በዚሁ ጋዜጣ በዚሁ አምድ ለውጡ ከባ’ተ አንስቶ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ በምጽፈው መጣጥፍ ለውጡን ዳር ማድረስና ማሳካት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ስል ሞግቻለሁ። ምክንያቱም እንደ 1966ቱ፣ 1983ቱ፣ 1997ቱ እና 2010ሩ ሌላ እድል ስለማግኘታችን እርግጠኛ አይደለንም። ይህ የመጨረሻው እድል ይመስለኛል። ይሄን ለውጥ ከእነ ውስንነቶቹና እጥረቶቹ ማጽናትና ማዝለቅ ብቸኛው ምርጫ ነው።
ይህ ለውጥ ቢጨናገፍ ቢኮላሽና ቢከሽፍስ ብዬ ሳስብ ስለሚያስፈራኝና ስለሚያባባኝ ማሰብ አልፈልግም። የሰይጣን ጆሮ አይስማና። ሆኖም ይህ ለውጥ የሚሳካው በምኞት አይደለም። ተቋማትንና ሥርዓትን መገንባት እንጂ። ይህ ከሞላ ጎደል እየተሳካ ይመስላል። ምንም እንኳ መንገራገጭና መደነቃቀፍ ቢበዛውም። የምርጫ ቦርድን ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን የመሳሰሉትን ተቋማት መገንባት ተችሏል። አፋኝና ኢዴሞክራሲያዊ የነበሩ ሕጎችን አብዛኛዎቹ ገለልተኛ ምክር ቤት ተቋቁሞ ተሻሽለዋል። እየተሻሻሉም ነው።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሒደትና ቅብብሎሽ ነውና በአንድ ጀንበር ይሳካል ተብሎ አይጠበቅም። አይንን ከትልቁ ስዕል ሳያነሱ መስራትን ይጠይቃል። ይሄን ለውጥ ከግራም ከቀኝም ከፊትም ከኋላም የሚጎሽሙትና አንዳንድ ጊዜም የሚጎትቱት ባለፉት 100 ዓመታት ያላወራረድናቸው እዳዎች ናቸው። የልዩነት ፣ የጥላቻ ፣ የቂም በቀል ፣ ያለመግባባት ፣ ይቅር ያለመባባል ፣ ያለመነጋገርና ያለመቀባበል የጥፋት ዕዳ።
እነዚህን የእዳ ጥፋቶች በብሔራዊ ምክክር ማወራረድና መቅደድ ያስፈልጋል። ለመጪው ትውልድ በእዳ ልናወርሰው አይገባም። ብሔራዊ ምክክሩ የለውጡ ትሩፋትም መዳኛም ነው። ለውጡ ምሉእ እንዲሆን አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና አለው። እንደ ሕዝብም ሆነ አገር መዳኛችን አንዱ ፍቱን መድሃኒታችን ነውና እንደ አይናችን ብሌን ልንሳሳለትና ልንከባከበው ይገባል።
በሰው ልጅ ታሪክ ፅንፈኝነት ፣ ዋልታ ረገጥነትና አክራሪነት በጊዜአዊነት የሚጠቅመው ጥቂት ፖለቲከኞችንና አክቲቪስቶችን እንጂ አገርንና ሕዝብን አይደለም፡፡ አገርን የሚጠቅመው በጥሞና በእርጋታ መመካከር ማንሰላሰል ነው፡፡ ዜጎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ማንኛውንም ልዩነት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍታት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም በቀደመው ሆነ በቅርቡ ታሪካችን ልዩነታችን በአፈሙዝ ኃይል ለመፍታት ፣ ለማፈንና ለመጨፍለቅ ያደረግነው ጥረት ልዩነታችንን ይበልጥ አሰፋው እንጂ አላጠበበውም። አልፈታውም፡፡ የለውጥ ኃይሉ ልዩነትን አለመግባባትን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ውጤታማነቱን ግን ቆም ብሎ መፈተሽና መመዘን ያስፈልጋል ፡፡
ለውጡ ከባተ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚያዘጋጃቸውን የ”አዲስ ወግ” የውይይት መድረኮችን ጨምሮ በሌሎች የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ፣ በፌዴራል ተቋማት ፣ በክልሎች ፣ እንደ ማሕበራዊ ጥናት መድረክ ባሉ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ በቅን አሳቢ ዜጎች ፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ‘ኢ.ቢ.ሲ/EBC’ “በልቦና ውቅር” ፣ “በወቅታዊ”ና “በካስተማ” ፣ ወዘተ .፤ ፋና “በዙሪያ መለስ” ሰላምን ፣ መቻቻልን ፣ ፖለቲካዊ ምህዳርን ፣ ለውጡን ፣ ውህደቱን ፣ የህዳሴ ግድብን እና ተያያዥ የሆኑ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከተ ቢያንስ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስብሰባዎች በመላ አገሪቱ ተካሂደዋል፡፡
