ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በአሸባሪው ሕወሓት አማካይነት የተከፈተውን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተ ሞት፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ በጠቅላላው የሰው ልጆች እንግልትና በአገር ሃብት ውድመት ደርሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ ስትፈተን ቆይታለች፤ በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖቻችንም ዛሬም ድረስ የመንግሥትን እንዲሁም የወገኖቻቸውን እጅ በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡
ከሰብዓዊ ድጋፉ በተጓዳኝ በጦርነቱ የወደሙትን ንብረቶች ወደ ቀድሞ ቁመናቸው ለመመለስ ብሎም የተጐዱትን አካባቢዎች እንዲያገግሙ አድርጎ ሰዎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማስቻል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም የበዛው ሥራ ወደፊት የሚጠብቀን ነው
በነገራችን ላይ ይህ አልጠግብ ባይ አሸባሪ ቡድን፣ ወርሮ ይዟቸው ከነበሩ የአማራና የአፋር አካባቢዎች በጀግናው መከላከያ ኃይል እንዲሁም በአፋር እና በአማራ ሚሊሻዎች፣ በፋኖና ሌሎችም የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት ቢመለስም፤ ዛሬም የደም ሱሱና አላርፍ ባይነቱ እያቅበዘበዘው በአፋር በኩል ዳግም ወረራ ቀስቅሶ ብዙኃንን እየገደለ እያፈናቀለ ንብረት እያወደመ ነው፡፡ ይህም በራሱ እራሱን ችሎ መፈታት ያለበት ጉዳይ ከመሆኑም በላይ አገር ሁሌም መከራ ውስጥ እንድትሆን እያደረገ ነው፡፡
በዚህ ቡድንና ጀሌዎቹ ምክንያት በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረውና አሁንም በሚታየው ትንኮሳ ምክንያት በሚፈጸመው ጥቃት ምክንያት ያለው ችግር ሳያንስ፤ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ድርቅ ደግሞ ሌላው ፈተና ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ የ2013 ዓ.ም የክረምት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡና በ2014 ዓ.ም የበልግ ዝናብ ባለመኖሩ ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩት ወገኖቻችን ለከፋ የድርቅ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ በከብት እርባታ ሕይወታቸውን የሚመሩት እነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዛሬ እንደወትሮው ወተታቸውን ከጓዳቸው እየተጎነጩ ልጆቻቸውን ማሳደግ ማስተማር ለአገር ኢኮኖሚም የበኩላቸውን ማበርከት የሚችሉበት ቁመና ላይ አይደሉም፡፡ ለድርቅ አደጋ ተጋልጠው ብዙ ስቃይን እያሳለፉ ነው።
የአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ የሕይወቱ የኢኮኖሚ ጠቅላላው የእሱነቱ መሠረት የሆኑት እንደ ልጆቹ የሚቆጥራቸው እንደ አይን ብሌኑ የሚንከባከባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳቱ ዛሬ ላይ ውሀና ግጦሽ የሚሆን ሳር አጥተው እየሞቱበት ነው። ቀሪዎቹም ቢሆኑ በሞት አፋፍ ላይ ያሉ በመሆናቸው ችግሩ በዚህ ከቀጠለ እጣ ፋንታቸው ሞት ነው።
በሁለቱ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የራሳቸውንና የእንስሳቱን ሕይወት ለማትረፍ የቻሉትን ያህል ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የተሳካላቸው አይመስልም። በዚህ ምክንያት ደግሞ አንዳንዶቹ አካባቢያቸውን ጥለው ውሃና ግጦሽ አለበት ወደሚሉት አካባቢ መሰደድን የመጨረሻ ምርጫቸው አድርገዋል። አርብቶ አደሩ የቤት እንስሳቶቹን ከራሱ ሕይወት ለይቶ አይመለከታቸም፤ የኑሮውና የኢኮኖሚ መሠረቱ በመሆናቸውም ያጋጠመው የድርቅ አደጋ እጅግ በጣም ከባድና አሳሳቢ ሆኖበታል።
የፌዴራልና የክልሎቹ መንግሥታት ድርቁ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ቢሆንም የጉዳዩን አሳሳቢነት ግን ተቃሏል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመጣባቸው ፈተና እጅግ ከባድ መሆኑን የተረዱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ችግሩን በቅርበት ለማየት ብሎም የመፍትሔው አካል ለመሆን ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ በመገኘት ምልከታ አድርገው ተጎጂዎችን አጽናንተው ወደፊት ሊደረግ ስለሚገባው ነገር ውይይት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል። ከዚህ ባለፈም ክልል ለክልል የሚደረገው ድጋፍም የሚበረታታ ነው፡፡
