
ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የብሔራዊ (አደይ አበባ) ስታዲየም ግንባታ ነው:: ይህ ግዙፍና ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታው ሲጠናቀቅም የስፖርት ቤተሰቡን የዘመናት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ኢትዮጵያ በርካታ አሕጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ ያስችላታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል። ግንባታው ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘው ጊዜ መጠናቀቅ አልቻለም።
መንግሥት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የስታዲየሙን ግንባታ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የግንባታው ማጠቃለያ ሥራዎችን ያካተተ ትልቅ የውል ስምምነትም ከትናንት በስቲያ ተከናውኗል:: ይህም መንግሥት በኢትዮጵያ ስፖርት ባለፉት ሰባት ዓመታት ከወሰዳቸው ርምጃዎች ትልቁና ተስፋ የተጣለበት ነው።
ስታዲየሙን ለማጠናቀቅ የተደረሰው ስምምነት የአፍሪካ መዲናና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ለሆነችው አዲስ አበባ ብሎም ለኢትዮጵያ ተጨማሪ እሴት ነው። ኢትዮጵያ በስፖርቱ ዘርፍ በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም በአትሌቲክስ ስፖርት ገናና ስም ያላት ሀገር ናት። በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በተወዳጅነቱ ቁጥር አንድ በሆነው እግር ኳስም ኢትዮጵያ ታሪክ የማይዘነጋው ዐሻራዋን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬ ሽን ( ካፍ) ምሥረታ ማ ኖሯ ይታወቃል::
በታላቁ የውድድር መድረክ ኦሊምፒክ ታሪክ የሚዘክራቸው በርካታ ድሎችን በወርቅ ቀለም የፃፉ እልፍ ክዋክብት አትሌቶችን ያፈራችው ኢትዮጵያ፣ አሕጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ አለመቻሏ ብዙዎች የሚቆጩበት ነው። ለዚህም ዓለም አቀፍም ይሁን አሕጉር አቀፍ መስፈርቶችን የሚያሟላ ስታዲየም ማጣቷ ትልቁ ምክንያት ሆኖ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያ ውድድሮችን በማስተናገድ ልታገኝ የምትችላቸውን ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጥቅሞችን አሳጥቷታል።
ለዚህ ምክንያት ሆነው ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አለመኖር ነው:: በየአካባቢው የታዳጊዎችን ፍላጎት ሊያሟሉም ሆነ የስፖርት ወዳዱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ሊመልሱ የሚችሉ ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደየደረጃው በበቂ ሁኔታ አልተገነቡም። በየክልሉ የተገነቡ ትልልቅ ስታዲየሞችም እንደ አጀማመራቸው ፍጻሜያቸው ሳያምር ባሉበት ሁኔታ ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ነባር ስታዲየሞችም ቢሆኑ ካፍ የሚያስቀምጠውን ዝቅተኛ መስፈርት ማሟላት ባለመቻላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ገለልተኛ ሜዳ እየፈለጉ በሌሎች ሀገራት በስደት ለመጫወት ከተገደዱ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው። በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ የአትሌቲክስ ውድድሮችና የዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጅቶችም በከባድና ምቹ ባልሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ይህንን አንገብጋቢ የስፖርቱን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ባለፉት 7 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስም ግንባታዎች እንዲፋጠኑ፣ ማሻሻያዎችና አዳዲስ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊና ግዙፍ ስታዲየም እንደሚኖራት በተከናወነው የብሔራዊ ስታዲየም የመጨረሻ ምዕራፍ የውል ስምምነት ወቅት ተጠቁሟል:: ከ2008 ዓ.ም በፊት የተጀመረው የብሔራዊ ስታዲየሙ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ቢጠናቀቅም የሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች መቀጠል ባለመቻሉ ሥራው ተቋርጦ ቆይቷል::
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥረት ከዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ መንግሥት በተገኘ 50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ የምዕራፍ ሁለት ሎት አንድ ግንባታ እንዲቀጥል መደረጉ የሚታወስ ነው:: አሁን ደግሞ የምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለትና ሦስት ግንባታዎች (የመጨረሻ ሥራዎች) የፊፋ እና ካፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲቀጥል በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ካሸነፈው የቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) ጋር የውል ስምምነት ተከናውኗል:: የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በስምምነቱ ላይ የስታዲየሙን የመጨረሻ ምዕራፍ ግንባታ ለማጠናቀቅ ለፕሮጀክቱ የ18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ውል መፈረሙን ጠቁመዋል::
በንግግራቸውም ‹‹የስታዲየሙ ግንባታ ከለውጡ በፊት ተጀምሮ ሲንከባለል የቆየ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በራሳቸው ተነሳሽነት ከአቡዳቢ መንግሥት ጋር በተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ስኬት ወደ 57 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ከ7 ወራት በፊት ተፈራርመን አሁን በአስደናቂ አፈፃፀም ላይ ይገኛል::” ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፣ የምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለትና ሦስት ስምምነት የአደይ አበባ ስታዲየምን መቶ ከመቶ ሥራውን በማጠናቀቅ የትኛውንም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ማስተናገድ የሚያስችል ነው:: የካፍና የፊፋ ደረጃን እንዲያሟላም ልምድ ያላቸው አካላት በጥናት በለዩት መሠረት ቀሪ ሥራዎች ይከናወናሉ:: ይህም ለኢትዮጵያ ስፖርት ልማት ስኬት ትልቅ ድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው:: ለዚህም ልዩ ትኩረት፣ ክትትል እና አመራር በመስጠት በቅርብ እየደገፉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በስፖርት ቤተሰቡ ስም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል::
የብሔራዊ ስታዲየም ስትራክቸራል ዲዛይን አዘጋጅና አማካሪ ድርጅት የሆነው የኤችኤም ኢንጂነሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር መሰለ ኃይሌ (ዶ/ር)፤ በውል ስምምነቱ የተካተቱ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል:: በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮንክሪትና አንዳንድ የሀገር ውስጥ ጨዋታዎችን ሊያከናውኑ የሚችሉ ክፍሎችን እንዲሁም የሜዳና የመሮጫ መም ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነው አልቀዋል:: ሁለተኛው ምዕራፍ ሥራም ለዚሁ ተቋራጭ ቢሰጥም በአፈፃፀሙም ችግር ምክንያት እንዲሰረዝ ተደርጓል:: ከዚያ በኋላም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥረት በምዕራፍ ሁለት ሎት አንድ ቀሪ የውስጥ፣ የሜዳ (የደርሶ መልስ ጨዋታ ማከናወን የሚያስችል) እና የመኪና ማቆሚያ (1ሺ500 መኪናዎችን የሚይዝ) ሥራዎች ማጠናቀቂያ ተከናውኗል::
በምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለት ደረጃውን የጠበቀ የተጫዋቾችና የአትሌቶች መልበሻ ክፍሎች፣ የመገናኛ ብዙኃን የሚገለገሉባቸው ክፍሎች እንዲሁም ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁት የቴክኖሎጂ ሥራዎች ይካተታሉ:: በሎት ሦስት ደግሞ 70 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ተብሎ የተገመተው የጣራ ማልበስ ሥራ ይከናወናል:: የስታዲየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅም የዓለም ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ የመዝጊያ ጨዋታዎች ማስተናገድ የሚችል ደረጃ አንድን የሚያሟላ ይሆናል:: 60ሺ ወንበር የሚኖረው የግዙፉ ስታዲየም ግንባታ የመጨረሻ ሥራዎችም ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ተጠናቀው ኢትዮጵያ ለማስተናገድ ላቀደችው የ2029ኙ የአፍሪካ ዋንጫ እንደሚደርስም ነው አማካሪው የገለጹት::
የብሔራዊ ስታዲየምን የመጨረሻ ሥራዎች ለማከናወን ውል የገባው የቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) ማናጀር ሚስተር ሲን በበኩላቸው ተቋማቸው በኢትዮጵያ የ20 ዓመት ሥራ ልምድ ያለውና 127 የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን መፈጸም የቻለ መሆኑን ጠቁመዋል:: አሁንም ባላቸው አቅም ሁሉ ሙሉ ጊዜና ትኩረት በመስጠት ፕሮጀክቱ በተቀመጠው ጊዜና በጥራት አከናውነው ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውንና እምነት ተጥሎባቸው ይህ ፕሮጀክት ስለተሰጣቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው ትልልቅ ውድድሮችን ለማስተናገድና ብሔራዊ ቡድኑንም ከስደት ለመመለስ እንዲያስችል በሚል ርብርብ ከሚደረግባቸው ስታዲየሞች ግንባታ ባለፈ በየአካባቢው ማኅበረሰቡን የሚያሳትፉ ማዘውተሪያዎች ግንባታም ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው:: በዚህም ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት በስፖርት ልማት በርካታ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ሚኒስትሯ አብራርተዋል:: በተለይም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተነሳሽነት ብቻ በ19 ስፍራዎች ላይ 34 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሊገነቡ ችለዋል:: እነዚህ ማዘውተሪያዎችም 3በ1 በመባል የሚጠሩ መካከለኛ ደረጃ ያላቸው ታዳጊዎች በየአካባቢያቸው በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ የሚያደርጉ ናቸው::
በአጠቃላይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት 10ሺ494 አዳዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እንዲሁም የነባር ስታዲየሞች ጥገና እና የደረጃ ማሻሻያዎች ተከናውነዋል:: ይህም 7ቱን ዓመታት ለስፖርት ልማት ጉዞ ስኬታማ ነበሩ ለማለት የሚያስችል ነው:: ምክንያቱም ስፖርት ላይ ለውጥ ለማምጣት ታዳጊዎችና ሕጻናት የሚሳተፉባቸውና በስፖርት ያላቸውን አቅም የሚያዳብሩበት መካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አስፈላጊ እንደመሆናቸው ግንባታቸው ላይ አቅዶ መሥራት ለስፖርት ውጤታማነት የራሱን እገዛ ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ ነው::
ከ2010 ዓ.ም አንስቶም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 2ሺ500 የሚሆኑ አዳዲስ መካከለኛ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተገነቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 1ሺ300 የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብቻ የሚገኙ እንደሆነም ሚኒስትሯ አብራርተዋል:: ከዚህ ጎን ለጎን እንደ ኮሪደር ልማቱ እንዲሁም በገበታ ለሀገር ባሉ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶችም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲካተቱ የተደረጉ ሲሆን፤ በመቶ ኪሎ ሜትር የሚለካ ምቹ የብስክሌት መጋለቢያ መንገዶችንም ማካተት ተችሏል::
ማኅበረሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች እንዲሁም ታዳጊዎች በሚማሩበት ስፍራ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉባቸው ታስበው ከተገነቡ መካከለኛና አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ማዘውተሪያዎች ባለፈ ትልልቅ ስታዲየሞች ላይም በርካታ ሥራዎች የተከናወኑባቸው ዓመታትም ነበሩ:: በተለይ ነባር ስታዲየሞች ደረጃቸውን የማሻሻል የካፍን ስታንዳርድ እንዲያሟሉ ለማድረግ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኛነት እየተሠሩ ይገኛሉ:: ከእነዚህም መካከል የባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየሞችን ማንሳት ይቻላል:: የአዳዲስ ስታዲየሞች ግንባታም እየተካሄደ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ፣ የሃላባ እና አቃቂ ቃሊቲ በቅርቡ ተጀምረው እየተፋጠኑ ያሉ ማዘውተሪያዎች መሆናቸውንም ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው አመላክተዋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም