
ዘንድሮ 15ኛ ዓመቱን የሚደፍነው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በተያዘው የፈረንጆች ወር አጋማሽ ይጀመራል። በአራት አሕጉራት ውስጥ በሚገኙ 15 ከተሞች እየተዟዟረ ዓመቱን ሙሉ የሚካሄደውና የዓለም አትሌቲክስ ክዋክብትን የሚያፋልመው ይህ ውድድር የሽልማት መጠኑን በመጨመር መመለሱ አትሌቶችን በይበልጥ ያተጋል የሚል ግምት አግኝቷል። ለውጡ ከገንዘብ ባለፈ በአዲስ ድረ ገጽ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን አጋርነት የታጀበም ይሆናል።
መነሻውን በቻይናው ዚመን አድርጎ የሚካሄደው ዳይመንድ ሊግ 32 የመምና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚስተናገዱበት ሲሆን፤ በስመጥር አትሌቶች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግበት መሆኑ ይታወቃል። ባለፉት ሁለት የዳይመንድ ሊግ ዓመታት ብቻ 13 የሚሆኑ የዓለም ክብረወሰኖች በተለያዩ ውድድሮች የተመዘገቡበትም ነበር። አትሌቶችን ለበለጠ ለተፎካካሪነት ያነሳሳል የሚል እምነት የተጣለበት የሽልማት ገንዘብ መጠን በእጥፍ ሲጨምር፤ በአጠቃላይ ለሽልማት ብቻ 9ነጥብ24 ሚሊዮን ብር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቷል። ይኸውም በተናጠል በአንድ ውድድር ብቻ ይገኝ የነበረው ከ10ሺ እስከ 30ሺ ዶላር ወደ 20ሺ እስከ 50 ሺ ዶላር አድጓል ማለት ነው።
ይሁንና ዳይመንድ ሊጉን ሊገዳደር የሚችል አዲስ ውድድር መጀመሩ ለአዘጋጆቹ ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። በዚህ ዓመት የሚጀመረው የግራንድ ስላም ውድድር በተወሰኑ ርቀቶች በዓመት ውስጥ ለአራት ጊዜ መካሄዱ የዳይመንድ ሊጉን አትሌቶች ይሻማል የሚለው የስጋቱ መነሻ ነው ቢባልም የስጋቱ ምንጭ ግን የሽልማት መጠኑ መሆኑ በግልጽ ይታያል። በአሜሪካዊው የቀድሞ አትሌት ሚካኤል ጆሃንሰን የተመሠረተው ይህ ውድድር አሸናፊ ለሚሆነው አትሌት 100ሺ ዶላር እስከ 8ኛ ለሚወጡ አትሌቶችም እንደየደረጃቸው እስከ 10ሺ ዶላር የሚሸልም መሆኑ ምናልባትም ስኬታማ አትሌቶችን ሊያስኮበልል እንደሚችል ይገመታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የዳይመንድ ሊጉ አዘጋጆች የሽልማት ገንዘብ ጭማሪው ከአዲሱ የግራንድ ስላም ውድድር ጋር ለመፎካከር በሚል የተደረገ አለመሆኑን እያንፀባረቁ ነው። ዋናው ጉዳይ በተለይ ከውድድሩ ማካሄጃ ጊዜ መቀራረብ ጋር የተገናኘ ሲሆን፤ ሁለተኛው የግራንድ ስላም ውድድር በቻይና ሻንጋይ ከሚደረገው ዳይመንድ ሊግ ጋር በእኩል ቀን የሚደረግ መሆኑንም በማሳያነት ያነሳሉ። በእርግጥም ቀሪዎቹ የግራንድ ስላም ውድድሮችም ከዳመንድ ሊጉ ጋር በቀናት ልዩነት የሚካሄዱ ናቸው። የዳይመንድ ሊጉ ሥራ አስኪያጅ ፒተር ስታስትኒ ‹‹ውድድሮች መብዛታቸው መልካም ነው፤ እኛም ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች እንኳን ደህና መጣችሁ እንላለን። ነገር ግን የውድድር ማካሄጃ ጊዜን በሚመለከት ግን ጥሩ አመለካከት አይኖረንም›› ሲሉ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል።
የውድድር ጊዜ መደራረቡ ውዝግብ ቢፈጥርም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች መጠናቀቅን ተከትሎ አትሌቶች ከሳምንታት በኋላ ወደሚጀመረው ዳይመንድ ሊግ ፊታቸውን ማዞራቸው አልቀረም። እንደተለመደውም በርካታ ወጣትና ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አዳዲስ ሰዓት የማስመዝገብ እንዲሁም ለቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና ተመራጭ ለመሆን በስፋት ከሚካፈሉባቸው ውድድሮች ቀዳሚው እንደሚሆንም ነው የሚጠበቀው። በተለይ በ800 ሜትር ሴቶች ትንግርት እየሆነችና በርቀቱ በዓለም የበላይነትን በመቆጣጠር ንግሥናውን ትጨብጣለች በሚል ተስፋ የተጣለባት ጽጌ ድጉማ ዘንድሮም ውድድሩን ታደምቃለች በሚል ትጠበቃለች።
በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር ርቀቶችም አትሌቷ ፍሬወይኒ ኃይሉ ዓመቱን በቤት ውስጥ ውድድሮች ድንቅ አቋም የጀመረች ሲሆን፤ በዳይመንድ ሊጉም ይህንኑ በማስጠበቅ የዓለም ሻምፒዮና ጉዞዋን እንደምታመቻችም የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው። የመካከለኛና ረጅም ርቀት ንግሥቷ ጉዳፍ ፀጋይም አስደናቂውን የውድድር ዓመት ጅማሬዋን በዳይመንድ ሊጉም በተመሳሳይ አቋም ታስቀጥላለች ተብሎ ይጠበቃል። የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ጉዳፍ በ1ሺ500 ሜትርም ድንቅ ተሳትፎ ያላት ሲሆን፤ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ የርቀቱን የበላይነት እንዳስቀጠለች ለመቆየት ጥረቷን በዳይመንድ ሊጉም አጠናክራ ትቀጥላለች። በወንዶችም እንዲሁ በመካከለኛ ርቀት ወጣት አትሌቶች ዳይመንዱን ለማንሳት እንዲሁም በቅርቡ ለሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ ለመሆን የሚያስችል ሰዓት ለማሟላት ይሮጣሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም