ክፉ ዜና ልብን እንደምን በኀዘን እንደሚያናውጥ እኛ ኢትዮጵያውያን በሚገባ እንረዳለን:: ተፈጥሮ፣ ተፈጣሪና ፈጣሪ ጭምር ጨክነውብን የቆዘምንባቸውና ያነባንባቸውን ቀደምትና የዛሬ ታሪኮቻችንን መለስ ብለን ብናስታውስ ብዙ ክስተቶች ወደ አእምሯችን እንደሚመጡ መገመት ይቻላል:: ጀንበራችን የጨፈገገችባቸው፣ ስሜታችን የዳመነባቸው፣ ተስፋችን የተሟጠጠባቸው ብዙ አብነቶች ትዝታዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ የታሪካችንም ገጾች ጭምር ናቸው:: ፍጡር ፈጣሪን እንዳይሞግት የሚያስጠነቅቀውን የአማኞች የእምነት ቀኖና ለጊዜው መዳፈሩን ትተን በአንድ ወቅት አንድ “ስም አይጠቀሴ” ባለሀገር ተናግሮታል በሚባል በአንድ ድንቅ ሞጋች የአፋዊ ሥነ ቃል ግጥም እንንደርደር::
“ስም የለሹን” አርሶ አደር ማስታወሳችን ፈጣሪን እንደማሳዘን ተቆጥሮ ራሱን አንድዬንም ሆነ አንባቢያንን እንደማያስከፋ በመተማመን እነሆ ቃላዊ ግጥሙን በጽሑፍ እናስታውስ፡- “የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣ አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፤ ቀና ብዬ ባየው ደመናው ቀለለኝ፣ እግዜሩን ሠፈራ ወሰዱት መሰለኝ::” ይህ መልዕክተ ጠጣር ሥነ ቃል ለንባብም ሆነ ለጆሮ እንደማይጥም አልጠፋንም::
የመልዕክቱ ኮምጣጣነት ስሜትን ማጨፍገጉም ግልጽ ነው:: ቢሆንም ግን ደፈር ብሎ መጥቀሱ ለዕውቀትና ለጸሎት ስለሚያግዘን መታወሱ ክፋት የለውም::
ላለፉት በርካታ ወራት ሳግና እምባ የስሜታችን መገለጫዎች ነበሩ:: ወራሪውና ግፈኛው አሸባሪ የህወሓት ቡድን በሀገር ላይ ያወረደውን መከራና ስቃይ ስናይና ስናደምጥ፣ ስንጋፈጠውና ስንመክተው መክረማችንም የሚዘነጋ አይደለም::
ውስጣችን በኀዘን ቆፈን ተቆራምዶ መሰንበቱም በግልጽ ይታወቃል:: ምርቃዜውም እስከ ዛሬ አልሻረም::
ዛሬም ይኼው አሸባሪ ቡድንና መጋለቢያ አጋሰሶቹ ከእኩይ ጥፋትና ውድመታቸው አደብ ስላላስገዙ ግልቢያቸውን አላቆሙም:: በግፍ የጨፈጨፏቸው ወገኖቻችንን ክቡር አጽም በሙሉ ሰብስበን በተገቢው መካን በክብር ለማሳረፍ የወራት ጊዜ ያስፈልገናል:: በግፈኞቹ የወደሙትን መሠረተ ልማቶች፣ የሕዝብና የግል ሀብት ፍርስራሾችንም ሙሉ ለሙሉ ጠርገን ለማጽዳትና ከፊሎቹንም ለትውልድ መዘክርነት አደራጅተን መልክ ለማስያዝ ምናልባትም የዓመታት ሥራ ይጠይቀን ይሆናል::
የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ወይንም መልሶ ለማቋቋምም እንዲሁ ያላሰለሰ ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል:: በባዕድ ምድር እየተሰቃዩ ያሉት የስደተኛ ወገኖቻችን የታደጉን ጥሪም በተፈጥሮ ጆሯችን ብቻም ሳይሆን በእዝነ ህሊናችን ውስጥም ጭምር እሪታው ፋታ እየነሳን እንዳለ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል::
እብሪተኞቹ ኃያላን መንግሥታትም በማያገባቸው ጉዳዮቻችን ሁሉ “ጣልቃ ካልገባንና እጅ ካልጠመዘዝን” በሚለው ፉከራቸው፣ ማስፈራሪያቸውና የማዕቀብ ሴራቸው ዕለት ተዕለት የዜማቸውን ቅኝት እየለዋወጡ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ በትጋት እንደሚሰሩ በግብራቸውም በቃላቸውም እያረጋገጡልን ነው:: ከማኅበራዊ ሚዲያው የሴረኞች “የጦርነት ቀጣና” ሲወነጨፉ የሚውሉት አፍራሽና የሀሰት ፕሮፓጋንዳ “ሚሳኤሎችም” የብዙ ዜጎችን እምነትና ተስፋ እየሸረሸሩ ለቁዘማ እየዳረጉ እንዳለ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው::
በየዕለቱ ተስፋን ለማኮማትር የሚርከፈከፈው የፈጠራና የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ውርጭ ብዙዎችን ለውስጥ ቆፈን ዳርጓል:: እነዚህን መሰል ሀገራዊ ፈተናዎች ያነሱን ይመስል የዕለት ዳቦ እንኳን እንደልብ እንዳናገኝ የኑሮ ውድነቱና ጥልፍልፉ የመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ሴራ ዜጎችን እያንገዳገደ ለእምባና ለምሬት መዳረጉን ደጋግመን ስንገልጽ ባጅተናል::
ያ የተከፋ አርሶ አደር ቀደም ሲል እንደ ተቀኘው ቅኔ ዛሬም ድርቅና ርሃብ ከጓዳችን አልርቅ ብሎ ተፈጥሮ ፊቷን አጥቁራብን እየተቀጣን ስለመሆናችን ምስክር የሚያስፈልገው አይደለም::
እነዚህ የድርቅ ተጎጂ ወገኖቻችን በርሃብና በጥማት በሰለለ ድምጽ “የወገን ያልህ!” ጥሪያቸውን እያሰሙ ድጋፋችንን በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው:: የልምላሜው መጠውለግ፣ የዝናቡ ጠል መጥፋት፣ የዱርና የቤት እንስሳቱ ሞትና ስደትም ሌላው ልብ ሰባሪ የወቅቱ ሀገራዊ ክፉ ትራዤዲ ነው::
ይህንን በመሰለውና ማዲያት በሸፈነው የዛሬው መልከ ኢትዮጵያ ላይ ነው፤ “ብርሃን ይሁን!” የሚለው የምሥራች አዋጅ ከታላቁ የህዳሴ ግድባችን ናኝቶ የወጣው::
“አሜን ብርሃን ሆኗል!”
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱ አንድ ታላቅ የጊዜው ክስተት መሆኑ ብቻም ሳይሆን እንደ ሌሎቹ ታሪኮቻችን ሁሉ ውሱን የብርሃን ፀዳል ለመፈንጠቅ የበቃው በብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ውስጥ በአሸናፊነት እየተወጣ ነው:: ልክ ሀገሪቱ በውስጥና በውጭ ጠላቶች ስትፈተን እንደኖረቸው ሁሉ ይህ ፕሮጀክትም እንዲሁ ያለፈው ውጣ ውረድ እንዲህ በቀላሉ ተተርኮ የሚጠናቀቅ አይደልም::
የውስጥና የውጭ ፈተናዎቹ ዛሬም እልባት አግኝተዋል ብሎ አፍ ሞልቶ ለመመስከር ያዳግታል:: ትግሉና ተግዳሮቱ ምናልባትም በአጭር ጊዜ የሚፈታ ሳይሆን የወደረኞቻችን መጻኢ ልጆች ሳይቀሩ ከዘመን ዘመን እያሸጋገሩ እንደሚቀባበሉት ይገመታል::
ዓባይ ወንዛችን ለዘመናት ሲፈስ የኖረው “የማያደምቅ ጌጥ” እንዲሉ በተስፋ ካልሆነ በስተቀር እውን ሆኖ ትሩፋቱን ለማየት ሳንታደል ዘመን ጠብቶ መሽቷል:: ምክንያቱና ሰበቡ ብዙና ውስብስብ ስለነበር ዝርዝሩን መተረኩ ያታክታል::
እንዲሁ ብቻ ከኋለኛው ትውልድ እስከዚህኛው ትውልድ ድረስ በአፍ እየተሸነገለ ሲዘመርለትና “ሲካደም” መኖሩ ለእርሱ ክብር ይሆን ካልሆነ በስተቀር ለቀደምቶቹም ሆነ ለእኛ ለዛሬዎቹ ቋሚ ዜጎች እስከ ትናንት ድረስ አንዳችም ፋይዳ አልነበረውም:: የግድቡን ግንባታ በተመለከተ የታለፈው የውስጥ ስውር ሴራና በጦርና በፕሮፓጋንዳ የታጀበው የስግብግብ ጠላቶቻችን ማስፈራሪያና ዛቻ የመልኩ ዝንጉርጉርነትና ብዛት በዝርዝር ተገልጾ የሚጠናቀቅ አይደለም::
ከጋራ የውሃ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በዓለማችን ላይ እንደኛው ዓባይ የዘመናት አጀንዳ ሆኖ የኖረ ሌላ ጉዳይ ስለመኖሩም እርግጠኛ መሆን አይቻልም:: በተለይም የፈርኦን ልጆችና ደርቡሾቹ ጎረቤቶቻችን የሌት ህልማቸውም ሆነ የቀን ቅዠታቸው ይሄው ወንዛችን ሆኖ ዘመናት እንደዘለቀ እነርሱም ያውቁታል፤ ለእኛም አልተሰወረብንም::
በቀጣይ ዘመናትም ቢሆን ይሄው ቅዠታቸው ተጠናክሮ እንደማይሸጋገር ምንም ዋስትና የለውም:: የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የተካተተበት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደ ዋናዎቹ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት (ግብጽ፣ ሱዳንና ዩጋንዳ) በመጓዝ ለውሃው ተጋሪ ሕዝቦችና መንግሥታት የሰላምና የትብብር መልዕክት ለማስተላለፍ ተሞክሯል::
የኢትዮጵያ መንግሥት በወንዙ አጠቃቀም ላይ ያለው የማይናወጥ መርህ በጋራ ተጠቃሚነት የተመሠረተ ጽኑ አቋሙ እንጂ የትኞቹንም የተፋሰሱን ሀገራት ለመጉዳት ሃሳቡ እንደሌለው የልዑኩ ቡድን አስረግጦ ለማስገንዘብ ሞክሯል:: ከየሀገራቱ ተወክለው እዚህ ድረስ ለመጡት መሰል የሕዝብ ውክልና ላላቸው ቡድኖችም ይሄው ኪዳን በሚገባ ተረጋግጦላቸዋል::
መንግሥትም ቢሆን በራሱ የዲፕሎማሲና ሌሎች በርካታ መድረኮች ላይ የጋራ ተጠቃሚነቱን መርህ እንደማይሸረሸረው ቁጥር ስፍር በሌላቸው ምስክሮች ፊት ማረጋገጫዎችን ከመስጠት ቦዝኖ አያውቅም::
ሀገሪቱ የወከለቻቸው ተደራዳሪዎችና አሸማጋዮችም ይሄንኑ አቋም በተለያዩ መድረኮች ላይ ለማጽናት ሞክረዋል:: ተገዳዳሪዎቻችን ይህ ሁሉ ሙከራ ሲደረግ እውነታው ሳይገባቸው ቀርቶ ሳይሆን ዝግ ህሊናና ግትር ሰብእናቸው ግድ እያላቸው እንደሆነም በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል:: ዛሬም ድረስ የህዳሴው ግድብ ብርሃን ብልጭ ማድረግ ከጀመረበት እለት ጀምሮ ኡኡታቸውንና እሪታቸውን በአዲስ ኃይልና ጉልበት ከማሰማትና ከመንፈራገጥ አላረፉም::
እንዲያውም ከትናንቱ ይልቅ ዛሬ “የአትያዙን ልቀቁን” እዬዬያቸው ይበልጥ ሳይጎላ አልቀረም:: የራሳቸው ብሂል ይገባቸው ከሆነ እንምከራቸውና “ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሉም ጉዞውን ቀጥሏል::” ይህ ጸሐፊ ዓባይንና የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በርከት ያሉ ጽሑፎችን ለማስነበብ ሞክሯል:: “ልብ ካላቸው ልብ እንዲሉም” መሟገቻውን በግልጽነት ለማሳየት ሞክሯል::
ዛሬ 375 ያህል ሜጋ ዋት የብርሃን ጸዳል የፈነጠቀው ታላቁ ግድባችን ነግ ተነገወዲያ የብርሃኑ ወገግታ እየደመቀ ሲሄድና የግድቡ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የወደረኞቻችን የጫጫታ ቱማታ የዚያንው ያህል “ድምቀት” ጨምሮ እንደሚበረታ ይጠበቃል:: ቢሆንም ግን ከሚጮኹት ጋር የራስን የጩኸት መዋጮ እያከሉ መንጫጫቱ ለሰሚውም ሆነ ለጯኺው መደናቆር ሊሆን ስለሚችል በዝግታና በጸጥታ ቀሪ ሥራዎችን ማጠናቀቁ ብልህነት ነው::
ከብርሃኑ ትሩፋት እኩል ለእኛ ለባለጉዳዮቹ በርካታ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በጥልቅ ጨለማ ውስጥ የዘፈቁን በመሰለበት በዚህ ወቅት የምሥራች መልእክቶች ከዳር ዳር እየተላለፉ ማድመጥ ለፈውስም ለመጽናናትም ይበጃል::
የእንኳን ደስ ያለን መልዕክቶቹም ልቦቻችንን ስለሚያሞቁ በቅንነት ብንቀበላቸው ክፋት የለውም:: መቼም በስኬትና በደስታ መካከል የምክር ቃል ከልብ መደመጡ ቢያጠራጥርም እንደ ዜጋ ድርሻን መወጣቱ አግባብ ስለሆነ አንዳንድ ጉዳዮችን ማስታወሱ ክፋት የለውም:: በታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በኩል መከናወን የሚገባቸው የኃላፊነት ድርሻዎች በዝንጋኤ ቸል እንዳይባሉ በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባል::
ከአንድ ዐሠርት እድሜ በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንም እንደ ልቡ በነጻነት እየተጋ ኃላፊነቱን እንዳይወጣ እያስነከሱት ያሉት ግልጽ ችግሮች ሊቀረፉና አባላቱም በትጋት እንዲንቀሳቀሱ ድጋፍና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል::
በተለይም ሕዝቡን አንቀሳቅሶ ለአንድ ዓላማ ለማሰለፍ ትልቅ ሚና የሚጫወተው የኪነ ጥበባት ዘርፉ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ የተደራጀባቸው ማሕበራትና የሚመለከታቸው ክፍሎች ግድ ሊላቸው ይገባል:: ለወረት ቅርብ የሆነው ይህ ሙያ “የሙቀቱና የቅዝቃዜው” መፈራረቅ ከግምት ውስጥ ገብቶ ባለመታከት ሊሰራበት ይገባል:: ኢትዮጵያ ሆይ እንኳንም ደስ ያለሽ! በጉባ ሰማይ ሥር ቀን ከሌት በትጋት እየሠሩ የብርሃን በኩራቱን ላበሰሩልን ለጀግኖቹ የህዳሴ ግድቡ ሠራተኞች አክብሮታችን ይድረሳቸው::
በዚህ ታሪካዊ ወቅት ዕድሜውን ለግሶን “ጉሮ ወሸባዬ!” እያልን ለመዘመር የታደልነው ዜጎችም ምንኛ ፈጣሪ አድሎናል? ውሃውን ለግሶ “ባለአደራ” ላደረገን ለፈጣሪ ከፍ ያለ ምስጋናችን ይድረሰው:: የፈነጠቀው የብርሃን ጸዳል ተስፋችንን አለምልሞ የነገ ዕድሜያችን ብሩህ እንደሚሆን የጋለ ተስፋ ሰንቆልናል:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014