‹‹የተፋሰስ ሥራዎቻችን ለግብርና ልማት ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ናቸው›› – ‹አቶ ጌቱ ገመቹ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ

አዳማ፡- የተፋሰስ ልማት ሥራዎቻችን ለሁሉም የግብርና ልማት ክንውኖቻችን ትልቁን ስፍራ የሚይዙ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ አስታወቁ። ዘንድሮ ለአንድ ወር በሚቆይ ንቅናቄ ስድስት ሺ ተፋሰሶች የተለዩ መሆናቸውንም ገለጹ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በአዳማ በአባ ገዳ አዳራሽ ለክልሉ የግብርና ባለሙያዎች በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ የሚሰጠውን ሥልጠና በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ ለአንድ ወር በሚቆይ ንቅናቄ ስድስት ሺ ተፋሰሶች ለማልማት ተለይተዋል።

በእነዚህ ተፋሰሶች ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆን ኪሎ ሜትር ላይ የተለያዩ የእርከን ሥራዎች ለማከናወን ታቅዷል። ይህ በሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ ይሠራል ተብሎም ይጠበቃል። በአጠቃላይ በክልሉ የሚሠሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ለሁሉም የግብርና ልማት ክንውኖች ትልቁን ስፍራ የሚይዙ ናቸው ብለዋል።

አቶ ጌቱ እንደተናገሩት፤ ይህንን ሥራ በትክክለኛው መንገድ መምራት ከተቻለ ሕዝቡ ከዚህ በፊት ከሚያገኘው ጥቅም በላይ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይቻላል። አምና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገበት ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ ልምድም የተገኘበት ነው። በተለይም ሐረር አካባቢ ሲሠራ የነበረው የተፋሰስ ልማት ሕዝባችንን በተጨባጭ ተጠቃሚ ያደረገ ነው ያሉት አቶ ጌቱ፣ ይህ የተፋሰስ ሥራ ለሁሉም የግብርና ሥራዎቻችን ትልቁን ሚና የሚጫወት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ በመግባቱ ሕዝቡ የተፋሰስ ልማት ሥራውን በንቅናቄ ለመሥራት ጊዜውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። ይህም ሕዝቡ ሥራውን እየሠራ ያለው በፍላጎት መሆኑን አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተሠራው ሥራ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች ጎልብተዋል። ውሃ በመጎልበቱ ደግሞ የልማት ሥራዎች እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል። ከተገኘው ውሃ ደግሞ ታችኞቹ አካባቢዎች ለሌላ የግብርና ሥራዎች ያዋሉባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

እሱ ብቻ ሳይሆን ከንክኪ ነፃ ያደረግናቸው ቦታዎች ላይ ወጣቶች ተደራጅተው፤ ንብ በማነብ፣ የወተት ላሞችን በማርባት፣ ከብቶች ማደለብ እና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በሚገኘው ውሃ የዓሣ እርባታ ሁሉ የተካሔደባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

ዘንድሮም በምንሠራው ሥራ ላይ እንደተለመደው ሁሉ የሕዝብ ትብብር ይደረጋል ብለን እንጠብቃለን። የአመራርና ባለሙያ ቅንጅት ከላይ እስከ ታች ድረስ በተለመደው መንገድ የሚኬድበት ይሆናል። በተሻለም ሁኔታ ይቀጥላል ብለን እናስባለን ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በዘንድሮው ሥራ ላይ ከዘጠኝ እስከ አስር ሚሊዮን የሚሆን ሕዝባችን በሥራው ይሳተፋል ብለን አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ የመጀመሪያው ዙር የኦሮሚያ ክልል የግብርና ባለሙያዎች በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዙሪያ ለስምንት ቀን የሚቆይ ሥልጠና መጀመራቸው ይታወቃል።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You