እንባ ዝም ብሎ የሚወጣ ጎርፍ አይደለም። ስሱነትን፣ ማዘንን፣ መራራትን፤ ባጠቃላይ ሰበነክ መሆንን ሁሉ ይጠይቃል፡፡ የችግሩንም ታላቅነት መገንዘብና ከውስጥ ማስቀመጥን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ውጤቱ እንድናመራ ያደርገናል፡፡ በተለይም የምንፈልገውን ለማግኘት መስመሩ እርሱ ነው፡፡ ሰዎችን ለመውደድና ለእነርሱም ለመድረስ ቁልፉ ይህ እንጂ ሌላ አይደለም። ምክንያቱም በማልቀስ ውስጥ እጅ መዘርጋት ይመጣል፤ በማልቀስ ውስጥ ስሱነት ይከሰታል፤ መጥፎ ነገር ከመተግበር መቆጠብም እንደዛው።
እንባችን መጥፎ ለተደረገባቸው ንጹሐንም መልስም ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ አባሽነቱን አንድም በምድር አለያም በሰማይ ያረጋግጥልናል፡፡ የደም ዋጋችንን ይመልሳልም፡፡ በተለይም አሁን ላለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ይህ የእንባ ጎርፍ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከውስጥ የሚመነጭ ተግባርን ይዞልን ብቅ ይላልና፡፡ ከውስጥ የመነጨ ሥራ ውጤቱ ዘላለማዊና የሚታይ ነው፡፡ ልዩነትና አድልኦ የለበትም፡፡ በዚህም ብሔሬ፣ ሃይማኖቴ … ሳይል ለሁሉም በሁሉም ይደርስበ(ለ)ታል፡፡ ድጋፉም ሆነ ምላሹ በሕብረት የሚከወን በመሆኑ ለውጡ የሚታይም ይሆናል፡፡ ለምንወደው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ሁሉ የምናደርገው ነገር ይበዛልም፡፡
እንባ መዋጮ ሲሆን ደግሞ ኃይል ይኖረውና ብዙዎችን የመታደግ ተግባርን እንድናከናውን ያግዘናል። ምክንያቱም ተግባሩ ፍቅርና ርህራሄን ያነገበ ነው። የተባለን ለማድረግ ፍላጎት የታከለበት ነው፡፡ ሙሉ እምነት፣ ሙሉ እውነትን የያዘ ተግባር፡፡ ስለዚህም ዛሬ ሰው በሰውነቱ መከበር የቀረበትን ሁኔታ ለማጥፋት ይህ ሁነት የግድ ያስፈልገናል፡፡ እንባ ለማዋጣት ዝግጁ የሆኑ ሰዎችን መሰብሰብ ይጠበቅብናል፡፡
የእኔ ለምንለው ብቻ ማንባትን የምናስቀርበት ጊዜ አሁን መሆን አለበት፡፡ ጩኸታችንም እንዲሁ ከልዩነት ሊወጣ ይገባዋል፡፡ በየአቅጣጫው የሚፈሰው የንጹሃን እንባ የሁላችንም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በእኩል ደረጃ እንባ ማዋጣት ይገባናል እንጂ ለአንዱ አልቃሽ፣ ለአንዱ ቀዳሽ መሆን አይገባንም፡፡
የሰው ዋጋ ሰው መሆን ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ የእንባ ዋጋውም እንዲሁ ሰው ለሆነ ሁሉ መንሰፍሰፍ ማለት ነው፡፡ የተጎዳው ሁሉ ሲለቀስለት መልሱም በእኩል ይመጣል፡፡ ላልተደረሰለት ጭምር ይደረሳል። ላልታየው ይታያል፡፡ ለዚህም የምናነሳው በመፅሐፍ ቅዱስ የተቀመጠችውን ራሔልን ነው፡፡ እርሷ ዝም ብላ እንባዋን አላፈሰሰችም፡፡ የደረሰባት ሰቆቃና ፈተና ወደ አምላኳ ቀና ብላ እንድታነባ አድርጓታል፡፡ ለመንታ ልጆቿ እንባዋን እንደጎርፍ አውርዳለች፡፡ ምክንያቱም መውለጃዋ በደረሰ ጊዜ ጡብ እንድትረግጥ ታዘዘች። ከዚያ ጡቡን ስጥረግጥ ከማኅጸኗ ያሉ ጽንሶቿ ወደቁ። ደንግጣ ብትቆም ግብጻዊው አሰሪ በጅራፍ ገርፎ ልጆቿን እድትረግጥ አድርጓታል፡፡
‹‹ልጆች እኮ ናቸው›› ብትለውም ‹‹የሰው ደም ጡቡን ያጠነክረዋል አብረሽ ርገጫቸው›› ነበር ያላት። ያን ጊዜ ራሄል ዝም አላለችም፡፡ ልጆቿን እየረገጠች ከዓይኖቿ እንባዋን እያፈሰሰች ‹‹የሰማይ አምላክ የለምን?›› ነበር ያለችው፡፡ የእስራኤልን ግፍ የሚያይ ብላ እንባዋን ወደ ሰማይ ረጨችው፡፡ ያን ጊዜም ከሰማይ ድምጽ ተሰምቷል፤ ጩኸቷም ዝም አልተባለም፡፡ ከልብ የወረደን እንባ የሚያብሰው አምላክም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የፈርኦን ሥራ ዋጋውን አግኝቷል፡፡ ራሔል ብቻ ሳትሆን እስራኤላዊያኑ እንዲድኑም ሆነዋል፡፡ ስለዚህም እንባ ግለሰብን ብቻ ሳይሆን አለምን ጭምር የሚያድን ነውና አሁን ያለብንን ችግር አንድም ከአምላካችን አለያም ደግሞ ከሰው አግኝተን የውጤቱ ተቋዳሽ እንድንሆን እንባ እናዋጣ፡፡
አሁን እንደ ፈርኦን ሕጻናቱን ከጡብ ጋር አብሮ የሚያስረግጥ፤ ሰው ሆኖ ለሰው ፈጽሞ የማይራራ ጨካኝ ሰው በምድራችን ላይ ተፈጥሯል፡፡ ለእንስሳቱ ጭምር ምህረት የማይሰጥ ሰይጣናዊ አስተሳሰብን ያነገበ ሰውም እየታየ ነው፡፡ በአፉ ሌላ በልቡ ሌላ የሆነ ሰው ዓለምን ሞልቷታል፡፡ ይህ ደግሞ ንጹሃኑ በማያውቁት ነገር አንገታቸው ሲቀላ፣ ሀብት ንብረታቸው ሲቃጠል ብሎም ቤተሰባቸው ፊታቸው ላይ ሲታረድ ማንም ምንም እንዳይላቸው ሆነዋል፡፡ ተፈናቅለው በማያውቁት ቦታ ላይ ሲሰፍሩ የሚደርስላቸው እንዳይበዛ አድርገዋል፡፡
አሁን ላለንበት ችግር ያበቃን ማዘናችን ከአንጀታችን አለመሆኑ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከሞትኩ አይነት አኗኗራችን ብዙ ነገራችንን ወስዶታል፡፡ የእንባን ዋጋ እንዳንረዳውና ወደ ተግባሩ እንዳንገባም ጋርዶናል። ምክንያቱም ብናውቀው ኖሮ እንባ መተንፈሻ ነው፤ መልስ ማግኛና ለሌሎች መኖርን መማሪያ ነው፡፡ እንባ ከክፉ መንፈሳችን ጭምር መሸሺያ ነው፡፡ እንባ እንጀራም ነው፡፡ ምክንያቱም ከሀብታሞች እጅ ላይ የምንፈልገውን ፈልቅቀን እንወስድበታለን፡፡ ራሱም ቢሆን ባላሰበው መልኩ እጅ ዘርጊ የሚሆንበት ነው። እናም ይህንን ሁሉ ለማግኘት የእንባ ማዋጣቱ ሥራ ያስፈልገናል፡፡ ለሁሉም አልቃሽ መሆን ይገባናል፡፡
በእርግጥ ለሁሉም እኩል ማልቀስ ብዙ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ልምምድን ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ነጋሪ አያሻንም፡፡ ታሪካችን በብዙ መልኩ ያስረዳናልና፡፡ ከሰው ጋር መብላትና መጠጣቱ፣ ማስተዛዘኑና ያለንን መካፈሉ፤ የእንግዳ መቀበል ሥርዓታችን ብዙ ብዙ የምንዘረዝራቸው ጉዳዮች ታሪካችንም ልምዳችንም ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን አፋዊ ሆነው በብዙ ነገር ተቀማናቸው፡፡ ያንን መልሶ ማምጣት እንዳንችልም ሆንን፡፡ እናም እንባ እናዋጣ፤ ልባዊነትን እንጋራ፤ ለሁሉም እንስሳ ማለታችንም ለዚህ ነው፡፡
‹‹ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ፣ ሴት ልጆች እና ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውሃ፣ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!›› ተብሎ በታላቁ መጽሐፍ እንደተነገረው፤ አሁን ላይ ብዙዎቻችን መሬት ላይ በግልጽ ይህንን የምንልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ምክንያቱም ብዙዎች በብሔር መርዝ ታመዋል፤ አታላዮች ሆነዋል፡፡ ዓይኖቻቸው እንባ ቢያፈሱም እንደ ራሔል ሳይሆን እንደ ቄሳር ሆኗል፡፡ የሰው ሕይወት የዝንብ ነፍስ እየመሰላቸው በፈለጋቸው መልኩ ይቀጥፉታል፡፡ ስለሆነም እነዚህን የሚያረጋጋና መንፈሳቸውን የሚገራ እንባ ያስፈልገናል፡፡
ሀይል የምናዋጣበትና አቁሙን የምናጎለብትበት እንባ ያሻናል፡፡ በንጹሃኑ ላይ የተቃጣው ዱላም ቢሆን መልስ ያስፈልገዋልና እንባችን ማበስ አለብን። በእርግጥ ለእንባ ዋጋ እንተምንለት ቢባል ላናገኝለት እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና ከልባችን ያለንን ለሁሉም እናጋራ፡፡ የእንባ መዋጮዋችንም ለታመሙት ፈውስ፤ ለታረዙት ልብስ፤ ለተጠሙት መጠጥ ለተራቡት መብል ይሆን ዘንድም እናድርገው፡፡ ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2014 ዓ.ም