ኢጣሊያ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ የማድረግ የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች።
ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባን በመቆጣጠር፣ ለአምስት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ቅን ተገዢዋ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም።
ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ።
ታዲያ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ እንድትቆይ ለአገራቸው ሉዓላዊነት የተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች የከፈሉት መስዋትነት ፈጽሞ የሚዘነጋ አይደለም። ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂና አስነዋሪ ግፍ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ለአገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት ከከፈሏቸው በርካታ መስዋዕትነቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም … የፋሺስት ኢጣሊያ አስተዳደር የኢትዮጵያ ወኪል የነበረውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመግደል የተደረገው ሙከራ ከ30ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን ለአሰቃቂ ሞት ዳረጋቸው።
አብርሃ ደቦጭ እና ሞገሥ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች ከሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው በግራዚያኒና ሹማምንቱ ላይ የሞከሩት ጥቃት በሰው ልጅ ታሪክ ከታዩት የጭካኔ ድርጊቶች መካከል አንዱ በኢትዮጵያውያን ላይ እንዲፈፀም ምክንያት ሆኗል። በየካቲቱ ጭፍጨፋ ኢትዮጵያውያን ስለከፈሏቸው እጅግ መራራ መስዋዕትነቶች በታሪክ መዛግብት ላይ ከሰፈሩት ምስክርነቶች መካከል ጥቂቶቹን በአጭሩ እንመልከት፡፡ ሀንጋሪያዊው ዶክተር ሳካ ላስዝሎ የራስ ደስታ ዳምጠው ሃኪም ነበሩ።
ዶክተር ሳካ ከባለቤታቸው ጋር ከ1926 እስከ 1928 ዓ.ም በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት የኖሩ ሲሆን፤ በ1928 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እስከ 1930 ዓ.ም ድረስ በከተማዋ ቆይተዋል። ጥንዶቹ በጦርነቱ ወቅት የታዘቧቸውን ድርጊቶች በፅሑፍና በምስል በማስቀረት መጽሐፍ ሆኖ እንዲታተም አድርገዋል።
ዶክተር ሳካ የነበራቸው በርካታ ቋንቋዎችን የመናገርና የመስማት ችሎታ ከሁሉም ወገኖች ቀዳሚ (የዐይን እማኝ) መረጃዎችን እንዲሰበስቡ ረድቷቸዋል። ዶክተር ሳካ ‹‹Fascist Italy Brutality in Ethiopia, 1935-1937 ፡ An Eyewitness Account›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳብራሩት፤ ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው ግፍና የፈፀመው የጦር ወንጀል እጅግ አሰቃቂና ከአዕምሮ የማይጠፋ ነው። ምንም እንኳን የኢጣሊያ መንግሥት ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያውያንን በጅምላ መጨፍጨፉንና በመርዝ ጋዝ መፍጀቱን ቢያምንም፣ አንዳንድ ኢጣሊያውያን ፖለቲከኞችና ምሁራን እስካሁን ድረስ ይህንን ሀቅ እንደማይቀበሉት ገልፀዋል።
ዶክተር ሳካ ፋሺስት ኢጣሊያ ሰይጣናዊ ግብሩን ይበልጥ ስላሳየበት ስለ የካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ የሚያስታውሱትን ‹‹… ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ። … በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም። ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ሥውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር … የፋሺስት ሹማምንት፣ እኔ በግሌ ‹ሴት› ብዬ ለመጥራት በማልፈልጋቸው፣ ሚስቶቻቸው ታጅበው በኢትዮጵያውያን ደም በጨቀዩት ጎዳናዎች ላይ የቅንጦት መኪናዎቻቸውን ሲያሽከረክሩ ያየሁበትን ምሽት ፈፅሞ አልረሳውም … ›› በማለት ጽፈውታል። በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን ብዙ የመከራ ናዳ
ቢወርድባቸውም የአገራቸውን ነፃነት ለማስከበር ሲሉ ለማመን የሚከብዱ መስዋዕትነቶችን እንደከፈሉም ሀንጋሪያዊው ዶክተር በመፅሐፋቸው ላይ ገልፀውታል።
የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ በሳልና ሚዛናዊ በሆነ ትንታኔ ያቀረቡት የታሪክ ምሁሩ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከ1848-1966›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ … የኢጣሊያ ፋሺዝም ፅልመታዊ ገፅታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ነው።
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት። ‹ጥቁር ሸሚዝ› እየተባሉ የሚጠሩት የፋሺስት ደቀ-መዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት። የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፣ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፣ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፤ የተማሩ ኢትዮጵያውያን በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ።
ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በአገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ …›› ብለዋል። ‹‹Demand Media›› የተሰኘ የድረ- ገጽ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ ‹‹ … የፋሺስት ኢጣሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ወረራ በአገሬው ሕዝብ ላይ ከባድ ጥፋትና ውድመት አስከትሏል፤ በኢትዮጵያ የሆነውም የዚሁ ማሳያ ነበር። ግርግር፣ ጭቆና፣ የዘር መድሎ፣ ጭካኔና ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት የወቅቱ መገለጫዎች ነበሩ። የፋሺስት ጦር በዓለም አቀፍ ሕግጋትና ድንጋጌዎች የተከለከሉ የመርዝ ጋዝና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችና የውጊያ/የጥቃት ስልቶችን በሙሉ ተጠቅሟል፤ በብዚ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን በግፍ ከመጨፍጨፍ ወደ ኋላ አላለለም። ስቅላት፣ በእሳት ማቃጠልና አንገት መቅላት ወራሪው ኃይል ግድያ የሚፈፅምባቸው መንገዶች ነበሩ …›› በማለት አሰቃቂውን ታሪክ መዝግቦታል። ከላይ የተጠቀሱት አሰቃቂ የመስዋዕትነት ታሪኮች የተከፈሉት ለኢትዮጵያ ነፃነትና ሉዓላዊነት ነበር።
ኢትዮጵያ ነፃነቷ ተጠብቆ በክብር እንድትኖር፣ ከጥቃቅን አስተሳሰቦች ተላቅቃ ዜጎቿ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት አገር እንድትሆን ለማድረግ የተከፈሉ መራራ መስዋዕትነቶች ነበሩ።
ኢትዮጵያ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት 50 ዓመታት፣ በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት፣ የኖረችበትና ያለችበት ሁኔታ የየካቲት 12 ሰማዕታትን ጨምሮ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከከፈሉት መራራ መስዋዕትነት ጋር ፈፅሞ የሚጣጣም እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ‹‹ሰማዕታቱ/ አርበኞቹ ያን ሁሉ ዋጋ የከፈሉት በግጭት፣ በድህነትና በኋላ ቀርነት ተተብትባ የተያዘች አገር ለማየት ነው እንዴ?!›› ያስብላል።
‹‹አሁን ያለውን ጨምሮ ከሰማዕታቱ/ አርበኞቹ ትውልድ በመቀጠል ኢትዮጵያን የተረከቧት ትውልዶች የአገሪቱ ነፃነት ምንም ዋጋ ያልተከፈለበት መስሏቸው ይሆን እንዴ?›› ብሎ የሚጠይቅም ሰው አይፈረድበትም። ከላይ የተጠቀሱትን የሰማዕታቱን ሰቆቃ እንዲሁም በከባድ መስዋዕትነት የተመዘገበው ድል ያስገኛቸውን በረከቶች እያሰብን የአሁኑን ትውልድ ነባራዊ ሁኔታ ስንመዝን ‹‹ለመሆኑ ይህ ትውልድ እና የሰማዕታቱ/ አርበኞቹ ትግልና ድል ይተዋወቃሉ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን።
አገሪቱ በድህነት፣ በግጭት፣ በዘረኝነትና በጦርነት ጎዳናዎች ላይ ደጋግማ መመላለሷ የየካቲት 12 መስዋዕትነቶችና የአርበኞች ድል ያስገኙላትን በረከቶች መዘንጋቷንና ማባከኗን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ይህ እጅግ የሚያሳዝን፣ የሚያሳፍርና የሚያስቆጭ መራራ ሃቅ ነው! የየካቲት 12 መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ከወራሪ ኃይል ጠብቆ የማቆየት አኩሪ ታሪክ ከመሆኑ ባሻገር መስዋዕትነቱ ያበረታው የአርበኞች ድል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች ጠንካራና ኃያል የሆነች አገር ለመገንባት የሚያስችል እምቅ አቅም ያለው ድል ነበር።
የየካቲት 12 ሰማዕትነት ወራሪው ኃይል ውሎ አድሮ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት የመገንዘብና ያን ጥፋት የመታገል አካል እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም።
ስለዚህ የየካቲት 12 መስዋዕትነት ዘላቂ ውጤት ድሉ/መስዋዕትነቱ ያስገኘውን መልካም ፍሬ መንዝሮማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠርና መገንባት ነበር።
ይህን ዘላቂ ውጤት ማሳካት የነበረባቸው ደግሞ ድሉን ካስገኘው ትውልድ ቀጥሎ የመጡት ትውልዶች ነበሩ። በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ እነዚህ ትውልዶች ግን ያን ማድረግ አልቻሉም/አልቻልንም።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ ለማመን የሚከብዱ ከባድ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ አገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም ‹‹ተተኪው ትውልድ›› (በተለይ ልኂቃኑ) ግን ያን ታሪክ ማወቅ አልቻለም ወይም አልፈለገም። ይባስ ብሎ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ አገር ለማፍረስ ታጥቆ ሲሠራ ኖረ፤ አሁንም በዚሁ ነውረኛ መንገድ መጓዝን የመረጡ ብዙ ናቸው፤… በዚህም የሰማዕታቱ መስዋትነት ባከነ፤ ተረሳ፤ ውለታቸውም ቅርጥፍ ተደርጎ ተበላ።
አሰቃቂው የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ተረት/ቀልድ እጅግ እየመሰለን ይሆን እንዴ ታላቁን ድል በማይመጥን አሳፋሪ ተግባራት ውስጥ ተዘፍቀን የምንዳክረውና አገሪቱን በሐፍረት አንገቷን ያስደፋናት?! ዘመናዊና ጅምላ ጨራሽ የሆኑ የጦር መሣሪዎችን የታጠቀውና ቁጥሩ የበዛው የፋሺስት ጦር ኋላቀርና በቁጥርም ጥቂት የሆኑ መሣሪያዎችን በያዙት ኢትዮጵያውያን አርበኞች መሸነፉስ የዕድል ጉዳይ መስሎን ይሆን?! በእውነቱ የየካቲት 12 ሰማዕታት ያን አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተቀበሉት አሁን የምናያትን አገር እንድትኖረን ነበር እንዴ?! የየካቲት 12 ሰማዕትነት ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝብ ጽናትና ተምሳሌት የሆነ የታሪክ ክስተት ነው።
የካቲት 12 እንዲህ ዓይነት የታሪክ ትርጉም ያለው ክስተት እንደሆነ ግን አላወቅንም አልያም ማወቅ አልፈለግንም። የየካቲት 12 ሰማዕታት ኢትዮጵያ በዘር፣ በሃይማኖትና በአመለካከት ሳይከፋፈሉ መስዋዕትነትን ተቀብለው ጠላትን ድል ያደረጉ ልጆች እናት መሆኗን ማሰብና አገሪቱ ከሰማዕታቱ በኋላ ባፈራቻቸው ‹‹ልጆቿ›› ምክንያት በአስከፊ የዘር ፖለቲካ ስትታመስና ስትሰቃይ መመልከት እጅግ አሳዛኝና አስገራሚ ተቃርኖ ነው፡፡ የካቲት 12 የተከፈለው የነፃነትና የሉዓላዊነት መስዋዕትነት ከመደበኛውና ብዙ ሰው ከሚናገረው የጽናትና ተምሳሌትነት ባሻገር በሁሉም ዘርፍ ጠንካራና ገናና የሆነች አገር እንድትኖር መሠረት የሚጥል ነበር።
የመስዋዕትነቱን በረከቶች ብናውቃቸውና ብንጠቀምባቸው ኖሮ በብሔር ፖለቲካ የምታመስ፣ ሚሊዮኖች በችጋር የሚሰቃዩባትና የሚፈናቀሉባት …. አገር አትኖረንም ነበር! በየዓመቱ የካቲት 12 ሲደርስ ‹‹ፋሺስት ኢጣሊያ ወገኖቻችንን ጨፍጭፏል … በአባቶቸቻችን ጀግንነት እኮራለሁ … በላይ ዘለቀ አባቴ፤ ሸዋረገድ ገድሌ እናቴ … የጃገማ ኬሎ ልጅ … ›› የሚሉ ገለፃዎችን መስማት የተለመደ ነው፤ አሁንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው።
የመገናኛ ብዙኃን ትኩረትም በእነዚህ ገለፃዎች የታጀቡ ዜናዎችና ዝግጅቶች ይሆናል። ይልቅስ በመገናኛ ብዙኃን መነገርና መፃፍ ያለበት ከየካቲት 12 ሰማዕትነትና ከአርበኞች ድል በኋላ የነበሩት ትውልዶች፣ በተለይ የአሁኑ ትውልድ፣ ‹‹የሰማዕትነቱንና የድሉን በረከቶችን ተጠቅሞ ከዘር ግጭት፣ ከልመናና ከድንቁርና የተፋታች ኃያል አገር መገንባት ያልቻለው ለምንድን ነው? የአያትቅድመአያቶቹን ውለታ የበላበት ምክንያት ምን ይሆን?›› የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው።
‹‹ፋሺስት ኢጣሊያ ወገኖቻችንን ጨፍጭፏል … በአባቶቸቻችን ጀግንነት እኮራለሁ … በላይ ዘለቀ አባቴ፤ ሸዋረገድ ገድሌ እናቴ … የጃገማ ኬሎ ልጅ … ›› እያሉ ማውራትና መፎከር ብቻውን ጥቅምም ትርጉምም የለውም።
ቀደምት ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነትና ባስገኙት ድል መኩራትና ድሉን መዘከር ጥሩ ቢሆንም የመስዋዕትነቱንና የድሉን ትሩፋቶች ሳይጠቀሙ፣ ድሀ (ደካማ የሆነች) አገር ይዞ ስለመስዋዕትነቱ ማውራት እንዲሁም በድሉ ‹‹መኩራት›› አና ድሉን ‹‹መዘከር›› ዋጋ የለውም! ቁም ነገሩ የየካቲት 12 መስዋዕትነት፣ የዓድዋም ሆነ የአርበኞች ድሎች ያስገኘልንን በረከቶች አውቆ እየመነዘሩ መጠቀምና ማኅበረሰባዊ ንቃት ያዳበረች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ ልዩነቶችን አስማምታ አንድነቷን የጠበቀች ኃያል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር (መገንባት) ነው፡፡
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014