አንዳንዶች ጦርነትን ከኢኮኖሚ ጋር አነጻጽረው ሲገልጹ የኢኮኖሚ ቀውስ ከጦርነት ያልተናነሰ ጦርነት ነው ሲሉ ይደመጣሉ ። ለዚህም ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ የኢኮኖሚ ቀውስ እያዳከመ የሚሄድ፣ከግለሰብ እስከ አገር የሚደርስ ጉዳት የሚያደርስና ከጉዳቱ ለማገገምም ጊዜያቶች ይወስዳል በማለት ነው። የኢኮኖሚ ጫና አንዱ መገለጫ የኑሮ ውድነት መሆኑ ይታወቃል።አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የተከፈተባት ጦርነት የፀጥታ መደፍረስ፣የዓለም ስጋት የሆነው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝና በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ድርቅ መከሰቱ በአጠቃላይ አገርን ውጥረት ውስጥ ከታቷል።
የችግሩ መብዛቱ የኢኮኖሚ ግሽበቱ እንዲባባስ ምክንያት ቢሆንም መሥረታዊ በሆነው ፍጆታ ላይ የሚስተዋለው የዋጋ መዋዠቅ ሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን ተረጋግተው በእቅድ እንዳይመሩ ፈተና ሆኖባቸዋል። የኑሮ ውድነቱ ልጓም የለውም በሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሷል።አሁን አሁንማ በሰአታት ልዩነት ያለው እስኪመስል ነው በአንድ የእቃ ዋጋ ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚስተዋለው።
ጭማሪውም አስደንጋጭ ነው። የእርስዎን እርዳታ ፈልጎ እጁን ለዘረጋ ሰው ሳንቲም አይታሰብም። አምስትና አስር ብርስ ምን ሊረባው። ልመናውም ተቀይሮ ምሳ ግዛልኝ፣ግዥልኝ ሆኗል። ዛሬ ተቋማት ለሰራተኛው ጥቅም ብለው በሚደጉሙት ካፌ(ምግብ ቤት) ውስጥ በአነስተኛ ዋጋ ምግብ ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው።ዋጋው ጨምሮ ተጠቃሚውን በመጠንና በጥራት የሚያረካ ነገር አለመገኘቱ ደግሞ ነገሩን የከፋ ያደርገዋል።
ከጎዳና እስከ መንደር ድረስ ‹‹አፈር ቅጠሉ ነጋዴ ሆኗል›› በሚባልበት በዚህ ዘመን፤እንደቀደመው በውስን የገበያ ቦታ ሳንገደብ ንግዱ ቤታችን ደጃፍ ላይ ደርሶ የዋጋ ውድድር አለመታየቱ እንዲህ ያለው የንግድ ሁኔታ በአገራችን የመጀመሪያው ሳይሆን ይቀራል? ሁሉም እንደሚረዳው ንግዱ ሲሰፋ ሸማቹም በዋጋ፣በጥራትና በአቅርቦት አማራጮችን አግኝቶ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል ነበር። በቀደመውም ሸማችና ገዥ ኧረ እርግጡን በል፣ቀንስ፣መርቅ ተባብሎ ነበር የሚገበያየው። በተግባር እየታየ ያለው ግን ይህ ሳይሆን ሁሉም ተመሳሳይ ቋንቋ ያላቸው ይመስል ዋጋ ጨመረ ነው ምላሻቸው።
‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› የሚለው አባባል የንግድ አካሄዱ ብትፈልግ ግዛ፣ባትፈልግ ተወው በሚለው አይነት ተቀይሯል። የእለት ፍጆታ ደግሞ ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ ሁከት ያስነሳል።ተገልጋዩም ጣቱን ወደ መንግሥት ይቀስራል። ያማርራል። መንግሥትም ዋጋ ለማርገብ አማራጭ ይሆናል ያላቸውን ሁሉ እርምጃ ከመውