ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ ያደረኩት ከማህበራዊ ድረ ገጽ ያገኘሁት አንድ መሳጭ ታሪክን ነው። ነገሩ እንዲህ ነው ፤ ሦስት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሀብታም የግመል ነጋዴ ሰው ነበር አሉ፤ ይህ ነጋዴ ያለውን ሀብትና ንብረት ለልጆቹ አከፋፍሎ ሳይሰጣቸው ድንገት ሞት መጣና ወሰደው።
ነገር ግን ሰውዬው ከመሞቱ በፊት የኑዛዜ ወረቀት አስቀምጦ ነበርና ኑዛዜው ተከፍቶ ሲነበብ ለመጀመሪያ ልጁ ያለውን ንብረት ግማሽ እንዲወስድ፤ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ የንብረቱን ሲሶ ማለትም አንድ ሶስተኛውን እንዲወስድ፤ ለመጨረሻው ልጁም የንብረቱን አንድ ዘጠነኛ እንዲወስድ ተናዟል። ይሄን ኑዛዜ ያስቀመጠው አባት (የግመል ነጋዴው) የነበረው ሀብት አስራ ሰባት ግመሎች ብቻ ናቸው።
ታዲያ ልጆቹ እነዚህን አሥራ ሰባት ግመሎች እንዴት አድርገው ይካፈሉ? አሥራ ሰባት ግመሎችን መጀመሪያ ግማሽ፣ ቀጥሎ ሲሶ፣ ከዚያ ደግሞ አንድ ዘጠነኛ አድርገው ለመከፋፈል በጣም ተቸገሩ።
ይህንን ተከትሎም በመካከላቸውም ድብልቅልቅ ያለ ጸብ ተነሳ። ከብዙ ቡጢና ስድድብ በኋላ ሰከን ብለው ማሰብ ጀመሩ። መቼም በቡጢ የሚገኝ መፍትሔ የለምና ቁጭ ብለው ከተነጋገሩ በኋላ ወደ አንድ ብልህ ሰው ዘንድ ሄደው ችግራቸውን አስረድተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠየቁት ።
ብልሁም ሰው ነገሩን በሚገባ ካጠና በኋላ የራሱን አንድ ግመል ጨመረና የግመሎቹ ቁጥር አስራ ስምንት አደረሳቸው፤ በኑዛዜው መሰረትም ማከፋፈሉን ጀመረ። ለመጀመሪያው ልጅ የአስራ ስምንቱን ግማሽ አስቦ 9 ግመሎችን ሰጠው፤ ለሁለተኛውም ልጅ የ18 ግመሎች ሲሶውን አስቦ 6 ግመሎችን ሰጠው ፤ ለሦስተኛው ልጅም የ18 ግመሎች 1/9ኛውን አስቦ 2 ግመሎችን ሰጠው ፤ልጆቹ የወሰዱትን የግመሎች ቁጥር አስራ ሰባት ደረሰ ።
ታዲያ አንድ ግመል ተረፈ? ብልሁም ሰው የተረፈችውን አንድ ግመል መልሶ ለራሱ ወሰደ። ይባላል። አንዳንድ ጊዜ አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው በሚያነታርኩን ነገሮች መካከል ከባዱ ነገር አሥራ ስምንተኛዋን ግመል ማግኘት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከላይ እንዳለው ታሪክ በንትርክ በቡጢ የሚገኝ መፍትሔ
የለም፤ ነገር ግን ብልህ አሸማጋይ ከሌለ ደግሞ ትርፉ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ፣ ስድብና ቡጢ ይሆናል ። ስለዚህ ሁል ጊዜም ቢሆን ችግሮች ሲያጋጥሙ የመጀመሪያው ነገር ያለ መፍትሔ የተፈጠረ ችግር አለመኖሩን ማመን ነው።
ቀጥሎ በተቻለ መጠን በጋራ ሜዳ ላይ ሆኖ የሚያቀራርብ ሃሳብ ለማግኘት መሞከር ነው። ይህ ምናልባትም የሌሎች ወገኖችን እርዳታ ሊያስፈልግ ይችላልና ያንንም በአግባቡ መጠቀም ከንትርክ፣ ከቡጢ አድኖ ተስማምቶ መኖርን ያድላል ፤ ከዚያም ነገሮች መስመር መያዝ ይጀምራሉ።
ብልህን የሚያስብለው፣ አዋቂን አዋቂ የሚያሰኘውም ዋና ቁምነገር መማር ማወቁ መመራመሩ ብቻ ሳይሆን ችግርን በብልሃት መፍታት መቻሉ ነው ለእኔ ፤ የችግርን መፍቻ ቁልፍ መንገድ የሚያውቅ የመፍትሔ ሰው ለመሆን መሞከሩ አግባብነት ያለው ነው። እኛም እንደ አገር በተለይም አሁን ያለንበት ወቅት አሥራ ስምንተኛዋን ግመል የመፈለግ ያህል ሆኖብናል።
ሁሉም ግራ በተጋባ መንፈስ ውስጥ ሆኖ የየራሱን ሃሳብ ከመሰንዘር ባለፈ ንትርክና ጭቅጭቅ አልፎም ቡጢ ገጥመን ያለንበት ጊዜ ነው።
ግን ንትርካችንም ሆነ እርስ በእርስ ቡጢ መሰናዘራችን ወገኖቻችንን ከመቅጠፍ፤ ለዓመታት የለፋንበትን ንብረት ውሃ እንዲበላው ከማድረግ፤ ባለፈ የፈየደልን አንድም ነገር የለም። ጭቅጭቃችን የምንፈልገውን ነገር ካልሰጠን ወይም ለችግራችን መፍትሔ ካላመጣልን ሰከን ብለን ማሰብን ማን ከለከለን? ሰከን ብሎ ለማሰቢያ ለራሳችን ጊዜ ሰጥተው አውጥተን አውርደን ይህ ቢሆን ይህ ነው፤ ያንን ብናደርግ ትርፉ ምንድን ነው? የሚለውን አጢነን የመፍትሔ ሰዎች ብንሆን አይሻልም? ለእኔ ከምንም በላይ የሚሻለው መንገድ ይህ ነው።
እንደ አገር ብዙ ፍላጎት አለን፤ የእኛ ብለን የምንመኘው ነገርም የትየለሌ ነው፤ ግን ሁሉን ማግኘት ሁሉም እንዲሳካ ማሰብ አይቻልም። ከፍላጎታችን ይልቅ የሚያስፈልገንንና ነገ ላይ ቀና አድርጎ በሰላም ያለንትርክና ቡጢ ሊያከርመን የሚችለውን ሃሳብ መግዛት ብንችል ጥሩ ነው።
ዛሬ ላይ ከተጣላናቸውም ሆነ ከተጣሉን ደም ከተቃባናቸውም ጋር ቢሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን እንድንመካከር ሃሳብ ቀርቧል፤ በዚህ ሃሳብ ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ያሉ ቢሆንም እኛን ግን እንደ አገር የሚጠቅመንየቱ ነው ?የተሰጠንን ነገር በሰላምና በፍቅር ተካፍለን አብረን መኖር ወይንስ በጣጥሰን ተካፍለን ነገ የሰው ቤት ቀለዋጭ መሆን።
(የሚያስቀላውጥ ከተገኘ ማለት ነው።) እንደእኔ ግን የሚሻለው እኛው ለእኛው ብልህ አማካሪ ሆነን የመፍትሔ ሰዎች አደራዳሪና አሸማጋይ ልባሞች ሆነን አገራችንን ካጎነበሰችበት ቀና እንድትል ፤ ወጥተው በዱር በገደሉ የተበተኑ ልጆቿ ተሰብስበውላት ስቃ እንድንያት ነው።
ይህንን ማድረግ ደግሞ እንኳን ለእኛ በፍቅር፣ በመተሳሰብ በአብሮነት ለኖርን ኢትዮጵያውያን አይደለም ለማንም የሚጠፋ አይመስለኝም። እናም ወገኔ ዛሬ ላይ የተመቻቸልንን የሰላም የእርቅ የምክክር መድረክ እንደቀልድ አይተነው እከሌ እኔን አይወክልም፣ እከሌ አቅም የለውም፣ ነጻ አይደለም፣ ገለልተኝነት ይጎለዋል፤ እያልን በአቃቂርና ባላዋቂነት አስተያየት በመስጠት ላይ ብቻ ተጠምደን የምናሳልፋት እያንዳንዷ ደቂቃ ዋል አደር ብላ እኛኑ ዋጋ የምታስከፍል እንዳትሆን መጠንቀቁ አይከፋም።
ያሉን ችግሮችም መፍትሄ የሌላቸው አይደሉምና ራሳችን አስራ ስምንተኛዋን ግመል ፈጣሪዎችና የችግሮቻችን መፍትሄ አቀባዮች መሆን ይጠበቅብናል።
ለዚህ አገራዊ ድርብ ኃላፊነት የምትሰየሙ ኢትዮጵያውያንም ሰውን ብልህ የሚያስብለውና አዋቂ የሚያሰኘው ዋናው ቁምነገር መማር ማወቁ መመራመሩ ብቻ ሳይሆን ችግርን በብልሃት መፍታቱ ፤ በጠቅላላው የመፍትሔ ሰው መሆኑ ነውና ከእናንተም የምንጠብቀው ይህንኑ ነው።
ከአድሎና መድሎ መጽዳት ሌላው አስፈላጊና ተገቢ ጉዳይ ነው። ለእኔ ብሔር ወይም ሃይማኖት ብላችሁ ያዳላችሁ እንደሆነ ግን ታሪክም ሲወቅሳችሁ እናንተም የህሊና ባለእዳ ሆናችሁ ትቀራላችሁ።
ዛሬ በአገራችን እያንዳንዷ ጉዳይ ላይ በክፉም ይሁን በደግ የምናኖራት ድንጋይ ነገ ለልጆቻችን፣ለልጅ ልጆቻችን ከዚያም በላይ ለሚመጣው ትውልድ ታሪክ መሆኗንም መገንዘብ ይገባል፤ ጥሩ አሸማጋይ የመፍትሔ ሰው ሆናችሁ ካለፋችሁ እንደሰውየው የራሳችሁን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም እውቀት ሳትሰስቱ በመስጠት አገራችሁን ከጠቀማችሁ ከብዝሃኑ ይልቅ የእናንተ የህሊና እርካታ የአገር ባለውለታነት ላቅ ያለ ነውና በዚሁ መንገድ መሄዱ ያዋጣል እላለሁ። አበቃሁ።
በዕምነት
አዲስ ዘመን የካቲት 18 /2014