የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ከዓመት በላይ በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት “በአንድም በሌላ መልኩ ተሳታፊ የሆኑ አገራትን ጥናት በማድረግ ይፋ ለማድረግ ይፈቀድልኝ” ሲል ለሴኔቱ ከሰሞኑ አቅርቧል። “ጅብ ከማያውቁት አገር ሄዶ …. አለ” እንደሚባለው አሜሪካ ባይሳካላትም ሥጋው አልቆ በአጥንቱ የቆመውን እና መቃብር አፋፍ ላይ የሚገኝውን አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ዳግም በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለማውጣት ያልገባችበት ጉድጓድ፣ ያልፈነቀለችው ድንጋይ እንደሌለ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አልፎ ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው።
“ላም ባልዋለበት ….” እንዲሉ አበው፣ ጁንታው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት በከፈተበት ወቅት አሜሪካ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጋም ነበር። በዚህ ሂደት ደግሞ በሰብዓዊ ድጋፍም ሆነ በሌሎች የልማት ተግባራት ምክንያቶች በአገር ውስጥ የነበሩ የራሷ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት አቅም ሆነውት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ታዲያ በዚህ መልኩ ከግብረአበሮቿ ጋር የጦርነቱ አቀጣጣይ እና ዋና ተዋናይ እርሷ ራሷ ሆና እያለ ሌሎች አገራትን ጥላሸት ለመቀባት የምታደርገው ሩጫ ግርም ድንቅ ከማለትም አልፎ ራሷንም ትዝብት ላይ የሚጥል ነው።
ምክንያቱም ከዓመት በላይ በዘለቀው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ግጭት አሜሪካ ሠራዊቷን በግንባር አሰልፋ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ፊት ለፊት ባትፋለምም፤ የጁንታውን የበላይነት ለማስፈን ያልገባችበት ቀዳዳ የለምና ነው። ኢትዮጵያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቷ ሽብርተኛ ብላ የፈረጀችውን ይሄን ቡድን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ የተጋችው አሜሪካ ምንም እንኳን ሽብርተኝነትን አጥብቃ እንደምትዋጋ ብትናገርም፤ ሐቁ ግን ጥቅሟን ከሚያስከብርላት ከየትኛውም ሽብርተኛ ቡድን ጎን ተሰለፋ እንደምትሠራ ለሕወሓት ባላት ጭፍን ፍቅር ግልጽ ብሎ የታየበት ነበር።
ጁንታው የሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊትን ከጀርባው በመውጋት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ግልጽ ጦርነት ካወጀ ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ የሽብር ቡድኑ ዋስ ጠበቃ ሆና ስትሠራ ቆይታለች። በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ “መብረቃዊ ጥቃት ወስደናል” ሲል በራሱ ላይ የመሰከረውን አሸባሪ ቡድን የፈጸመውን የአገር ክህደት ወንጀል አንድ ቀን እንኳን ተሳስቷት አላወገዘችም። ይልቁንም መንግሥት ተገዶ በክልሉ በገባው ሕግ የማስከበር ዘመቻ “ሰብዓዊ መብት ተጣሰ፣ ሰብዓዊ እርዳታ አልደረሰም” በሚል የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብን በዓለም አደባባይ ስትከስና ስትወቅስ ከረመች አንጂ።
ከሕግ ማስከበር እርምጃው መጠናቀቅ በኋላም መንግሥት በክልሉ ሲደረግ የነበረውን የሰብዓዊ እርዳታ 70 በመቶ ሲሸፍን፤ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በክልሉ በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ያደረገውን ጥረት አሜሪካ እንደ ኃጢያት ነበር የቆጠረችው። ይልቁንም በክልሉ “የሰብዓዊ ርዳታ አልደረሰም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተስፋፍቷል፣ መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ይውጣ” እያለች መንግሥት ክልሉን አረጋግቶ እንዳያስተዳድር የጎን ውጋት ሆና መጎትጎቱን ተያያዘችው እንጂ። ከዚህም አልፎ “ጅቡቲ ያለውን ጦሬን በኢትዮጵያ ላይ አዘምታለሁ” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ ጭምር ስታደርስ ነበር።
ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለፌዴራል መንግሥት የቀረበን የተናጠል ተኩስ አቁም ጥያቄ ተቀብሎ መንግሥት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ሰጥቶ ክልሉን ለቆ ከወጣም በኋላ እንኳን ይህንን የመንግሥት ውሳኔ አሜሪካ አንዴ እንኳን ተሳስታ አልደገፈችም፤ ይልቁንም ህጸጽ ስትፈልግ ነው የተስተዋለው።
