አዲስ አበባ፡ ለኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ የሚያስፈልገው ችግርን ብቻ አጉልቶ የሚያወራ ዜጋ ሳይሆን ለልማቷና ለሰላሟ ተግቶ የሚሠራ መሆኑን አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ገለጸ። ሕዝቡ የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ጥፋትን የሚሰብኩ የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሴራ ማጤን እንደሚጠበቅበት አመልክቷል።
አትሌት ፈይሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቀው፣ ኢትዮጵያ በርካታ ስኬቶችና ችግሮች ያሉባት ሀገር መሆኗን በውል በመገንዘብ ስኬቶቿንና ችግሮቿን በሚዛናዊነት መግለጽ ተገቢ ነው።
ከለውጡ ወዲህ ፈርጀ ብዙ ለውጦች ተመዝግበዋል። በተለይ በጋና ክረምት በማምረት በስንዴ ራስን በመቻል ከልመና እና ከዚህ ከሚመነጭ ውርደት ለመላቀቅ ተችሏል። ገዥና ተቃዋሚ በመባባል እንደ ጠላት የመተያየት ፖለቲካ ባሕል ወደ ተፎካካሪና አብሮ መሥራት ተሸጋግሯል ብሏል።
ከሁሉም በላይ የነበሩ የውጭና የውስጥ ጫናዎችን ተቋቁሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ወደ ማገባደድ ተደርሷል ያለው አትሌት ፈይሳ፣ የሀገር አንድነትን ማስቀጠል መቻልም ከስኬቶቹ ጥቂቶች እንደሆኑ አስታውቋል ።
አንዳንድ ወገኖች አውቀውም ይሁን ባለማወቅ የተመዘገቡ ስኬቶችን በዜሮ በማባዛት ጊዜያዊ ችግሮችን እያራገቡ መሆናቸውን ያመለከተው አትሌቱ፤ ያሉ ችግሮችን መግለጻቸው ክፋት ባይሆንም የድርሻቸውን ሳይወጡ ስኬትን በማጠልሸት ችግር ብቻ አጋኖ ማራገብ ግን ለሀገርም ሆነ ለወገን እንደማይጠቅም አስገንዝቧል።
ሕዝቡ ችግሩን ለመቅረፍ የሚሠራ አካልና የራሳቸውን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ጥፋትን የሚሰብኩ የፖለቲካ ነጋዴዎችን ሴራ ማጤን ይጠበቅበታል ብሏል። ኢትዮጵያ ክብሬና ሀገሬ ናት የሚል ሁሉ በቃል ሳይሆን በተግባር ማሳየት እንዳለበትም ጠቁሟል ።
በሀገሪቱ የኑሮ ውድነት መኖሩ የማይካድ ሐቅ ነው፤ ዓይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ ችግሩ በአሜሪካም ስለመኖሩ በዛ በነበረባቸው ጊዜያት ማስተዋሉን ያወሳው አትሌት ፈይሳ፤ ልዩነቱ በአሜሪካ ምርት ለመጨመር የሚያስችል የሀገር ውስጥ ፀጥታ እና መረጋጋት እንዳይኖር የሚተጉ፤ የኑሮ ውድነቱን አጋነው የሚሰብኩ የፖለቲካ ነጋዴዎች አለመኖራቸው እንደሆነ አመልክቷል። ከችግሩ ለዘለቄታው ለመውጣት ተግቶ መሥራት የግድ እንደሚሆን አመልክቷል።
የጭፍን ተቃውሞና የጭፍን ድጋፍ ባሕል ካልተቀረፈ ለሀገሪቱ አደጋ ነው ያለው አትሌቱ፤ አንድ የፖለቲካ ነጋዴ ጥፋት ስለሰበከ ብቻ መስማት አያስፈልግም፤ ተጨባጭ ሁኔታን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል። ለሀገር የሚበጀውም ድጋፍና ተቃውሞ በምክንያት ሲሆን እንደሆነም አሳስቧል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም