እማማ በለጡ፤ እማማ ዙፋን እና አቶ አሸብር ሶስቱም ቡና የሚጣጡ ጎረቤታሞች ናቸው። ሁል ጊዜ ቡና እየተጠራሩ ፖለቲካውን ሲያቦኩት ይውላሉ። በመንደሩ ከእነርሱ ውጪ ያለ አይመስላቸውም። ሰፈሩ ያለእነርሱ ጭራሽ ሊኖር እንደማይችል እርግጠኞች ናቸው። እነርሱ ይሁን ያላሉት አይሆንም። ያልፈቀዱለት አያልፍም።
ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ወሬያቸው ዝብርቅርቅ ይላል። አንዴ ደርግ፣ ኢሰፓ እና ኢህአፓ ብለው ወሬውን ሳይቋጩ፤ መልሰው ስለ ኢዲዩ፣ ኢጭአት ብቻ ስለሁሉም ስላረጁት ፓርቲዎች እና ስለንጉሳዊ አገዛዝ ሳይቀር እያነሱ ይጥላሉ። አንዱ ሌላውን እየወቀሰ፤ አንዳንዴም እስከ መዘላለፍ ይደርሳሉ። አንዴ ፖለቲካውን ከፓርቲ ጋር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከብሔር ጋር መልሰው ከሃይማኖት ጋር ብቻ ወደ ተመቻቸው እየለጠፉ፤ ቡና በጠጡ ቁጥር ከንፈራቸውን እያጣመሙ ‹‹ወቸው ጉድ›› እየተባባሉ አንዱ ሌላውን ያሽሟጥጣል።
እነ እማማ ዙፋን ብቻ አይደሉም፤ የእነርሱ ልጆች በበኩላቸው በየጋዜጣው፣ በየቤተ ዕምነቱ ፣በየድረገጹ ሳይቀር ስለፖለቲካ በተነሳ ቁጥር አለን ባዮች ናቸው። ያው እንደዘመኑ ሰው ማለት ነው፤ ነገሩማ ዛሬ ማን ፖለቲከኛ ያልሆነ አለ? ሁሉም ፖለቲከኛ ነው። ነጋዴው፣ ሹፌሩ፣ መምህሩ፣ የጤና ባለሙያው፣ አርሶ አደሩ ሁሉም ፖለቲካውን ይፈተፍተዋል። ከመሥራት ቀድሞ ማውራት ግንባር ቀደም ያሰኛል የተባለ ይመስላል። ይቅርታ የምጠላው ‹‹ግንባር ቀደም›› የሚለውን ሐረግ ተጠቀምኩ። ያው ነገር ሲደጋገም ይለመዳል። አንዳንዴ ደግሞ ምንም እንኳ መልዕክቱ መልካም ቢሆንም ሲደጋገም ይጠላል። ልክ እንደ ‹‹ግንባር ቀደም›› እንደሚለው ሐረግ ማለት ነው።
የእነማማ በለጡ የተደጋገመ የፖለቲካ ሰጣ ገባ ግን ሌላውን እየዘነጋ ከኔ ወዲያ ላሣር አይነት ዲስኩር ስለበዛበት ከመልካምነቱ ይልቅ ትዕቢቱ ስለሚበዛ ያበሳጫል። ሲበዛ በተለይ ሲደጋገም ከማስጠላትም ያልፋል። እና ባይገባቸው እንጂ እማማ በለጡም ሆኑ እማማ ዙፋን በተለይ አቶ አሸብርም የሚሔዱበት መንገድ አሰልቺ ሆኗል። ሁሉንም እጅ እጅ ያለው ይመስላል።
እርግጥ ነው፤ ሰው የፈለገውን ሃሳብ የመግለፅ መብት አለው። ወሬው ታዲያ እንደእነ እማማ በለጡ አይነቱ የተለየ ጥግ ይዞ እኔ መብለጥ አለብኝ ብሎ የተለያየ ማሳያ እየጠቀሱ ‹‹የበላይ መሆን ይገባኛል›› አይነት ሃሳብ የሚበዛበት አስተያየት መስጠት ያናቁራል፤ መፋቀርም ሊኖር አይችልም። ይሔ አካሔድ ለማንም አይበጅም። እንደአንድ አብረው እየበሉ እየጠጡ ተሰብስቦ በሠፈር መኖር ቀርቶ በሁሉም ደጅ ስቃይ ያንዣብባል። የጎመን ወጥ በፍቅር መብላት ጥል ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል የሚለውን አባባል ለማሰብ ያስገድዳል።
ነገሩ እማማ በለጡ ብቻ አይደሉም ወይዘሮ ዙፋንም የእዚህ ሃሳብ ተጠቂ ናቸው። እንደውም ጀማሪዋ እርሳቸው መሆናቸው እንደማይቀር ብዙ ጊዜ ይወራል። በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ የበላይ ሆኜ መኖር ያለብኝ እኔ ነኝ ይላሉ። ሃይለኛ ነኝ ባይ ናቸው። በዚህ ምክንያት ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም ከሃይለኛ ይሻላል ትዕግስተኛ የሚለውን ብሒል አያውቁትም።
ነገሩ በጣም በሚገርም መልኩ የእማማ ዙፋንም ሆነ የእማማ በለጡ ቤተሰቦች አንዳንድ የዋሆች ካልሆኑ በቀር በአደባባይ ‹‹እኛ የበላይ መሆን አለብን›› አይነት ሃሳብ አያስተላልፉም። እንደውም ብዙዎች በአፋቸውም ቢሆንም፤ ‹‹ጊዜው የእኩልነት ነው፤ ማንም የበላይ ወይም ማንም የበታች መሆን የለበትም።›› በሚለው ሃሳብ ላይ ቢስማሙም፤ በተግባር ግን የበላይ ነን ለማለት ሲሞክሩ ደጋግመን ታዝበናል።
አቶ አሸብር የበላይነቴ ካልተረጋገጠ ሠፈሩ መፍረስ አለበት የሚል አቋም አላቸው። እማማ በለጡን ከእማማ ዙፋን ለየት የሚያደርጋቸው አቶ አሸብርን በሚመለከት አንዳንዴ በየትኛው መንገድ ላይ እንደቆሙ አያስታውቁም። አንዳንዴ ለአቶ አሸብር የሚወግኑ ይመስሉና መልሰው ግማሽ ነፍሳቸው ጎትቷቸው አቶ አሸብርን ይቃወማል። ‹‹አይ በቃ አቶ አሸብርን ተቃውመውታል›› ሲባል በተቃራኒው እንደገና ከአቶ አሸብር ጎን መሆናቸውን እየገለፁ ውስጥ ውስጡን ያጉተመትማሉ። ከእናንተው ወገን ነኝ ለሚላቸው ሳይደብቁ ‹‹እኛ እንደውም ከእማማ በለጡ ጋር ሳንሆን ከአቶ አሸብር ጋር መሆን እንፈልጋለን፤ እንደውም የቡናውን ቡድን እንዲመራው የምንፈልገው አቶ አሸብርን ነው። ምክንያቱም እርሱ ጀግና ነው። እርሱ የቡና ቁርስ ያቀምሰናል።›› ይላሉ። ያው እንዲህ ባዮቹ ዳቦ መላስ የለመዱ የእነወይዘሮ በለጡ ወገኖች ናቸው።
የእማማ በለጡ ዘመድ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች በሚያስገርም መልኩ የወይዘሮ በለጡ የስጋ ልጆች መሆናቸው ቢረጋገጥም ህልማቸው ሆዳቸው ላይ ብቻ መሆኑን ያሳያሉ። አቶ አሸብር የሚበሉትን እንካችሁ ሲላቸው የገዛ ወገናቸውን አሳልፈው ለጅብ ይሰጣሉ። ለዛውም ለማያጠግብ ሆድ መሙያ ሲሉ የገዛ ወገናቸውን በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያርዳሉ። አንዳንዴም ከሰውነት ተራ ወርደው ጅብ ሆነው ሰው ይበላሉ። በተለይ ከራሳቸው ከእማማ በለጡ ዘመድ በላይ የእማማ ዙፋንን ዘር ማንዘር ለማጥፋት ሰማይ ሳይቀር ይቧጥጣሉ።