ምዕራባውያንና አሜሪካ በሰብዓዊ ርዳታ ስም በተለይ የዩ.ኤስ.ኤይድ አርማ ያለበት በቫይታሚን የበለጸገና ኃይል ሰጭ ምግብ ለሽብር ቡድኑ አባላት በማቅረብ ቡድኑ አጎራባች ክልሎችን በወረራ እንዲይዝ በአንድም በሌላ መንገድ ሲደግፉ ነበር። ጁንታው ሕጻናትን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ በጦርነቱ አሰልፎ የእሳት ራት ሲያደርግም በዓለም የጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት አሜሪካውያንና ምዕራባውያን አይተው እንዳላዩ በዝምታ ነው ያለፉት። ይልቁንም የሽብር ቡድኑ ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳለው አድርገው የዜና አውታሮቻቸው ሲያስተጋቡም ተደምጧል።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ለመፈትፈትም በማስተባበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተደጋጋሚ ስብሰባ እንዲጠራ በማድረግ ምክር ቤቱ ከተቋቋመበት ሕግና ተልዕኮ ውጭ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአንድ ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ከ10 ጊዜ በላይ ተቀምጦ ተወያይቷል። የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጠራው ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና የሚያሳድር ውሳኔ እንዲተላለፍ ያልሸረበችው ሴራም አልነበረም።
በሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ዘመቻና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ረገድም የመገናኛ ብዙኃኗን የሐሰት ዘገባዎች እንዲሁም ሽብር የመንዛት አቅጣጫ የሆነው ተደጋጋሚ የዜጎቿን ከኢትዮጵያ ውጡ ውትወታ በኩል ከፍ ያለ ሥራ ሠርታለች፡፡ የሽብር ቡድኑ አዲስ አበባን በአጭር ጊዜ ውስጥ ይይዛል ብላ ጮቤ ስትረግጥም ነበር። መንግሥትም አገር ለቆ እንዲጠፋ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ሲሠራ እንደነበርም የመንግሥት አካላት ጭምር ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቁጭ ብዬ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ከማይ አንገቴ ይቀላ” በሚል ወደ ጦር ሜዳ ወርደው በግንባር ሠራዊቱን እየመሩ በድል ላይ ድል ተጎናጽፈዋል። የኢትዮጵያ ጥምር ጦር በተባበረ ክንድ የውስጥና የውጭ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን በአጭር ጊዜ አንገት አስደፍቷል። ይህኔ የጁንታው አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ በድሮን ተቀጠቀጥን። ድረሱልን “ኡኡታውን” አቀለጠው። በዚህ ጊዜ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ዱባይ እና ቱርክ አቅንቶ “ድሮን የምትሸጡት እናንተ ናችሁና እባካችሁ ድሮን ለኢትዮጵያ አትሽጡ” እያለ ሲማጸን እንደነበር ዓለም አቀፉ የዜና ወኪል ሮይተርስ ዘግቧል።
እነቱርክን እባካችሁ ለኢትዮጵያ ድሮን አትሽጡ እያለች ስትማጸን የነበረችው አሜሪካ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕወሓትን በአየር ኃይል አይደብድብ እስከማለት ደርሳለች። (እዚህ ጋ ልናስተውለው የሚገባ እነዚህ አገራት ለኢትዮጵያ ድሮን ሸጠው ቢሆን እንኳ፤ ዛሬ አሜሪካ ለዩክሬን በገፍ ከምትልከው የቦንብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ አንጻር እንዴት ተመልክታው ይሆን?) ነገር ግን የኢትዮጵያ የወገን ጦር ከአየር ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ በወሰደው እርምጃ ሕወሓት ከፍተኛ ኪሳራና የሞራል ስብራት ደርሶበት ሬሳውን በየመንገዱ እያንጠባጠበ በወረራ ከገባበት የአማራና የአፋር ክልል ተጠራርጎ ሊወጣ ችሏል።
መንግሥትም ለትግራይ ሕዝብ ዳግም የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ ላለመግባት ወሰነ። አሜሪካ ይህንን የመንግሥት ውሳኔ “ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይበል የሚያስብል ነው” በሚል አሞካሸች።
“የአብዬን እከክ ወደማን ለከክ” እንዲሉ አበው አሜሪካ የሰሜኑ ጦርነት ዋና ተዋናይና የሽብር ቡድኑ ቀንደኛ ደጋፊ እሷ ራሷ ሆና እያለ ሌሎች አገሮችን ለመወንጀል የምታደርገው ሩጫ አሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷና ተቀባይነቷን የሚያሳጣት ነው። የጦርነቱ ዋና ተዋናይ እሷ ራሷ ሆና እያለ “መሐረቤን ያያችሁ” የሚል የልጆች ጨዋታ እየተጫወተች ትገኛለች።
ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በውስጥና በውጭ ተናበው የከፈቱትን ጦርነት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመው በመመከት በድል ላይ ድል ማስመዝገብ ችለዋል። በ”በቃ” ዘመቻ የምዕራባውያንንና የአሜሪካ የተንሻፈፈ አመለካከት በዓለም አደባባይ ማሳየት ተችሏል። የአፍሪካ ኅብረት 35ኛው የመሪዎች ስብሰባም በኢትዮጵያ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም በፓን አፍሪካኒዝም መሥራቿ ኢትዮጵያ ያለምንም እንከን በሰላም ተጠናቋል። ነገም ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እንደብረት አጠንክረው ከተጓዙ በድል ላይ ድል የማይጎናጸፉበት፣ ወደ ብልጽግና ማማው የማይወጡበት ምንም ምክንያት የለም!
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን የካቲት 9/2014