እንዴት ሰነበታችሁልኝ? እናተዬ የሕይወት ሩጫ ፋታ አይሰጥም አይደል? የሚገርመው ደግሞ ሩጫችን ሲጨምር የምንሮጥለት ነገር እየቀነሰ መሄዱ የሩጫችንን ያህል የሮጥንለት ነገር አለመሙላቱ የስገርማል፡፡ ወይ ጉድ ከሰው ጋር ለየን፤ ከወዳጅ ጋር አራራቀን እኮ፡፡ ግለኝነቱ ጠንክሮ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን ያላላው፤ ማህበራዊ ትስስራችንን ያሳሳውና አብሮነታችንን የሸረሸረው ምን ይሆን? አሁንማ አብረን ቁጭ ብለን የምናወራው መጓጓዣ መኪና ውስጥ ብቻ ሆኗል እኮ ጉድ ነው።
ሰብስቦ ሳንፈልግ በጋራ አስቀምጦ የሚያስጉዘን ታክሲ የወጋችን መጠንሰሻ፣ የገጠመኞቻችን መነሻና የትዝብታችን መዳረሻ ሆኗል ታክሲ፤ ከቀናት በፊት ታክሲ ተሳፍሬ ስጓዝ የሰማሁት ገጠመኝ መነሻነት ትዝብቴን እያነሳሁ ላወጋችሁ ወደድኩ፡፡ “እማዬ እኔ ትልቅ ስሆን ቢራ እጠጣና መኪና ይደርሰኛል! ከዚያ ሁሌም አንቺን በመኪናው ይዤሽ ወደፈለግሽበት እወስድሻለሁ፡፡” ታክሲ ውስጥ አንድ የ4 ዓመት ሕፃን ከእናቱ ጋር በሚያደርገው ውይይት መሀል ከልጁ የሰማሁት ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ ሆነኝ፡፡
ሐፃን ነውና እሱን አልታዘብኩትም፤ ለሕፃናት የማያስቡትን ሚዲያዎች ለትውልድ ግድ የሌላቸውን ምርት አቅራቢያዎችና ገቢያቸውን ብቻ የሚያስቡትን የማስታወቂያ ድርጅቶች ታዘብኳቸው እንጂ፤ ይገርማል! እዚህ ሀገር ላይ ህግ አክባሪ ተቋም፣ መመሪያና መተዳደሪያ አክባሪ ሠራተኛ፣ ደንብ አስከባሪ መስሪያ ቤት ጠፍቶ ይሆን እንዴ? ስለኛ ግድ ሳይኖራቸው እዩን የሚሉን በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ማስታወቂያዎቻችን ግን ወዴት ይሁን የሚያደርሱን? “ማን ይመለከታል? ምነስ ያስከትላል?” ተዘንግቷል። ይሄ ማህበራዊ ሀላፊነት ይሉት ነገር አፈር ደቼ በልቷል። ምን አገባኝ እኔ ብሩን ልሰብስብ እንጂ በምን መልክ ልሰብስብ አያሳስባቸውም፡፡
በብሄራዊ ጣቢያዎቻችን ብሄራዊ ስካር ስከሩ እንባላለን፡፡ ወዳጆቼ አባት ከሕፃን ልጁ ጋር ቁጭ ብሎ የሚመለከታቸው ማስታወቂያዎች እናት ከሴት ልጇ ጋር የምትሰማቸው ስርዓት አልባ ምናምናችንን ገዝተው ይጠቀሙ ባዮች ነፃነት ነሱን፤ሃያ አራት ሰዓት ባልተገደበ ሁኔታ እንዳሻቸው የሚያስተዋውቁት ተገቢነት የሌለው ማስታወቂያ ልጁን እንዲህ እንዲያስብ ህልሙ እንዲዛባ አደረገው፡፡ በትንሽ አዕምሮው የሚያስበው የምኞቱ ጥግ ጠጥቶ መሸለም ሆነ፡፡ የሚመጥነው ተለክቶ አልተሰጠውማ ምን ያድርግ ተገኝ ብሩ የሚያየውን የሚሰማውን ተመኘ፤ የሚመኘውንም ተናገረ፡፡ ደሞ እኮ የተገረምኩት ያሳሰበን የልጁ እንደዚያ ማለት ብቻ አይደለም የናትየዋም ምላሽ እንጂ፡፡ የልጁ እናት በተናገሩት ነገር ተከፋሁ።
በእነዚያ የስካር መንፈስ በሚጣሩ ማስተወቂያዎች የተጸነሰ ህልሙን ለተነፈሰው ልጅ እናቱ የሰጠችው ምለሽ እቅፍ አድርጋ ጉንጩን እየሳመች ጎሽ የኔ አንበሳ አንተ እኮ መኩሪያዬ ነህ! ብትለውስ? እም እሱን ነው የምፈልገው፤ እ… መኩሪያዬ ጉድ! እናት በልጅዋ የስካር ሽልማት መኩራትን ፈለገች፡፡ ልጁ ምን እያሰበ መሆኑ ተዘንግቷት ይሆን? ቆዩኝማ ዕድሜ አያስተምርም? ከፍ ሲባል ከፍ ያለ አተያይ አይለመድም? ዕድሜ ሲጨምር መገሰጫና ማረሚያ አይለይም? እናትነት በራሱ ምንም ሳይጨመር በጎና ክፉ ምኞት አያስለይም? የልጁ እናት ቅር አሰኘችኝ፤ ልጅማ አልኮል ጠጥቶ ከሚያመጣው ድሎት በትምህርት በርትቶ፤ ቀለም ጠጥቶ የሚያወራው ተረት በስንት ጣዕሙ፤ ስካሩ ውስጥ የሞላ የጤና መቃውስ ዘግናኝ አደጋ ሲብስም ሞት እኮ ነው ያለው እናትየዋ አላሰበችውም፡፡
እኔ ምለው የኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ግን ምን ነካቸው? ለትውልድ አይታሰብም? የሚሠራው ሀገር ለመለወጥ፤ ሀገር ለማነጽ አይደል እንዴ? ኧረ ተው አንተዛዘብ ተው፡፡ የሚገርመው ይሄን ያለ ልክ የሚሰበከውን የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ያሳሰበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ አዋጅ አውጥቶ አጽድቋል። ይበል የሚያሰኝ ነው። ያለ ልክ እንዲፈነጩ ተፈቅዶላቸው ከኢትዮጵያዊነት መለያ ከሆኑ እሴትና መልካም ልምዶች ጋር እየቀላቀሉ፣ ከጀግንነት፣ ከአብሮ መኖርና መተሳሰብ ውብ ባህላችን ጋር አዛንቀው ሀበሾች ውብ ናችሁ! ባህላችሁም ደስ ይላል! ስካርም ደንባችሁ ነው፡፡ እያሉን ነው፡፡
ከታሪካችን ጋር እየቀየጡ ለአደጋ ምክንያት ለጤንነት ጠንቅ መሆኑን ረስተው ማዋረዱን ደብቀው አስካሪ መጠጣቸው የደስታና የፌሽታ ምንጭ መሆኑን በተከሸኑና ሲሰሙዋቸው በሚያሰክሩ ቃላት ይሰብኩናል፡፡ ወዳጆቼ የአልኮል መጠጦችን ስያሜ ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ፡፡ በማስታወቂያቸው ስካርን የእኛ ባህል እንዳስመሰሉት ሁሉ ስያሜያቸውንም ከኛ ቀምተዋል፡፡ ሀበሻ ባህሉንና ታሪኩን እንደሚወድ ገብቷቸዋል፡ ፡
በተፈጥሮ ሀብቱ እንደሚማረክ ተረድተዋል፡፡ የጋራችን መጠሪያችንን ቀምተው፤ የተፈጥሮአዊ ሀብቶቻችንን ስም ነጥቀው፣ የታሪካዊ ቦታዎቻችን ስያሜ ወስደው በማን አለብኝነት ለራሳቸው መጠሪያ አደረጉት፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚዲያ በሚታየው የአልኮል መጠጥ ማስታውቂያ አግባብነት ላይ መክሮ ስርዓት ለማስያዝ የሚያስችል አዋጅ አፅድቋል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ መድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ቀርቦ በምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ የጸደቀው አዋጅ አሁን ላይ በአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት ሙሉ በሙሉ መተግበር ባይችልም ቀድሞ ለትውልድ ግድ ሳይሰጣቸው ባሻቸው መልክ ያቀርቡት የነበረውን ማስታወቂያ ሳይወዱ እንዲያቆሙ ተገድደዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ትላንት በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ የአየር ሰዓት ተከራይቶ በመጠጥ ማስታወቂያ ሁለት ሰዓታት ሙሉ ያ …ዬ… ዩ….እያለ አንድ የረባ ቁም ነገር የሌለው ፕሮግራም ሲያቀርብ የነበረ የባህር ማዶ ዘፈን ጋባዥ “በዓለም ላይ የሌለ ህግ ወጣብን…አልኮል አታስተዋውቁ ተባልን፤ የትም ሀገር ተሰምቶም አይታወቅም..” እያለ ወሬና ቁም ነገር የጠፋበት በሬዲዮ ሞገዱ ላይ ድምፁን የሚያስተጋባውን ሰው ስሰማ ይበልጥ አዘንኩበት፡፡ አያችሁ ወዳጆቼ ለሱ መብት ጥያቄ ማለት ያላግባብ ትውልድን በሚያነትብ መልክ የሚቀርበውን ማስታወቂያ እያስተላለፈ ያለገደብ የሚያገኘውን ገቢ ቀነሰ ብሎ መጮህ ነው፡፡
ባይገርማችሁ የዚያን ቀን የሬዲዮ ፕሮግራሙ ሙሉው “እንዴት እንከለከላለን ሌላ ዓለም ላይ የሌለ ህግ ነው” ብሎ ዘራፍ ሲል ነበር ሰዓቱ ያለቀበት፤ እኔ ምለው የትኛው ሀገር ላይ ሰምቶ ይሆን ስርዓት በሌለው መልክ የሚተላለፍ ማስታወቂያ የማያውቁትን መናገር ለዚያውም ለራስ ጥቅም ብሎ፤ አያስተዛዝብም? ወይኔ አሳዘነኝ ይሄኔ እሱ ከራሱ ውጪ የሚመለከተው ዓለም ስለሌለ ይሆናል እኮ ዓለም ላይ የሌለ ህግ ነው ብሎ የተሟገተው፤ ሌላው ዓለም በእንደዚህ ዓይነት ማስታወቂያች ላይ የሚታየውን ጠንከር ያለ ክለከላ ቀድመን ተግብረን ቢሆን ኖሮ ወዳጆቼ ይህ ሰው ፈጽሞ ፕሮግራሙን ለአየር ማብቃት አይችልም ነበር፡፡
ግለሰቡ በራሱ የእነዚህ ማስታወቂያዎች ውጤት ሁሉ ይመስለኛል፤ ለማንኛውም ወዳጆቼ አነሰም በዛ አምላክ ለኛ የፈቀደውን፤ ወደኛም ያቀረበውን መብላታችን በዚያም መኖራችን አይቀሬ ነው። አይደል? በኑሯችን ለወገን አስበን፤ ለትውልድ ተጨንቀን፤ መልካም ነገር ዘርተን ማለፍ መቻል ደግሞ አቻ የሌለው ሰናይ ተግባር ነውና ጉዟችንንና ሥራችንን ሀገር በሚገነባ፤ ትውልድ በሚያንጽ መልኩ ብናደርግ ባይ ነኝ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በተገኝ ብሩ