በአገራችን በተደጋጋሚ በድርቅ ስትጠቃ ዐይተናል ሰምተናልም፤ አንዳንዶች ሲናገሩ ድርቅ በየአሥር ዓመቱ ዳግም ዑደት (recycle) እያደረገ የሚከሰትባት ሀገር ናት ይላሉ። በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላታቸውም ድርቅን ሲፈቱ ማሳያ አድርገው ኢትዮጵያን ጠቅሰው ነበር።
እነሱ ምንም ይበሉ ምንም አንቀየምም፤ ይልቁንም ለእኛ የሚበጀን ድርቅን ለመቋቋምና ድህነትንና ቸነፈርን መዋጋት ነው። ይሁን እንጂ ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ችግር አይደለም።
በአውሮፓውያንም በ17ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ድርቅ በተደጋጋሚ ይከሰት እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ።
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ያወጣው መረጃ ከ1927 እስከ 1977 በድርቅ ከተጠቁ አገራት መካከል ህንድ በ1893፣ 1958 እና 1935፣ ኢትዮጵያ በ1966 እና 1977፣ ቻይና በ1927 እና 1928፣ ባንግላዴሽ በ1943፣ ሶቪየት ኅብረት በ1921 እና ሱዳን በ1983 በድርቅ ተጠቅተው ነበር።
ከ80 በመቶ የሚልቁ ዜጎቿ በዝናብ ላይ በተመሰረተ ግብርና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ ያሉባት ኢትዮጵያ፤ የዝናብ ጥገኝነቷ ለተደጋጋሚ ድርቅ እና ይሄን ተከትሎ ለሚፈጠር ረሃብ ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል።
በመሆኑም ይሄን ታሪክ መቀየር የግድ የሚል የሕልውና ትግል ሊሆን የሚገባው ሲሆን፤ ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ እና የመስኖ ልማትን ማስፋት፤ የአርብቶና አርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ለነገ የሚባል ተግባር ሊሆን አይገባውም። ዜጎችም ጠላታቸው የሆነውን ድህነት ታሪክ ለማድረግ መረባረብ አለባቸው።
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ለዙፋኑ መናወጥና መገልበጥ ድርቅ አንዱ ምክንያት ነው። በወቅቱ በወሎና በትግራይ ብዙ ዜጎች በድርቁ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ሕይወታቸው ሲጠፋ የዓለም አቀፍ ዜና ወኪሎች ድርቁን እየዘገቡትና በዜና እያራገቡት እንጀራቸውን ጋገሩበት የሚሉ አሉ። (እነ ጆናታን ድልቢልቢን የመሳሰሉ የውጭ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ያስታውሷል)፤ የለም በድርቅ ችግር ላይ ወድቀው የነበሩ ዜጎች እንዲድኑ ያስቻሉ ናቸው የሚሉም መኖራቸው አይዘነጋም።
የዘውዳዊ መንግሥት ተገርስሶ በወታደራዊ መንግሥት አስረኛው ዓመት ላይም እንዲሁ ከላይ በጠቀስናቸው አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ተከሰተ። ከድርቁ የተረፉትም በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ለልመና ተግባር ለመሰማራት ተገድደው ነበር።
በየቀበሌ የኅብረት ሱቆችም ጥራጥሬ እጥረት አጋጥሞ ስለነበርም በቤተሰብ ልክ እንዲሸምቱ ሲደረግ፤ ፓስታና መኮሮኒም እንዲሁ በቤተሰብ ይሰጥ ነበር። ስንዴና ጤፍ እየጠፋ በመምጣቱም ነዋሪው ሩዝን በቀበሌ ኅብረት ሱቅ ሸምቶ ክፉ ጊዜውን ለማሳለፍ ተገድዶ ነበር።
ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ፤ የደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ድርቅ የሚለውን ቃል ሲፈታው በጋ፣ ቦና፣ ዝናም የጠፋበት፣ የታጣበት ዘመን (ተረት) “ቅቤ መዛኝ ድርቅ ያወራል” በሚል ሲሆን፤ ቸነፈር የሚለውን ደግሞ የበሽታ ስም፣ ዕልቂት መቅሰፍት ከጦርነት በኋላ የሚመጣ ሰውን እያጨናፈረ ፈጥኖ የሚገድል ህመም በግእዝ ብድብድ ይባላል፤ ዐባር ቸነፈር እንዲሉ ዕን3፤5 ማቴ 24፥7፤ ይለዋል።
በተመሳሳይ የከሳቴ ብርሃን ተሰማ መዝገበ ቃላትም ይህንኑ ቃል ሲፈታው፡- ተስቦ፣ ወረርሽኝ፣ መቅሰፍት፣ የነፋስ ተላላፊ በሽታ፣ ደዌ ቸነፈር ይባላል በሚል ይተረጉመዋል።
እንደ መዝገበ ቃላቱ ትርጓሜ ከሄድን ዓለም እያሰጋ ያለውና በአገራችን ከዓመት በፊት የተከሰተውና ብዙ ሰዎች በሞት እየነጠቀን ያለው ኮረና ነው።(ነፍስ ሔር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እና ወ/ሮ አበበች ጎበና፤ የኒያ ፋውንዴሽና የጆይ ኦቲዝም ማለትም የአዕምሮ ዝግመት ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘሚ የኑስ በኮሮናቫይረስ ህመም መሞታቸው ይታወሳል ፤ሌሎች ያልጠቀስናቸው ታዋቂ ሰዎችና ደራሲያንም በዚሁ ወረርሽን ያጣናቸው አሉ።) የኮረና አንዱ መተላለፊያው ትንፋሽና መቀራረብ ነው። አፋችሁንና አፍንጫችሁን ተሸፋፈኑ፣ መጨባበጥ ይቅር የተባለውም ከተፅዕኖው አንፃር ነው።
በጥቅሉ የወረርሽኙን ተፅዕኖ ካየነው ኮረናን እንደብያኔው ቸነፈር ልንለው እንገደዳለን። ወደ ድርቁ ስንመለስ ንጉሡን የናጠውና የገለበጠው ድርቅ ተመልሶ በ1970ዎቹ አጋማሽ ከች አለ። (WIDER) World Institute for development Economic Research of the United Nations University (Ethiopian famines (1973-1985) በሚል ርዕስ ባወጣው ጥናታዊ ጽሁፍ በአሥሩ ዓመታት ሁለት ዙር የድርቅ አደጋዎች 2ነጥብ5 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸውን ያስረዳል። በንጉሡ ዘመን የነበረው ድርቅ ከወሎና ትግራይ በተጨማሪ በደቡብና በሐረር አካባቢዎች መከሰቱን ይኸው ጥናታዊ ጽሁፍ ያሳያል። በፈረንጆቹ በ1984 አጋማሽ ብቻ 175ሺ የሚገመቱ ዜጎች ሞተው ነበር።
ያለነው ድሃ አገር ውስጥ ነው። ትልቁ ጠላታችን ደግሞ ድህነት ነው። መጀመሪያ ድህነትን እንዋጋ ቀጥሎ የሚቀጥለው ይደርሳል። ሁሉም ሕገ መንግሥቱ በቀደደለት ቦይ መፍሰስ ይችላል፤ መሣሪያ ያልታጠቀ ሰውን ማጥቃት እንደፈረንጆቹ “ቦይ” መሆን እንደእኛ አለመብሰል ነው።
ድርቅ አበቃ የምንልበት ዘመን ላይ የደረስን አይመስለኝም፤ በድርቅ አደጋ ተፈናቅለው ዜጎች ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲሠፍሩ ተደርጎ ነበር፤ ሰዎች ከድርቅ አደጋ ተርፈው ሕይወታቸውን እንደገና ጀምረዋል። ከህዝብ ጋር ተጋብተዋል ተዛምደዋል። ልጅና የልጅ ልጅ ያዩም አሉ። ዛሬ ግን ጥራዝ ነጠቆችና የዘውግ ፖለቲካ የሚያራምዱ አካላት ሕይወት ማጥፋትና ማጥቃትን እያሳዩን ነው። መጤ ከአካባቢ ይውጣ የሚል አመለካከት ይታያል።
ታሪኩ እንዳይደገም ይታሰብ፤ ነገ ውጡ እያሉ የሚያጠቁ አካላት በድርቅ እንዳይጠቁ እና መጤ ወደ ተባሉት ሰዎች ተሰደው እንዳይወጡና እዛም መጤ እንዳይባሉ ሰጋሁኝ። ጠላታችን ድርቅና ቸነፈር ነው እንጂ ህዝብ አይደለም። በያዝነው ዓመት ብቻ በአፍሪካ 16 አገራት የረሃብ አደጋ እንዳንዣበበባቸው የአፍሪካ ኅብረትን ጠቅሶ በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ተዘግቦ ነበር። ረሃብ ሲሆን ደግሞ ከድርቅ የከፋ ነው። እንደ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል የቦረና ዞን ያሉት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቸገሩ ማኅበረሰቦችን በመደገፍ የአየር ንብረት ለውጡን መፋለም አስፈላጊ ሲሆን፣ የመካከለኛ ጊዜ የውሃ ልማት ፕሮጀክቶች ደግሞ ችግሮች ሳይከሠቱ መፍትሔ ለማበጀት ያስችላሉ።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 20 /2014