ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወንበዴዎች እየፈጠሩት ካለው ምስቅልቅል ጋር ተያይዞ በሰፈራችን ሰዎች እና በአቶ አሻግሬ ልመንህ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ እየተካረረ እና መስመር ስቶ ሰፈራችንን ሊያስብለው ምንም አልቀረውም፡፡ የጸባቸው መነሻም አቶ አሻግሬ በኃላፊነት ለመጠበቅ የተረከበውን የገበያ ማዕከል በተደጋጋሚ በወሮበሎች ሲዘረፍ ከዘራፊዎቹ ለመከላከል ባለመቻሉ ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በእኛ ሰፈር በርካታ የገበያ ማዕከሎች ይገኛሉ፡፡ እነኝህ የገበያ ማዕከሎች በተለያዩ ዘበኞች ይጠበቃሉ፡፡ ነገር ግን በአቶ አሻግሬ የሚጠበቀው የገበያ ማዕከል በተደጋጋሚ ይሰረቃል፤ ጥቃትም ይደርስበታል፡፡ የሚሰረቁት እና ጥቃት የሚደርስባቸው ደግሞ የሐበሻ የጥበብ ልብሶች የሚሸጡባቸው ሱቆች እየተመረጡ ነው፡፡
ጥቃት አድራሾችም ከአንድ ሰፈር የተሰባሰቡ፤ የገበያ ማዕከሉን መኖር የማይሹ ጥላቻን እና መገዳደልን ያረገዙ ቡድኖች ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ በሰፈራችን የሚገኙ የሐበሻ ልብስ መሻጫ ሱቅ ያላቸው ነጋዴዎች እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ከዘበኛው ጋር ለመወያየት በማሰብ ዘበኛውን ለውይይት እንደሚፈልጉት ነገሩት። ውይይቱንም በገበያ ማዕከሉ አዳራሽ ተገናኝተው ጀመሩት፡፡
ስብሰባውም አቶ አሻግሬ እና ጋሼ ሳለሁ- ድረስ እየመሩት ተጀመረ፡፡ ስብሳባውን የሚመሩት አቶ አሻግሬ እና ጋሼ ሳለሁ- ድረስ ስለስብሰባው አጀንዳ ቀድመው ማብራሪያ የተሰጡበት ይመስል ስብሰባውን ቀጥታ ተሰብሳቢዎች እንዲናገሩ ዕድል በመስጠት አስጀመሩት፡፡
ከሰፈራችን ሰዎች በአንደበተ ርዕቱነቱ የሚታወቀው ጋሼ ልሳነወርቅ የመጀመሪያውን የመናገር ዕድል አገኘ። ጋሼ ልሳነወርቅ ጉሮሮውን ለንግግር ከሞረደ በኋላ እንዲህ አለ «ኃላፊነት ከሕግ ወይም ከተፈጥሮ የሚሰጥ ከእንቁ የበለጠ ክብርን በውስጡ የያዘ ነው፡፡ ከእንቁ የበለጠ ክብርን ከሰዎች በአደራ የተቀበለ ተሿሚ ደግሞ የተሰጠው ኃላፊነት ከእንቁ የበለጠ መሆኑን ተገንዝቦ ከእንቁ አስር እጅ በበለጠ ሊጠብቀው ይገባል፡፡
