ወገኖቼ፣ ሁላችሁም እንደምታውቁት አገራችን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ መዛባት ባስከተሏቸው ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ትገኛለች። እነዚህን ውስብስብ እና ከፍተኛ ችግሮች ተቋቁሞ የገጠመንን ፈተና ለማለፍ ሁላችንም የየግላችን ስሜትና ፍላጎት ለጊዜው ወደጎን በመተው፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ከአመራሩ ጎን ተሰልፈን አቅማችን የፈቀደውን ያህል የድርሻችንን ልንወጣ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ እኔ ያቀረብኩት ሃሳብ ይበልጣል ከማለት ይልቅ የትኛው ሃሳብ ለጋራ ህልውናችን የበለጠ ይበጃል በሚል የጋራ ህልውና እሳቤ ላይ ልናተኩር ይገባናል።
ይህን ስናደርግ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ሆኑ በአንዳንድ ሁኔታዎች ተታለው ወይም ተሳስተው ከብሔራዊ ጥቅማቸው በተቃራኒ በመቆም ለታሪካዊ ጠላቶቻችን በመሣሪያነት ለማገልገል የተሰለፉ አንዳንድ ወገኖቻችን በአዘጋጁልን ስውር ወጥመድ ተጠልፈን ከመውደቅ እንድናለን። ይህንን የምለው ለሁላችንም ለኢትዮጵያውያን የሚበጅና የተሻለ አማራጭ መስሎ ስለታየኝና ስለእማምንበትም ነው እንጂ ለአመራሩ የተለየ ድጋፍ ለማሰባሰብ አስቤ አይደለም። ለኢትዮጵያችን የተሻለ ነገን ከመመኘት የመነጨ እንጂ ለፖለቲካ አመራሩ ድጋፍ የማሰባሰብ የእኔ አላማም ሆነ የሥራ ድርሻዬ አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም።
ምክንያቱም እኔ ዛሬ በ74 ዓመት የሽምግልና ጊዜዬ ከማንም ምንም ዓይነት ጥቅምና ተወዳጅነት የምፈልግ ሰው አይደለሁም፤ ልፈልግም አልሻም። ነገር ግን የአገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል። በኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ፣ ጉዳትና እንግልት አንጀቴን ያቆስለዋል፤ ልቤንም ያደማዋል። ይሁን እንጂ ከዚህ ከገባንበት ውስብስብ ችግር ለመውጣትና ወገኖቻችንም እየደረሰባቸው ካለው አሳዛኝ ጉዳትና እንግልት ለመታደግ የምንችለው በመለያየትና በመወነጃጀል ሳይሆን የግል ስሜታችንንና ፍላጎታችንን ወደ ጎን በመተው ለጋራ ህልውናችን ቅድሚያ ሰጥተን በተባበረ ክንድ ለመታገል ስንችል መሆኑን በጽኑ ስለማምን ነው። በሕይወት ዘመኔ ካየሁትና ከተረዳሁት ያረጋገጥኩትም ይህንኑ ሀቅ ነው።
«ከበሮ በሰው ላይ ሲያዩሽ ታምሪ ሲይዙሽ ትደናገሪ» እንደሚባለው ሁሉ፤ የሚሠሩ ሰዎችን ስህተቶች እያጎሉ እንደመወንጀሉ በመሪነት መድረክ ላይ ወጥቶ መመዘኑ ቀላል አይሆንም። ይህን ስል ማንኛውንም ወገን ለመተቸትና ለመንቀፍ ሳይሆን ጠቃሚ መስሎ የታየኝን ምክርና ልመናም ለማቅረብ ነው። ለምሳሌ፣ በ1969 እና በ1970 ዓ.ም በአገራችን የነበረውን የተለያዩ ቡድኖች እኔ ያልኩት መሆን አለበት የሚል አባዜና ሕዝብና መንግሥትን የማለያየት ጥረት ያደረሰብንን ጉዳትና በታሪካችንም ላይ ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ በጥሞና ማጤንና ካለፈው ስህተታችን መማር ይገባናል እላለሁ። አገራችን አሁን ያለችበትን ውስብስብ ችግር ሳናጤን በየራሳችን መንገድ ተጉዘን የየቡድናችንን ፍላጎት (ምኞት) የምናሳካ ከመሰለን ግን የጠላቶቻችንን ዓላማ የምናሳካበትንና ሁላችንም በየተራ የምንጠፋበትን መንገድ የመረጥን ይመስለኛል።
የአገራችን ዘላቂ ሰላምና የሕዝባችንም በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ ተገንብቶ ማየት፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተከብሮለት በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ሠርቶ የመኖር የዜግነት መብቱ ያለምንም መሸራረፍ እንዲረጋገጥለት ማድረግ፤ ሁሉም ጤነኛ አእምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ የሚመኘውና የሚጓጓለት ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ስለጓጓንለትና ስለተመኘነው ብቻ በፈለግነው ፍጥነትና ሁኔታ እውን ሊሆን እንደማይችል እስከ አሁን አገራችን ያለፈችባቸው ታሪካዊ ክስተቶችና አሁንም ያለንበት ሁኔታ በግልጽ የሚያሳየን ሀቅ ነው። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ለኢትዮጵያ ህልውናና ለሕዝቦቿም የጋራ ደህንነትና ሰላም የምናስብ ወገኖች ሁላችንም ሀሳቦቻችንንና ፍላጎቶቻችንን አቻችለን በአንድነት በመቆም ከመታገል ውጪ ከዚህ ከገባንበት ውስብስብ ችግር ሊያወጣን የሚችል ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።
ኢትዮጵያ አገራችን በጥሩ የአየር ንብረትና በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ከመሆኗ በተጨማሪ፤ የበርካታ ብሔረሰቦች አገርም ናት። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች እንደነብር ለምድ ለኢትዮጵያ ጌጦቿና ውበቷ እንጂ ለልዩነት ምክንያት ሊሆኑ አይገባም። በረጅሙ አብሮ የመኖር ታሪካችንም ችግር አልነበረም። ይህ አሁን አገራችንንና ሕዝባችንን እየበጠበጠ ያለው የጎጠኝነት ትርክት በወያኔ ከመሰበኩ በፊት እነዚሁ ብሔረሰቦች ተፋቅረውና ተዋደው፣ ተጋብተውና ተዋልደው በመረዳዳትና በመተባበር ለዘመናት በሰላም አብረው የኖሩና ለአገራቸው ነፃነትና ዳር ድንበር መከበር በጋራ ተሰልፈው ደማቸውን እያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን እየከሰከሱ በጋራ ጥረታቸውና ትግላቸው ነፃነታቸውን ሳያስደፈሩ መኖራቸውን ወዳጅም ጠላትም የሚመሰክረው ሐቅ ነው።
ከታሪክ እንደምንረዳው ይህ ኢትዮጵያን በብሔረሰብ የማደራጀትና የመከፋፈል ስውር ደባ በኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የተባበረ የነፃነት ትግል የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ተመትቶ በመባረሩ ኢትዮጵያውያንን በብሔረሰብ በማደራጀት ለመከፋፈል ተዘጋጅቶልን የነበረው ስውር ዳባ ከሽፎ ነበር። ይሁን እንጂ ከ50 ዓመታት በኋላ አውቀውም ይሁን ተሳስተው የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ዓላማ አንግበውና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው በተሰለፉ ወገኖቻችን አማካይነት ተግባራዊ ሆኖ በሕዝባችን መካከል ጸንቶ የኖረውን ፍቅርና አንድነት በማናጋት እየበጠበጠን ይገኛል።