ይሁንና ችግሩ ሰፊ ከመሆኑም በላይ በመንግሥት ድጋፍ ብቻ ፍጻሜ የሚያገኝና ተጎጂዎችም ከችግራቸው የሚወጡ አይመስልም፡፡ በመሆኑም ድርቁ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቋቋም እንዲቻል ሁሉም አካል ድጋፉን ማድረግ እንዳለበት ይሰማኛል፡፡
ዛሬ ላይ እንደቀድሞው ጊዜ ምዕራባውያኑ ችግራችንን ተሰምቷቸው ስንዴያቸውን ይለግሱናል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ ሞኝነት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጡት ልጃቸው የሆነው አሸባሪው ሕወሓት በአገር ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሃይ ከማለት ይልቅ የሕዝብና የአገር ጉዳት ምንም ሳይመስላቸው ለራሳቸው ጥቅም ብለው ገዳዩ ቡድን ወደስልጣን እንዲመለስላቸው የሚችሉትን ሁሉ እየጣሩ ጥረታቸውም መና እያጣ መጥቷል፡፡
ይህም ከዝምታቸው ጋር ተዳምሮ የእኛ ቁስል እንዳይሰማቸው ይልቁንም ጥርሳቸውን ነክሰውብን የምንጠፋበትን መንገድ እያፈላለጉ ያሉ አስመስሎባቸዋል፡፡ ታዲያ አሁን ላይ እነሱ ብንራብ ብንጠማ ደንታቸው ካልሆነ እኛ ለእኛ እናንሳለን እንዴ? እንደ እኔ እንኳን የሶማሌንና የኦሮሚያን ጥቂት አካባቢዎችችግር ቀርቶ የብዙ ነገሮችን ሁኔታ መቀየር የሚችል ኃይል ያለን ዜጎች ነን፡፡
“ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለሀምሳ ሰው ጌጡ ነው” እንደሚባለው፤ ዛሬ ወገናችን ላጋጠመው የድርቅ አደጋ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንችለውን ብናደርግ ነገ ራሳቸውን ችለው ይቆማሉ ። ራሳቸውን ከመቻላቸውም በላይ ዛሬ በሕይወት እንዲቆዩ ላደረግናቸው ለእኛ፤ እንዲሁም ለአገራቸው የሚተርፍ የእንስሳት ሀብት አርብተው ያሳዩናል። ከዚህ አንጻር እነዚህ ሕዝቦች በላያቸው ላይ ከተጫነው የሞት ስጋት ልናድናቸው ልንታደጋቸው ይገባል። ይህ ደግሞ የወገናዊነት የውዴታ ግዴታችን መሆኑንም መገንዘብ ያሻል ።
አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ዛሬ ካጋጠመው የድርቅ አደጋ እንዲቋቋም መደገፍ ነገ በሕይወት እንዲቀጥል ማድረግ ብቻ ሳይሆን ነገ የማኅበረሰቡ ሕይወት ሳይመሰቃቀል በአገር ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጫና ሳያጋጥም መደበኛ የሆነው ሕይወት እንዲቀጥል ማድረግ ነውና ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ወደ ተግባር መግባት አለበት።
“ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም” ነውና የአገራችን ብሒል እኔ ምን አለኝና ምን እሰጣለሁ? ማለት ሳይሆን ለወገን ትንሹም ብዙ መሆኑን በመገንዘብ ከቁሳዊ ድጋፍ ባሻገር ሞራላዊ ድጋፍ የጉልበት የእውቀት አስተዋጽኦም ትንሽ ስላልሆነ ሁሉም በሚችለው አቅሙ በፈቀደው መጠን መንቀሳቀሱ የዜግነት አበርክቶው ነው፡፡
አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ በሚያረባቸው እንስሳቶች የምንጠቀመው ሁላችንም ነን፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የከተማና የገጠሩ ነዋሪ በጠቅላላው አገር ናት ። በመሆኑም ዛሬ የሞት አደጋ ያንዣበበባቸውንና በድርቁ እየተጎዱ ያሉትን እንስሳት ለመታደግ መኖ፣ ውሀ እንዲሁም ለነዋሪው ምግብ ነክ እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ ይመስለኛል።
በአገር ላይ ጦርነት ፣ ድርቅና ረሀብ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት መፈናቀል ሲያጋጥም ኢትዮጵያውያን የመተጋገዝና የመረዳዳት ባህላችን አኩሪ ነው። ይህንን ደግሞ አሁን በቅርቡ እንኳን ሕወሓት ባደረሰብን ችግር የተጎዱ ወገኖቻችንን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በነቂስ ድጋፋችንን በማሳየት ገልጸነዋል፤ አረጋግጠናልም፡፡ በዚህ ሥራችን ደግሞ ወዳጅ ጠላታችንን አስደምምናል፡፡ ታዲያ ይህንን የመተባበር የመተጋገዝ የአለሁ ባይነት ወኔያችንን የሚፈልጉ ወገኖች ዛሬም ተከስተዋልና ሁላችንም በጦርነቱ የተፈናቀሉና የተጎዱትን ከመደገፍ ጎን ለጎን ፊታችንን በድርቅ ወደተጎዱ ወገኖችም እናዙር፡፡ አበቃ!
በእምነት
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014