ካልሆነ ግን የኃላፊነት ክብር የሚገባቸው ተሿሚዎች እስኪመጡ ድረስ ሕዝብ ማመጹን ይቀጥላል፡፡ አገርም ከልማት ይልቅ በጥፋት ንፍር ውሃ ትበላለች፡፡ ሕዝቦቿም ድህነት በተባለ ደዌ እየተለበለቡ እንዲኖሩ ይፈረድባቸዋል፡፡ ስለሆነም ተሿሚዎች ሕዝብ የሚሰጣችሁን ኃላፊነቶች እንደእንቁ ተንከባከቧቸው። በትክክለኛው የኃላፊነት ሐዲድም በማሽከርከር የተሰጣችሁን ኃላፊነት እንቁ መሆኑን ኃላፊነትን ለሰጡ ሰዎች ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ »
ጋሼ ልሳነ-ወርቅ ንግግሩን ቀጥሎ፤ ‹‹በገበያ ማዕከሉ የሚገኙ ከሀበሻ ልብስ መሸጫ ሱቆች ውጪ ያሉ ሰዎች የእኛ ሱቅ እስካልተዘረፈ ድረስ ምን ያገባናል በሚል ዝም ብለው ማየታቸው ያንገበግባል፡፡ ጤፍ ሊጭን የመጣ መኪና ጤፍ ሲያጣ ገብስ ሊጭን እንደሚችል ስለምን ማሰብ ተሳናችሁ? የእኔ ሱቅ እስካልተዘረፈ ድረስ ምን አገባኝ ብሎ ማየቱ የገበያ ማዕከሉን ህልውና ስጋት ላይ ይጥላል፡፡ ስለሆነም ዛሬ ላይ ተረባርበን ሌቦችን እና ገዳዮችን አደብ ማስያዝ ካልቻልን እንዲሁም ለጥበቃ ኃላፊነት የሰጠነውን ሰው በጋራ ለምን ማለት ካልቻልን ነገ ላይ የምንጎዳው ሁላችንም ነን›› ብሎ ወደ መቀጫው ተመለሰ፡፡
በሁለተኛነት ዕድል ያገኘችው ደግሞ ወይዘሮ ጉዲት ነበረች፡፡ የሰፈራችን ሰዎች ጉዲት ያሏት የምትናገረው እና የምትሠራው ሥራ አስገራሚ እና ጥበብ የተሞላበት ስለሆነ ነው፡፡ ወይዘሮ ጉዲት ንግግሯን ቀጠለችና እኔ የአቶ አሻግሬን ሥራ ስመለከት ግማሹ በሽሮ ግማሹን በዶሮ ሆኖብኛል፡፡ ግማሹን እየጠበቀ ግማሹ ሲሠረቅ እና ሲቃጠል ቁጭ ብሎ የሚያይ ጥበቃ ግማሹ በዶሮ ግማሹን በሽሮ ከማለት ውጪ ምንስ ሊባል ይችላል? ስትል ተሰብሳቢውን ጠየቀች፡፡
የሽሮ እና የዶሮ ጣዕም የሚታወቅ ነው፡፡ ሁለቱን ምግቦች በአንድ መሶብ አቅርበን እንግዳዎቻችንን ተጋበዙልን ማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ምግቦች የሚቀርቡበት እና የምንመገብበት አውድ ለየቅል ነው፡፡ የተለያየን ነገር በተለያየ ጊዜ ሲቀርብልን እንጂ የተለያየን ነገር በአንድ ጊዜ መጠቀም ተጠቃሚውን ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ተጠቃሚውም ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር ነው ፡፡
የሚገርመው ስንት እና ስንት ሸቀጦችን ከያዘው የገበያ ማዕከል ውስጥ የሐበሸ ልብስ የሚሸጥበት ሱቅ እየተመረጠ መሰረቁ እና መቃጠሉ አይደለም፡፡ ለምን የሐበሻ ልብሶች ብቻ የሚሸጥባቸው ሱቆች እንዴት ይዘረፋሉ? ሱቆቹ ሲዘረፉ እና ሲቃጠሉ ለጥበቃ ኃላፊነት የሰወዱትን አቶ አሻግሬ የት ሄደህ ነው? ተብሎ ሲጠየቅ አቶ አሻግሬ ለምን ተጠየኩ? ብሎ የሚደነፋው ድንፋታ እና ጥያቄውን የጠየቀውን ሰው ለማሰር ወይም ለመግደል የሚያደርገው ያዙኝ ልቀቁኝ ባይነቱ ያበሳጨኛል ስትል ንግግሯን ቀጠለች፡፡
ጉዲት የግንባሯ ስር እንደሚወጋ በሬ ቀንድ ተገትሮ አቶ አሻግሬ ለምን የሐበሻ ልብሶች ብቻ ተለይተው የወሮበሎች ሲሳይ ሊሆኑ እንደቻሉ ሲጠየቅ የሚመልሰው መልስ ከተጠየቀው ጥያቄ ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ አፍ ሲናገር አፍንጫ ያሽሟጥጣል እንዲሉ የሐበሻ ልብስ በተሰረቀ ቁጥር አቶ አሻግሬ ዘራፊ ሲመጣ ድረሱልኝ የሚባልበትን እና የሰፈራችን መተዳደሪያ አዋጆች ሲታወጁ የሚለፍፍበትን ማይግራፎን ያነሳና ዘራፊዎችን ለማጥፋት እየሠራሁ ነው፡፡ ዛሬ ሦስት ሌቦችን ገደልኩ ፤ ሁለቱን ደግሞ ማረኩ ይለናል፡፡
ይሄ ዓይነት ተደጋጋሚ መልስ እሳት መጣብህ ቢለው ሳር ውስጥ ተደብቄአለሁ ዓይነት ነው፡፡ ችግር ተፈጠረ ሲባሉ ተፈጠረ ለተባለው ችግር ሁነኛ መሻሪያ መፍትሄ እንደመፈለግ ሳር ውስጥ ተደብቄያለሁ ዓይነት መልስ መመለስ ስለእውነት ተገቢ አይደለም።ገዳዮቻችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደርግ እንደሆነ እንጂ የገበያ ማዕከላችንን ህልውና አንድም ስንዝር ማሳደግ አይችልም አለች፡፡
ጉዲት ንግግሯን ቀጥላ ችግሩ በጊዜ መቀረፍ እንደሚገባው ለማሳየት ስለአንድ ንጉሥ ተረት ለተሰብሳቢው አወጋች ፡፡
ተረቱም እንዲህ ይላል፡-በድሮ ዘመን ከእኔ ዝርያ ውጭ ጎበዝ፣ ጀግና እና ሁሉን ማድረግ የሚችል የለም እያለ የሚታበይ አንድ ንጉሥ ነበር፡፡ ንጉሡ ከባለቤቱ አንድ ሴት ልጅ ብቻ ይወልዳል፡፡ የልጃቸው አንድ መሆን የሚያስጨንቃቸው ንጉሡ እና ንግሥቲቱ ልጃቸው አድጋ እስከሚድሯት እና እራሷን እስከምትተካ ያለውን ጊዜ በጉጉት ይጠብቁ ነበር፡፡
ከጠሩት ውሻ የቀጠሩት ቀን ቀድሞ ይደርሳል እንዲሉ ልጃቸውን ለመዳር ሲጠባበቁ የነበሩ ወላጆች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ቀን ደረሰላቸው፡፡ ልትዳር ስትጠበቅ የነበረችው ሙሽሪት የንጉሥ ልጅ አይደለች፤ በአገሪቱ የሚገኝ የተከበረ የንጉሥ ልጅም ተፈልጎ ተዳረች፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው! የሙሽሪት ጥጋብ «ሰማይን በእርግጫ!» ሆነ፡፡ ያገባቸውን ልጅ በሠርጋቸው ማግስት በጥፊ መታ ፈታችው ፡፡
እናት እና አባት የመጀመሪያ ባሏን ብትፈታም ልጅ እንድትወልድላቸው ከፍተኛ ጉጉት ስለነበራቸው ሁለተኛ ባል አጋቧት፡፡ ሙሽሪት አሁንም በሠርጓ በበነጋታው ባሏን ደብድባ ወደ ቤቷ መጣች። ለአምስት ጊዜም ባል አገባች፡፡ አምስቱንም ባሎች ከሠርጓ በበነጋታው እየጣለቻቸው መጣች፡፡ በዚህም የሙሽሪት እናት እና አባት ክፉኛ አዝነው እሳት እንደገባ ጅማት እርር ድብን ብለው ተቀመጡ፡፡ ራሷን ተክታ ዘራችንን ታበዛልናለች ብለው ተስፋ የጣሉባት አንዲት ልጃቸው የቤተሰቦቿን ተስፋ የሰው ልጅ በማይደርስበት ጥቅጥቅ የጨለማ ዋሻ ውስጥ በመጨመር ተስፋቸውን ከንቱ አደረገችው፡፡
በዚህም እናት እና አባት ክፉኛ አዝነው እየኖሩ ሳለ ወሬውን የሰማ አንድ ገበሬ ልጅ «ልጃችሁን ስጡኝ?» ሲል ንጉሡን ጠየቀ፡፡ ንጉሡም ልጄን ለገበሬ ልጅ አልድርም አላሉም፡፡ ይልቁንም ልጃቸው ለሚስትነት የማትበቃ፣ ስንት የተከበሩ የነገሥታት ልጆችን እንኳን አላገባም ብላ ያስቸገረች እና ለሱ ለገበሬው ልትገዛለት እንደማትችል እንጂ ልጃቸው አግብታ ብትወልድ እንደሚደሰቱ ይንገሩታል፡፡ ገበሬውም እርስዎ ይፍቀዱልኝ እንጂ እርሷን ለማስተካከል የሚፈጀውን ማገዶ ለእኔ ተውት ሲል ንጉሡን ጠየቀ፡፡ ንጉሡም አንተ ቻል እና አስተካክላት እንጂ እኔማ ልጄ አግብታ ወልዳ ባያት ምንኛ ደስተኛ በሆንኩ ሲሉ ለገበሬው ልጅ ይነግሩታል፡፡
የገበሬው ልጅም ልጅዎትን ለማጨት ስመጣ በማደርገው ነገር ቅር እንዳይሰኙብኝ ፡፡ የማደርገው ነገር በሙሉ እርሷን ወደ መስመር ለማስገባት መሆኑን ይወቁልኝ ይላቸዋል፡፡ ንጉሡም ብቻ ልጄ አግብታ ልጅ ለመውለድ ትብቃልኝ እንጂ የፈለገውን ብታደርግ አልቀየምም ይሉታል፡፡
የገበሬው ልጅም የንጉሡን ልጅ ለማጭት ሲመጣ ጓደኞቹን በግ እያስጎተተ መጣ፡፡ የጋብቻው ውል ከተጻፈ በኋላም ባል ያመጣውን በግ ሊታረድ በቀረበ ጊዜ በግ እያሰቡ የመጡ ጓደኞቹን ያለምንም በቂ ምክንያት አንገታቸውን እቆርጣለሁ ብሎ ተገላገለ፡፡ የተናደደ በመምሰልም ሊታረድ የቀረበውን የበግ አንገት በጎራዴ ቀላው፡፡ የታጨችው ሙሽሪት ያጫትን ሙሽራ ኃይለኝነት በተመለከተች ጊዜ ደነገጠች፡፡
ሠርጋቸውም ደረሰ፡፡ የሠርጉ ዕለትም ሙሽሪት እያየች ሰዎችን በጎራዴ ካልቆረጥኩ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ይል ያዘ፡፡ ይሄን የተመለከተችው ሙሽሪትም በፍርሃት መግቢያ ቀዳደው ይጠፋታል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ለሙሽሪት እና ለሙሽራው ምግብ ይቀርብላቸዋል። ምግቡ በቀረበ ጊዜም ሙሽራው ጎራዴውን ከሰገቡ ወጣ፤ ገባ እያደረገ በጣም እየጮኸ ሙሽሪትን አጉርሽኝ! ሲል አዘዛት፡፡ በባሏ ኃይለኛነት በፍርሃት ቆፈን የተዘፈቀችው ሙሽሪትም ሰው ምን ይለኛል ሳትል ባሏን እስኪበቃው ድረስ እንደሕፃን ልጅ አጎረሰችው፡፡
በማግስቱ ሙሽሮቹ ለሠርጉ ለምላሽ ወደ ንጉሡ ቤት ተመለሱ፡፡ በተመለሱ ጊዜም ምግብ ይቀርብላቸዋል፡፡ ሙሽሪት ፍጹም ተረጋግታለች፡፡ እናት አባቷ ቤት ምግብ እንደቀረበላቸውም ሙሽራው ሙሽሪትን አጉርሽኝ ብሎ አዘዛት፡፡ ሙሽሪትም ከዚህ ቀደም ያገባቻቸውን ባሎቿን እንደማትደባደብ ሁሉ ዛሬ ላይ ግን ባሏ ያዘዛትን ትእዛዝ ትፈጸም ገባች፡፡ ይህን የተመለከቱ አባት ምን ቢሉ ጥሩ ነው! እባክህ ልጄን ያስተካከልካት እንዴት አድርገህ ነው? እኔንም እኮ ሚስቴ በጣም እያስቸገረችኝ ነው፡፡ ዘዴውን አሳውቀኝ? ይሉታል፡፡
የልጅ ባልም ንጉሡን እርጥብ እና ደረቅ የሆኑ ሁለት ጠማማ እንጨቶች እንዲያስመጡ ይነግራቸዋል፡፡ ንጉሡም የተባሉትን ሁለት ጠማማ እንጨቶች አመጡ። የልጅ ባልም ንጉሡ ያመጧቸውን ጠማማ እንጨቶች እሳት ውስጥ ጨመራቸው፡፡ ትንሽ አቆይቶም ከእሳት ውስጥ አወጣቸው፡፡ መጀመሪያ እርጥቡን ጠማማ እንጨት ለማቃናት ሞከረ፤ ተቃና፡፡ ቀጥሎም ደረቁን ሊያቃና ሞከረ፡፡ ደረቁ ግን ተሰበረ፡፡ በዚህ ጊዜ የልጅ ባል ምን ቢል ጥሩ ነው! እኔ ያገባዋት ልጅ ገና እርጥብ ልጅ ናት ወይም ለጋ ስለነበረች ተቃናች፡፡ የእርስዎ ግን ዕድሜአቸው የገፉ ወይም የደረቁ ስለሆኑ ለማቃናት ቢሞክሩ ይሰበራሉ፡፡ ሁሉም ነገር መስተካከል የሚችለው በለጋነቱ ነው ሲል መለሰላቸው፡፡
እናም አለች ጉዲት፤ ከዘራፊዎች እና ገዳዮች ጋር ተያይዞ የተፈጠው ግጭት እየተባባሰ ሳይመጣ ጉዳዩ በለጋነቱ ቢስተካከል መልካም ነው፡፡ ብላ ወደ መቀመጫዋ ስትመለስ ሁሉም ነጋዴዎች ድጋፋቸውን ለማሳየት ቆመው አጨበጨቡ፡፡
በሦስተኛነት ብሶቱን እንዲናገር ዕድል ያገኘው ደግሞ በቅጽል ስሙ ፈላስፋው እየተባለ የሚጠራው ጋሼ ሕይወቴ ነበር፡፡ ፈላስፋው የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም ሲል ከኪሱ የማትለየውን ትንሽዬ ማስታወሻው ላይ የጻፈውን እያነበበ ማብራራቱን ቀጠለ፡፡
ፈላስፋው እንዳለው ጨዋ የሆነ ሰው ተሹሞ ከፍ ከፍ ያለ እንደሆነ ትሁት ይሆናል፤ አይታበይም፡፡ ባለጌ ሰው ሲሾሞ ይታበያል፡፡ የሾሙትን ሰዎች በሁሉም ነገር ይንቃል፡፡ ይህ የአቶ አሻግሬ ሁነኛ ባህሪ ነው፡፡ የትህትና ፍሬዋ ፍቅር ነው፡፡ የትዕቢት ግን ፍሬዋ ጥል እና ውርድት ነው፡፡ ስለዚህ የትህትናን ፍሬ አብረን መመገብ እየቻልን ስለምን የትዕቢትን ፍሬ ለመብላት እንደዚህ ተቻኮልክ ሲል አቶ አሻግሬን ጠየቀ?
ሶቅራጥስ እንዳለው የሚያፈቅርህ ሰው ስታጠፋ እና ስትሳሳት ይመክርሃል፡፡ የሚጠላህ ግን ችላ ይልሃል፡፡ እንዲያውም በጥፋትህ እንድትገፋበት ያበረታታሃል፡፡ እኛ ይሄን ሁሉ ወቀሳ በግልጽ የነገርንህ ስለምወድህ ነው፡፡ ምክንያቱም ዘራፊዎች አሁን የገበያ ማዕከላችንን ህልውና እየተፈታተኑት ስለሆነ ነው፡፡ ዘራፊዎችን ለመፋለም አሁን ላይ ሁሉም ነገር በእጃችን ላይ ነው፡፡ ዕድሉን ከእጃችን ካመለጠን በኋላ መልሰን ለማግኘት ስለምንቸገር ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ እጅ ላይ ያለን ዕድል መጠቀም ይገባል የሚለውን ለተሰብሳቢዎቹ ለማብራራት በከፋ አካባቢ የሚዘወተረውን «የወፏ ምክር» የተሰኘውን ተረት እንድናገር ይፈቀድልኝ ሲል ጠየቀ እና ንግግሩን ቀጠለ።
አንድ ሰው በጫካ እየሄደ እያለ አንዲት ወፍ ያገኛል፡፡ ይይዛታል፡፡ ያለምንም ምክንያት ወፏ በመዳፉ ጨምቆ ሊገድላት ሲታገል ወፏ ከመሞቷ በፊት አንድ ወይም ሁለት ቃላት ትናገር ዘንድ የያዛትን ሰው ፈቃድ ጠየቀችው፡፡ ሰውየውም ፈቀደላት፡፡ ወፏም እንዲህ አለች «እባክህ አትግደለኝ፡፡ ሦስት ጠቃሚ ምክሮችን እሰጥሃለሁ፡፡ ሰውዬም ምክሮቹን ለመስማት ጓጉቶ መናገር እንድትጀምር ፈቀደላት፡፡
ወፏም እንዲህ አለች፤ የመጀመሪያው ምክር በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ፡፡ ሁለተኛው ምክር፤ ስለሆነው ነገር ሁሉ አትቆጭ፡፡» ካለችው በኋላ ዝም አለች። ሦስተኛውንም ምክር ትነግረው ዘንድ ሲጠይቃት «ሦስተኛው ምክር ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ካለቀከኝ አልነግርህም፡፡» አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰውዬው ሦስተኛውን ምክር ለመስማት በጣም ጓጉቶ ስለነበረ ወፏን ሲለቃት ከአንድ ዛፍ ላይ በርራ ወጥታ «ያልኩህ ምንድን ነበር? ታስታውሳለህ?» ብላ ጠየቀችው፡፡ እርሱም «በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ፡፡» አላት፡፡
«ሁለተኛውስ?»
«ስላለፈው ነገር ሁሉ አትቆጭ፡፡»
«አዎ፡፡ ነገር ግን የነገርኩህን ነገር አልተቀበልክም። ባትለቀኝ ኖሮ ከሆዴ ውስጥ ለልጅ ልጆችህ የሚሆን ወርቅ ታገኝ ነበር፡፡ ይኸው ነው፡፡» አለችው፡፡
ሰውዬው «ሦስተኛውስ ታዲያ?» አላት፡፡
እሷም «ሦስተኛው የሁለተኛው ምክር ድጋሚ ነው። ስላጣኸው ነገር አትቆጭ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ደህና ሁን፡፡ ምክሬንም ባለመቀበልህ በድህነት ትኖራለህ፡፡» አለችው ይባላል ብሎ ንግግሩን ጨርሶ ወደ መቀመጫው ሲመለስ ፈላስፋውም እንደ ዮዲት በጭብጨባ ታጅቦ ተቀመጠ፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም