ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ለማደስ ተስማሙ

አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት ገደማ የቆየውን ግንኙነታቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ለማደስ፤ በሀገራቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መስማማታቸውን አስታወቁ። ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በአዲስ አበባ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አጠናቀው ወደሀገራቸው ተመለሱ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንዳስታወቀው ሐሰን ሼክ መሐሙድ ከትናንት በስቲያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። ውይይቱን ተከትሎ መሪዎቹ ባወጡት የጋራ መግለጫም፤ ለአንድ ዓመት ገደማ የቆየውን የሀገራቱን ግንኙነት ለማደስ ተስማምተዋል።

መሪዎቹ በውይይታቸው በሀገራቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል፤ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር፤ በየሀገራቱ ያላቸውን ሙሉ የዲፕሎማሲ ውክልና በመመለስ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን መግለጫው አመልክቷል።

ለቀጣናው መረጋጋት የሁለቱ ሀገራት በመተማመን እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳትም፤ በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማሻሻል፣ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና የጋራ ግቦችን እውን ለማድረግ በትብብር ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም መግለጫው አትቷል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላቸውን ትብብር፤ በኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፤ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ለማስፋት እና የጋራ ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ስለመድረሳቸው በመግለጫው ተመልክቷል።

መግለጫው፤ የአንካራው ስምምነት ከሀገራቱ የወዳጅነት እና የአጋርነት መንፈስ የመነጨ መሆኑን፤ መሪዎቹም ለስምምነቱ ትግበራ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ፤ በስምምነቱ የተቀመጠውን የቴክኒክ ድርድሮች በፍጥነት ለማስጀመር መሪዎቹ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቋል።

የአንካራው ስምምነት በቱርክ ፕሬዚዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋን አሸማጋይነት፤ በሀገራቱ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በውይይት እና በድርድር ለመፍታት በመሪዎቹ መካከል የተደረሰ ሥምምነት መሆኑ ይታወሳል።

ስምምነቱ በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ስር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር በር በኮንትራት፣ በኪራይ እና በሌሎች አማራጮች የምታገኝበትን መንገድ የሚያመቻች ነው።

ሀገራቱ አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት፣ ነፃነት እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ስምምነት ላይ የደረሱበት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ለከፈሉት መስዋዕትነት ሶማሊያ እውቅና እንድትሰጥ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ እንዲፈጸም የሚጠይቅ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ግብዣ ወደ አዲስ አበባ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ በካምፓላ ከዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና ከኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ በአዲስ አበባ ቆይታቸው በቅርቡ ታድሶ ለሕዝብ ይፋ በሆነው በታላቁ ቤተመንግሥት ለእሳቸው እና ለልዑክ ቡድናቸው የራት ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን የዓድዋ ሙዚየምንም ጎብኝተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You