ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ወጥረው ከያዟት ዘርፈ ብዙ ትብታቦች እንድትላቀቅ እና የቀደመ ገናናነትና የታሪክ ባለቤትነቷን የሚመጥን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መሰረቶችን ማኖር በዚህ ዘመን ትውልድና በአሁኑ መንግስት ላይ የወደቁ ትልቅ የቤት ሥራዎች ናቸው።
ይሄን ኃላፊነት ወስዶና ትውልዱን አስተባብሮ የቤት ሥራውን ከመወጣት አኳያ መንግስት ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል። በዚህ ረገድ ከሰሞኑ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት፤ ወቅት መንግስት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የጸጥታ ሁኔታዎችን አቃልሎ ከመሻገር አኳያ አምስት “ዲ”ዎችን አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ጸጥታ ሁኔታ አንጻር የመንግስት አቅጣጫና አካሄድ አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል።
እነዚህም አምስት “ዲ”ዎች (5D) በሚል የሚገለጹ ሲሆን፤ ዲፌንስ(መከላከል)፣ ዲስከሽን ወይም ዲያሎግ (ውይይትና ምክክር)፣ ዴሞክራሲ፣ ዴቨሎፕመንት (ልማት) እና ዲፕሎማሲ ናቸው። እኔም በእነዚህ አምስት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ስለ ጉዳዮቹ ይዘትና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ችግሮች የመፍትሄ አካል የመሆናቸው እውነት ላይ እንደሚከተለው ለማንሳት ወደድኩ።
ዲፌንስ (መከላከል)
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ውስጥ በመጀመሪያ የተቀመጠው ዲፌንስ ወይም መከላከል የሚለው ሀሳብ ነው። በእርሳቸው ገለጻ መሰረት መከላከል የሚለው እሳቤ፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት እንዲሁም ሰላም አስጠብቆ ማቆየት የሚቻልበትን ሂደት ይመለከታል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ጠንካራ የመከላከል አቅም መፍጠር ሲቻል እና አገር እንደ አገር፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ጥቅምና ሉዓላዊነቱ ከሰላሙ ጋር ተዳምሮ መረጋገጥ ሲችል ነው። በዚህ ረገድ በሁሉም ሴክተር መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ እንሰራልን ሲሉ ተደምጠዋል።
ታዲያ ይህ እንዴት ይሆናል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የመጀመሪያው ጉዳይ የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በዘመናት የታሪክ ሂደቷ ውስጥ ድንበሯ ሳይደፈር፤ ሉዓላዊነቷም ሳይሸራረፍ ዘልቃለች። ይህ ደግሞ በሕዝቦቿ ተጋድሎ፤ በመሪዎቿ ጥንካሬና ጥቃትን አልቀበልም ባይነት ላይ ይመሰረታል።
አሁንም ቢሆን ከውጭም ከውስጥም ተባብረው አንድነቷን ሊንዱ፤ ሕዝቦቿን ሊያዋርዱ የሚውተረተሩ አያሌ ጠላቶች ከመፍላት አልቆሙም። የቅርቡ ሁነትም (አሸባሪው ሕወሓት በውጭ ጋላቢዎቹ እየታገዘ የፈጸመው አገር የማፍረስ ተግባርና ክህደት) የዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው። በዘመናት ውስጥ የሚፈጠሩ መሰል አጋጣሚዎች ደግሞ የራሳቸውን ክፉ ጠባሳ ብቻ ሳይሆን መልካም እድልም ሰጥተው ነው የሚያልፉት።
አሁናዊው የአሸባሪው ሕወሓትና ጋላቢዎቹ ተግባርም ኢትዮጵያ በተግባር የተፈተነ የአገር መከላከያ ሰራዊት እንድትገነባ፤ በሰው ሃይልም፣ በሎጀስቲክስም፣ በቴክኖሎጂም እንድታስታጥቅ፤ የባህር አማራጮችንም እንድታማትርና በዛው ደህንነቷን ማረጋገጥና ጥቅሞቿን ማስጠበቅ የምትችልበትን አጋጣሚ የፈጠረላት ሆኗል። ይሄን አይነት ሁሉን አቀፍ መከላከያ ሰራዊት መገንባት መቻል ደግሞ አንዱ የመከላከል አቅጣጫ እንደመሆኑ፤ ይሄው ተጠናክሮ ሊቀጥል በእጅጉ የተገባ ነው። ጠንካራ የመከላከል አቋም ያለው መከላከያ ኃይል ከመገንባት ጎን ለጎን ግን ይሄን የሚያደርግ ትውልድ መገንባት ሌላው የመከላከል አንዱ ትኩረት ሊሆን ይገባል።
ምክንያቱም ተከላካይ ማኅበረሰብ የመገንባት ሂደቱ ጤናው የተጠበቀ ሕዝብ ባለቤት መሆንን ይጠይቃል፤ እውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂን የታጠቀ ወጣት የግድ ስለሚልም ዜጎችን ከአላዋቂነትና ከኢምክንያታዊነት መጠበቅን ይጠይቃል፤ በአካል ጎልብቶና ጠንክሮ መገኘትን ስለሚጠይቅ በልቶ ከማደር ባሻገር የተመጣጠነ አመጋገብ ሥርዓት ያለው ማኅበረሰብ እውን ማድረግን ይሻል፤ ፍቅር በመካከሉ የነገሰ፣ መተሳሰብናመተባበርን ባህሉ ያደረገ፣ ለጋራ ሰላሙና ህልውናው የአባቶቹን ወኔ ተላብሶ የሚታገል ልበ ሙሉና አርበኛ ትውልድ መፍጠርን አጥብቆ ይሻል።
ዲስከሽን (ውይይት)
ዲስከሽን ወይም ዲያሎግ (ውይይት እና ምክክር) ሁለተኛው ጉዳይ ሲሆን፤ ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ አሸናፊ የሚያደርጋትን ህብረትና ኃይል እንድታገኝ የበለጠ እድል የሚፈጥርላት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ውስጥ የጎላ ታሪክና ልዕልና ያላት ከመሆኑ ባሻገር፤ በዚህ ታሪክና ልዕልና ውስጥ የተገለጠ አንድነቷ ከፍ ብላ ለመታየቷ ትልቅ ቦታ አለው። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ከከፍታዋ፣ ኢትዮጵያውያንም ከገናናነታቸው ማማ ዝቅ እንዲሉ ያደረጓቸው የዘመናት የታሪክ ሂደት ንትርኮችና ቁርሾዎች አሉ።
እነዚህ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት የበለጠ እንዲጎሉ እና የመነጣጠያ ምክንያት እንዲሆኑ ለማድረግ በጉልህ ተሰርቶባቸዋል። ከዚህ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የታሪኳ ግዝፈት፣ የነጻነቷ ፋናነት፣ የመቻል ግስጋሴዋ እረፍት የማይሰጣቸው፤ ስለ እድገትና ልማቷ፣ ስለ ብልጽግና ጉዞዋ፣ አጠቃላይ ለውጧን ባሰቡ ጊዜ በመበለጥ ስሜት የሚንገበገቡ የሩቅም የቅርብም ባላንጣዎች፤ በታሪክ ጅረት ውስጥ በመልካም የማይመለከቷትና ለጦርነትም ሲመኟት ብቻ ሳይሆን ሲተነኳኩሷት የቆዩ አገራት አሉ።
ዛሬም ድረስ ከመልካም ጉርብትና ይልቅ በተልዕኮ አጀንዳ ራሳቸውን የቃኙ፤ ከትብብር ይልቅ በእኔ አውቅልሻለሁ እሳቤ ሊጫኗት የሚሹ፤ በጋራ ከመልማት አካሄድ አፈንግጠው እኛ ስንበለጽግ አንቺ ሃብትሽን ዝም ብለሽ ተመልከቺ ብለው የሚመጻደቁ ራስ ወዳድ መንግስታትም ከየአቅጣጫው እረፍት አልሰጧትም።
በመሆኑም የቀደመችው ኢትዮጵያ ዛሬም ዳግም በኃያልነቷ፣ በነጻነቷና በምሳሌነቷ ገጽ ላይ እንድትውል፤ ኢትዮጵያውያንም በቆየ የአንድነትና የሕብረት ዙፋናቸው፣ በአይበገሬነት ክንዳቸው፣ በመተሳሰብና መተጋገዝ እሴታቸው እንዲገለጡ በአንድ በኩል የውስጥ አንድነታቸውን የሚያላሉ እነዚህ ለንትርክ የተዘጋጁና የተበጃጁ የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሽሩ ማድረግ፤ በሌላ በኩል ከአገራት ጋር በትብብርና አብሮ መልማት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖራት ማስቻል ይገባል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የቆየ ኅብረትና አንድነታቸውን የሚያጠነክሩበትን፤ የታሪክ ጠባሳቸውን በይቅርታ ተሻግረው በንጹህ ልብ ስለ ነጋቸው በጋራ የሚቆሙበትን እድል የሚሰጥ የውይይትና ምክክር መድረክ አስፈላጊ ሆኗል። በዚህ ረገድ መንግስት አገራዊ የምክክር መድረክ እንዲካሄድ አቅጣጫ አስቀምጦ እና በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ ተቋም መስርቶ፣ ተቋሙን ወደ ተግባር የሚያስገቡ ኮሚሽነሮች ተሰይመዋል። ቀጣዩ ሥራም ኮሚሽነሮቹ በሚያወጡት የአሰራርና የጊዜ እንዲሁም የአጀንዳ ቅርጽ አንጻር የሚፈለገውን የመነጋገሪያና የመግባቢያ መድረክ እውን ማድረግ ይሆናል።
ይህ ውይይትና ምክክር ታዲያ ላይ ላዩን ለይምሰል የሚከወን ሳይሆን፤ በጠቅላይ ሚንስትሩ እንደተገለጠውም የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የመከራከሪያ ሃሳብ አለን የሚሉ ወገኖችን፣ በጥቅሉ ምልዓተ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ሊሆን የሚገባው ነው። በዚህ መልኩ የሚከወን ውይይትና ምክክር በውስጥ ያሉብንን ልዩነቶች በመነጋገርና መተማመን ላይ ተመስርቶ በመፍታት የውስጥ አንድነትን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሳደግ፤ በጋራ ቆሞ ጥቅምና ፍላጎቱን፣ ሉዓላዊነትና ሰላሙን የሚያስጠብቅ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ታላቅ ሕዝብ እውን ማድረግ የሚያስችል ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የጠነከረው የውስጥ አቅም በመልካም ጎርብትና ማዕቀፍ መቃኘት ስለሚኖርበት፤ ከኢትዮጵያ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚገናኙ አገራት ጋርም መነጋገር፣ መመካከርና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን አስፍኖ መሄድ መቻል ተገቢነት ያለው ጉዳይ ነው።
በመሆኑም የዲስከሽን ወይም የምክክርና ውይይት እሳቤው በውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የልዩነት ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ፈትቶ ለተሻለ ትብብርና አብሮነት ራስን የማዘጋጀት ከፍ ያለ ስራ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የተወሳሰቡ ችግሮቿን ውል ለማበጀት፣ ያልተመለሱ የሕዝብ ጥያቄዎቿን ለመመለስ፣ በጥቅሉ በውስጥም በውጭም ያሉ የልዩነት ውቅሮቿን ነቅላ የአንድነት መሰረት የምታጸናበት፣ ከአገራት ጋር መልካም ጉርብትናም ትብብርም የምትፈጥርበትን መንገድ የሚቀይስ ሁነኛ መስመር ነው።
ዴሞክራሲ
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዴሞክራሲ የብዙ ነገሮች ማጠንጠኛ ነው። ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንም መሰረታዊው ዋስትና ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም በጅምር ያለውን የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት እና ልምምድ ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሻገር ተገቢ ነው። ይህ ግን በአፍ ስለተነገረ፣ በፍላጎት ደረጃ ስላለ እውን የሚሆን አይደለም።
ይልቁንም በየትኛውም የመንግስት አካል (በሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው) እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የዴሞክራሲ ልምምዱን ከፍ ማድረግ፤ አሰራሮችም ዴሞክራሲያዊነትን እንዲላበሱ ማስቻል ከሁሉም የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። ሊገነባ የሚያስፈልገው ዲሞክራሲ ደግሞ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፤ ዓለም አቀፍ ይዘቱን የጠበቀ፤ ኢትዮጵያውያን ለሚናፍቁት ከፍታና የብልጽግና ጉዞ መደላደል ሆኖ የሚያገለግል፤ ለይምሰል ሳይሆን ሆኖ ሲተገበር የሚታይ፣ ለእኩልነትና በጋራ ለመኖር መሰረት የሚሆን፣ ሕዝቦች ከላይ የሚጫንበትንና ተገድደው እንዲቀበሉ ከሚደረግበት አካሄድ ወጥተው ራሳቸው የሥልጣንም የውሳኔም ባለቤትነታቸውን የሚጎናጸፉበት፣ ወዘተ. ሊሆን ያስፈልጋል። ይሄን አይነት ዴሞክራሲ መገንባት ሲቻል አብዛኛውን የኢትዮጵያ ችግር ማቃለል እና የሚፈለገውን ሰላም እውን ማድረግ የሚቻልበትን እድል ይፈጥራል።
ዴቨሎፕመንት (ልማት)
ልማት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ከምንም በላይ የሕልውናቸው ማስጠበቂያ ሁነኛ መሳሪያቸው ነው። ልማት ከአገር ዕድገት ጋር ብቻ የሚያያዝ ሁነት አይደለም። ይልቁንም ከዜጎች በልቶ የማደር፣ ሰርቶ የመኖር፣ የተሻለ ኑሮን ከመምራት፣ መሰረታዊ የሆኑ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ከሚባሉት ልብስ፣ ምግብና መጠለያ ዓይነት ጉዳዮችን አሟልቶ መኖር ጋር የሚያያዝ ነው።
የራበው ሰው ረሃቡን ለማስታገስ የሚጓዝበት የራሱ መንገድ ይኖራል፤ ሰርቶ የማይኖር ወጣት ስራ በመፍታቱ እጆቹን ለጥፋት ያነሳል፤ የተሻለ ኑሮን መምራት ያልቻለና መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ያላሟላ ማኅበረሰብ አንድ ቀን ዝምታውን መስበሩ አይቀሬ ነው። የእነዚህ ጉዳዮች ድምር ውጤት ደግሞ ለአገር ሰላምና መረጋጋት የራሱን አሉታዊ ጫና ማሳደሩ እውን ነው።
ከዚህ አኳያ የልማት ጉዳይ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ህልሟን የማሳካት ጉዞ ብቻ ሳይሆን፤ ልማትና ብልጽግና ላይ ካልተሰራ ሰላሟ አደጋ ላይ ይወድቃል፤ ዴሞክራሲው መሰረቱ ይናጋል፤ የመከላከል ሂደቱም ምሉዕነት ይጎድለዋል፤ በጥቅሉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ምስቅልቅል ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ግብ እንዲመታ ማድረግ በእጅጉ ፈታኝ ይሆናል። ከዚህ አኳያ ልማት(ዴቨሎፕመንት) ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እና ውጤት ማምጣት ለነገ የማይተው ተግባር ሊሆን ያስፈልጋል።
ይህ የልማት ሂደት ሁለት ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላል። አንዱ ቁሳዊ ልማት ሲሆን፤ ሁለተኛው ሰብዓዊ ልማት ነው። ከቁሳዊ ልማት አኳያ በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ሊያሳልጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ለይቶ መስራት እና የኢኮኖሚ አቅሟን ማፈርጠምን የሚመለከት ነው።
በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ለዕድገቷ የሚያግዙ እምቅ ሃብቶቿን ለይቶ ማልማት አንዱ አቅጣጫ ሲሆን፤ ያላትን ሃብት በውጤታማ የአጠቃቀም መርህ ላይ ተመስርቶ ለተሻለ ብልጽግናዋ ጉዞ ማዋል፤ ልማቱን በግለሰቦች ኪስ የሚለካ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ የሚገለጽ ሊሆን ያስፈልጋል።
ከሰብዓዊ ልማት አኳያ ይሄን ቁሳዊ ልማት እውን ማድረግ የሚችል በቴክኖሎጂም፣ በአስተሳሰብም፣ በክህሎትም የበለጸገ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የሚያተኩር ነው።
ይሄኛው ልማት ቁሳዊ ልማቱ ለውጤት እንዲበቃ፤ አጠቃቀሙና ተደራሽነቱም ለሁሉም እንዲሆን የሚያስችል እሳቤን የሚያስጨብጥ፤ ሌብነትና የሃብት ብክነትን ለመከላከል የሚያስችል፤ ወዘተ. አቅም የሚፈጥር ነው። በመሆኑም የእነዚህ (ቁሳዊና ሰብዓዊ ልማቶች) ድምር ውጤት በአንድ በኩል ኢኮኖሚውን መገንባት የሚያስችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ውጤታማ የኢኮኖሚ አጠቃቀምን ለመተግበር እንዲሁም ከኢኮኖሚው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የሚያስችል ነው።
ዲፕሎማሲ
የኢትዮጵያ የውስጥ አንድነቷን ለመፍጠር ከምታደርገው የምክክርና ውይይት ሂደት፤ ሰላምና ሉዓላዊነት እንዲሁም ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ከምታከናውናቸው የመከላከል ተግባራት፤ የውስጥ ዴሞክራሲዋን የማጎልበት እና ልማቷን የማፋጠን ተግባራት በተጓዳኝ፤ ዲፕሎማሲዋን ማጠናከር ስትችል ቅቡልነቷን እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ አድርጎ የማሳየት አቅሞ ላቅ ያለ ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ ተሳትፎና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነችባቸው የዲፕሎማሲ ጉዞዎች አሉ። በዩናይትድ ኔሽን ምስረታም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ወቅት የነበራት ሚና፤ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል እና ይሄን ተከትሎ ያስመዘገበችው ድል የፈጠረላት ከፍ ያለ ገጽታ፤ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝነቷ ያሰባሰበላት ብርቱ አፍሪካዊ ክንድ ተጠቃሽ ማሳያዎች ናቸው።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ የሆኑትና የተፈጸሙ የዲፕሎማሲ ጫናዎችና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ውጣ ውረዶችን የተሻገረችውም በእነዚህ ከፍ ብለው በሚገለጹ የዲፕሎማሲ ጉዞ ልዕልናዋ አማካኝነት ነው። የራሷን ሃብት አልምታ ለመጠቀም የዓባይ ወንዝን ገድባ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ባደረገችው ጥረት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት እና የእነርሱ ተከታይና አጋዥ በሆኑ ጀሌዎች ምክንያት ኢትዮጵያ በብዙ ተፈትናለች።
ይሁን እንጂ የጥበብ ምንጭ የስልጣኔ መሰረት የሆነውን ዓባይ ወንዟን ገድባ ለመልማት የተነሳች አገር የዲፕሎማሲው ጥበብ አይጠፋትምና እንደ ትናንቱ ሁሉ በዚህ ወቅት የዲፕሎማሲውን የበላይነት ተቆናጥጣ ተወጥታዋለች። ይህ የበላይነት የተወሰደባቸው ኃይሎች የውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው አገር ለማመስና ለማፍረስ በኢትዮጵያ ላይ በተፈጸመው ጦርነትና የአገር ክህደት ወቅትም፤ በዲፕሎማሲው ብቻ ሳይሆን በሃሰት ወሬ መጠነ ሰፊ የፖሮፖጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶባት ነበር።
ይህ ችግሩን ከውስጥም ከውጭም ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረገና ከፍ ላለ ጫናም የዳረገ ሂደት ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በተለመደው የአንድነት ገመድ ሕዝቦቿን አስተሳስራ፤ የፓን አፍሪካኒዝም ቅኝት አፍሪካውያንን አሰናስላ በመስራቷ ዳግም የዲፕሎማሲውን ጫና መቀልበስ፤ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻውንም ማክሸፍና መሻገር ችላለች።
ይህ የዲፕሎማሲውን ከፍታ ጠብቆ በአሸናፊነት የመሻገር አቅም አሁንም ቀጣይነት ሊኖረው፤ የኢትዮጵያ ሁለንተናታዊ ብልጽግና እውን እየሆነ በሄደ ቁጥር ጫናው እየበረታ የሚሄድ መሆኑን ተገንዝቦም ከፍ ባለ ደረጃ የዲፕሎማሲውን ዘርፍ መምራት እንደሚያስፈልግ እሙን ነው።
ምክንያቱም ጠንካራ ዲፕሎማሲ የውስጥ አቅምን አስተባብሮ መጠቀምን፤ የውጭ ወዳጅና አጋር አገራትን ከጎን ማሰለፍን፤ ስለ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ፍላጎትና ተስፋ በጥበብ አስረድቶ ማሳመንን፤ የጋራ ተጠቃሚነትና መደጋገፍ ሁነኛ የግንኙነት መስመር አድርጎ መጠቀምን ይጠይቃል።
ለዚህ ደግሞ የዲፕሎማሲው ዘርፍ ሹመኞችንና ባለሙያዎችን አቅም ከማሳደግ፤ በየተሰማሩበት ቦታ ውጤታማ ሆነ ለመገኘት የሚያስችላቸውን ስልቶች ቀይሶ ከማስጨበጥ፤ በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን እንደ እስካሁኑ ሁሉ የአገራቸው ዲፕሎማትና ልሳን ሆነው የሚሰሩበትን ጠንካራ አሰራር ከመዘርጋት፤ የውስጥ አንድነቱ የዲፕሎማሲው ትግሉ ጽኑ መሰረት ሆኖ እንዲቀጥል ከማስቻል፤ ከአገራት ጋር የባለ ብዙም ሆነ የሁለትዮሽ ትብብርና ግንኙነቶችን በጥበብ እንዲመራ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራን በእጅጉ የሚጠበቅ ይሆናል።
በአጠቃላይ ከላይ የጠቃቀስኳቸው አምስቱ ዲዎች (ዲፌንስ፣ ዲያሎግ ወይም ዲስከሽን፣ ዴሞክራሲ፣ ዴቨሎፕመንትና ዲፕሎማሲ) ኢትዮጵያን ከአሁናዊ ችግሮቿ መሻገሪያ አድርጎ ከመጠቀም አኳያ ከመንግስት የሚጠበቅ ትልቁ የቤት ሥራ መሆን አለበት።
ይህ እውን እንዲሆን ግን መላው ኢትዮጵያውያን ተቀራርበው በመመካከር እና በመነጋገር መስራት፤ እንደ እስካሁኑ ሁሉ ኢትዮጵያን በማጽናት ሂደት ውስጥ የማይፋቅ አሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። አበቃሁ፤ ሰላም!::
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014