ከሆድ ፍላጎት የዘለለ የህሊና ፍላጎት፤ ነፃነት እና ፍትህን የመሰለ ትልቅ ጉዳይ ለእነርሱ ምናቸውም አይደለም። እርግጥ ነው። የወይዘሮ በለጡ ልጆች ሁሉም ህልማቸው ሆዳቸው ነው ማለት አይቻልም። ማጠቃለል አይገባም፤ ነገር ግን በገዛ የቅርብ ዘመዳቸው ዳቦ ከመላስ እና ቡና ቁርስ ከመቅመስ አልፈው፤ ከመጉረስ ባሻገር ጠግበው ለመብላት የሚስችላቸው መንገድ ሲጠረግ፤ ለመጠበቅ አለመፈለጋቸው ያሳዝናል። ማሳዘን ብቻ አይደለም ያስተዛዝባል።
እማማ ዙፋን ደግሞ ይለያሉ። ብዙ ጊዜ የሀብታም ወይም የታዋቂ ባለሥልጣን ስም ሲጠራ ዘመዴ ነው ማለት ይቀናቸዋል። የሆነ ባለሥልጣን ዘመድ ንዎት ብለው እነ እማማ በለጡ እና እነ አቶ አሸብር በተደጋጋሚ ሲጎዷቸው ኖረዋል። አንዳንዴ አብረው ቡና ቢጣጡም ለመገዳደል ጫፍ የደረሱ የጥላቻና ጥላሸት የተቀባቡ ጠላታሞች ይመስላሉ። እማማ ዙፋን በዚህ ሳቢያ ብዙ ጊዜ የባለሥልጣን ዘመድ ናቸው ተብለው ከመከበር ይልቅ መሰቃየት ዕጣ ፋንታቸው ሆኖባቸዋል።
በተደጋጋሚ እማማ ዙፋን በአቶ አሸብር እና በእማማ በለጡ ብዙ በደል ይፈፀምባቸዋል። ይሔ ነገር ሲደጋገምባቸው ያለቃቅሳሉ። ነገር ግን ገፍተው ሁለቱንም አይሸሹም፤ ይልቁኑ እማማ በለጡ እና አቶ አሸብር በየአጋጣሚው ስሜታቸውን ሊጎዱ ሊኮረኩሟቸው ቢፈልጉም እርሳቸው የዋዛ አይደለሁም፤ የያዘኝ ታጋሽነት ነው እያሉ ጉራቸውን ይቸረችራሉ። የበላይ ነኝ ማለት ይፈልጋሉ። በዚህ ሳቢያ ተደጋጋሚ ኩርኩም አጋጥሟቸዋል። እርሳቸው ግን ከኩርኩሙ ይልቅ ኩራቱን መርጠዋል።
ወፈርፈር ብለው የሚንጎማለሉት እማማ በለጡ ከነጥፋታቸውም ቢሆን፤ መልካም ሰው የሚባሉ አይነት ናቸው። እንደዕድል የወረሱት ሀብት ብዙ በመሆኑ እንብዛም ችግርን አያውቁም። እንደነአቶ አሸብር እና እንደእማማ ዙፋን ዓይነት ጠኔ አልጎበኛቸውም። ጠግበው የሚያድሩበት ጊዜ ብዙ ነው። ቀድሞ እንኳ ለራሳቸው ለሌላም ይተርፉ ነበር። የሚገርመው ግን ጠገብኩኝ በቃኝን አያውቁም። በሀብት ላይ ሀብት መቆለል ይፈልጋሉ። ቢችሉ የወይዘሮ ዙፋንን አጥር አልፈው መውሰድ ይከጅላቸዋል።
በዚህ የእማማ በለጡ ተግባር እማማ ዙፋን ብዙም ቅር አይሰኙም። ምክንያቱም የእነእማማ በለጡ ጊቢ የእማማ ዙፋን ልጆችም መጫወቻ ነው። ታዲያ የእማማ በለጡ ጊቢ ቢሰፋ ቢጠብ የሚጠቀሙት በጋራ በመሆኑ አያሳስባቸውም። እማማ በለጡም አሁን አሁን አዲስ አመል እያበጁ እንጂ ቀደም ሲል ለምን የእማማ በለጡ ልጆች ደጃፌን ረገጡ ብሎ አምቧጓሮ መፍጠር እጅግ ነውር ስለነበር፤ እርሳቸውም ይህን ሳያደርጉት ብዙ ዘመናትን አስቆጥረው ነበር። በነበር ቀረ፤ አሁን ግን ብዙ ችግር አለ።
