በዓለማችን ላይ አያሌ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች ይፋ ይደረጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በኮምፒውተርና በእጅ በሚያዙ ተንቀሳቃሽ “ስማርት” ስልኮች ላይ ተጭነው ተግባራዊ የሚሆኑ አፕሊኬሽን አሊያም “መተግበሪያ” እያልን የምንጠራቸው የዲጂታሉ ዓለም ዘመናዊ ስሪቶች ይገኙበታል።
እነዚህ መተግበሪያዎች በዋናነት ከእጅ ንክኪ ለሆኑ ግንኙነቶችና የስራ ክንውኖች የሚጠቅሙ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከቀደመው ይልቅ በዚህ ዘመን መተግበሪያዎቹ በስፋትና ለልዩ ልዩ ግልጋሎት ተሰርተው የሚሰራጩ ሲሆን ከሰው ልጆች የእለት ተእለት ክንውን ጋርም ጥብቅ ትስስር ፈጥረዋል።
የዲጂታል ማርኬቲንግ፣ ማሕበራዊ ግንኙነትና አያሌ ፍላጎቶችን በቀላሉ በእጆቻችን ላይ በኮምፒውተርና ስማርት ስልኮች ይዞ የመዞር እድልን ፈጥረውልናል።
በሌላ በኩል የኮምፒውተርና የበይነ መረብ ዘመን ዓለማችንን ከተቆጣጠረ ዘመን አንስቶ አዳዲስ ማሻሻያዎችና የፈጠራ ውጤቶችም በተለያዩ የቴክኖሎጂው አንቀሳቃሾች ይፋ ይደረጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ በቅርቡ የሰማነው “ማይክሮሶፍት” ይፋ ያደረገው “የደሕንነት ዝመና” ፕሮግራም ሲሆን ሌሎች አያሌ መረጃዎችም በየጊዜው ይፋ ይደረጋሉ።
ከዚሁ የበይነ መረብና የሳይበር ምህዳር መረጃዎች ሳንወጣ ይህንን ቴክኖሎጂና የዘመኑን ዲጂታል ዓለም ተገን በማድረግ ሕፃናት ላይ ስለሚደርስ “ጥቃትና” እርሱን ተከትሎ ማሕበረሰቡ ሕፃናትና ታዳጊዎችን ከዘመኑ ረቂቅ የቴክኖሎጂ መጭበርበር እንዴት መጠበቅ እንደሚኖርበት የሚያስጠነቅቁ መረጃዎች ይፋ ይደረጋሉ።
በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ አምድ ላይም በዋነኝነት የእነዚህ መተግበሪያዎች፣ “የማይክሮሶፍት የደሕንነት ዝመና” ትግበራ፣ በታዳጊዎች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን ተገን ያደረገ ማጭበርበር በሚመለከት ትኩረት አድርገን አንዳንድ መረጃዎችን ከእናንተ አንባቢዎቻችን ጋር ልንለዋወጥ ወድደናል።
ለመሆኑ በየጊዜው በስልኮቻችንና በኮምፒውተሮቻችን ላይ የምንጭናቸው መተግበሪያዎችን ትክክለኛ ግልጋሎት እናውቀዋለን? ልጆቻችንንስ ከዚህና መሰል የሳይበር ጥቃት እንከታተል ይሆን? የደሕንነት ዝመናና ተያያዥ ጉዳዮች ላይስ ምን ያህል ግንዛቤው ይኖረን ይሆን? የቴክኖሎጂ ቁሶችን ደሕንነቱንና ተያያዥ ጉዳዮችንስ ምን ያህል ከግምት ውስጥ አስገብተን እየተገለገልንበት ነው? የሚቀጥለው ጽሁፍ ለነዚህና ሌሎች በሰዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋ እናደርጋለን።
የመተግበሪያ ጠቀሜታ እና ደህንነት አጠባበቅ
መተግበሪያ ስንል ስራዎች ቀላል እና ቀልጣፋ እንዲሁም ተደራሽ እንዲሆኑ ዒላማ በማድረግ በግለሰብ እንዲሁም በተቋም ደረጃ (መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ) ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው።
እነዚህም የሞባይል፣ የኮምፒውተር (በተለያየ የኦፐሬቲንግ ሲስተም አሰራር እና መስተጋብር መሰረት ያደረጉ)፣ የዌብ እና በተለያዩ መሳሪያዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ መተግበሪያዎችን መጫዎቻዎችን (ጌሞችን) ጨምሮ የሚያጠቃልል ይሆናል።
የመተግበሪያ ደህንነት ምንድን ነው?
መተግበሪያዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ላልታለመላቸው ዓላማ በሚታወቁም ሆነ በማይታወቁ አካላት (ሰዎች ወይም መተግበሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ) ስራ ላይ ሊውል ይችላል።
ይህም በተጠቃሚዎችም ሆነ በመተግበሪያው ባለቤት በሆነው ግለሰብ ወይም ተቋም የተለያዩ መጠነ ሰፊ የሆኑ ጥቃቶችና ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህም የመተግበሪያው ባለቤትም ሆኑ ተጠቃሚዎች ከእንደዚህ አይነት ጥቃቶች ለመጠበቅ የመተግበሪያ ደህንነት ዘዴዎችን ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ምን ምን አይነት ጥቃቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ?
የሳይበር ወንጀለኞች በላቀ ተነሳሽነት፣ በተደራጀና በረቀቀ መንገድ በመተግበሪያዎች ወይም በአፕሊኬሽኖች ውስጥ ክፍተት በመፈለግ እና ያንን ክፍተት በመጠቀም ጥቃት ይፈጽማሉ።
የሳይበር ወንጀለኞች ትክክለኛ መተግበሪያን (በተለይ አገርን፣ ተቋምን ወይም ግለሰብን ዒላማ ያደረገ) ወደ ኮድ ደረጃ በመመለስ (ወይም የተገላቢጦሽ ምህንድስናን በመጠቀም) የመመንተፊያ ወይም የመበዝበዣ ዘዴዎችን በማስረጽ ወይም በመጨመር እና ተጠቃሚዎች አውርደው ስራ ላይ እንዲያውሏቸው የጥፋት ተልዕኮ ያላቸው መተግበሪያዎችን ድር ላይ በማስቀመጥ ተጠቃሚዎችን እና ድርጅቶችን ለማጥቃት ይሞክራሉ።
በዚህም አጥቂዎቹ የተለያየ አይነት እና ውስብስብ በሆነ መንገድ መጠነ ሰፊ ጥቃት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ከእነዚህም ውስጥ፤ ዳታን፣ አእምሯዊ ንብረትን እና ሚስጥራዊ መረጃዎችን ይሰርቃሉ፤ መረጃን ብሎም መሰረተ ልማትን ያወድማሉ፤ የተቋምን የመረጃ ሀብትም ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ያደርጋሉ፤ የተጠቂውን ተቋም (ወይም ግለሰብ) የደህንነት ፈቃድ እና የተደራሽነት ሁኔታን በመጠቀም ሌላን ተቋም ማጥቃት ይችላሉ፤ ለረዥም ጊዜ መቆየት የሚያስችል የርቀት መቆጣጠሪያ (remote control) ሥርዓቶችንም ከተጠቂው ተቋም ውስጥ በድብቅ በመጫን ሌላ መጠነ ሰፊ እና ውስብስብ የጥቃት አይነቶችን ሊተገብሩ ይችላሉ፤ በርካታ ተንኮል አዘል መተግበሪያዎችን እንደ ቫይረስ፣ ራንሳምዌር፣ ትሮጃን፣ ሩትኪት የመሳሰሉ ማልዌሮችንም በመጫን የተቋሙን የአሰራር ሂደት በመበከል ሊያበላሹ ይችላሉ።
እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል?
