በታሪክ እንደ አገር፣ ሕዝብና መንግሥት እንዲህ ተፈትነን አናውቅም። የአገራችን ህልውና በዚህ ልክ በቋፍ ላይ ሆኖም አላየንም። ከውስጥ በአሸባሪው ሕወሓትና በቡችሎቹ እነ ሸኔ፤ ከውጭ ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ፤ ምዕራባውያንና አሜሪካ፤ በዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት፤ በግብረሰናይ ድርጅትነት እና በብዙኃን መገናኛ ሽፋን በሚንቀሳቀሱ ተቋማት በትርነት የተናበበና የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ አሉታዊ ዘመቻ ህልውናችን ጥያቄ ላይ ወድቆ ነበር።
ከሦስት ወራት በፊት እነዚሁ ሟርተኞች ኢትዮጵያ የእነ ሶሪያን የእርስ በርስ ጦርነት የሚያስንቅ ቀውስ ውስጥ ልትዘፈቅ ነው፤ አገሪቱ ሊያከትምላት ነው፤ አሸባሪው ሕወሓት አዲስ አበባን ሊቆጣጠር ነው፤ ወዘተረፈ የሚሉ 72 ሟርቶችን በ48 ሰዓት እስከማሟረት ደርሰው ነበር። ሆኖም፣ መጀመሪያ ታላቁ የ1ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት ጥሪ ከሞላ ጎደል በስኬት መጠናቀቁ፤ በመቀጠል የአፍሪካ ኅብረት 35ኛው ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሔዱ ሟርቱን ሁሉ ከንቱ አድርጎት ኢትዮጵያን ዳግም በክብር ከፍ አድርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ የዳያስፖራ ጥሪ ምላሽ ያለ አንዳች ኮሽታ ተግባራዊ መሆን፤ ለ35ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጥርጊያ መንገድ ያቀና ነበር ማለት ይቻላል። አሜሪካና ምዕራባውያን ዜጎቻቸው አዲስ አበባን በተገኘው በረራ በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ሌት ተቀን በሚወተውቱበትና በሚያስጨንቁበት ክፉ ቀን የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ከመላው ዓለም ወደ አዲስ አበባ መጉረፋቸው የእነ አሜሪካን፣ የምዕራባውያንና የሚዲያዎቻቸውን ቅሌት ገሀድ ያወጣ ነበር። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ካስመዘገቡት አኩሪ ገድል ባሻገር ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ ወደ ኢኮኖሚው ማስገባታቸው ምጣኔ ሀብቱን ከኮቪድና ከጦርነት ሀንጎቨር እንዲያገግም አግዞታል።
በዚህ ላይ 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ እነ አሜሪካንና ተቋሞቻቸውን ሌላ የሀፍረት ከል አከናንቧቸዋል። የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ በፈተናችን ወቅት ከጎናችን ለነበሩ ወዳጅ የአፍሪካ አገራት ፣ ሩሲያና ቻይና ኢትዮጵያን ደግፈው መቆማቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበረ የሚያረጋግጥ በትክክለኛው ጊዜና ቦታ የተገኘ ሁነት ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመሪዎች ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር፤ በጅምርና በውጥን የቀረውን ነፃነት ማለትም የፖለቲካ ወይም ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት ለመቋጨት አልያም ሙሉኡ ለማድረግ ሦስት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል። ምክንያቱም፣ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ነፃ ከወጣች ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ቀንበር እየማቀቀች ትገኛለች። ዛሬም የኢኮኖሚ፣ የትርክትና የፖለቲካ ጥገኛ ነች። ነፃነቷ ሙሉኡ አይደለም። ዛሬም ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቿ እርዳታ፣ ብድር፣ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት፣ የሚዲያና የባህል ተጽዕኖ ነፃ አልወጣችም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመክፈቻ ንግግራቸው ምርትንና ምርታማነትን በማሳደግ፤ ፓን አፍሪካዊ ሚዲያ በማቋቋም እና በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል በመሆን ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነፃ በመውጣት በጅምርና በውጥን የቀረውን ነፃነት እንቋጨው፣ ሙሉኡ እናድርገውና አፍሪካን ለተሟላ ነፃነት እናብቃት ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ ባሳለፍነው ዓመት አፍሪካውያን ወገኖቻችን ከጎናችን ባይሆኑ ኖሮ ህልውናችን አደጋ ውስጥ ይገባ ነበር በማለት አፍሪካዊ አንድነትና ወንድማማችነት የሚጫወተውን የማይተካ ሚና አሳይተዋል። አፍሪካውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን ስለቆማችሁ እናመሠግናለን ብለዋል። ያለፈው ዓመት በኮቪድ 19 እና በጦርነቱ የተነሳ ለአፍሪካ በተለይ ለኢትዮጵያ ፈታኝ ወቅት ነበር። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር ለህልውናችንም ትልቅ ፈተና ነበር። በአንጻሩ ችግሩን ለመሻገር የተደረጉ ጥረቶች ግን አመርቂ ነበሩ ብለዋል።
በተለይ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ በአፍሪካ ደረጃ የኮቪድ 19 ክትባት እንዲመረት በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ኢትዮጵያ ደግሞ ከወረርሽኙ ባሻገር ተገዳ በገባችበት ውስጣዊ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከፍተኛ ፈተና ተጋርጦባት ቆይታለች። በዚህም ሰላምን ለማስከበር በተደረገው ጥረት የሰላም ጠንቅ የሆኑ ውስጣዊ ኃይሎችን ከድርጊታቸው መግታት ተችሏል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስከተልም ኢትዮጵያ የገጠማት ፈተና በዚህ ብቻ ያበቃ አልነበረም። በተለይ ከሕግ ማስከበር ሥራችን ጋር ተያይዞ አጋጣሚውን የተጠቀሙ የውጭ ኃይሎችም ህልውናችንን አደጋ ላይ ጥለውት ነበር። በዚህ ሂደትም የውጭ ሚዲያዎች የነበራቸው አፍራሽ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው፤ አፍሪካ የራሷን ትርክት የምትቀርጽበትና ድምጿን የምታሰማበት ፓን አፍሪካዊ ሚዲያ ያስፈልጋታል ብለዋል። ለዚህ ርእይ ተግባራዊነት አገራት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል፣ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የየአገራቱ መሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አድርገዋል። ይህን ጥያቄ ቀደም ሲል የሊቢያው ጋዳፊ፣ የዚምባቡዌው ሙጋቢ፣ የደቡብ አፍሪካው ራማፎዛ፣ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫኬር እና ሌሎችም በየአጋጣሚው ሲያስተጋቡት የነበር ጥያቄ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተቋማዊና አኅጉራዊ አድርገው አንስተውታል። የአገራት መሪዎችም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አበክረው ምላሽ መስጠት ጀምረዋል።
ድርቅና የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም የደን ጭፍጨፋ ለአፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው ያነሱት ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ይህንን ለመቋቋም በርካታ ችግኝ ተከላን ጨምሮ የአፈርና ውሃ ተግባራትን ስታከናውን መቆየቷን፤ ከዚህ አንጻር ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለይ የአረንጓዴ አሻራን ተግባራዊ ማድረጓን፤ ለዚህም በአራት ዓመት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ በሦስት ዓመት ብቻ 18 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል እቅዷን ማሳካት መቻሏን፤ በቀጣዩ ዓመት የያዘችውን ሰባት ቢሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድ ስታሳካ ደግሞ አጠቃላይ የተከለቻቸውን ችግኞች ብዛት 25 ቢሊዮን በማድረስ ከፍተኛ ስኬት ታስመዘግባለች ብለዋል።
የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ በመስኖ ላይ ትኩረት በማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት 20 ሚሊዮን ኩንታል ተጨማሪ የምግብ ምርት ማምረት ችላለች። ኢትዮጵያ አፍሪካ በ2063 የያዘችውን እቅድ ለማሳካት እየሠራች ነው ብለዋል። በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አፍሪካ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት የተሸጋገረችበት ከመሆኑ ባሻገር በአህጉሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን የመሪ ክፍተት ለመሙላት ኢትዮጵያ ተነሳሽነቱና ዝግጁነቱ እንዳላት ያሳየችበት መድረክ ነበር ማለት ይቻላል።
በዚሁ ጉባኤ ትላልቅ አህጉራዊ አጀንዳዎች ተነስተዋል። አፍሪካ በተለይ ከሰላምና ጸጥታ አንጻር የሚያጋጥሟትን ችግሮች የሚፈታ የአፍሪካ ኃይል እንደሚያስፈልጋት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት እና የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ፍሊክስ ሺሲኪዲ አሳስበዋል። አያይዘውም ኅብረቱ ካጋጠሙት ፈተናዎች አንዱ የሰላምና የፀጥታ ስጋት ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በተለይ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የነበረው ውዝግብ በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ኅብረቱ እነዚህ አገራት ወደግጭት ሳያመሩ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት አድርጓል። ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ መንቀሳቀሱን አውስተዋል። ሽብርተኝነት በአፍሪካ አንዱ የሰላምና ፀጥታ ስጋት እንደነበር ፕሬዚዳንቱ ሺሲኪዲ ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ፤ አፍሪካውያን ከየትኛውም አገር ጋር የሚያደርጉት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ መስተጋብር የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። አፍሪካ በጋራ ተጠቃሚነት ጥቅሞቿን በፍትሐዊነት ማስከበር እንጂ የሌሎች መጠቀሚያ መሣሪያ መሆን የለባትም ሲሉ አስገንዝበዋል።
ከሩሲያም፣ ከቻይናም፣ ከጃፓንም ሆነ ከየትኛውም የሌላ አህጉር ጋር በሚኖራት የኢንቨስትመንትና የልማት ሥራዎች የጋራ ተጠቃሚነትን ብቻ መሠረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ዘርፈው ለመሄድ የሚያስቡ አገራት አሁን ላይ ተቀባይነት የላቸውም። ይልቁንም በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመረኮዘ ግንኙነት ብቻ ነው አዋጭ የሚሆነው። ለዚህም አፍሪካውያን የራሳቸውን ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮች ዙሪያ አተኩረው መሥራት ይገባቸዋል።
አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ሕዝባቸውን በበቂ ሁኔታ መጥቀም የሚችል ዕምቅ አቅም አላቸው። በተለይ የአህጉሪቷ 60 በመቶው መሬት ለግብርና የሚሆንና የሚታረስ መሬት መሆኑ አህጉሩ ጥቅም ላይ ያልዋለ ትልቅ እምቅ አቅም እንዳለው ያሳያል። በተጨማሪም እንደ ወርቅ ፕላቲኒየምና የተለያዩ ውድ ማዕድናት በየአካባቢው እንደሚገኙ ገልጸዋል። ይህንን ሀብት አውጥቶ ለመጠቀምም ጥረት ማድረግ ይገባል። በዚህ የልማት እሳቤና ጥረት አጋር ሆነው የሚመጡ አካላት ግን ለብቻ ተጠቃሚነትን ሳይሆን የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው ብለዋል የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት።
የአህጉራችን መጻኢ ዕድል ያለው በእጃችን ላይ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ይህን ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም አካታች፣ ግልጽና በፍትሃዊነት ላይ የተመሠረተ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል።
በፍትሃዊነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንትም ሆነ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጠቀሜታው ለአፍሪካውያን ነው። የአህጉሪቷን ተፈጥሮ ሀብት በአዋጭ መልኩ ማውጣትና መጠቀም ከተቻለ ኅብረተሰብን ከአስከፊ ድህነት መታደግ እንደሚቻል የወቅቱ የኅብረቱ ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል አስታውቀዋል። ለዚህም የአፍሪካ አገራት ቁርጠኛ አቋም መያዝ አለባቸው። በሊቀመንበርነት ዘመኔ የአህጉሪቷን ጥቅም ለማስከበርና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የብዝኀነት ዲፕሎማሲ ለማጎልበት እሠራለሁ ብለዋል።
በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመት ሙሳ ፋኪ፤ አፍሪካውያን አህጉራችንን ከተለያዩ ጥቃቶች ለመጠበቅ የማንንም አካል እገዛ መጠበቅ አይኖርብንም። ይልቁንም በእራሳችን መንገድ አፍሪካውያን የውስጥ አቅማችንን ተጠቅመን እራሳችንንና አህጉራችንን ከተለያዩ ጥቃቶች እንዲሁም ከውጭ ጣልቃ ገብነት መከላከል የምንችልበትን መንገድ መከተል አለብን ብለዋል። የራሳችንን አህጉር ለመጠበቅም ስንነሳ ከውጭ ሳይሆን የውስጥ አቅማችንን መጠቀም እንደሚገባን እያሰብን መሆን አለበት። ያለን ኃይል በአግባቡ ከተደራጀና ከተመራ አህጉራችንን ከዘርፈ ብዙ የውጭ ጫናዎችና ጥቃቶች ለመጠበቅ በቂ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በአፍሪካ ጉዳዮችና በተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ ያለው የተለያዩ አገራት ፍላጎት እያደገ መጥቷል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህ የአገራት ፍላጎት የውስጥ ሰላማችንን ይበልጥ እንዳያሳጣን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል። በተለይ በሰሀራ አገራትና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚታየውን የውጭ ጣልቃ ገብነትና የሽብር ጥቃት መበራከት አሳሳቢ ነው። በማሊና በተለያዩ አገራት የውጭ ጣልቃ ገብነት ተስተውሏል። ይህን በአፍሪካውያን አገራት ላይ የተጋረጠ ጥቃት ለመከላከል የአህጉራችንን የውስጥ አቅም መጠቀም ይገባናል ሲሉ ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፓን አፍሪካኒዝም ይለምልም !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014