አዲስ አበባ ፦ ለሀገራቸው እና ሕዝባቸው በትልቅ ብቃት፣ በታማኝነት፣ በሐቀኝነት፣ በላቀ ስብዕና በማገልገል የሀገር ባለውለታ የሆኑት የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ትናንት ተፈፅሟል::
የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ አስከሬን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ሽኝት ተደርጎለታል።
አቶ ቡልቻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ናሲሴ ሰርዳ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ።
አባታቸውን በልጅነት በሞት ቢያጡም አጎታቸው ጎቡ ሰንበቶ አሳድገዋቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገውላቸዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊምቢ አድቬንቲስት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና በሕግ ዲግሪዎች ተመርቀዋል።
በወቅቱም በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተመረቁ 10 ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ወደ አሜሪካ በመሄድ በሲራኪዩዝ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው፤ በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን አገልግለዋል። በዘመናዊ የግል ንግድ ባንኮች ምሥረታ ታሪክ ተጠቃሽ የሆነው የአዋሽ ባንክ እና የአዋሽ ኢንሹራንስ መሥራች ናቸው።
“ኢትዮጵያ ከፍ የምትለው ተባብረን ስንሠራ ነው”፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ የፖለቲካ አካሄድ ከውድመት ውጭ ለውጥ እንደማያመጣ ከመናገርም አልፈው በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ተወዳድረው ፓርላማ በመግባት ለሕዝባቸው ድምፅ ለመሆን የበቁ ናቸው።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄን በመመሥረት እና ሊቀመንበር በመሆን በፖለቲካው ላይ የራሳቸውን ዐሻራ አሳርፈዋል። ፓርቲያቸውን ወክለው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።
አቶ ቡልቻ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ታኅሣሥ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አዲስ ዘመን በእኝህ የሀገር ባለውለታ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን በመግለጽ፤ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል ።
በጋዜጣ ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም