። ከጅምሮ ተሓህት በስሁት ትንታኔ የተመሰረተ ቡድን መሆኑን የድርጅቱ መስራችና ነባር ታጋይ አይተ ገብሩ አስራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በሚለው መፅሐፋቸው ገፅ 38 ላይ እንዲህ አረጋግጠውልናል ።
“የማገበት /ተሓህት/ መስራች አባላት ትግሉ መደባዊ ይሁን ብሔራዊ የጠራ ግንዛቤ ባይኖራቸውም ፤ የብሔር መብት እስከ መገንጠል የሚለውን አስተሳሰብ ያራምዱ የነበረ ሲሆን በዚህ ዙሪያ ብዙ ውዝግብ አልነበረም።” ይሉናል ። ትህነግን ጨምሮ የአገራችን ፖለቲካ ድርጅቶች ለምን ይከሽፋሉ? ይወድቃሉ? የሚለው ጥያቄ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ቢሆንም ፤ ይህን ጥያቄ ባንሰላሰልሁ ቁጥር ሶስት ገዥ ነጥቦች ወደ አእምሮዬ ይመጣሉ።
1ኛ. ፖለቲካዊ ትንተናው በአመክንዮና በተጠየቅ ሳይሆን በስሜትና በግዕብታዊነት የተቃኘ መሆኑ፦ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ መስራች አባል አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ በዚያ ሰሞን “አርትስ” ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው” ትላንትም ሆነ ዛሬ እንደ አገር እንደ ሕዝብ የገጠሙንን ፈተናዎች ለመሻገር ሳይንሳዊ ጥልቅ ትንተና ያስፈልጋል። ትንተናው ግን በግዕብታዊነትና በስሜት ሊሆን አይገባም ።” ብለዋል።
ዛሬ ለምንገኝበት ውርክብ የዳረገን የ60ዎቹ ትውልድም ሆነ እሱን ተከትለው የተቀፈቀፉ ነፃ አውጭ ፓርቲዎች በስሜትና በደም ፍላት ተመስርቶ የተደረገ ትንተናና የደረሰቡት የተሳሳተ ድምዳሜ ነው ማለት ይቻላል።
2ኛ. ለችግሮች አገረኛ መፍትሔ አለመሻት፦ ላለፉት 50 ዓመታት እንደ መስኖ ውሃ እነ ሌኒን፣ ስታሊን፣ ማርክስ፣ ኤንግልስ፣ ማኦ፣ ማኪያቬሊ፣ ወዘተ. በቀደዱን የርዕዮተ ዓለም ቦይ መፍሰሳችን አልያም ሲገድቡን መገደባችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ። ሆኖም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ ዛሬም ጥያቄዎቻችን አለመመለሳቸው ችግሮቻችን አለመፈታታቸው ሳያንስ ይበልጥ ተወሳስበው ውላቸው ጠፍቷል።
ለዚህ ነው ለአንደኛው ችግር መፍትሔ ስናበጅ ሌላው እንደ እንቧይ ካብ ከጎን የሚናደው። ከሌኒን ኮርጀን የብሔር ጥያቄን እንደፈታልን ስናስመስል ነው አገራዊ ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀው። ከሶቪየት ገልብጠን የዕዝ ኢኮኖሚን ስንተገብር ፈጠራ የኮሰመነው ኢኮኖሚው የደቀቀው።
ከደቡብ ኮሪያ፣ ከጃፓንና ከቻይና እንዳለ ቀድተን ልማታዊ መንግስት ስናነብ አገር የጥቂቶች ሲሳይ ሆና ያረፈችው። ለነገሩ ጠንካራ አገራዊ አንድነትና ተቋማት በሌሉበት ልማታዊ መንግስት አይታሰብም።
እነዚህ ማሳያዎች ችግሮቻችንን በተናጠል እና በተኮረጀ ርዕዮተ ዓለም ወይም ፖሊሲ ለመፍታት ያደረግነው ሙከራ መክሸፉን ያሳጣሉ። ለዚህ ነው አገር በቀል ወደ ሆነና ዙሪያ መለስ እይታ ማተኮር የሚያስፈልገው።
3ኛ. የተረክና የታሪክ ምርኮኛ መሆን፦ሰለሞን ሥዩም የተባሉ ፀሐፊ በፍ-ት-ሕ መፅሔት ከአንድ አመት በፊት ባስነበቡት መጣጥፍ ታሪካችን ሶስት የትርክት ዘውጎችን መፍጠሩን ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡን ጠቅሰው አትተዋል።
አክሱማዊ ፣ ሴም ኦሪየንታላዊ እና ስር -ነቀላዊ ናቸው። ሶስተኛው የስድሳዎቹ ትውልድ የፈጠረው ነው። የታሪኩንም የፖለቲካውን ትርክት ከስሩ ለመቀየር፣ ለመንቀልና ለመፈንቀል ነው የሰራው።
ትርክት ቀድሞ በተቀመጠ ድምዳሜና ብያኔ ላይ የሚዋቀር መሆኑ የውርክቡ መግፍኤ ነው። የዚህ ትውልድ ቅርሻ የሆኑ “ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጭዎች “በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ታሪክን በሸውራራ ትርክት ለመቀየር ያደረጉት ጥረት በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶላቸው ነበር ማለት ይቻላል ። በእነዚህ የፈጠራ ትርክቶች በዜጎች መካከል ጥላቻን ፣ መጠራጠርንና ልዩነትን ጎንቁለው በማሳደግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ችለዋል።
በተዛባ ትርክት ለቆሙ የጥላቻ ጣኦታት እንድንሰግድ መስዋዕት እንድንገብር አድርገዋል። አገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! አሜን ።
እውነቱን ለመናገር
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014