በ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምስረታ አካል የሆነው የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው የካቲት 24 2011 ዓ.ም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተመርቋል። “የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለከተማው ወጣትም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪዎች ትልቅ የስራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩም ሆነ የአካባቢው ነዋሪ በጉጉት የሚጠብቀው ትልቅ ሀብታችን ነው” ያሉት አቶ ደስታ አንዳርጌ የደብረብርሃን ከተማ ከንቲባ ናቸው ።
በደብረብርሃን ከተማ ሰፊ ቁጥር ያለው የተማረ የሰው ኃይል በመኖሩና ብዙ ወጣቶችም በስራ ዕድል ያልተጠቀሙ በመሆናቸው፤ በበጀት ዓመቱ ብቻ ከ9ሺህ በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተመዝግበዋል። በዚህም በፓርኩ ውስጥ ለመስራት እንዲችሉ ከአካባቢው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎችና ለከተማው ወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን፤ አጎራባች ዞኖችንና ከተሞችንም ታሳቢ ያደረገ የስራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ከ10 እስከ 13 ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች የስራ ዕድል ይፈጥራል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚፈጥረውን የስራ ዕድል ተከትሎም የመኖሪያ ቤት እጥረት እንዳይገጥም በከተማዋ ያለውን መሬት በቁጠባና በፕላን በመጠቀም የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ደስታ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፤ ትላልቅ ባለኮከብ ሆቴሎችን መገንባትና ሪል ስቴቶችን ማሳተፍ አስፈላጊና ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ወሳኝ ይሁን እንጂ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ለአብዛኞቹ ፓርኮችም ትልቅ ችግር ሆኖ ይገኛል። አሁን የተመረቀው የደብረብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግን በኤሌክትሪክ ኃይል በኩል የከፋ ችግር አይገጥመውም ያሉት ከንቲባው፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት በደብረ ብርሃን ትልቅ አቅም ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ለብዙ ፋብሪካዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፤ በቂ የውሃ አቅርቦት በከተማዋ መኖሩ የኢንዱስትሪ ፓርኩ በፍጥነት ወደስራ እንዲገባ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በመሆኑም በርካታ የውጭ ባለሀብቶችም በግል ለማልማት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከፍተኛ የሆነ የስራ ዕድል ይዘው የሚመጡ መሆናቸው ይታወቃል። ይህ አሁን የተመረቀው የደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ ፓርክም የከተማዋን ወጣት ጨምሮ ሰፊ ቁጥር ያለውን የአካባቢ ነዋሪ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በታላቅ ተስፋና ጉጉት እየተጠባበቀው ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኩ 75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ በውስጡም ስምንት ሼዶች ተገንብተዋል።
በሌላ በኩል በባህርዳር ከተማ የሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ አፈፃፀሙ 87 ነጥብ ስድስት በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ቀሪውን ስራ በፍጥነት አጠናቅቆ ወደ ስራ ለመግባት የከተማ መስተዳድሩ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወነ ይገኛል። አቶ ሙሉቀን አየው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ፤ ቀሪዎቹ ቁሳቁስ የማሟላትና ጥቃቅን የሚባሉ ስራዎች በመሆናቸው ፓርኩ እነዚህን አጠናቅቆ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ከተማ አስተዳደሩ ከፌዴራል የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም፤ ከአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ጋር ተያይዞ ከትራንስፖርት፤ ከመኖሪያ ቤትና አጠቃላይ ከሰራተኛ ደህንነት ጋር ክፍተት እንዳያጋጥም የግል ባለሀብቱ፣ የፌዴራል ኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽንና ከተማ አስተዳደሮች ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት መስራት ተገቢ ነው ብለዋል። የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባ ከ10 ሺህ በላይ በከተማዋና በአካባቢዋ ለሚገኙ ወጣቶች የስራ ዕድል ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህም በከተማዋ የሚገኙትን ስራ ፈላጊ ወጣቶች የቤት ለቤት ምዝገባ በማድረግ ሰፊ ቁጥር ያለውን የሰው ኃይል መመዝገብ ተችሏል። በቀጣይም ኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚፈልገውን የትምህርት ዝግጅትና የስልጠና አይነት በመለየት የሰው ኃይል ለማቅረብ ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን ከንቲባው አስረድተዋል። የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ44 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና ስምንት ሼዶች ያሉት ቢሆንም፤ የተሰሩት ሼዶች በቂ አለመሆናቸውን በመግለፅ ተጨማሪ ሼዶች ቢገነቡና ቦታዎቹ ባይባክኑ መልካም ነውም ብለዋል። ፕሮጀክቱ ለባለሀብት የሚውል ቀሪ 25 ሄክታር መሬት ያለው በመሆኑ፤ በቀጣይ ባለሀብቶች ወደ ከተማው ገብተው እንዲያለሙ፤ በዋናነት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራም እየተሰራ ነው።
በተጨማሪም፤ ፕሮጀክቱን ለማስመረቅ 35 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ መሰራት ያለበት በመሆኑ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን መንገዱን ለመስራት በዝግጅት ላይ ይገኛል። አቶ ሽፈራው ሰለሞን የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ኮርፖሬሽኑ በዋናነት በግንባታ ላይ አተኩሮ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። በመሆኑም፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በቂና ጥራት ያለው ምርት እያመረተች ወደ ውጭ ለመላክና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራች ትገኛለች። በዚህም አሁን ያላትን የማምረትና ወደ ውጭ የመላክ አቅም ለማስፋት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግና የኢንዱስትሪ ልማት አቅምን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል። በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይም የሰራተኞች ምርታማነት መቀነስና ተረጋግቶ የመስራት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይ ነው። በመሆኑም፤ በመንግስት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት፤ የደመወዝ ማስተካከያ በማድረግ፤ እንዲሁም ባለሀብቶቹ ትራንስፖርትና በቂ ምግብ እንዲያቀርቡ በማድረግ የሰራተኞችን ደህንነት ጠብቆ ፍልሰቱን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው። በአሁን ወቅት ስድስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ስራ ገብተዋል ያሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በጥናትና በጨረታ ላይ ያሉትን ጨምሮ በሰመራ፣ በአይሻና በአሶሳ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች እንደሚገነቡ ተናግረዋል። በአጠቃላይ የ18 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ጎን ለጎንም ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ ይመቻቻል። እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደ ስራ በገቡት ስድስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ42 ሺህ በላይ ሰራተኞች የስራ ዕድል አግኝተዋል። ይህን ጥሩ ጅምር አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ የሚመረቁትን ጨምሮ ሰፊ ቁጥር ያለውን የሰው ኃይል ወደ ስራ ለማስገባት የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ኮርፖሬሽን እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ አነስተኛ ቢሆንም፤ ሊሰለጥን የሚችል ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት ያለባት አገር በመሆኗ፤ ይህን የሰው ሃይል ተጠቅማ ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ከፍተኛ ካፒታል ወደሚጠይቁ ኢንዱስትሪዎች ለመሸጋገር በሂደት ላይ ናት። በተጨማሪም፤ ከውጭ የሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብዓት እንዲሆኑ እየተሰራ ነው። በዚህ ሂደትም የኮምቦልቻ፤ የሀዋሳና የቦሌ ለሚ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። አልባሳትን በሚመለከትም ጥጥና ተያያዥ ግብዓቶችን ከሀገር ውስጥ አርሶ አደር በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል በቀጣይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
የግል ባለሀብቶችን በስፋት ለማስገባት በዋነኝነት የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መኖሩን የተናገሩት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ችግሩን ለመፍታትም ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገኙበት አካባቢ ጊዜያዊ የኃይል ማመንጫ እየቀረበ ሲሆን፤ ችግሩን በዘላቂነት በመፍታት ባለሀብቱን ወደ ዘርፉ መሳብ አስፈላጊ ነው ብለዋል። አቶ አማረ አስገዶም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ 11 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በከፊል ተጠናቅቀው የኦፕሬሽን ስራቸው ተጀምሯል። ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙና በተያዘው ዓመት ወደ ኦፕሬሽን ስራ የሚገቡ ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአጠቃላይ 30 የመንግስትና የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ።
ኮርፖሬሽኑ ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚውለውን በጀት የሚያገኘው ከተለያዩ ርዳታዎች ሲሆን፤ ከአውሮፓ ፈንድ ሼባ ቦንድ 750 ሚሊዮን ዶላር በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለኮርፖሬሽኑ ተመድቧል። አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በዚሁ በጀት እየተገነቡ ይገኛሉ። ሁለተኛው የበጀት ምንጭ ከግምጃ ቤት (ትሬዠሪ) ሽያጭ የተገኘ ሶስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በዚህ በጀት የጅማና የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየለሙበት ይገኛሉ። ሶስተኛው የበጀት ምንጭ ደግሞ፤ ቀደም ሲል ለኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ ተብሎ የተቀመጠ ፈንድ ሲሆን፤ በዚህም ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቷል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ አራት መቶ ሚሊዮን ዶላር የቂሊንጦና የቦሌ ለሚ ሁለት ፓርኮች ለምተዋል። ከቻይና መንግስት ኤግዚን ባንክ በተገኘው 3 መቶ ሚሊዮን ዶላር ብድር ደግሞ፤ የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማልማት ተችሏል። በቅርቡ ከሚመረቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል በ400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነቡት የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለትና የቂሊንጦ፤ በ70 ሚሊዮን ዶላር የሚገነባው የባህርዳር እና በ130 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው የድሬ ዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኙበታል። በቀጣይ የሚጀመሩት ሶስት አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የበጀት ምንጫቸው ጆብ ኮምፓክት የሚል ስያሜ ያለውና የዓለም ባንክ፤ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎች አጋር ደርጅቶች የሚሳተፉበት የበጀት ምንጭ ሲሆን፤ ግንባታው 500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል።
ባለፉት ሶሰት ዓመታት በኮርፖሬሽኑ ብቻ አጠቃላይ 4 መቶ 40 ቢሊዮን ብር ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ወጪ ተደርጓል። ከአንድ ሚሊዮን ሜትር ስኩዬር በላይ የፋብሪካ ሼዶችም ተገንብተዋል። በአጠቃላይ፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጠራል። ወደፊት ለሚፈጠሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት የሚውልና በመሬት ባንክ የነበረ 12 ሺህ ሄክታር መሬት ርክክብ ተደርጎ በኮርፖሬሽኑ እጅ ይገኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በበፍሬህይወት አወቀ