በእኔ እምነት ማንኛውም የሰው ዘር ከአንድ ምንጭ ከአዳምና ከሄዋን (አደምና ሐዋ) ብቻ የተቀዳ ነው። ስለሆነም ሁሉም ሰዎች እንዲሟላላቸው የሚፈልጉት ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብት/ሰብአዊ ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች/ አንድ ዓይነት ናቸው። ይህን ስል ግን እንደየማህበረሰቡ የእድገት ደረጃ፣ የኢኮኖሚ አቅም፣ ከመኖሪያ አካባቢና ከባህል ልዩነት የሚመነጭ በማህበረሰቦች መካከል መጠነኛ የፍላጎት(መጠንና የዓይነት) ልዩነት ሊኖር አይችልም ለማለት አይደለም። ልዩነቱ ከማህበረ ሰቡ የኢኮኖሚ አቅም፣ ማህበረሰቡ ከደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃና የአኗኗር ስልት አንጻር የሚኖር ፍላጎትን በአቅም ላይ ተመስርቶ ለማሟላት ከሚደረግ ምርጫ የሚመነጭ ነው እንጂ፣ በሰው ልጆች መካከል መሠረታዊ የፍላጎት ልዩነት የለም ለማለት ነው።
ስለሆነም፣ ሰዎች በቆዳ ቀለም፣ በመኖሪያ አካባቢ፣ በቋንቋ፣ በባህልና በአኗኗር ስልት ቢለያዩም ሰብአዊ ባህርያቸውና ፍላጎታቸው ግን ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ነው። ስለዚህም ቅዱሱ መጽሐፍ፣«በአንተ ላይ ሊደረግብህ የማትፈልገውን በሌሎች ላይ አታድርግ፣ ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ደግሞ ለሌሎች አድርግ፤» (ሉቃ. 5፥31) እንዲል፤ በእኔ እምነት ከአንዳንድ የሥልጣን ጥም ሰብአዊ ህሊናቸውን ካሳጣቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በስተቀር የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ፍላጎትና ምኞት የአገራቸው ዳር ድንበርና ነፃነት በአስተማማኝ ሁኔታ ተከብሮና በመላ አገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ማየት፣ በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት አድልዖና ልዩነት የሌለበት ፍትሕና ዴሞክራሲ በመላ አገሪቱ ተረጋግጦ ማየት፣ እንዲሁም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ ያለምንም ገደብ ተከብሮለት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሠርቶና ንብረት አፍርቶ የመኖር ሙሉ ኢትዮጵያዊ መብቱ ተረጋግጦለት ማየት ነው።
ከዚህ ባለፈ ግን በመላ አገሪቱ ያለውን ኢትዮጵያዊ መብቱን በሚያሳጣ መልኩ በብሔረሰብ ክልል ተወስኖ እርስ በእርሱ እየተጣላና እስከ ዛሬ ድረስ አባቶቻችን በጋራ ጥረታቸው የገነቧቸውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተቋሞች የማፍረስ ዓላማም ሆነ ፍላጎት የለውም። ይህን በማለቴም የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ምክንያቱም ካለፉት 40 ዓመታት በፊት የነበረው ታሪካችን የሚያሳየን በአንድ ኢትዮጵያ ጥላ ስር ተሰባስበን፣ ተባብረን፣ ተከባብረንና ተረዳድተን በጋራ በመቆም ነፃነታችንና ዳር ደንበራችን ሊደፍሩ የሚመጡትን ጠላቶቻችን በተለያዩ ጊዜያት አሳፍረን እየመለስን ነፃነታችን በአስተማማኝ ሁኔታ አስከብረን መኖራችንን ነው።
አሁን በቅርቡም በታሪካዊ ጠላቶቻችን አነሳሽነትና አይዟችሁ ባይነት፣ በአንዳንድ እራስ ወዳድና ከብሔራዊ ኃላፊነታቸው ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ባስቀደሙ ወገኖቻችን መሣሪያነትና ግንባር ቀደም ተዋናይነት እርስ በእርሳችን ለማፋጀትና አገራችንን ለማፍረስ ታቅዶ የተደረገብንን ወረራ (ምንም እንኳን እንደ አገር የደረሰብን ጉዳት በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም) ለመቋቋምና ለጊዜውም ቢሆን አደብ ለማስገዛት የቻልነው በአንድነታችንና በተባበረ ትግላችን መሆኑ የሚታወቅ ነው።