የመተግበሪያ ደህንነት ተጠቃሚዎች፣ ደንበኞች፣ የንግድ አጋሮች እና ሰራተኞችን ጨምሮ የውስጥ እና የውጭ ባለድርሻ አካላት የሚጠቀሙባቸውን ማናቸውም ዓይነት አፕሊኬሽኖች (እንደ ሌጋሲ፣ ዴስክቶፕ፣ ድር፣ ሞባይል፣ ማይክሮ አገልግሎቶች ያሉ) ድርጅቶች ከጥቃት እንዲጠብቁ ያግዛል።
ይህም አንድ መተግበሪያ ከመመረቱ ጀምሮ በሚኖረው የንድፈ ሃሳብ ደረጃ እና በመመረት ላይ እያለም አስፈላጊውን የፍተሻ ሂደቶችን በመተግበር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክፍተቶችን መዝጋት፣ የመተግበሪያውን የስራ ላይ ከባቢ ሁኔታ ደህንነት በመፈተሽ እንዲሁም አስፈላጊውን የደህንነት ግብዓቶችን በተገቢው መንገድ ማመቻቸት፣ በስራ ላይ ባለበት ጊዜም ወቅታዊ የሆነ የደህንነት ፍተሻና ግምገማ ማካሄድ፣ በየጊዜው የሚለቀቁትን የመተግበሪያ የደህንነት እድሳት አማራጮችን በተጠንቀቅ መጠበቅ እና ማዘመን፣ ምንጫቸው ያልታወቁ መተግበሪያዎችን አለመጫን፣ ታማኝ ካልሆኑ የመተግበሪያ ማከማቻ ድሮች መተግበሪያዎችን አለማውረድ እና አለመጫን እንዲሁም ታማኝ ያልሆኑ የድር ጣቢያዎችን ወይም ድር መተግበሪያዎችን ከማሰስ መቆጠብ፣ እንደ ተቋም ለተጠቃሚዎች ወይም ለሰራተኞች ተገቢውን የደህንነት አጠባበቅ ዘዴዎችን በማስተማር እና ሥልጠናዎችን በመስጠት የመተግበሪያ ደህንነትን እንደተቋም፣ እንደ ግለሰብ ወይም እንደ ተጠቃሚ ማስጠበቅ እና ከጥቃት ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል።
ማይክሮሶፍትና የደህንነት ዝመና
“ማይክሮሶፍት” ለተወሰኑ የዊንዶው-10 “ቨርዥኖች” ከግንቦት ወር ጀምሮ የደህንነት ዝመና ማቅረብ እንደሚያቆም ገልጿል። ማይክሮሶፍት ኩባንያ ለዊንዶውስ-10 ቨርዥን 20H2 እና ከዚያ በፊት ለነበሩ ምርቶች የሚያቀርበውን የደህንነት ዝመና ከፈረንጆቹ ግንቦት 10/2022 ጀምሮ እንደሚያቋርጥ ገልጿል።
በግንቦት ወር የደህንነት ዝመና ከሚቋረጡባቸው የዊንዶውስ-10 ምርቶች ውስጥም ቨርዥን (version) 1909 እና 20H2 ይገኙበታል። እንደ ማይክሮሶፍት ማሳሰቢያ የዊንዶው ተጠቃሚዎች ወሳኝ የሆኑ ወርሃዊ የደህንነት ዝመናዎችን ለማግኘት፣ የሚከሰቱ የደህንነት ተጋላጭነቶችን ለመድፈን እና የኮምፒውተራቸውን አገልግሎት ፍጥነት ለማሳደግ የዊንዶውስ-10 ምርቶቻቸውን ማሻሻል ይገባቸዋል ብሏል።
ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን እነዚህን መረጃዎች ሰምተን ይሆን? በፈረንጆቹ ጥር 21/ 2022 ለዊንዶውስ-10 ተጠቃሚዎች የምርት “21H2” ማቅረቡን ያስታወሰው ማይክሮሶፍት ከዚህ ባለፈም ለዊንዶውስ-11 ምርቶች “21H2” ከፈረንጆቹ ጃኑዋሪ 27 ጀምሮ በስፋት ተደራሽ ማድረጉን ጠቁሟል።
በዚህም የዊንዶውስ ምርት ተጠቃሚ ሆነው የሚጠቀሙበት ኮምፒውተር ዊንዶውስ-11 ለሆኑና መስፈርቶችን ለሚያሟሉ ደንበኞቹ በሙሉ የዊንዶውስ 11 ኦፕሬቲንግ ሲስተም ማቅረቡን ገልጿል።
እርስዎም የዊንዶውስ-10 ምርትዎን ለማሻሻል ካሰቡ በቅድሚያ ‘start’ የሚለውን አማራጭ በመምረጥ፣ ‘setting’ የሚለውን መጫን በመቀጠል ከቀረቡ ዝርዝሮች ውስጥ ‘update & security’ የሚለው መምረጥ ‘check for update’ የሚለውን በመጫን የቀረበልዎትን የኮምፒውተር ዝመና መተግበር ይችላሉ።
ወይም “type here search” የሚለው ቦታ ላይ “check for updates” ብሎ በመጻፍ የሚመጣውን አማራጭ በመጫን ኮምፒውተርዎን ቨርዥን በማሳደግ በራስዎ፣ በተቋምዎ እና በአገር ላይ ሊድርስ የሚችለውን የሳይበር ጥቃት መከላከል ይችላሉ።
ወላጆችና የቴክኖሎጂ ተጋላጭነት
ከላይ ካነሳናቸው ሁለት ርእሰ ጉዳዮች መካከል ልናነሳው የወደድነው የመጨረሻው ጉዳይ በታዳጊዎችና ሕፃናት ላይ ቴክኖሎጂን መሰረት አድርጎ ሊደርስ ስለሚችል ጥቃትና እርሱን እንዴት መከላከል እንደምንችል ነው።
ለመሆኑ ወላጆች ታዳጊ ልጆቻቸው በበይነ-መረብ አማካኝነት ከሚደርስባቸው አደጋ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይገባቸዋል? በይነመረብ በሰው ልጆች የእለት ተእለት የመማር፣ የግብይት፣ በበይነመረብ ለሚደረጉ ጨዋታዎች፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በቀላሉ ለመገናኘት እና ተግባቦት በመፍጠር ረገድ ያለው ሚና ላቅ ያለ ነው።
ነገር ግን በይነመረብን በጥንቃቄ መጠቀም ካልተቻለ በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳቶችን ሊያደርሱ የሚችሉ የመረጃ መንታፊዎች፣ የማንነት ስርቆት ፈጻሚዎች፣ የሳይበር ትንኮሳ አድራሾች እና ሌሎች አካላት መኖራቸውን ማወቅ ይገባል። ወላጆችም ለራሳቸው ከሚያደርጉት የጥንቃቄ እርምጃ ባሻገር ታዳጊ ልጆቻቸው በበይነመረብ የቀጥታ ግንኙነት በሚያደርጉበት ወቅት በህገወጦች ሊደርሱባቸው የሚችሉ አደጋዎችን ማወቅ እና የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል።
በመሆኑም ወላጆች በታዳጊ ልጆቻቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ከዚህ በታች የቀረቡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ጠቃሚ ይሆናል። የመጀመሪያው በበይነ-መረብ ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመከታተል የልጆችን ኮምፒውተር በቤት ውስጥ የሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፤ የልጃችንን የመረጃ ማፈላለጊያ ታሪክ በየጊዜው መፈተሽ።
የመረጃ ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሶፍትዌር መጠቀም፤ ልጆች የሚጠቀሙባቸውን ሌሎች ስልኮችም ሆነ ኮምፒውተሮችን ማወቅ፤ የታዳጊ ልጆችን የሚጠቀሙበትን መሳሪያ የይለፍ-ቃል (password) ማወቅ፤ በበይነመረብ አማካኝነት የሳይበር ትንኮሳ “cyber bullying” እንደተፈፀመ ወይም የሳይበር ትንኮሳ ጥቃት ከሚፈጽም አካላት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠቁሙ የልጆችዎ ባሕርይ ለውጦች ካሉ ማስተዋል፤ የታዳጊ ልጅዎ ለልጅዎ በበይነ-መርብ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ መፍጥር እንዴት መረጃዎችን ማግኝት እንደሚቻል እና ስለ ጠንካራ የይለፍ-ቃል አጠቃቀም አስፈላጊነት እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል፣ ማስተማር ተገቢ ነው፤ ልጆች የሳይበር ትንኮሳ ሆነ ማንኛውም ሰው ቢያስቸግሯቸው ሁል ጊዜ ለወላጅ ማሳወቅ እንደሚችሉ እና እንዳለባቸው ማሳወቅ፤ ታዳጊዎች በበይነ-መረብ አማካኝነት የሚያገኝዋቸውን እንግዳ ሰዎች እንዳያነጋገሩ ማበረታታት እና መምከር፤ በበይነ-መረብ ብቻ የሚያውቋቸውን ሰዎች ለማግኝት መሞከር ሊያደርስ የሚችለውን ከፍተኛ አደጋ ማስረዳት ያስፈልጋል።
ሊገጥማቸው የሚችሉ የጥቃት ተጋላጭነቶች ታዳጊ ልጆች በአሁኑ ጊዜ ከሳይበርና ከቴክኖሎጂ ነክ መገልገያዎች ጋር ከፍተኛ ግንኙነት እና መስተጋብር እንዳላቸው እርግጥ ነው።
ይህ ቴክኖሎጂ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባሻገር በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ካልተደረገ በታዳጊ ልጆች ላይ በርካታ ጉዳቶችን ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ወላጆች እና አሳዳጊዎች ታዳጊ ልጆች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚፈጥሩትን መስተጋብር ጋር ተያይዞ ሊደርሱባቸው የሚችሉ ጉዳቶች በመገንዘብ ከፍተኛ ክትትል ሊያደርጉ ይገባል።
ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ስጋቶች የትኞቹ ናቸው?
ተገቢ ያልሆኑ ይዘቶች (Inappropriate content) ይህም ሲባል፤ የወሲባዊ ይዘት ያላቸው (የህፃናት\ አዋቂዎች ፖርኖግራፊ፣ ከፊል እርቃን እና \ወይም እርቃን ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን መመልከት፤ የአመፅና የስቃይ ምስሎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች፤ የወንጀል ቡድኖችን የሚደግፍ የሚያበረታታ ይዘት ያላቸው መረጃዎች ፤ ሕገ ወጥ ተግባር የሚያሳዩ ማስታወቂያዎች፤ ጽንፈኛ ድረገፆች፤ የሽብርተኛ ድርጅቶችን፣ ቦታዎችን ወዘተ መረጃዎች፤ ነውጠኛ ባህሪን የሚያበረታቱ የትስስር ገጾች፤ ጸያፍ ንግግሮችንና ጸያፍ ድርጊቶችን የሚጠቀሙ ይዘቶችን ያካትታል፤ የቻት ሩም ጓደኞች ፤ አንዳንድ የበይነ መረብ አዳኞች(predators) ወደ ቻት ሩም ወይም በማሕበራዊ የትስስር ገጾች ተጠቅመው ታዳጊ ሕጻናትን ማግኘት ይችላሉ።
በእነሱ ዕድሜ ላይ የሚገኙ መስለው በመቅረብ ጓደኛ ይሆኗቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እንደዚህ አይነት ሰዎች በአንድ ወቅት በአካል ለማግኘት ይሞክራሉ ብሎም በታዳጊዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ሊፈፅሙ ይችላሉ።
የሳይበር ትንኮሳ (Cyber Bullying) ፤ በማሕበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች አማካኝነት የሚደርስ የሳይበር ትንኮሳ (cyber bullying): ህጻናት በማንነታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ዘለፋ እና ስድብ ነክ ትችት በሥነ-ልቦናቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረስ አልፎ ራስን የመጥላት ብሎም ራስን የማጥፋት ስሜት ውስጥ ሊያስገባቸው ይችላል። በቀጥታ በበይነ መረብ ማጭበርበሪያዎች (Online Scams) ብዙውን ጊዜ በበይነመረብ ለሚሰነዘሩ ማጭበርበሪያዎች ዋነኛ ዒላማ የሚሆኑት አዋቂ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ቢቆጠርም ታዳጊዎች ለዚህ አይነት ማጭበርበሪያዎች በጣም የተጋለጡ ናቸው።
ታዳጊዎችን በሚፈልጉት እና ሊያገኙት በሚፈልጉት ነገር ጋር በማያያዝ በሀሰት ሊጭበረበሩና ለከፋ ጉዳ ሊደረጉ ይችላሉ። በመሆኑም ወላጆች የታዳጊ ልጆቻቸውን የበይነ መረብ ቀጥታ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ለሳይበር ትንኮሳ፣ መጭበርበር እና ግብረገብነት ለጎደላቸው ይዘቶች ተጋላጭ መሆናቸውን በመረዳት ለእነዚህ ጥቃቶች እንዳይጋለጡ ከፍተኛ የሆነ የቤተሰብ ክትትል ያስፈልጋቸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014