በሰለጠነው ዓለም ማንኛውንም ጉዳይ በተለይም የግጭትና የቅራኔ መነሻ የመሆን ዕድል ያላቸውን የተለያዩ ጉዳዮች በውይይት ሲፈቱ ይታያል::
እኛ ኢትዮጵያውያን ግን እንዳለመታደል ሆነና ከመደማመጥ ይልቅ መደነቋቆር፣ ከውይይት ይልቅ ንትርክ፣ የሀሳብ የበላይነትን ከማንገስ አልፈን የአፈሙዝ የበላይነት በማረጋገጥ ብዙዎች እንደቅጠል ሲረግፉ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ዛሬም ድረስ ችግሮቻችንን የምንወያይበትና የሀሳብ የበላይነትን የምናከብርበት ስክነት አጥተን በብዙ ችግሮቻችን ታጥረን ተቀምጠናል::
ለወትሮው ውበት ጌጣችን፤ መለያ ኩራታችን፤ የሆኑ አንድ ሺ አንድ ልዩነቶቻችን ዛሬ ላይ አጥር ተበጅቶላቸው የችግሮቻችን ምንጮች መሆን እርስ በእርስ እንድንባላና እንድንናከስ አድርገውናል::
እርግጥ ነው ይህ ሁሉ የሆነው በምክንያት ነው:: ታድያ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ትናንት ‹‹ልዩነታችን ኩራታችን›› ብለን ያንቆለጳጰስነው ጉዳይ እሾህ ጋሬጣ በመሆን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል:: ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኢትዮጵያዊነት በተፈተነበት በዚህ ወቅትም ልዩነቶቻችን እንደትናንት ሁሉ ዛሬም ነገም ከነገ ወዲያም ጌጣችን፣ ኩራት መለያችን ሆኖ ሊቀጥል ግድ ነው::
ይህ የግድ ሊሆን የሚችለውም ችግሮቻችንን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት ከመነጋገርና ከመወያየት ባለፈ የሀሳብ የበላይነት የሚነግስባቸው የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር ብቻ ነው:: በሚፈጠሩ መድረኮችም ያልዳበረውን የመነጋገርና የመወያየት ባህል በማዳበር ለግጭት መንስኤ ናቸው የተባሉትን ማንኛውንም ችግሮች በመፍታት ልዩነቶችን ማጥበብ ይቻላል::
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ደካማ የሆነውን የመነጋገርና የመወያየት ባህላችንን ከማሻሻል ባለፈ ቀጣይነት ያላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ለአገሪቱ ብሎም ለህዝቦቿ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል::
በተለይም የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉና ህዝቦች በጋራ ተከባብረውና ተባብረው መኖር እንዳይችሉ ያደረጋቸውን ማንኛውንም ችግር ለመፍታት ሁነኛ አማራጩ ኢትዮጵያዊ በሆነ ጨዋነት ባህልና እሴቶችን በጠበቀ መንገድ መወያየትና የሀሳብ የበላይነትን ማክበር ብቻ ነው::
ላለፉት በርካታ ዓመታት ህዝቦች ቅራኔ ውስጥ ገብተው ብዙ ዋጋ እየከፈሉባቸው ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ምርጫ የሌለው አማራጭ እንደሆነ የሚነገርለት ብሔራዊ የምክክር መድረክ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል ስለመሆኑም በአንድ ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሲናገሩ እንደተደመጠው፤ የመንግሥት ሥርዓትን ጨምሮ የመሬት፣ የሰንደቅ ዓላማ፣ የህገመንግሥት፣ የቋንቋ፣ የማንነትና ሌሎችም ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስለመኖራቸውና በርዕሰ ጉዳዮቹም ላይ የጋራ ውይይት በማድረግ ወደ መፍትሔ ማምጣት እንደሚገባ በማንሳት ስለአገራዊ የጋራ ምክክሩ አስፈላጊነት ተናግረዋል::
ታዲያ ይህ በብዙ የታመነበት አገራዊ የጋራ የምክክር መድረክ እያንዳንዱን የማህበረሰብ ክፍል የሚያካትት በመሆኑ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቋንቋና የብሔር ልዩነቶቻችን ውበት ሆነው እንዲቀጥሉ ዕድል የሚሰጥ ሊሆን የግድ ነው:: ልዩነታችን ውበት ኩራታችን ከመሆን ባለፈ የግጭትና የቅራኔ ምንጭ እንዳይሆን ከብሔራዊ የምክክር መድረኩ በርካታ ሥራዎች ይጠበቃሉ::
በተለይም የግጭት መንስኤ ናቸው የተባሉትን ጉዳዮች ነቅሶ ከማውጣትና ለውይይት ወደ ህዝቡ ከማቅረብ አንጻር ብዙ ይጠበቃል:: ትናንት የተዘራው መጥፎ ዘር ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ ዙሪያችንን ሊውጠን በከበበን በዚህ ወቅት መፍትሔ መሻት የግድ ነውና አሁን ላይ ወደ መፍትሔው መጠጋት ጀምረናል::
ይሁንና አሁናዊ ችግሮቻችንን ከመፍታት ባለፈ መሰል ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ችግሩን ከነሰንኮፉ መንቀል ያስፈልጋል:: ይህም ሲባል በህዝቦች መካከል ቅራኔን የሚፈጥሩና የግጭት መንስኤ የሆኑትን ችግሮች በሙሉ ከስር መሰረታቸው ማጥናትና ተገቢውን ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል:: ይህ ካልሆነ ግን ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ነውና ብሂሉ የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ይቸግራል::
አካታች አገራዊ ምክክሩ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በመነጋገር መፍትሔ የሚያስቀምጥላቸው ሲሆን፤ ከዚህም ባለፈ በቀጣይ መሰል ችግሮች የሚፈጠሩበትን ዕድል ለመድፈን ትልቅ አቅም ይኖረዋል::
ይህን አቅም መፍጠር ሲቻልም ኢትዮጵያ በብዙ እየተፈተነችባቸው ያሉ ችግሮቿን መቅረፍ ይቻላል:: በመሆኑም ብሔራዊ ምክክሩ በቀጣይ በኢትዮጵያ ሀሳብ እንጂ ጠመንጃ የማይነግስበት የፖለቲካ ስርዓትን መገንባት የሚያስችል ይሆናል ተብሎም ይታመናል::
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያውያን በብዙ የተፈተንበትና በስጋት ተሸብበን የተቆራመድንባቸው ዓመታት ስለመሆናቸው አንድ ሺ አንድ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል:: የሰላም ዕጦቱን፣ መፈናቀሉን ረሃቡን፣ የኑሮ ውድነቱን፣ በጠራራ ጸሐይ የሚደረገውን ዝርፊያና ቅሚያዎች በሙሉ መንግሥት አለ ወይ የሚያስብሉ ናቸው::
ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት ታድያ ዋና ማጠንጠኛው ከድህነታችን በተጨማሪ ስርዓት አልበኝነትና አገራዊ ለሆኑ ባህልና እሴቶቻችን ጀርባ መስጠታችን ነው:: በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የተረሱ ውርስ የጋራ አገራዊ ባህሎቻችንን እና እሴቶቻችንን በማጎልበት ኢትዮጵያ ከተዘፈቀችበት ውስብስብ ችግር ማውጣት ይገባል::
ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በራሳችን አቅም መፍታት እንድንችል መደማመጥ የግድ ይለናል:: የሁሉም ነገር መሰረቱ አስተሳሰብ ነውና ለመደማመጥ ደግሞ አስተሳሰባችንን መቃኘት ያስፈልጋል::
‹‹ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ›› እንዲሉ ከረፈደ የተጀመረው ብሔራዊ የምክክር መድረክ በተለይም አሁናዊ የአገሪቷን ችግር ከመፍታት አንጻር ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ ቢታመንበትም በቀጣይ ግን መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋልና በማህበረሰቡና በአገር ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣትም ሕጻናት ላይ መስራት ምርጫ የሌለው አማራጭ መሆኑ የግድ ነው::
ህጻናት ወደዚህች ምድር ሲመጡ ምንም አይነት አስተሳሰብ ሳይዙ የሚመጡ መሆናቸው ይታወቃል:: ነገር ግን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከወላጆቻቸው፣ ከአካባቢያቸውና ከትምህርት ቤት በሚያገኙት ነገር አስተሳሰባቸው ይሞላል::
በመሆኑም ከልጅነት ጀምሮ የያዙትን አመለከካትና አስተሳሰብ አዋቂ ከሆኑ በኋላ ለመቀየር ብዙ ዋጋ ያስከፍላል:: ስለዚህም ልጆች ላይ በመስራት ትውልዱ ውጤታማና ትክክለኛ አስተሳሰብ ይዞ ማደግ እንዲችል ያግዛል:: ለዚህም ወላጆችን ጨምሮ የአካባቢው ማህበረሰብና አስተማሪዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው::
በአገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለተፈጠሩት ችግሮችም መነሻቸው ትውልዱ ላይ በተዘራ መጥፎ ዘር ምክንያት በመሆኑ ልዩነቶች ተንጸባርቀዋል:: እያጋጠሙ የመጡ በርካታ ችግሮችን ለማርገብና ልዩነቶችን ለማጥበብ የታሰበው አገራዊ የምክክር መድረክም ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር ለዴሞክራሲ ስርዓት ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነውና በተለይም ምሁራን ለተግባራዊነቱና ውጤታማነቱ የጎላ ድርሻ አላቸውና ሚናቸውን በአግባቡ ቢወጡ መልካም ነው::
በአገሪቱ ዓመታትን ያስቆጠሩ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማንነት ቅራኔዎች ስለመኖራቸው በተደጋጋሚ የሚሰማ በመሆኑ ይካሄዳል የተባለው አገራዊ ምክክርም ለቅራኔዎቹ መፍትሔ በመስጠት መጪውን ጊዜ ብሩህ በማድረግ የዜጎች ደህንነት ተረጋግጦ፣ ሰላም የሰፈነበት እና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ለመመስረት የጋራ መግባባት ላይ ያደርሰናል ተብሎ ይጠበቃል::
ጎን ለጎንም እንደ አገር ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ መፍታትና ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሻገርን በመለማመድ የውይይትና የመነጋገር ባህልን ለትውልድ ማሻገር ይገባል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 /2014