እናቴ ደህና ዋይ ብሎ ተሰናበተኝ። ሶስት ሺህ አራት መቶ ብር አስራት ለቤተ ክርስቲያን በስሜ ስጡልኝ ፤እኔ ቸኩያለሁ ብሎ አባቱን ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ድረስ ሸኝቶት፤ እርሱ መኪናውን እያሽከረከረ ወደ መስሪያ ቤቱ፤ ቀጥሎም ተሽከርካሪውን መስሪያ ቤት ግቢ አቁሞ በታክሲ ተሳፍሮ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓዘ።
አየር መንገድ ከደረሰ በኋላም ታላቅ እህቱን በስልክ በረራ መጀመሩን ነግሯታል። ‹‹ሰፈራችን ደርሻለሁ ነይ ውጪ አውሮፕላኑ ቤታችንን እያለፈ ነው እይኝ›› እያለ ቀልዶ ተሰናብቷታል ይላሉ። መጋቢት አንድ ቀን 2011 ዓ.ም የተከሰከሰው አውሮፕላን ልጃቸውን የነጠቃቸው ወይዘሮ ምንትዋብ ምትኩ ። የስንታየሁ እናት ወይዘሮ ምንትዋብ ልጃቸው በሰላም እንደደረሰ ወድሞቹንና እህቱን ጠየቁ። ‹‹አልደወለም ቆየት ብሎ ይደውላል ኔት ወርክ አስቸግሮት ይሆናል›› አሏቸው።
ባለፈው ሲሄድም ቆየት ብሎ እንደደወለም አስታወሷቸው። ግን መረጋጋት አልቻሉም። እነርሱ ግን አደጋውን ሰምተው ነበር። ‹‹ሁልጊዜ ሲጓዝ እንደደረሰ ይደውልልኛል። አሁን ግን መድረሱን ሳይነግረኝ ዘገየብኝ። ሆዴ ሲረበሽ ነበር የዋልኩት። ቴሌቪዠን ከፈትኩ ወደ ኬንያ እየበረረ የነበረው አውሮፕላን ስለደረሰበት አደጋ በዜና ሲናገር ሰማሁ።
ደነገጥኩ ራሴን ስቼ ወደቅኩ። ከእዛ በኋላ የሆነውን አላስታውስም›› ሲሉ ሃዘን በተቀላቀለው አነጋገር የልጃቸውን መርዶ የሰሙበትን አጋጣሚ ነገሩኝ። ወይዘሮ ምንትዋብ ጥቁር ለብሰዋል፣ ነጠላ አጣፍተዋል፣ በለቅሶ ብዛት ድምጻቸው ሰሏል፣ በሀዘን ፊታቸው ጠቁሯል። ደህና ግባ ብለው የተሰናበቱት ልጃቸው ወጥቶ ሳይመለስ ቀርቶባቸዋል። ልጃቸውን ሞት ነጥቋቸዋል። በእነ ምንትዋብ ቤት ደጃፍ ድንኳን ተተክሏል። በእርሳቸው ደጃፍ ሀዘንተኛ እያስተናገደ ነው። ጎረቤቱም ቤተሰቡን እያጽናና፣ አስከሬን እየተጠባበቀ ይገኛል። የአስናቀ ግርማና የስንታየሁ ሻፊ ጓደኝነት የሚጀምረው በ1997 ዓ.ም ነው። አዳማ አጼ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ አንደኛ ዓመት ተማሪ እያሉ ነበር የተዋወቁት።
ስንታየሁ የከፍተኛ ማዕረግ ተማሪ እንደነበር አስናቀ ያስታውሳል። በአጭር ጊዜ ከፍተኛ እድገት ያስመዘገበ፣ ንቁ፣ ከሰው ጋር ተግባቢና ቁምነገረኛ እንደነበረ ይናገራል። የሁለቱ ጓደኛሞች ጉዞ በስራው አለምም ቀጠለ በ2000 ዓ.ም ሞኤንኮ አብረው ተቀጠሩ። ስንታየሁ በድርጅቱ ታሪክ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበ ከሲኒየር ቴክኒሽያንነት በአንዴ ቴክኒካል ስራ አስኪያጅ ሆነ። በድርጅቱ ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ሁለት ጊዜ አሸንፎ ጃፓን ድረስ ተጉዞ ተሸልሟል። ጃፓን ስልጠናም ወስዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቷል። በሙያው በአፍሪካ ባሉ የቶዮታ ኩባንያዎች መካከል በተደረገ ሙያዊ ውድድር አሸንፏል። በቶዮታ ኩባንያ ስር ባሉ ኩባንያዎች የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተዘዋውሮ አሰልጥኗል። ስንታየሁ ለአፍሪካውያን ባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ስልጠና ለመውሰድ ኬንያ ይጓዝ ነበር።
የሁለቱ ጓደኛሞች የ14 ዓመታት ጓደኝነትም ወደ ፊት አልቀጠለም። ቅዳሜ ዕለት በስልክ ተሰነባብተዋል። ጓደኛው እስካሁንም የጓደኛው ሀዘን ከውስጡ እንዳልወጣ ገልጾልኛል። ቢቢሲ አማርኛው እንደዘገበው፤ ዋና አብራሪው ያሬድ ጌታቸውና ሃሰን የሚተዋወቁት ከዓመታት በፊት ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ህንፃ ፀጉር ቤት ያሬድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የበራሪ ፅሁፍ ወረቀት ይዞ ሃሰን [ፓይለት ነህ] ብሎ ያሬድን በጠየቀበት አጋጣሚ ነበር። ያሬድ ኬንያ እንደተወለደ ነግሮት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ ያወሩት በስዋሂሊ እንደነበር ሃሰን ያስታውሳል። ሀሰን እንደሚለው ያሬድ ስፖርት የሚወድ አይነት ሰው የነበረ ሲሆን ለራግቢ ግን ልዩ ፍቅር ነበረው።
ያሬድና ሃሰን አዘውትረው ይገናኙ የነበረው ግእዝ የሚባል የፈረንሳይ ሬስቶራንት ራግቢ ስፖርት ለመመልከት ነው።መጀመሪያ አካባቢ ሀሰንም መኪና ስላልነበረው አብዛኛውን ጊዜ ያሬድ ያሽከረክር የነበረውን የአባቱን አሮጌ መኪና እየሾፈረ ብዙ ቦታዎች መሄዳቸውንም ሃሰን ያስታውሳል። ያሬድና ሃሰን ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት የነበረ ሲሆን በሎሜ ስካይ አየር መንገድ ስራ ስላገኘው ጓደኛቸው ነበር ያወሩት። ያሬድ የተወለደው ኬንያ ውስጥ ነው።
እናቱ ኬንያዊ ሲሆኑ አባቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የልጅነት ጊዜውን በኬንያ ያሳለፈ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ተከታትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቬሽን ትምህርት ቤትን ተቀላቅሏል። ጓደኛው የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪ የእነሱ ጓደኛ ያሬድ እንደሆነ ሲነግረው ለማመን በጣም እንደከበደውና ሊሆን አይችልም የሚል ስሜት እንደተሰማው ይናገራል። “ለማመን የሚከብድ ነገር ነው።መተኛት አልቻልኩም እስካሁን ድንጋጤ ውስጥ ነኝ” ብሏል ሃሰን።
ቻይና እሁድ ዕለት በቢሾፍቱ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይነት አውሮፕላኖቿ እንዳይበሩ ማገዷን ሲኤንኤን ዘግቧል።ቦይንግ 737 ማክስ 8 የተባለው ይህ አውሮፕላን በስድስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መከስከሱ ታውቋል። ከስድስት ወራት በፊት የኢንዶኖዥያ አውሮፕላን ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰበት ይታወሳል።እሁድ ዕለት ጧት ላይ የተከሰከሰው የኢትዮጵያው አውሮፕላን አብራሪ በረራውን ከጀመረ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አውሮፕላኑ ችግር እንዳጋጠመው ሪፖርት አድርጎ እንደነበርም ተገልጿል።
ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ 2:38 ደቂቃ ላይ 149 መንገደኞችና 8 የበረራ ሰራተኞችን ይዞ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ላይ የደረሰውን አደጋ የሚመረምር ኮሚቴ እንዳዋቀረ በትዊተር ገፁ አስታውቋል። አየር መንገዱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የኢትዮጵያ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመተባበር የአደጋውን መንስኤ ይመረምራሉ ተብሏል።የሟቾች ማንነት ከታወቀ በኋላ አስከሬናቸው ለቤተሰቦቻቸው እንደሚሰጥ አየር መንገዱ አስታውቋል።በአደጋው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦችም መርዶው ተነግሯቸዋል።በአውሮፕላን አደጋው በአጠቃላይ የ157 ሰዎች ህይወት አልፏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2011
በዘላለም ግዛው