የአበረታች ቅመሞች ምርመራ ማዕከል በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ ማዕከል ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት (AIU) ባለሙያዎችም በስፍራው ተገኝተው እንቅስቃሴውን መመልከታቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

የስፖርቱ ዓለም ስጋት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ነው። ስፖርተኞች በአቋራጭ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚያከናውኑት ይህ ሕገወጥ ተግባር ተፈጥሯዊ አቅማቸው ተጠቅመው ውጤታማ ለመሆን ለሚጥሩ ስፖርተኞች አደጋ እየሆነ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎች ወቅቶች ከስፖርተኞች በሚወሰደው የደምና ሽንት ናሙና የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነታቸውን በመለየት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት በአትሌቲክስ ስፖርት የሚጎላ እንደመሆኑም በአትሌቲክስ ውጤታማ የሆኑ ሀገራት የተለየ ትኩረት ይደረግባቸዋል፡፡ በርካታ አትሌቶች ያሏትና በስፖርቱ ስመጥር የሆነችው ኢትዮጵያም ትኩረት ተደርጎባታል። ኢትዮጵያ በአትሌቶች ላይ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ምርመራን በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በሌሎች ሀገራት ስታከናውን ቆይታለች፡፡ የራሷን የምርመራ ቤተሙከራ ለመገንባት ዕቅድ መኖሩ በተለያዩ ጊዜያት ተጠቁሟል። በዚህ ወቅትም ወደ ተግባራዊነት በመሸጋገር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ፎረንሲክ የምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከል የስፖርት አበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነትን ለመለየት የሚያስችለውን አቅም በመፍጠር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም የዓለም አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት (AIU) ባለሙያዎች ጎብኝተዋል፡፡ ሰንዳፋ በኬ የሚገኘውን ማዕከል ከዓለም አቀፉ ተቋም የምርመራ ተወካይ ራፋየል ሮክስ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ስለሺ ስህን እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ተገኝተው እንቅስቃሴውን የተመለከቱ ሲሆን፤ በማዕከሉ የፎረንሲክ ምርመራ ምክትል ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የጉብኝቱም ዓላማ በኢትዮጵያ የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ ማዕከል ለማስጀመር የተደረጉ ተግባራትና ያለበት ደረጃ ማየት እንደሆነም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡ ማዕከሉ የሚያስፈልገውን መስፈርት ለማሟላት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም ከኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን እንዲሁም የዓለም አትሌቲክስ ኢንቲግሪቲ ዩኒት (AIU) ጋር በመሆን እንደሚሠራም ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ተቋማቸው ለአትሌቲክስ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግና ያደጉ ሃገራት እየተጠቀሙባቸው ያለውን የምርመራ ማዕከል መሣሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አመራሮችም በቅርቡ በማዕከሉ ተገኝተው እንቅስቃሴውን ተመልክተዋል፡፡ ማዕከሉ በፎረንሲክ ዘርፍ በርካታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የያዘ፣ በተለይም ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሣሪያዎች ያሉት በመሆኑ በኢትዮጵያ ስፖርት ውጤታማነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል። በዓለም አቀፍ መስፈርትና አሠራር አንጻር ቴክኒካዊ ሰነዶችን በማዘጋጀት በማዕከሉ ያሉ የምርመራ መሣሪያዎች የሚለዩበት አሠራር ይፈጠራልም ተብሏል።

ከማዕከሉ ጉብኝት ጎን ለጎን ከብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ውይይት ተካሂዷል። የአፍሪካውያን ዶፒንግ በመባል የሚጠራው የዕድሜ ማጭበርበርም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ራስ ምታት የሆነ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ በተደረገው ውይይት ስለ ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባ፣ አሠራር፣ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል እንዲሁም በቅንጅት መሥራት ስለሚቻልበት ሁኔታ ንግግር ተደርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አትሌት ስለሺ ስህንም ከዚህ ጋር በተያያዘ የዕድሜ ችግርን ለመቅረፍ የብሔራዊ መታወቂያ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በአትሌቲክስ ልማት አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነትም ከቀናት በፊት አከናውነዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በቅርቡ ይፈራረማሉ በሚል የሚጠበቅ ሲሆን፤ በርካታ ስመጥር አትሌቶችን ያፈራው የኦሜድላ አትሌቲክስ ክለብን በስፖርቱ እያበረከተ ያለውን ድርሻ ለማጠናከር መሥራትም በውይይቱ የተካተተ ሃሳብ ነው፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You