ሙስና (ጉቦ)- ብዙውን ጊዜ አንድ ባለስልጣን ወይም አካል በአደራ የተሰጠውን ኃላፊነትና ሥልጣን ከህግ እና ከሥነ ምግባር መርሆዎች በተቃራኒ ለግል ፍላጎትና ጥቅም ማዋል እና ያልተገቡ ዕድሎችንና ግንኙነቶችን መፍጠርን የሚያመለክት ፅንሰ-ሀሳብ ነው።
ሙስና መቀበልን ብቻ ሳይሆን፤ በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ ላሉ ባለሥልጣናትን ጉቦ መስጠትንም ያካትታል።በቀላል አነጋገር ሙስና የግል ጥቅምን ለማግኘት ስልጣንን ወይም ቦታን አላግባብ መጠቀም ነው፡፡
ጥቅሞቹ በተለያዩ ዘርፎች ማለትም ፖለቲካ ፣ ትምህርት ፣ ስፖርት ፣ ኢንዱስትሪ ፣ ወዘተ ሊገለፁ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም ።በመሠረቱ አንድ ወገን የሚፈለገውን ምርት ፣ አገልግሎት ፣ ቦታ ወይም ሌላ ነገር ለማግኘት ለሌላው ጉቦ ይሰጣል ።ልብ ማለት የሚያስፈልገው ግን ጉቦ ሰጪውም ሆነ ጉቦ ተቀባዩ አካል ሕግን የሚጥሱ መሆናቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የህልውና ትግል ውስጥ ውጤት ለማምጣት እስከ ህይወት መስዋዕት እየተከፈለ ይገኛል።
ከዚህም በዘለለ በሽብርተኛው ቡድን የወደሙ ንብረቶችን ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገም ይገኛል። ታድያ በዚህ መሀል የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሯሯጡ ሰዎች በስፋት ተስተውለዋል።
የሙስና ዓይነቱና ብዛት በየጊዜው የሚቀያየር ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የሙስና ወይም የአሰራር ንቅዘት ግን ዓይን ያወጣ እስከመሆን ደርሷል፡፡ አብዛኛዎቹ የለውጥ ሥራዎች ውጤታማ ቢሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ግን የተደረጉት ለውጦች ቀድሞ የነበረውን የህዝብ እንባ በማበስ ረገድ ብዙ ያልተራመዱ ናቸው ማለት ይቻላል።በተለይ በቤት ግንባታና በህገወጥ መሬት ወረራ በኩል ከቀደመው እኩል የሚሆን ኢፍትሀዊነት ተስተውሏል።
ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር አስጠናሁ ባለው ጥናት በርካታ ጉዶች ተመልክተናል። ታዲያ መንግሥት ባለበት አገር እንዲህ አይነት ዓይን ያወጣ ዘረፋ ማን ፈፀመው? የሚለው ጥያቄ ብርቱ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡ የለውጥ አመራሩ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አዲስ አበባ ከተማ ያለአግባብ ከኦሮሚያ ክልል መሬት ወስዷል በሚል ከፍተኛ ውዝግቦች እንደነበሩ አይረሳም።
በውዝግቡም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች በህገወጥ መንገድ ተይዘዋል የተባሉ ቤቶችም ሲፈርሱ ተመልክተናል።አንድ የሚያስማማን ጉዳይ በህገወጥ መንገድ ወይም በአካባቢው የሚገኘውን አርሶ አደር አፈናቅሎ መኖር አይቻልም።
ነገር ግን አርሶአደሩን በአነስተኛ ገንዘብ ከቦታው እንዲለቅ በማድረግ በከፍተኛ ገንዘብ መሬቱን የቸበቸቡት አመራሮች በድሎትና በከፍተኛ ስልጣን መንበር ላይ ሲቀመጡ መሬቱን በከፍተኛ ገንዘብ የገዛው ነዋሪ ግን ከቤት ንብረቱ በድጋሚ በሸጡለት አመራሮች ሲፈናቀል ማየት የአንድ ወቅት ለቅሶ ሆኖ አልፏል፡፡
እነዚህ ከላይ ያስቀመጥናቸው ጉዳዮች በቸልታ የታለፉ በመሆናቸው አሁን ላይ ዓይን ባወጣ መልኩ የትኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ገንዘብ መስጠት ግዴታ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል።በቅርቡ እንኳን የመምህራን ዝውውር ለማድረግ በየክፍለ ከተማው የሚከናወኑ ህገወጥ ተግባራት ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ አንድ ነዋሪ ሊያገኛቸው ከሚገባው ነገሮች አንዱና ቀላሉ የመታወቂያ ጉዳይ አነጋጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው።
የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያና የቀበሌ ቤት ለማግኘት ብዙም መልፋት አይጠይቅም።ምክንያቱም በህጋዊ ደረሰኝ የተጠየቁትን ገንዘብ ከፍለው መውሰድ የሚቻልበት አሰራር በመዘርጋቱ ነው። ይህ የተዘረጋው አሰራር ህጋዊነት ተላብሶ የሚሰራ የሙስና ተግባር ሲሆን የሌብነት ገመዱ እስከ ክፍለ ከተማ የተዘረጋ ነው።
በዚህም በየቀበሌው ለአቅመ ደካማ፣ ለህመምተኞች እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች እንዲሰጥ የተቀመጡ ቤቶች አየር በአየር መቸብቸብ በአሁኑ ወቅት የደራ ገበያ ሆኗል፡፡ ሌላው አድሏዊና ሙስና የተንሰራፋበት አካሄድ የኮንዶሚኒየም እደላ ሥራው ነው።
በ2005 ዓ.ም ዳግም ምዝገባ ተብሎ ምዝገባ ቢካሄድም ቤት የተረከበው ግን ጥቂቱ ነው። ይህ ለምን ሆነ ቢባል መልሱ ሙስናና የነቀዘ አሰራር መኖሩ ነው።የኮንዶሚኒየም አሰጣጥ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ኢ-ፍትሀዊ የሆነ የቤት እደላዎች መኖራቸውን በቅርቡ የከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው የኦዲት ሥራ መገኘቱን ተጠቅሷል።
ከኢ-ፍትሀዊ እደላዎች በተጨማሪ በህገወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችም መገኘታቸው ይታወሳል። እዚህ ጋር ሳይጠቀስ የማያልፈው ጉዳይ የኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ከአሰራራቸው ጀምሮ በሚደረግባቸው የቅሸባ ሥራ ለተጠቃሚው ከመድረሳቸው በፊት ፈራርሰው ይታያሉ።
ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው በመገናኛ ልዩ ቦታው 24 አካባቢ የተገነቡት 40/60 ቤቶች ናቸው። ቤቶቹ ተጠናቀው ለተጠቃሚው መተላለፍ ከሚገባቸው ጊዜ ከማለፋቸው ባሻገር እየፈራረሱ ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻ የምንመለከተው የመንግሥት መስሪያቤቶች ሆነ በሌሎች ተቋማት ያለው የሙስና ዓይነት በየጊዜው ተለዋዋጭ በመሆኑ ጭራው ሊያዝ አለመቻሉን ነው። በግዥና በግንባታ ስም የሚወጡት ወጪዎች ከመብዛታቸው የተነሳ አንዳንዴ ምን ተሰርቶ ወይም ተገዝቶ ገንዘቡ እንደወጣ ማስረጃ ሲቀመጥ አይታይም።
ከእድሳት ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ወደ ሥራ ቢገባም ሥራው ሲጠናቀቅ ግን የወጣበት ገንዘብና የተሰራው ሥራ ተራርቆ የሚታይባቸው አጋጣሚዎችም እየተበራከቱ መጥተዋል። ሊታወቅ የሚገባው ለአንድ አገር እድገት የሁሉም ሰው ርብርብና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ነው።
ይህ ሆኖ ግን በአንድ እጅ እየሰሩ በአንድ እጅ መስረቅ ከባለህበት እርገጥ ሊያወጣን አይችልም።ለውጥ ለማምጣት መራብ፣ መጠማት እንዲሁም ሌሎች መስዋዕትነቶችን መክፈልን ይጠይቃል።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ አገራት በሚደረግ የለውጥና የእድገት ጉዞ ውስጥ ለሙስና ተግባር ራስን ማዘጋጀት ሳይሆን ለውጡን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ መስዋዕትነትን ለመክፈል መዘጋጀት አስፈላጊ ናቸው።
ስለዚህም ነው አሁናዊው የሙስና ተግባር ህግ ማስከበርን ይፈልጋል የምለው፤ እናም ጊዜው የሌብነት አስተሳሰብን በማስወገድ ለጋራ እድገት መቆም የግድ ይላል፡፡
በአምኃየስ መርዕድ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 /2014