84 ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ስንል ሁለቱን ባለገድል ወጣቶች እናገኛለን። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን። ደግሞ ለወጣት ገድል! አላችሁ አይደል! በእርግጥ ኢትዮጵያ ዛሬም ሆነ ትላንት የባለ ብዙ ገድል ወጣቶች አገር ናትና አልተሳሳታችሁም።
ታሪክ የዱላ ቅብብሎሽ እንደመሆኑ የትላንቱ ዘመን ትውልድ ወጣት ለዛሬው እያስተላለፏት ነው እዚህ የደረሰችው። በዚሁ መልኩ የዛሬው ዘመን ትውልድ ወጣት ደግሞ ለነገው ዘመን ትውልድ ወጣት እያስረከቧት ኢትዮጵያ ነገም ትቀጥላለች።
ይሄ አትዮጵያውያን ወጣቶች እስካሉ ድረስ መሆኑ መቼም አያጠራጠርም! ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ለሕይወታቸው የማይሰስቱ የዚያኛው ዘመን ወጣቶች ሲያደርጉት የነበረው ተጋድሎ በእጅጉ ያስደምማል።
ዛሬ 85ኛውን ዓመት የምንዘክርለት የየካቲት 12ቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ጭፍጨፋ ጋር የሚታወሱት የሁለቱ ወጣቶች የአብርሃ ደቦጭ እና የሞገስ አስገዶም ጀግንነት ማሳያ ነው። ወጣት አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ህቡዕ ፀረፋሽስት እንቅስቃሴ ያደርጉ የነበሩ የዛን ዘመን ጀግኖች አርበኞች ናቸው። ወጣቶቹ በኢጣሊያ ወረራው ወቅትና ግራዚያኒ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ድሆችን በመጥራት ምጽዋት ለመስጠት በተሰየመበት መንበር የእጅ ቦንብ እስከ ወረወሩ ድረስ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ።በተለይ አብርሃ ደቦጭ ቀደም ሲል በዘመዶቹ አማካኝነት ጣሊያንኛ ቋንቋ የማወቅ ዕድል አግኝቶ እንደነበር ይነገራል።
አዲስ አበባ ባለው የፋሽስት ፖለቲካ ቢሮ ተቀጥሮ እንዲሠራም አስችሎት እንደነበርም ድርሳናቱ ይተነትናሉ። በዚህ ቦታ መሥራቱና ቋንቋ ማወቁ የፋሺስቶችን የግፍ አገዛዝና የዘር መድልዎ አሠራር በቅርብ ለማወቅ እንዳስቻለውም ይነገርለታል። የፋሽስት ሥራን በቅርቡ ማወቁ ለአገሩ የነበረውን ፍቅር ይበልጥ አጠናክሮለታል።በባዕድ እጅ ቅኝ መገዛትን በእጅጉ እንዲፀየፍም አድርጎታል።
ወጣቱ ጓደኛው ሞገስ አስገዶምም የአደጋው ቀያሽ ከሚባለው አብርሃ ደቦጭ ተመሳሳይ ስሜትና ፍላጎት የነበረው ወጣት እንደነበር ታሪክ መዝግቦለታል። ታድያ በተማሪነት ደረጃ እንዲህ ዓይነት የአገር ፍቅርና መውደድ የተጠናወታቸው ሁለቱ ወጣቶች በገዛ አገራቸው እየተቀማጠለ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ላይ የዘር መድሎና ጭፍጨፋ ሲፈፅም የነበረውን የፋሽስት ጦር መሪ ግራዚያኒ የመበቀል ዝግጅት ሲያደርጉ እንደቆዩም የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
የፋሽስቶችን የግፍ አገዛዝና የዘር መድልዎ አሠራር ከሌላው ስብሐት ከተባለ ሦስተኛ ሰው ጓደኛቸው ጋር በመሆን መላ የሚፈልግ በሚመስል መልኩ ይወያዩበት እንደነበርም ይወራል። ይህ ሁኔታም በፋሽስቶች ላይ እንዴት አደጋ መጣል እንዳለባቸው እንዲያውጠነጥኑ ያደረጋቸው መሆኑንም መረጃዎች ይጠቅሳሉ። አብርሃ ደቦጭ ወደ ፊት ላቀደው ጸረ ፋሽስት ጥቃት እንዲረዳው በባዶ እግሩ ከአዲስ አበባ 10 እና 15 ኪሎ ሜትሮች እየወጣ በጫካ ውስጥ ፈንጂ ለመወርወር የሚያስፈልገውን ልምምድ ያከናውን እንደነበረም መረጃዎቹ ያብራራሉ።
ከዚህ ጎን ለጎን የቤት ዕቃዎቹን ሸጦ ባለቤቱን ደግሞ ወደ ደብረ ሊባኖስ ወስዶ ማስቀመጡን፤ በዚህም አደጋ የሚጥልበትን ቀን ቆርጦ የነበረ መሆኑ እንደሚጠረጠር መረጃው ይጠቅሳል። እንግዲህ እነ አብረሃ ደቦጭና ሞገስ በዚህ ዝግጅት መካከል ሆነው ነው ግራዚያኒ በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ድሆችን በመጥራት ምጽዋት ለመስጠት መወሰኑ ተሰማ፡፡
አደጋው በግራዝያኒ ላይ በተጣለበት የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ሁለቱ ወጣቶች ከተኙበት የተነሱት ወፍ ጭጭ ሳይል ነበር፡፡ ከዛም የፋሽስት ኢጣሊያን ባንዲራን ጦር ላይ ሰፍተውና የእጅ ቦምቦቻቸውን አዘጋጅተው ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት አቀኑ፡፡
በኋላም ቀትር ላይ (ስድስት ሰዓት) ሆኖ ማርሻል ግራዚያኒን ንግግር ማድረግ መጀመሩን ያወሳል። በዚሁ ቅጽበት ጀግኖቹ፣ ቆራጦቹና ቅኝ መገዛትን የተጠየፉት ሁለቱ ድንቅዬ ወጣቶች አከታትለው የእጅ ቦምቦችን ወረወሩበት። ፍንዳታው ያስከተለው ረብሻ ከመረጋጋቱና ፋሽስቶችም የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ፣አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በቤተ መንግሥቱ የጓሮ በር ሹልክ ብለው በመውጣት ለማምለጥ መቻላቸውንም ይሄው የታሪክ ድርሳን ጠቅሶታል።
እነሱም ምንም ሳይነኩ ከግቢው ማምለጣቸው ተዓምር ያሰኛል። ፋሽስት ቦንቡን በመወርወር አደጋ ለማድረስ ሙከራ አድርገው የነበሩት ሁለቱ ወጣቶች መሆናቸውን እንዴት ለማወቅ ቻለ የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል። እንደ አንዳንዶች ግምት ከባንዳ ውጪ አሜን ብሎ የተቀበላቸውና የተገዛላቸው ባይኖርም በወቅቱ አስተዳዳሪዋ ነን ብለው ራሳቸውን በሾሙባት አዲስ አበባ ከተማ በነበረው የፖለቲካ ቢሯቸው አብርሃ ይሠራ የነበረ በመሆኑ ነው የሚሉ አሉ። በሚሠራበት ጊዜ ለነሱ የነበረውን ጥላቻ በአንዳንድ ሁኔታ በግልጽ ያዩ ነበር ባይ ናቸው። በዚሁ ጊዜ አመለካከቱን ደህና አድርገው አጥንተውታል የሚሉም አሉ።
ገሚሶች ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ በውጭ ኃይሎች ድርጎ ትራፊ እየተወረወረላቸው ደሴ ላይ የልጃገረዶችን ስም በዝርዝር ሰጥተው በቅጥረኛው የጥፋት ኃይል ሲያስደፍሩ ሳይቀር እንዳየነው ሁሉ በዚያም ዘመን የነበሩ ባንዳዎች ናቸው እነሱ መሆናቸውን የጠቆሙትም ሆነ ያስገደሏቸው ይላሉ።
በተለይ ስብሐት የተባለውና በየዋህነት ሁሉንም ሚስጥራቸውን ሲያካፍሉት የነበሩት ሦስተኛ ጓደኛቸው ጠቁሞ አስያዛቸውና ለመገደል አበቃቸው የሚሉም ይገኙበታል። ሁሉም አስተያየቶች የሚያስኬዱ ሊሆኑ መቻላቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በወቅቱ ፋሽስት እነ አብርሃን ለያዘ 10ሺህ ሊሬ ሽልማት እሰጣለሁ ማለቱም አይዘነጋም።
ሲያስቡት ይሄን ሽልማት የቋመጠ ሊያሲዛቸው የማይችልበት ምክንያት የለም። ግን ደግሞ በዚህ በኩልም ሶስተኛው ጓደኛቸው ስብሐት ቀዳሚው ተጠርጣሪ መሆኑ አይቀርም። ያም ሆነ ይህ ሁለቱ ጀግኖች ወጣቶች ከሸዋ አርበኞች ጋር ተገናኝተው የነበረ መሆኑንና አርበኞቹ ወጣቶቹ ከኢጣሊያ ጋር ይሠሩ የነበሩ በመሆናቸው ብዙም ዕምነት ስላልጣሉባቸው በራሳቸው መንገድ ከአገር ለመውጣት ሲሞክሩ መያዛቸው እንደምክንያት ይቀርባል። አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ወደ ሱዳን ለመሄድ አርበኞቹን ተሰናብተው መሄዳቸው ሆኖም በጎጃም አድርገው ከአገር በመውጣት ሱዳን ሲደርሱ ባልታወቁ ሰዎች ተይዘው መገደላቸውም ይነገራል።
ያም ሆነ ይህ ፈጣሪ የሁለቱን ወጣቶች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ኢትዮጵያን አሁን ለደረሰችበት ለማድረስ የየራሳቸውን መስዕዋትነት ከፍለው ያለፉ ጀግና ሰማዕት ወጣቶች ናቸው።
የያኔዎቹ የነዚህ ወጣቶች የጀግንነት ገድል ለዛሬዎቹ ወጣቶች ትልቅ ተሞክሮ ትቶ ያለፈ በመሆኑ የአሁኖቹ ወጣቶች የተጠቀሙበትና አገራችሁን ከየትኛውም ጥቃት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፤ ከራስ በላይ ለአገር ዋጋ መክፈልን በተግባር መግለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ፈጣሪም የሁለቱን ወጣቶችም፣ ስለ ነጻነት ዋጋ የከፈሉትንም ነፍስ በአፀደ ገነት አኑርልን! ሰላም!::
ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014