
በስፖርቱ ዓለም የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ የቻሉ ምርጥ ስፖርተኞች በቴኒስ፣ ጎልፍ፣ ሞተር፣ ቤዝቦል እና በመሳሰሉት ስፖርቶች የሚፎካከሩበት የግራንድ ስላም ውድድር በአትሌቲክስ ስፖርትም ከዛሬ ይጀምራል። ትኩረቱን በመም የአጭርና መካከለኛ ርቀት ላይ ያደረገው ይህ ውድድር መዳረሻውን አሜሪካ ያደረገ ቢሆንም መክፈቻውን ግን በአጭር ርቀት የስመጥር አትሌቶች ባለቤት ከሆነችው ጃማይካ ይነሳል።
አራት ዙሮች ያሉት ውድድሩ ከመነሻው የበርካታ አትሌቶችን ቀልብ መሳብ የቻለ ሲሆን፤ 34 የፓሪስ ኦሊምፒክ ቻምፒዮናዎችን ማሰባሰብ ችሏል። በጥቅሉ 96 አትሌቶች በ48 ውድድሮች ሲካፈሉ በአንድ ውድድር በሚኖረው የሶስት ቀናት ቆይታም በአትሌቶች መካከል ጠንካራ ፉክክር ይታያል ተብሎ ይጠበቃል። በቀድሞው የአጭር ርቀት አትሌት ሚካኤል ጆሃንሰን የተመሰረተው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ፣ ነገ እና ከነገ በስቲያ በጃማይካ ዋና ከተማ ኪንግስተን በሚገኘው ‹‹ኢንዲፔንደንስ ፓርክ›› የሚካሄድም ይሆናል።
በየአራት ዓመቱ የሚካሄደውን ኦሊምፒክ ተምሳሌት በማድረግ በየዓመቱ ለአራት ጊዜ የሚደረገው ይህ ውድድር በጥቂት ርቀቶች የተመረጡ አትሌቶችን ያሳትፋል። ለሶስት ቀናት በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይም አንድ አትሌት እንደሚካፈልበት ርቀት በሁለት ውድድሮች የመካፈል ግዴታ ይኖርበታል። በእያንዳንዱ ግራንድ ስላም (ሁለት ውድድሮች) አሸናፊ የሚሆነው አትሌት የ100ሺ ዶላር ተሸላሚ ሲሆን፤ አራቱን ዙሮች በበላይነት ሲፈጽምም 400ሺ ዶላር የግሉ ማድረግ ይችላል ማለት ነው። የገንዘብ ሽልማቱ እስከ 8ኛ ደረጃን ይዘው ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ሲበረከት የመጨረሻው መጠን 10ሺ ዶላር ነው።
ይኸውም አትሌቶችን በእጅጉ ይስባል የተባለ ሲሆን፤ በመካከላቸው የሚኖረው ፉክክር ደግሞ እየተቀዛቀዘ ለሚገኘው የመም ውድድር ወደነበረበት ሞቅታ ይመልሰዋል የሚለው የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው። ውድድሩን የመሰረተው አሜሪካዊው ውጤታማ የቀድሞ አትሌት ሚካኤል ጆሃንሰን ከ100 እስከ 400 ሜትር ባሉት ርቀቶች ተሳታፊና እአአ በ1992ቱ የባርሴሎና፣ የአትላንታ እና የሲድኒ ኦሊምፒኮች አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል። በተመሳሳይ በአምስት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ላይም 8 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበ ጠንካራ አትሌት ነው።
የመም ውድድሮችን መታደግ እንዲሁም አትሌቶች የሚገባቸውን እንዲያገኙ ማድረግ ለዚህ ውድድር ምስረታ ምክንያት መሆኑን የሚጠቁመው ጆሃንሰን ውድድሮችን በመጨመር ለአትሌቶች የፉክክር ዕድል መስጠትንም አልሟል። የዚህ ውድድር መካሄድ ለስፖርት ቤተሰቡ አስደሳች ቢሆንም ተፎካካሪነቱ እንዳይነካበት ስጋት ካደረበት ዳይመንድ ሊግ በአይነ ቁራኛ መታየቱ ግን አልቀረም። ያም ሆኖ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ‹‹አትሌቶች ተጨማሪ ገቢ ሊያገኙ የሚችሉበትን ውድድር ማግኘታቸው መልካም ነው። ምርጥ አትሌቶች በሚሳተፉበት ርቀት ትኩረትና እንደሚያሳዩት ርቀት ሊከፈላቸው ይገባል›› በማለት ድጋፋቸውን አሳይተውታል።
ከነገ አንስቶ በእረፍት ቀናቱ በሚከናወነው አዲሱ የሩጫ ውድድር ላይም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተሳታፊዎች ይሆናሉ። በወንዶች ረጅም ርቀት 3ሺ እና 5ሺ ሜትር ሁለተኛው ባለፈጣን ሰዓት አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት ተሳታፊነቱን አረጋግጧል። በሞስኮና ቤጂንግ የዓለም ቻምፒዮናዎች የብርና የነሐስ እንዲሁም በሪዮ ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቱ አትሌት ከረጅም ጊዜ ጉዳት በጠንካራ አቋም የተመለሰ አትሌት መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ርቀት በኦሊምፒክና በሌሎች ቻምፒዮናዎች ላይ ውጤታማ ከሆኑት የኬንያ፣ አሜሪካ እና ጓቲማላ አትሌቶች ጋርም አጓጊ የአሸናፊነት ተጋድሎ የሚያደርግ ይሆናል። ከሰሞኑ በአሜሪካ አንድ ውድድር ላይ ዘግይቶ በመካፈል አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ የቻለው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጥላሁን ኃይሌም በዚህ ርቀት በተፎካካሪነት ይካፈላል።
በሴቶች አጭር ርቀት 800 እና 1ሺ500 ሜትር አትሌት ድርቤ ወልተጂ ተሳታፊ ትሆናለች። በቅርቡ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌቷ በርቀቱ ስመጥር ከሆኑት የኬንያ፣ አሜሪካ እና አውስትራሊያ አትሌቶች ጋር ትፎካከራለች። ባለፈው ዓመት በተደረገው የዓለም ቻምፒዮናም ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ወጣቷ አትሌት በፈታኙ ውድድር ራሷን ለቶኪዮው የዓለም ቻምፒዮና እንደምታበቃም ተስፋ ተጥሎባታል።
በረጅም ርቀት ደግሞ የጎዳና እና የሀገር አቋራጭ ውድድሮች ተሳታፊ አትሌቷ ጽጌ ገብረሰላማ ትጠበቃለች። ከኬንያ፣ አሜሪካና ጃፓን አትሌቶች ጋር የምትሳተፈው አትሌቷ የሀገሯ ልጅ ጽጌ ገብረሰላማ በተፎካካሪነት በውድድሩ የምትካፈልም ይሆናል። እአአ በ2022ቱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናው በ3ሺ ሜትር አሸናፊዋ አትሌት ፈተና እንደምትሆንባቸውም ተገምቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም