በምሥራቅ ወለጋ ዞን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ በልማት ሥራዎች መነቃቃት እየተፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

– በዞኑ 235 የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ወደ ሰላም መንገድ ተመልሰዋል

አዲስ አበባ:- በምሥራቅ ወለጋ ዞን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የልማት እንቅስቃሴዎች መነቃቃት እያሳዩ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋሪ ነገራ ገለጹ። 235 የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ወደ ሰላም መንገድ መመለሳቸውም አመለከቱ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋሪ ነገራ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል።

ዞኑ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ቢሆንም በፀጥታው ችግር ሳቢያ ሀብቱን በአግባቡ አልምቶ ተጠቃሚ መሆን ሳይችል መቅረቱን ያስታወሱት አቶ ዋቅጋሪ፣ በአሁኑ ሰዓት ግን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ዞኑ ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል ብለዋል።

በፀጥታ ችግር ምክንያት ግንባታቸው ተቋርጦ የነበሩ ፕሮጀክቶች ሁሉም ወደ ሥራ መመለሳቸውን ጠቅሰው፣ በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚሠሩ የፕሮጀክት ሥራዎችን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግሥት በጀት በ19 ቢሊዮን ብር 25ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል የመስኖ ፕሮጀክት ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት መጀመሩን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ የአርጆ ዲዴሳ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቋል ብለዋል።

ከነቀምቴ-አንዶዴ፣ ከነቀምቴ-ሳሲጋ-ሶጌ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በፌዴራል መንግሥት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉ በጀት ቢላ-ዘንጊ-ሀቤ ዶንጎሮ አንጋርጉቴ ከአርጆ ጉደቱ-ጂርማ-ሶጌ የመንገድ ፕሮጀክቶችም እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ከጊዳአያና-ሊሙ-ገሊላ-ሀሮ ሊሙ 68 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና እንዲሁም 28 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ጊዳ-ኤቤንቱ መንገድ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

መንግሥት ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ለማሳደግ በሰጠው ትኩረት መሠረት በዞኑ ባልተለመደ መልኩ የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁመዋል። በተያዘው ዓመት 21 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተሰጠው ትኩረት ባለፈው ዓመት 129 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርት ማምረት መቻሉን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው 226 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን 181 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር እንደተሸፈነ አመልክተዋል።

በዞኑ መንግሥትና ሕዝብ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ 235 የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎች ወደ ሰላም መንገድ እንደተመለሱ ገልጸው፣ ሕዝቡ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በንቃት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You