ግለ ትዝታን እንደ መነሻ፤
ይህ ዐምደኛ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን በአካል ያወቃቸውና ደጋግሞ በቅርበት ያያቸው በታዳጊነት የዕድሜ ዘመኑ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ፤ አንድም፡- ቆፍጣናው ወጥቶ አደር (ወታደር) አባቱ ለቤተሰቡ አዘውትሮ ይተርክ የነበረውን ንጉሣዊ ገድላቸውን በነጋ በጠባ ያደምጥ ስለነበር፤ ሁለትም፡ – ምክንያቱን በውል ባንረዳውም አባባ ጃንሆይ (ቀድሞ በልጅነት ወራት ብዙዎቻችን በምንጠራቸው የፍቅርና የአክብሮት ስም መጥራቴን ልብ ይሏል) ወደ ሠፈራችን ወደ ኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ ወቅት ሳያሰልሱ አዘውትረው ይመጡ ነበር።
አንዳንዴም ወዴት እንደሆን ባይገባንም ወደ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ቁልቁል ያዘቀዝቁ ነበር። በልዕልት ፀሐይ ስም ይታወቅ የነበረው ሆስፒታል ዛሬ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተብሎ የስም ውርስ የተላለፈበት ነው። ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ፈጥኖ ደራሽ ግቢ ሲመጡም ሆነ ቁልቁል ወደ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ሲያዘቀዝቁ ዛሬ በአስራ ስምንት ቁጥር አውቶቡስ ማዞሪያነት በሚታወቀው መስቀልያ መንገድ ላይ ቆመው፣ ወይንም የኮልፌ “ዳውን ታውን” ይባል በነበረው የአበበ አፍኔ ሱቆች ዝቅ ብለው ቤተሰብ መምሪያ በማይታወቅበት ዘመንና ይሄ ምንትስ የሚሉት ዘር ማምከኛ ባልተፈለሰፈበት ዘመን ያለ ዕቅድ ለተፈለፈለው እኛን መሰል የአካባቢው ውሪ በነፍስ ወከፍ የአንድ ብር ዳረጎት ያድሉን ነበር። እኛ ዳረጎተኞች ውሪዎች ደግሞ በምላሹ የንጉሡን ውለታ እንመልስ የነበረው የሚከተለውን የሙገሳ መዝሙር ቅኝት በሌለው ዜማ እያንቋረርን ነበር፡-
አባባ ጃንሆይ፣ አባባ ጃንሆይ፤የእኛ እናት አባት፣
አሳድገውናል፣ አሳድገውናል፤ በማር በወተት።
በእኛ በማቲዎቹ ዘንድም ሆነ በትላልቆቹ ሠፈርተኞች ዘንድ የአባባ ጃንሆይ መምጣት የሚታወቀው በጋሽ በቀለ ጢሞ የዶቅዶቄ ድምጽ መሆኑን ባላስታውስ ታሪኩን አጎለድፋሁ። ብዙ ሰው በቀለ ጢሞን ይጠራ የነበረው “ጋሼ” የሚል ቅጽል በስሙ ላይ እያከለ እንጂ በወታደራዊ ማዕረጉ አልነበረም። ሞላ ያለ ሰውነት የነበረው ጋሽ በቄ የግራና የቀኝ ፂሙን አሹሎና ኮስታራ ፊቱን አጨፍግጎ ሲመለከቱት አንዳች የፍርሃት ድባብ ያሰፍናል።
ሁሉም ሰው ጋሽ በቄ ጢሞን አንተ ይለው ስለነበር እኔም የያኔው ውሪ የዛሬው ጎልማሳ አፌን ሞልቼ የተዳፈርኩት ከጀማው አጠራር ላለማፈንገጥ እንጂ ክብሩን ለማሳነስ አይደለም። ለነገሩ ዛሬም ቢሆን የጋሽ በቄ ጢሞን ማዕረግ ምን እንደነበረ አላስታውስም፤ በንባብም አልደረስኩበትም። ብቻ የሚይዘው የሞተር ቢስክሌት የታርጋ ቁጥር 80 እንደነበር አስታውሳለሁ።
ጋሽ በቄ ጢሞ ንጉሡን ለምን እንደሚያዋክባቸው ባናውቅም እንደ ክረምት አሸን አካባቢውን ያጥለቀለቀው ውሪ የአንድ ብር ዳረጎቱን ተቀብሎ ሳይጠናቀቅ ሞተር ብስኪሌቱን እያስጓራ አባባ ጃንሆይን አክለፍልፎ ይወስድብናል።
ለንጉሠ ነገሥቱ አቤቱታ ለማቅረብ መሬት ላይ ተደፍተው ፍትሕ የሚማጸኑ ዜጎችንም ከክብር ጠባቂዎቻቸው ጋር እያዋከበ ያርቃቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። ከንጉሡ ጉብኝት ጋር የነበረኝን ሦስተኛውን የልጅነት ትውስታ ልዘክርና ተጨማሪ ተያያዥ ታሪክ አስታውሼ ከዛሬ አገራዊ ትዝብቴ ጋር ለማመሳከር ልሞክር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በአራት ኪሎው ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ስለነበር ንጉሡ ስፖርተኞችን ለማበረታታት አዘውተረው ወደ ትምህርት ቤታችን ግቢ ይመጡ ስለነበር እግረ መንገዳቸውንም ወደ እኛ መማሪያ ክፍል ዘው ብለው እየገቡ ጸጉራችንን በማሻሸት “የነገዋ የኢትዮጵያ ተስፋዎች!” እያሉ እንደ መርግ የከበደ አገራዊ አደራ ይጥሉብንና ይመርቁን ነበር። አይ ዘመን! ወደ ዋናው መነሻዬ ልመለስና ንጉሠ ነገሥቱ ኮልፌ አካባቢ መምጣታቸውን እማማ የአስናቁ እናት ልክ እንደሰሙ በሰንዱቃቸው ውስጥ ለክት ያስቀሙጡትን ነጠላ “በብርሃን ፍጥነት” መዘው በማውጣት ደረብ አድርገው ንጉሡ ለሕጻናቱ የአንድ ብር ዳረጎት ወደሚያድሉበት አካባቢ ቀረብ ያለ ገላጣ መሬት ላይ ነጠላቸውን አንጥፈው “አቤት! አቤት! አቤት! ንጉሥ ይፍረደኝ!” በማለት በአቧራ ላይ እየተንከባለሉ መጮኻቸውን ሳስታውስ ዛሬም ድረስ ውስጤ እንደ ሞገድ ባህር ይናወጣል።
የአስናቁ እናት ከትውልድ ቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ኮልፌ የመጡት አንድ የአካባቢያቸው ፊውዳል ሹም ከመሬታቸው ላይ በግፍ ነቅሎና አስፈራርቶ ከአገር እንዲባረሩ ምክንያት በመሆኑ እንደነበር በስፋት ታሪካቸውን ሲናገሩ ከወላጆቻችን እንሰማ ነበር። ግፍ ከትውልድ ቀዬአቸው ያሰደዳቸው እኒህ ምስኪን እናት ንጉሡ በዚህና በዚያ አካባቢ ያልፋሉ በተባለበት ቦታ ሁሉ እየተገኙ ነጠላቸውን መሬት ላይ አንጥፈው ለፍትሕ መጮኻቸው እንደ ወትሯዊ ልማድ በመቆጠሩም በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ አንድ ሰው ፍትህ አጣሁ ብሎ ሲናገር ከተደመጠ “እንደ አስናቁ እናት የንጉሥ ነጠላህን ይዘህ ሩጥ” እየተባለ ይተረትበት ነበር። ለፍትሕ ይጮኽ የነበረ ድምጽና ምላሽ አጥቶ አቧራ ሲቅም የኖረ “የንጉሥ ነጠላ!” ይህ ታሪክ የአንድ ድምጻዊያን የዚያን ወቅት የዜማ ግጥም ያስታውሰናል፡-
በአንድ ገጽ ወረቀት ጀምሬ አቤቱታ፣
ስንት ዓመት በሸንጎ ልኑር ስንገላታ።
አንተ የበላይ ሹም የእኔ ፍትሕ ሰጭ፣
ዶሴዬን መርምረው አይሁን ተቀማጭ።
እንዲታይ ነው እንጂ ወደ በላይ ቀርቦ፣
መች እንዲቀመጥ ነው መዝገብ ቤት አጣቦ።
ዛሬ ሺህ ዓመት ንገሥ የምንለው ዘውደኛ ባይኖርም የአስናቁ እናትን መሰል “በንጉሥ ነጠላ” የሚወከሉ ማሕበራዊ ጩኸቶች ግን የሉም ማለት አይደለም።
“የጊዜያችን የንጉሥ ነጠላ!”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም በተወካዮች መንበር ፊት ቀርበው “ለእንደራሴዎቻችን” ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ከእንደራሴዎቹ የቀረቡትን አብዛኞቹን ጥያቄዎች በተመለከተ “በአስናቁ እናት ነጠላ” ብንመስል ከእውነታው እጅግም አያርቀንም። ለምን ቢሉ በዛሬዎቹም መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውስጥ ጎራ የሚል ባለጉዳይ “ነጠላ ማንጠፍ” ይቀረውካልሆነ በስተቀር ጉዳዩን በቀላሉ ተኮሶ ይገላገላል ብሎ ለመደምደም ያዳግታል።
“የፍትሕ ያለህ ጩኸቱና እሪታው” ከኋለኛው ዘመን ቢተካከል እንጂ የመሻሻል ተስፋ እንደሌለው አስረግጦ መናገሩ እንዴት በጅምላ ተወቀስን አሰኝቶ ጥርስና ከንፈር አያስነክስም። ይህ ጸሐፊ ላለፉት ሦስት ዐሥርት ተኩል ዓመታት ያህል ያለመታከት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተባባሪ ዐምደኛነት ይህንን መሰል የሕዝብ ብሶት በብዕሩ ሲያስተገባ ቢኖርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮቹ ሲባባሱ እንጂ ሲሻሻል ባለማስተዋሉ ብዕሩ የሚያፈሰው ቀለም ተለውሶ የሚወጣው ከእምባ ጋር ተቀላቅሎ ጭምር ነው። በአገሪቱ መፍትሔ አጥቶ ሥር እየሰደደ የሄደውን የሕዝብ ብሶት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ ገላልጠው ለማሳየት ስለሞከሩና መፍትሔዎችንም ስላመላከቱ ጸሐፊው ላቅ ያለ አክብሮቱን ባይገልጽ ንፉግነት ይመስላል።
“መማለጃ የዐይናማውን ብርሃን ያሳውራል” እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ “ጉቦ” እንደ ቀደምት ዘመናት የሚጠየቀው በአዩኝ አላዩን ስቅቅና መሸማቀቅ ሳይሆን በግላጭ ከሆነ ሰነባብቷል።
ይህ ጸሐፊ “የበጎ ፈቃድ አምባሳደር” በሆነበት አንድ ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ የግሉን ጉዳይ ሊያስፈጽም በሄደበት አጋጣሚ አንዱ ሠራተኛ ዐይኑን በጨው አጥቦና አጉረጥርጦ “ጉዳይህ ፈጥኖ እንዲፈጸምልህ ከፈለግህ ይህንን ያህል ገንዘብ ክፈለኝ” ማለቱን ጠቅሶ ትዝብቱን በዚሁ ጋዜጣ ላይ ማስነበቡ አይዘነጋም።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሸንጎ የቅርብ ጊዜ ጉባዔውን እያካሄደ በነበረበት ዕለትም ይሄው ጸሐፊ የግሉን ቀላል ጉዳይ ለማስፈጸም በከተማው ሁለት ቢሮዎች ውስጥ ጎራ ባለባቸው ጊዜያት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደቀረቡለትና ይህንኑ ችግር ለአዲሱ የከተማው የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ “ነጠላውን የማንጠፍ ያህል” ደውሎ እጅግ መረር ባለ ድምጸት ብሶቱን መዘርገፉን መጥቀሱን ማስታወሱ ተገቢነት ይኖረዋል። ቀደም ባሉት ዘመናት “የአስናቁ እናትን መሰል ነጠላ” እያነጠፉ “ለንጉሥ አቤቱታ የሚቀርበው” “አባባ ጃነሆይ ቢሰሙም ባይሰሙም” መጉላላት ካልሆነ በስተቀር ምንም ክፍያ አይጠየቅበትም።
ጩኸቱ ንጉሡ ጆሮ ከደረሰ እሰየው፤ “የምስኪኑ አቧራ” እንዲራገፍ መመሪያ ተሰጥቶ መፍትሔ ይገኛል። ንጉሡ ጩኸቱን እንዳይሰሙ በእነ ጋሽ በቄና በክብር ዘበኞቹ ከተጋረዱም “አቤቱታ አቅራቢው” እምባውን ወደ ሰማይ እየረጭ የፈጣሪን ፍርድ ይጠብቃል። “የያኔው ፈጣሪ” ርሁሩህ ሳይሆን አልቀረም መሰል እምባ ቆጥሮ ግፈኞችን በአደባባይ መቅጣትን ያውቅበት ነበር። ንጉሡን ራሳቸውን ጨምሮ። ዘንድሮ ነጠላ ማንጠፍ ብቻም ሳይሆን ነጠላው ላይ የሚርከፈከፍ ባወንድ ከሌለበት ኡኡታውም ሆነ እሪታው ዋጋ ያለው አይመስልም።
የተገልጋዩ እምባ ዋጋ ያጣበት፣ ጉቦ የአደባባይ መደራደሪያ የሆነበት ይህ ወቅት አገሪቱን የት አድርሶ ምን ላይ እንደሚያፈርጣት ለመተንበይ በራሱ ተስፋ እንዲመክን ያደርጋል። በተለይም ስለ ለውጥ ሲነገርለት እንጂ ጋት ያህል ፈቅ ያላለው የፍትሕ ሥርዓት ሁነኛ አትኩሮት ሊደረግበት እንደሚገባ እንደ ትናንቱ ዛሬም ሕዝቡ ሕጉን ራሱን “በሕግ አምላክ” እያለ በመማጠን ላይ ነው። “አንተ ግቢ በልጄ ሞት መከራ እንደተሳለቅህ ብድራቱን አግኝ!” እያሉ ከአንድ ፍርድ ቤት ሲወጡ ያጋጠሙኝን እናት ባስታወስኩ ቁጥር እማማ የበቀሉ እናት ትዝ ይሉኛል።
ዛሬም እኛ ግፉዓን ዘመናችንንና እግዜሩን የምንሞግተው “ነጠላችንን አንጥፈን” በጽኑ የብሶት ጩኸት ፋታ እየነሳነው “አቤት! አቤት! ፈጣሪ ሆይ ግፋችንን ተመልከት!” በማለት ነው – ብዙ አገራዊ ምክንያቶችን እየጠቃቀስን። በየትኛውም የመንግሥት ተቋም ጎራ ያለ ተገልጋይ ዜጋ ጉዳዬ በአግባቡና በደንቡ መሠረት ተፈጽሞልኝ ሳልጉላላ ወይንም እጅ እጄን የሚመለከቱ “ኅሊና ሙቶች” ሳያጋጥሙኝ ደስ ብሎኝ ወጣሁ የሚል ከተገኘ አንድም “የማለዳ ጸሎቱ የሙሰኞችን ዐይን ጋርዶለታል” አለያም የተስፋችን ክር ሙሉ ለሙሉ እንዳይበጠስ እየታገሉ ያሉ ጥቂት ለኅሊናቸውና ለወንበራቸው የታመኑ የሕዝብ አገልጋዮች አጋጥመውታል።” ምክንያቱ ይሄው ብቻ ነው። በተለየ ሁኔታ ግን የንግድ ስራዎችን ለማደስና የሚዘጉ ድርጅቶችን ፕሮሰስ ለማድረግ በገቢ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት መገኘት፣ ውልና ማስረጃ የሽያጭና የግዢ ሰነዶችን ለማስፈጸም፣ ትራንስፖርት ቢሮዎች ዓመታዊ የተሽከርካሪ ብቃትን ለማረጋገጥ ወይንም የመኪና ግዥና ሽያጭን ለመፈጸም ውጣ ውረዱ ከታለፈ በኋላ ጥቂት የማይባሉ ሠራተኞች “ጉዳይህን/ሽን ፈጽሜለሁ!” በሚል አራራይ ድምጽና ማስተዛዝን ሲቁለጨለጩ ማስተዋል የተለመደ ክስተት ነው።
አንዳንዱማ አፍ አውጥቶ “ከፋም ለማ እናንተ እየተሻሻጣችሁ ገንዘብ ታንቀሳቅሳላችሁ፤ የእኛ ደመወዝ እኮ ከጉሮሮ የማትወርድ ነች!” የሚሉ ብሶቶች የተለመዱ ማስገደጃዎች ናቸው። ለምን እንዲህ እንደሚባል አንባቢው ይረዳዋል።
መታወቂያ ለማሳደስ ወይንም መሬትና ግንባታ ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወረዳና ክፍለ ከተሞች ላይ የተሰየሙ የበርካታ አገልጋዮችን ጉዳጉድ ብዕር የሚገልጸው ሳይሆን እዚያው በቦታው ተገኝቶ መመልከቱ ይበልጥ የተሻለ ያደርገዋል።
አቤቱ ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል! የተጨማለቁትን የበርካታዎቹን የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የታመቀ ክርፋት አደባባይ ገላልጦ ለማጋለጥ እንዲቻል የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች በምርመራ የጋዜጠኝነት ሙያቸው ሚናቸውን በነፃነት መወጣት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበቀደሙ ንግግራቸው አስረግጠውና መረር አድርገው መመሪያ የሰጡ ስለሆነ ራሳቸው ጋዜጠኞቹ ጤነኛ ሆነው ለማሕበራዊ በሽታዎቻችን መፍትሔ እንዲሆኑና ነጠላ ከማንጠፍ እንዲታደጉን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት በማስታወስ የአደራ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
ለመሆኑ “ሜዳውም ፈረሱም ያውላችሁ የተባላችሁት የሚዲያ ተቋሞቻችን ግልቢያውንና ጉጉሱን ትቋቋሙት ይሆን!?” የአስናቁ እናት ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ የሚያነጥፉት ነጠላ ብቻ ሳይሆን…”አንባቢው የመሰለውን ይሙላበት። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014