እማማ ዙፋን በየአጋጣሚው ከቤታቸው ወጣ ብለው ወደ እማማ በለጡ ቤት ጎራ ይላሉ። እማማ በለጡ ከጥንት ጀምሮ በተለይ እናታቸው እንግዳ የሚቀበሉ በመሆናቸው እርሳቸውም እማማ ዙፋንን ተቀብለው ያስተናግዳሉ። ነገር ግን ደግሞ በተቃራኒው እንግዳ ሆነው የመጡትን እማማ በለጡን ቡና አፍልተው ከማጠጣት ይልቅ በግልምጫ አፈር ከድሜ ያበሏቸዋል። እማማ ዙፋን በዚህ ጊዜ ያለቅሳሉ። የሚያመልኩት አምላክ አለ ብለው ወደ ሚያምኑበት ወደ ሰማይ አንጋጠው ‹‹ተመልከት›› እያሉ እንባቸውን ሲያፈሱ ጉንጫቸውን በቅጡ ሳያርስ መሬት ላይ እየተድቦለቦለ ይወርዳል።
እማማ ዙፋን ጥሩ ነገራቸው ስለሠፈር ሲነሳ ደማቸው ይሞቃል። የሚናገሩትን አያውቁም፤ ክፋቱ ግን እርሳቸው ብቻ ሠፈር ወዳድ እንደሆኑ ማሰባቸው ነው። ሠፈር ከተባለ ስለእርሳቸው ብቻ የተወራ ይመስላቸዋል። ሌሎች ደግሞ ይበሳጫሉ፤ እኛ ያልነው እማማ ዙፋንን እና የእርሷን ዘመድ ብቻ አይደለም። ስለ ሠፈር ከተነሳ ሠፈሩ የእማማ በለጡ እና የአቶ አሸብር እንዲሁም የሌላውም የደንድርም፣ የከድርም፣ የአቶ ወልደጊዮርጊስም፣ የአቶ ሙሉጌታም የሁሉም ሠፈር በመሆኑ፤ ሁሉም ሊታሰቡ ይገባል። ይላሉ።
ነገሩ አሁን ጊዜው ሠፈሩ የሁሉም መሆኑ ሊታወቅ የሚገባበት ነው። በዋናነት የሚያስፈልገው ደግሞ ሥራ ነው። ከርሃብ ለማምለጥ መሥራት የግድ ነው። ‹‹ ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ ወፍጮው እንዳጓራ መስከረም ዘለቀ›› እንደሚባለው ከመስከረም እስከ መስከረም ለመጥገብ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትቶ ሥራ ላይ ማተኮር ይገባል። በመሠረታዊነት የሚያግባባው ሃሳብ ደግሞ ሁሉም እኩል መሆኑ ነው። የማንም ደም የተለየ አይደለም። የትኛውም ሰው ደም ሥሩ ቢቆረጥ ያው ቀይ ነው።
እየተደመረ-እየተቀነሰ
እየተባዛና- እየተካፈለ
ሒሳብ መዝገባችን በተወራረሰ
ያንዱ ደሙ በዝቶ ያንዱ ባላነሰ ቢባልም፤ የማንም ደም በዝቶ የማንም ደም ሊያንስ አይችልም። የሁሉም ደም ያው ደም ነው። ደግሞም ከጥንት ጀምሮ የአንዱ ደም ከአንዱ ጋር ተደምሮ እና ተባዝቶ ሁሉም እርስ በእርሱ ደም ተወራርሷል። ሁሉም የሠፈሩ ሰው ደም ተወራርሶ እየኖረ ባለበት በዚህ ጊዜ እንደእና እማማ ዙፋን እና እንደ እማማ በለጡ አይነቱ የእኔ ደም ወርቅ ነው፤ እኔ የበላይ መሆን አለብኝ የሚል ሃሳብ ይዞ መሟገት አይገባም። በተለይ በዚህ ጊዜ ብዙ ርቀት አያስጉዝም። ያለበለዚያ ሁሉም እንደአቶ አሸብር ሠፈር በማመስ ችግር መፍጠር የየዕለት ተግባር ያደርገዋል። በዚህ ጊዜ ሠፈሩ ይጠፋል። ማንም በዚያ መንደር መኖር አይችልም።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2014