በእኔ እምነት ይህ በታሪካዊ ጠላቶቻችን የሚመራውና በአንዳንድ ብሔራዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በዘነጉ ወገኖቻችን ግንባር ቀደም ተዋናይነት የሚከናወነው ወረራ ለጊዜው ተገታ እንጂ ጨርሶ አልተወገደም። ስለሆነም ወረራውን እስከ መጨረሻው ለማስወገድና የሕዝቡን አንድነትና ሰላም በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለመገንባት፣ ምን ጊዜም ተከብሮ የኖረው የአገሪቱ ዳር ድንበር እንደተከበረ እንዲኖር ለማድረግ የሁላችንም አንድነትና የተባበረ ጥረት ያስፈልጋል። አገራችን አሁን ከአጋጠሟት ውስብስብ ችግሮች ለማውጣትና በውጤቱም የጋራ ተጠቃሚ ለመሆን ሁላችንም በመካከላችን አንዳንድ አለመግባባቶችና የሐሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን እነሱን እንደሌሉ ቆጥረን ወይም ወደ ጎን ትተን እና ጊዜው ሲደርስ መክረን ለማረም ተዘጋጅተን ከአመራሩ ጎን በመሰለፍ ይህን የፈተና ጊዜ በአሸናፊነት ለማለፍ መሥራት አለበን ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ባለፈ ግን በአንደኛው ወይም በሌላኛው ምክንያት በመነሳት ከአመራሩ የሚታዩ አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶችን አጉልቶ በማውጣት ጠንካራ ጎኖችን ደግሞ እንደሌሉ አድርጎ በማቅረብ መሪና ተመሪን ለማለያየት የሚደረገው ሙከራ ሁላችንንም ከመጉዳት እና የጠላቶቻችን ዓላማ ለማሳካት ከማገለግል በስተቀር ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። በእኔ እምነት ይህንን ከአመራሩ የሚታዩ አንዳንድ ስህተቶችን እያጎሉ መሪና ተመሪን የማለያየት ሥራ የሚሠሩ ወገኖች አንድም በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሥውር ደባና ጊዜያዊ ጥቅም ተታለውና ተጠለፈው ወድቀው ነው፤ አለበለዚያም ይህንን ክፍተት ተጠቅመው መንግሥትን ከሕዝብ ለመነጠልና በሚፈጠረው ክፍተትም ወደ ሥልጣን ኮርቻ ለመቆናጠጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጠርልናል ብለው ስለሚገምቱ ነው።
ይህን ስል በመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ጉድለቶች አይነሱ ወይም አይገለጹ ለማለት አይደለም። ነገር ግን አሁን አገራችን ካለችበት ውስብስብ ችግር አንጻር ቅሬታዎቹና ጉድለቶቹ ከገንቢ ሀሳቦች ጋር የአመራሩን ሥራ ሂደት ለማቃናትና አስተዋጽዖ ለማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ በቅንነት ላይ ተመስርተው ቢቀርቡ የምንመኘውን የመንግሥት ሥርዓት ለማምጣት ይረዳናል፣ በውጤቱም ሁላችንም ተጠቃሚ ልንሆን እንችላልን ከሚል መንፈስ በመነሳት እንደሆነ ይታሰብልኝ። ምክንያቱም በቅንነት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልዩነት መኖሩና መነሳቱ ጥሩ ሲሆን ጠቃሚ የሚሆነው ግን መጀመሪያ ለጥሩ ሥራ በአግባቡ እውቅና በመስጠት ተከሰቱ የሚባሉ ስህተቶችን ደግሞ ከማሳየቱ ጎን ለጎን የመፍትሄ ሃሳቦችንም አብሮ ማቅረብ ሲቻል የልዩነት ሀሳቡ የገንቢነት ሚና ይኖረዋል ሁላችንንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብዬ ስለማምን ነው።
ከዚህ መንፈስ ውጪ ስህተቶችን ብቻ አጉልቶ በማሳየት ኅብረተሰቡ በአመራሩ ላይ እምነት እንዲያጣ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ ግን፣ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ፍላጎት ለማሳካት ከመሞከር፣ የሕዝባችንን አንድነትና ህብረት ለማናጋት ከመጣር፣ የአገራችንን ልማትና እድገት ወደኋላ ለመጎተት የሚደረግ አፍራሽ ሚና ከመሆን ውጪ ሌላ ሊሆን አይችልም የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ይህችን አገር መልአክ መጥቶ እስከ አላስተዳደራት ድረስ ስህተት የማይሠራ መሪ ሊኖር አይችልም። ሰው የሆነ ሁሉ ፍጹምነት የለውምና ነው። ይህን ስል ግን መንግሥትም የራሱን ጉድለቶች እየገመገመ ማረምና በውስጡ አፍራሽ ሚና የሚጫወቱ ቡድኖችና ግለሰቦችም ቢኖሩ በመረጃ ላይ ተመስርቶ በማጽዳት ተገቢውን የመንግሥት ሚና መወጣት እንዳለበት ከማሳሰብ ጋር ነው።
በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለኢትዮጵያውያን ደህንነት፣ ፍቅርና አንድነት የሚያስብና በዜጎች ላይ እየደረሱ ባሉ ጉዳቶችና እንግልቶች የሚቆረቆር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የሚታዩ የአሠራር ግድፈቶችን ለማስወገድ ተባብሮ መስራት ይኖርበታል። ለዚህም ሆን ተብሎ የሚሠራ አሻጥር በመረጃ ላይ ተመስርቶ አመራሩን በማጋለጥና ማዕከሉን ማጠናከር ይገባዋል። በተመሳሳይ በየአካባቢው በሽብር ፈጠራ ላይ ተሰማርተው ወገኖቻችንን የሚገድሉ፣ የሚዘርፉና የሚያፈናቅሉ ቡድኖችን ቢቻል መክሮና አስተምሮ በመመለስ ካልተቻለም በተባበረ ክንድ በመምታትና በማስወገድ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን በማድረግ ዜጎች መብታቸው ተከብሮና በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተውና ይመቸኛል ብለው በሚያስቡት የአገሪቱ ክፍል ሀብትና ንብረት አፍርተው ሊኖሩ የሚችሉበትን አስተማማኝ ሥርዓት መመስረት ይገባልም።
ይሄን ማድረግና የሕግ የበላይነትን ማስፈን እስከ አልቻልን ድረስ ግን ይኸኛው ወገን ተበደለ ያኛው ወገን ደግሞ በደለ እያልን ብንቆጭና በዜጎች መካከል ያለውን አንድነትና ህብረት ከማጠንከር ይልቅ ልዩነቱን ለማስፋት ብንሞክር የጠላቶቻችን ዓላማ ለማሳካት አስተዋጽዖ እናደርግ እንደሆነ እንጂ፤ በየአካባቢው የሚገኙ ወገኖቻችንን ከሚደርስባቸው እንግልትና ጉዳት ነፃ ለማውጣት የሚያግዝ ተጨባጭ አስተዋጽዖ ለማድረግ አንችልም የሚል ጽኑእ እምነት አለኝ።
ስለዚህ እባካችሁ ወገኖቼ አሁን አገራችን ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር ሁኔታዎችን ሁሉ በመመልከት የእኔ ሀሳብ ትክክል ነው፣ የእነገሌ ግን ጎጂ ነው፣ ለወገኖቼ የምቆረቆረው እኔ ነኝ፣ እነ እገሌ ግን የወገኖቻቸውን ጥቅም አሳልፈው ሰጥተዋል፣ እያልን እና ስህተቶቻችንን ብቻ እየነቀስን በማውጣት የችግሩ ተጨማሪ አካል ከመሆን ርቀንና መወነጃጀላችንን ትተን፣ ሳናውቀውም የታሪካዊ ጠላቶቻችን ዓላማ በተዘዋዋሪ መንገድ እያስፈጸምን መሆኑን በጥልቀት በመረዳት፣ ከግል ፍላጎታችንና ስሜታችን ርቀን በመመካከርና በመተባበር በቅድሚያ የአገራችን ህልውና በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የሁሉም ዜጎች መብት በእኩልነት የሚከበርባትን አገርና የመንግሥት ሥርዓት ለመገንባት የየበኩላችንን አጋዥ ሚና ለመጫወት እንጣር እላለሁ።
መለያየት ለጥፋት እንጂ ለልማት አይሆንምና ሰላሙን ይስጠን!
ዋለልኝ ሲሳይ
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2014