ሆኖም እነዚህ ስብሰባዎች የሚመለከታቸውን አካላት ስለ ማሳተፍ አለማሳተፋቸው፤ አወያዮች ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር አግባብነት ያለው ልምድና የትምህርት ዝግጅት ይኑራቸው አይኑራቸው፤ ርዕሰ ጉዳዮች ወቅታዊና ችግር ፈቺ ይሁኑ አይሁኑ፤ የተግባቦቱ አግባብ ስብሰባ ይሁን ምክክር ወይም ማንሰላሰል፤ ወዘተ . እርግጠኞች ስለመሆናቸው መረጃም ማስረጃም የለኝም ፡፡
ምክንያቱም “ስብሰባዎች” ያመጡትን የአመለካከት ለውጥ ያስመዘገቡትን ውጤት የሚለኩበትን ሥርዓት ወይም ግብረ መልስ የሚተነትኑበትን ሥነ ዘዴ አልያም አስተያየት የሚሰበስቡበትን መንገድ አልገለጹልንም ፡፡
ሆኖም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙዎቹ አልያም ሁሉም “ ስብሰባዎች “ በቅድመ ፍላጎት ዳሰሳ ፣ በቅድመም ሆነ በድህረ አስተያየት ስብሰባ ፣ በግብረ መልስ ከፍ ሲልም በጥናት የሚካሄዱ አለመሆናቸውን መገመት እችላለሁ፡፡ የተሰብሳቢዎች ስብጥርም ሆነ የጥናታዊ ፁሑፍ አቅራቢዎች አመራረጥ ሳይንሳዊ አለመሆኑን ለመናገርም ሞራ መግለጥ አያሻም፡፡ በእርግጥ ከለውጡ ወዲህ አዳዲስ ተሰብሳቢዎችን እና ሰብሳቢዎችን በአዲስ አቀራረብ ማየቴን አልክድም፡፡ ሆኖም ካስመዘገቡት ውጤት አንጻር ሲመዘኑ ዛሬም ብዙ እንደሚቀራቸው ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡
ላለፉት 50 ዓመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ሲሰራበት የኖረ የፈጠራ ትርክት ፣ ልዩነት ፣ ጥላቻ ፣ መጠራጠር ፣ ወዘተ . ለውጡ በባ’ተ ማግስት በአንድ ጀምበር ይወገዳል የሚል ቅዠት የለኝም ፡፡ ስብሰባም ሆነ ሌላ ተቀራርቦ የመወያያ የመነጋገሪያ መንገድ ብቻውን እንደ ቋጥኝ የተጫኑን ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ችግሮች ሁሉ ከላያችን አንከባሎ ይጥላል የሚል ገራገር እምነትም አልሰነቅሁም፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ለውጡን ተቋማዊ የማድረግ በዚህ ዙሪያ በአንድነት መሰባሰብ እና የሕግ የበላይነትን በራሱ በመንግሥት መዋቅርም ሆነ በገዥው ፓርቲና በመላ አገሪቱ ማረጋገጥን እንዲሁም ችግርና ቀውስ የመፍታት አተያያችን አንድ በአንድና ተናጠላዊ ሳይሆን ሁለንተናዊ ምልከታን (wholistic approch)ን እንደሚጠይቅ ተገንዝበን በቅንጅት መሥራት እንዳለብን ማጤን ይጠይቃል፡፡
ይሁንና ላለፉት 30 ዓመታትም ሆነ ከለውጡ ወዲህ ከፌዴራል እስከ ጎጥ ፣ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ አመራር የተሳተፈባቸው “ ስብሰባዎች ፣ ኮንፈረሶች፣ አውደ ጥናቶች ጉባኤዎች ፣ ወዘተ .” የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ ናቸው የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ ይህን ድምዳሜዬን የሚያረጋግጥልኝ የግብረ መልስ ወይም የሕዝብ አስተያየት ጥናት እጄ ላይ ባይኖርም ተደጋጋሚና ተከታታይ ስብሰባ የተደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አድሮ ጥሬ ሲሆኑ እየታዘብሁ ነው።
ከዚህ በላይ በዘመናዊው የአገሪቱ ታሪክ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ በፖለቲካ ፣ በማንነት ፣ በሃይማኖት ፣ በታሪክ፣ በተረክ ፣ በሰንደቅ ዓላማ ፣ በጀግኖች ፣ ወዘተ . እንዲህ ተከፋፍለን ፣ በትንሹ በትልቁ ተለያይተን ፣ ሆድና ጀርባ ሆነን አናውቅም፡፡ ለነገሩ በልዩነትና በጥላቻ ላይ ላለፉት 30 ኣመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሲሰራ በኖረ አገር ሳንለያይ ብንቀር ነበር የሚገርመው፡፡ በተቀናጀና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ባይሆንም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ይሄን ልዩነት ለማጥበብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
ይሁንና በልዩነቶቻችን ፣ በግጭታችን ፣ በሞታችን ነግደው የሚያተርፉ ቡድኖች ይህን ቀለበት ሰብረን እንዳንወጣ በተደጋጋሚ እንቅፋትና ጋሬጣ ሲሆንብን በመንገዳችን እንደ ጅብራ ሲገተሩበን እየተመለከትን ነው፡፡ እዚህ ላይ ሰሞነኛውን የኦነግ ሸኔ ጭፍጨፋ ልብ ይሏል፡፡ እነዚህን እንቅፋቶች በጥበብ በማስተዋል ከመሻገር ጎን ለጎን ለውጡ ገዥ ሃሳብ ሆኖ እንዴት ቢካሄድና ቢመራ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ቆም ብለን ማሰብ ማንሰላሰል አለብን፡፡
ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት ልዩነታችን በውይይት፣ በመነጋገርና በመመካር ካልሆነ በኃይል መፍታት እንደማንችል ውድቀታችን ታሪካችን አስተምሮናልና። በሰከነ አእምሮ ቁጭ ብሎ ከመወያየት፣ ከመነጋገር ከዚያ ከመቀባበል ውጭ አማራጭም አቋራጭም እንደሌለን ታሪካችን ህያው ምስክር ነው፡፡ በነገራችን ላይ መለያየቱ፣ መከፋፈሉ ፣ መጠላላቱ ፣ መጠራጠሩ፣ አለመደማመጡ የእኛ የኢትዮጵያውን እጣ ፈንታ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡
ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወይም ካለፉት 70 ዓመታት ወዲህ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ አሜሪካውያንና አውሮፓውያን እንዲህ አንድነታቸው ላልቶ ፣ ተከፋፍለው አያውቅም። ጆ ባይደን በተወሰነ ደረጃ እያለዘቡት ቢሆንም የራሽያና የዩክሬን ፣ የአሜሪካ ፣ የኔቶና የአውሮፓ ሕብረት ወቅታዊ ፍጥጫ የኒዩክሌር ጦርነት እንዳያስነሳ ተሰግቷል። 3ኛው የዓለም ጦርነትም በዓለማችን ደጅ ላይ ቆሞ እያንኳኳ ነው።
ይህን የመለያየት ፣ የመከፋፈል ፣ የጽንፈኝነት አባዜ ምዕራባውያንም ሆነ አሜሪካውያን ምን ይደረጋል ብለው ተስፋ ቆርጠው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። በሚዲያዎቻቸው ፣ በሲቪል ተቋማትና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት አካላት ማለትም በሕግ አውጪው ፣ ተርጓሚውና አስፈፃሚው ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለመቀልበስ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው ጄምስ ፊሽኪን እና የቴክሳሱ ዩኒቨርሲቲ ሮበርት ሉስኪን በዚህ ረገድ ችግር ፈቺ መፍትሔ በማፍለቅ በፋና ወጊነት ይጠቀሳሉ፡፡
የእነዚህ አሜሪካውያን ሃሳብ፤ “አሜሪካውያን በአንድ ጣራ ስር” ይሰኛል ፡፡ ይህ ሃሳብ አዲስ መንገድ የሚመራ እና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ስለአገኘሁት ላጋራችሁ ፈለግሁ። ከሁሉም በላይ በቅርቡ ለምናካሂደው አገራዊ ምክክር ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት “አገራዊ ምክክር በዴሞክራሳያዊ ምክክር ፤”ሊታጀብ ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
ይሄም መካንና ሾተላይ የሆኑ ስብሰባዎቻችን ወልደው ለመሳም የሚያግዝ ለአካለ መጠን የሚያበቃ መላ ስለሆነ ግድ ይለናል፡፡ በዜጎች መካከል ያለን ፅንፍ የረገጠ የተካረረ ልዩነት ፤ ከመንግሥት ጋር ያላቸውን የማይታረቅ ተቃርኖ ፤ በፖሊሲዎች ላይ የያዙትን የተለያየ አቋም ፤ ወዘተ . በጥሞና በመመካከር በማንሰላሰል ለማጥበብ ፣ ለማስታረቅ የሚያስችለው ይህ አዲስ ዕይታ የምክክር ዴሞክራሲ (Delibrative Democracy) ይባላል፡፡
ይሄን ተከትሎ በታዳሚዎች መካከል የተደረገው ምክክርና ማንሰላሰል ምን ያህል ልዩነታቸውን እንዳጠበበ እና አቋማቸውን እንዳለዘበ ወይም እንዳስቀየረ ለማወቅ የሚሰበሰብ አስተያየት ደግሞ የምክክር አስተያየት (Deliberative Pool) ይሰኛል፡፡ ሁለቱም ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት እንደሚያስፈልጉን አበክሮ ሊታሰብባቸው ይገባል ።
የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲው ጄምስ ፊሽኪን እና የቴክሳሱ ዩኒቨርሲቲ ሮበርት ሉስኪን በ109 አገራት የምክክር ዴሞክራሲ ካካሄዱ በኋላ በ28 የምክክር አስተያየት ሰብስበው ተንትነዋል፡፡ አስተያየቱን ያሰባሰቡት የየአገራቱን ዜጎች ለሁለት ከፍለው በሚያወዛግቧቸው አንገብጋቢና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ አነጋጋሪ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ አልያም ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ከመወያየታቸው በፊትና ለሳምንት በገለልተኛ ባለሙያዎች እየታገዙ በጥሞና ከተመካከሩ በኋላ ነው አስተያየት የተሰበሰበው። የምክክሩ አስተያየት ከተጠናቀረባቸው ቀዳሚ አገራት መካከል ሀንጋሪ አንዷ ናት ፡፡ በዚህች አገር በጥሞና ምክክር የተደረገው እንደ ሁለተኛ ዜጋ በሚቆጠሩትና መገለልና መድልዎ በሚደርስባቸው ሮማኖች ላይ ነው ፡፡
ከምክክሩ በፊት የሮማኖች ጉዳይ ብዙ ግድ የማይሰጣቸው ሀንጋሪያውያን ከምክክሩ በኋላ ብዙዎቹ ሃሳባቸውን በመቀየር ሮማኖችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቁጠሩም ሆነ አድልዎና መገለል መፈፀሙ ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
እነ ፊሽከን ያካሄዱት ሌላው ምክክራዊ ዴሞክራሲ በአሜሪካ ዳላስ ነው፡፡ በዚህ ምክክር 523 ዴሞክራቶች፣ ሪፐብሊካኖች ፣ ቀኝ አክራሪዎች ፣ ግራ ዘመሞችና ሌሎች የሚቃረን አቋም ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ስለስደተኞች ፣ ስለውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ፣ ስለጤና ፣ ሰለኢኮኖሚ እና ሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮች በየዘርፉ ገለልተኛ ባለሙያዎች እየታገዙ ለሳምንት ከተመካከሩ ፣ ካንሰላሰሉና በቡድን በቡድን ተከፍለው ከተወያዩ በኋላ በተሰበሰበ የምክክር አስተያየት በአግራሞት እጅን በአፍ የሚያስጭን ውጤት ተገኘ፡፡ ከምክክሩ በፊት አይን ለአይን ለመተያየትና ሰላምታ ለመለዋወጥ ፈቃደኛ ያልነበሩ ተሳታፊዎች በመከሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ከተጠበቀው በላይ መግባባትና መቀባበል ችለዋል ፡፡
እንደ ማጠቃለያ
ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በኃይል ሳይሆን በጥሞና ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ አግባብ በመወያየት፣ በመመካከርና በማሰላሰል ማጥበብ እንደሚቻል ከላይ በተመለከትናቸው ግኝቶች አረጋግጠናል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ “ስብሰባዎች” ን በተለይ በቀጣይ የምናካሂደውን አገራዊ ምክክር ውጤታማ መሆኑን የምንመዝንበት አሰራር ሊኖር ይገባል፡፡ ተወያየን ፣ ተነጋገርን ፣ ተመካከርን ፣ ወዘተ . ለማለት ብቻ ስብሰባ ማድረግ የለብንም፡፡ እንደነ ፊሽከን ስብሰባዎቻችንን በጥሞና በጥልቀት ወደ መመካከር ማንሰላሰል መቀየርና ውጤታቸውን መለካት አለብን፡፡ ይህን የስታንፎርድ እና የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲዎችን ልሒቃንን ግኝት ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ቀምረን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ምክክሮችን የምናካሂድባቸው ስልትና የታለመላቸውን ግብ ማሳካት አለማሳካታቸውን የምንመ ዝንበት አገራዊና ወጥ የሆነ አሰራርና አደረጃጀት ስለመዘርጋትም አበክሮ የመጨነቅ የመጠበቢያው ጊዜ አሁን ነው፡፡ አበክሬ አገራዊ ምክክሩ በምክክራዊ ዴሞክራሲ ቢቃኝ !? ያልሁት ፤ የአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነትና ስኬታማነት መለኪያና መመዘኛ ከወዲሁ እንዲበጅለት ነው።
ሁላችንም ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የዜግነት ድርሻችንን ለማበርከት እንዘጋጅ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም