ለውጤታማ የአንድ ብዙዎች ይደልዎ!
የአንድ ብዙነት ርዕሰ ጉዳይ የፍልስፍና መልክ ያለው ይምሰል እንጂ ይዘቱ በጥልቀት ሲፈተሸ ግን ሞጋች የሆነ መልዕክት እንዳዘለ መረዳት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው አንድ ሰው አንድ ነው፡፡ እንደማናችንም አንድ ነፍስ፣ አንድ አካልና የግሉ የሆነ ስሜት ያለው፡፡ መልኩም እንደማናችንም የተገኘበትን የደም ሐረግ ወርሶ ሰው የተባለ ሰው እንጂ በልዩ ፍጡርነት የሚታይ ላይሆን ይችላል፡፡
በትምህርቱ ዝግጅትም ቢሆን እንደማናችንም ከሀ ሁ እስከ ፐ ፑ ከፊደል ገበታ ጋር ታግሎ እያደገ በመሄድ በምርምር ብቃቱ የልሂቅነት አንቱታን ሊያተርፍ ይችል እንደሆን እንጂ፤ የሰውነቱ አንድነት ግን እንዳለ ነው፡፡ የሥልጣን እርከኑ ከፍታ ወይንም የፖለቲካ አቋሙ የገነነ ቢመስልም፤ በአገር መዝገብ ውስጥ ስሙ የሚሰፍረው እንደ አንድ ዜጋ እየተቆጠረ እንጂ በሁለትና በሦስትነት አምሳል ላይጠቀስ ይችላል፡፡
በአካል ሲታዩ እንደ አንድ ሰው ቢቆጠሩም በአስተሳሰባቸው፣ በአርአያነታቸው፣ በተሰጧቸው፣ በእውቀት ልህቀት አቅማቸው፣ በጥረታቸው፣ በብርታትና ትጋታቸው ፍሬያቸው ተንዠርግጎ ለአገራቸው አለኝታ በመሆን እንደ ዐምድ የሚቆጠሩ የአንድ ብዙ ዜጎች ግን እላይ ከጠቀስናቸው መስፈርቶች በእጅጉ ያፈነገጡ ናቸው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት አቅመ ግዙፍና የስኬት አድማስ አካላይ ዜጎች እንደማናችንም የአንድ ሰው መለያ (ማሊያ) በመልበሳቸው ብቻ እከሌ ተብለው እየተጠሩ ከተርታው ሰው ጋር “ተራ ሆነው” ሊጠቀሱ የሚገባ አይመስለንም፡፡
የሙዚቃው ንጉሥ ነፍሰ ኄር ጥላሁን ገሠሠ በአንድ የዜማ ሥራው ውስጥ፡-
የቤት የአደባባይ የማን ማንነቱ፣
ሰው ቁምነገሩ እንጂ ገላጭ መስታወቱ፣
በወል ስም መጠራት ወይ አንተ ወይ አንቱ፣
አይሆንም መለኪያ ለሰው ሰውነቱ፡፡
ስንት አየሁ ስንት ሰው ያሉ የነበሩ፤
ለመልካም ሥራ እንጂ ለራስ የማይኖሩ፡፡
በማለት አዚሞ ያለፈው ምናልባትም ከላይ በተጠቀሰው መሰል ሸጋ አመለካከት ተማርኮ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አንድ ሆነው የብዙዎችን ሚና ተወጥተው የብዙኃንን ታሪክ የለወጡ፤ አንድ ነፍስ ኖሯቸው የሚሊዮኖችን ሩሕ የታደጉ በርካታ ተጠቃሽ አርአያ ሰብ ግለሰቦችን አገራችንም ሆነች ግዙፏ ዓለማችን በሺህ ምንተ ሺህ ቁጥር በማፍራት “ለበረከት ይሁኗችሁ” በማለት ባርከው ሰጥተውናል፡፡ የመልካም ተግባራት ከዋክብት ለመሆን የበቁበትን ተጋድሏቸውን በተመለከተም ከመነሻ እስከ መድረሻቸው ድረስ የተጓዙበት የውጣ ውረድ ጎዳናዎች ምን እንደሚመስልም ሲተረክ ደጋግመን አድምጠናል፤ በጽሑፍ የሰፈረውን ዜና መዋዕሎቻቸውንም በአድናቆት ሳናነብ አልቀረንም፡፡
አንድ አገራዊ አብነት በመጥቀስ በምሳሌ እናጠናክረው፡፡ ኃይሌ ገ/ሥላሴ አንድ ሰው ነው፡፡ አንዲት ነፍስ ብቻ ያለው አንድ ዜጋ፡፡ በጥረቱና በላቡ ብርታት ግን አገሩንና ሕዝቡን በስፖርት አደባባይ ከፍ አድርጎ የኩራታችን ምክንያት በመሆን ለኢትዮጵያና ለራሱም ጭምር አንቱታን አትርፎ ተጨብጭቦለታል፡፡ አንዱ ኃይሌ በስፖርቱ መስክ ብቻም ሳይሆን በኢንቨስትመንትና በሰብዓዊ አገልግሎቶችም ጭምር የበርካታ ወገኖቹን ሕይወት በመታደግና ኑሯቸውን በመለወጥ ስሙን በሕዝቡና በአገሩ ልቦች ውስጥ አጥልቆ ለመትከል ችሏል፡፡ ኃይሌ አንድ ሆኖ የሁለትም፣ የሦስትም፣ የአራትም . . . ሰብዕናዎችን ያህል የበጎነት ፍሬዎችን በማዝመር በአንድ እሱነቱ ውስጥ በርካታና በአብሪ ከዋክብት የሚመሰሉ ብዙ ኃይሌዎችን አባዝቶልናል፡፡ ኃይሌ ምሥጋናችንን ተቀበል!
የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ፣ መራሔ መንግሥትና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ በአገራቸው ተንሰራፍቶ የነበረውን የአፓርታይድ ሥርዓት ታግለው ያሸነፉት የአንድ ብዙ ሰብዕና ባለቤት በመሆን፤ “ከዘረኝነት የፀዳች፣ የተባበረችና ዴሞክራቲክ ደቡብ አፍሪካን የምንፈጥረው እንደ አንድ ግለሰብ ራሳችንን ቆጥረን ሳይሆን የአንድ ብዙ በመሆን በምርጫ ድምጻችን ብዙኃኑን አሸናፊ ማድረግ ስንችል ብቻ ነው” በሚለው ዲሞክራሲያዊ ፍልስፍናቸው የሕዝባቸውን ልብ ስለማረኩ ነው፡፡
ከአገራችንና ከአፍሪካ ወጣ ስንል የምናስታውሰውም ስሙ እጅግም በብዙዎች ዘንድ የማይታወቅ የአንድ ብዙ ተጠቃሽ ባለ ታሪክ አስደማሚ ተግባር ይሆናል፡፡ ይህ ሰው ጆን ዋላክ የተባለ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ሚ/ር ዋላክ አንድ ሰው ብቻ ሳይሆን ሺህ ዋላኮችን ጠቅልሎ የተሸከመ ግዙፍ ሰብዕና ያለው ባለራእይ ነው፡፡
ግለ ታሪኩ እንዲህ ይነበባል፡፡ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በአሜሪካዊቷ ሜይን ክፍለ ግዛት ኦትስፊልድ በተባለ ቦታ በወቅቱ የጦር ሰለባ ከሆኑ አገራት የተመረጡ ሕጻናት የሚስተናገዱበትን አንድ የክረምት ማሳለፊያ የእረፍት ካምፕ ያቋቁማል፡፡ ስያሜውም “ዓለም አቀፍ የሰላም ካምፕ” የሚል ነበር፡፡
በየክረምቱ ንቁና በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ሕጻናትን ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከባልካን፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከሕንድና ከፓኪስታን አገራት እየጋበዘ ወደዚህ የሰላም ማዕከል መጥተው የክረምት እረፍታቸውን እንዲያሳልፉ ያደርጋል፡፡ በዚህ የእረፍትና የጉብኝት ጊዜያትም “ጠላቶቻችን” ብለው ከሚጠሯቸው ምዕራባውያን ሕጻናት ጋር አብረው እንዲጫወቱ፣ እንዲወያዩ ያደርጋል፡፡ አብረው ይጫወታሉ፤ አብረውም ውለው ያድራሉ፡፡
ፕሮግራሙ ተጠናቆ ሕጻናቱ ወደየአገራቸው ሲመለሱ ግን እርስ በእርሳቸው፤ “ጠላቴ የምለው ወገን ለካንስ እንደኔው መልክ፣ ስሜትና ነፍስ አለው።እንደኔው ለካንስ ለሰላም መዘመር ይችላል፣ እንደኔው ይደሰታል፣ ይፈራል፣ ያፈቅራል፣ የሰውን ልጅ ያከብራል ወዘተ.” የሚል ስሜት ተጋብቶባቸው ወደየቦታቸው ይመለሳሉ። በአገራቸውም የሰላም አምባሳደር በመሆን ቁርሾ አርግዘው ለመበቃቀል የሚፈላለጉትንና በርዕዮተ ዓለም የተራራቁትን አገራት፣ ሕዝቦችና መንግሥታት የማቀራረብ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ይህ ውጤታማ ተልዕኮ ለነገው ሕጻናት የወደፊቷን ብሩህ ዓለም ለመፍጠር ከተደረጉት የዓለማችን ስኬታማ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ተብሎ ሽልማት ተዥጎድጉዶለታል፤ መንግሥታትም አድናቆታቸውን ሳይሰስቱ ገልጸውለታል፡፡
ገጣሚው እንደሚከተለው ቢቃትት እውነት አለው፡፡ እኛም የዚህ ገጣሚ ስሜት ቢጋባብን የግላችንን የሰውነት አቋም ለመፈተሸ የሚበጅ ይመስለናል፡፡
በተራሮቼ ልክ እጁን የዘረጋ፣
እስኪ አንድ ሰው ስጡኝ፤ እኔን የተጠጋ፡፡
አድማሴ የማይርቀው ሜዳዬ ያልታከተው፣
አንድ ሰው ጠቁሙኝ የአንድ ብዙ የምለው፤
ርሃቤ የሚርበው፤ ስሜቴ የሚጥመው፡፡
በዓላማው ጽኑ አእምሮውም ግዙፍ፣
ዘመን ተሻጋሪ ዕቅድ ሥራው ህሉፍ፣
አንድ ሰው ጠቁሙኝ ራዕዩ ሚያከንፍ፡፡
የትብታቡ ጥልፍልፍነት ውል ባሳጣው ዘመናችን ውስጥ ከራሳቸው የኑሮ ቀለበት አፈንግጠው ለብዙኃን የሚኖሩ የአንድ ብዙ ማረፊያዎችን ፈጣሪ ባያድለን ኖሮ ኮምጣጣው አኗኗራችን ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለንም፡፡
ያለውጤት ራሳቸውን የሚያባዙ አንዶች፤
የአንድ ብዙነትን ክብር ሳይሆን “የተሰነጣጠረ ማንነትን” መለያቸው ያደረጉ በርካታ ዜጎችና ሹመኞችን አስመልክተን ከራሳችን ተሞክሮዎች አገራዊ መልካችንን በሂሳዊ መስታወት መፈተሹ ለደዌያችን ፈውስ ሊሆን ስለሚችል ጨከን ብለን ብንዳብሰው ሳይጠቅመን አይቀርም፡፡ ዜጎችን ብቻም ሳይሆን ራሱን መንግሥትን ጭምር ክፉኛ የተጣባው ይህን መሰሉ በሽታ ሥር እየሰደደ ከሄደ የት አድርሶ ምን ላይ እንደሚያሳርፈን ለመተንበይ አዳጋች ስለሚሆን ከወዲሁ እንዲታረም ደፈር ብለን ጆሮ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
ወይ በፍሬያቸው አለያም በጥረታቸው ምሳሌ መሆን የተሳናቸው አንዳንድ ዜጎች ለፖለቲካው አሸርጋጅ ስለሆኑ ብቻ በማይመጥናቸው ሁለንተናዊ አገራዊ ወጭት ውስጥ እጃቸውን እየነከሩ ለጉርሻ ሲሽቀዳደሙ ማስተዋል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብርቃችንም ድንቃችንም አይደለም። በተለይም በፖለቲካው ሜዳ ውስጥ ደጋግሞ ሲተገበር ማስተዋሉ “ቃር ቃር አሰኝቶ” ስለወጣልን እንደ ባህል ቆጥረን በአሜንታ ያጸደነቅነውም ይመስላል፡፡
መንግሥት ዙሪያውን ከበው እንዲያሟሙቁለት የሚፈልግ እስከሚመስል ድረስ “ጥቂት በኩራን ብቻ” አንዱ ማንነታቸው ተሰነጣጥሮ እዚህም እዚያም እንደ ጨው ሲነሰነሱ እያስተዋልን መገረማችን አልቀረም። ሲበዛም ልክ እንደ ዛሬው ብዕራችን ግንፍል ብሎ ያመረቀዘውን እባጭ ለመዳበስ ይጨክናል፡፡ ለመሆኑ “አንድ ሰው ስንት ነው?” ብለን ለመጠየቅም እንገደዳለን፡፡
በአንድ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ተመድቦ “ካብ አይገባ ድንጋይ” የሆነን አንድ ግለሰብ በድክመቱና በንዝህላልነቱ ምክንያት ከነበረበት ኃላፊነት ሲነሳ ራሱን እንዲፈትሽና እንዲያሻሽል ገለል አድርጎ የጥሞና እድል ከመስጠት ይልቅ ወደ ሌላ የገዘፈ ኃላፊነት ሲመደብ እያየን እንደ ማሽላው “እያረርን ስቀናል።” ድርጊቱ ተደጋግሞ ስለሚተገበርም “ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” እንዲሉ ልክ እንደሆነ በመቁጠር በአሜንታ እስከ መቀበል ደርሰናል፡፡
አንድ የመንግሥት ሹመኛ የሚመራውን ተቋም በውጤታማነትና በመሰጠት እንዲያገለግል ከመቆጣጠርና ከመከታተል ይልቅ አቅሙና ጫንቃው ሊሸከማቸው የማይችላቸውን በአሥርና በሃያ ቦርዶች፣ ብሔራዊ ኮሚቴዎች፣ ተጨማሪ ሹመቶችና ከፍታዎች ላይ ማንጠልጠሉ እንዲያገለግል ብቻም ሳይሆን [የጤንነቱ ጉዳይ እንኳን ቢዘነጋ] ለአወዳደቁ ያለማሰብ ጭምር ይመስለናል፡፡ “ዝንጀሮ አለ በቂ ምክንያት አድቬንቸር ወዳድነቱ ግድ ብሎት በዛፎች ላይ እየተንጠለጠለ ሽቅብ በወጣ ቁጥር መቀመጫውን ማጋለጡን ይዘነጋል” የሚለው የአፍሪካውያን ብሂል እዚህ ቦታ ቢጠቀስ ቦታው ይመስለናል፡፡ ይህን መሰሉ ክፉ “አመል” በእኛ አገር ብቻ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች አገራት የሚስተዋል ተሞክሮ ስለመሆኑም እርግጠኛ መሆን ያዳግታል፡፡
ለአገራዊ ችግሮቻችን መፍትሔ አመንጭነት የሚጥሩ ውሱን፤ ያውም የአቅማቸው አጥንት የተልፈሰፈሰ ሰዎች፣ ለሽልማትና ለሹመት እነዚያው ሰዎች፣ ለምክክርና ለውይይት እነዚያው ሰዎች፣ ለቦርድ አባልነትና ለተሞክሮ ቀማሪነት እነዚያው “ብፁዓን ሰዎች”፣ ለሽምግልናና ለእርቅ ጉዳዮች እነዚያው “አንቱዎች”፣ ለድግስና ለምርቃት ፕሮግራሞች እነዚያው “ቅዱሳን ሰዎች” ወዘተ. መሆናቸውን በብዙ ማስረጃዎች ማሳየት ይቻላል፡፡ “አንድ ሰው ምን ያህል ነው?” አሰኝቶ እንድንጠይቅ ግድ ያለንም ይህን መሰሉ ሥር የሰደደ የ“አገራዊ መታወቂያችን” ጉዳይ ነው፡፡ “ሰሚ የሚኖር ከሆነ?” የሚል ስጋታችን ሳይዘነጋ፡፡
የሚዲያ ተቋሞቻችንም ሳይቀሩ አንድን ግለሰብ ብቻ በእንግድነት “አየራቸው ላይ እያንሳፈፉና ገጻቸው ላይ እያሽሞነሞኑ” እንደሚውሉ እያስተዋልን ነው። ግለሰቡ ባልሰለጠነበትና ሙያው ባልሆነ መስክ ልክ እንደ ዋና በሳል ባለሙያ “authority” ለኢኮኖሚ ትንታኔ፣ ለፖለቲካዊ ሂሶች፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ እንደ ተሟጋች፣ ለመዋቅራዊ አደረጃጀት እንደ ጠቢብ፣ ለኪነ ጥበባት ሃያሲነት፣ ለስፖርት ኮሜንታርነት ወዘተ. ደጋግሞ ሲጋበዙ መመልከትን ተላምደነዋል፡፡ ለመሆኑ አገሪቱ የብቁ ዜጎቿንና ሥልጡኖቿን ዝርዝር (Roster) መዝግባ እንደሙያቸው በሰለጠኑበት መስክ ለማሰማራት ዐይኗን የጋረዳት ምን ይሉት በሽታ ይሆን? የፖለቲካው የዓይን ማዝ ወይንስ የምንግዴነትና ከእኛ በላይ ለአሳር የሚባል “የትምክህት ሞራ?” እግዜሩ ይወቀው፡፡
መንበረ በየነ የተባለች የቀድሞው የክብር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ባልደረባ ድምጻዊት ከበርካታ ዓመታት በፊት እንዲህ ብላ አዚማ ነበር፡-
”ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ፣
በዋለበት ሜዳ አይቀርም ማፍራቱ፡፡
ጥበብ የገበየ እጅግ ተመራምሮ፣
ያለቦታው ሲሆን ይሆናል ደንቆሮ፡፡
ጠላት ያሸበረ በጦር በጎራዴ፣
ሊሆን የማይችል ነው ሲራራ ነጋዴ፡፡‘
“ልብ ያለው ልብ ያድርግ የቦርከና ወንዝ ማለት ይሄ ነው!” አለ ይባላል በክፉ ቀን ሚስቱን የሸጠ አንድ ባላገር፤ ከገዢዎቿ ጋር እያባበለ ሲሸኛት፡፡ ምናልባት አምልጠሽ ከመጣሽ ይህ የቦርከና ወንዝ ምልክት ይሁንሽ ማለቱ ነበር፡፡ ብዕራችንም እንደዚያው፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014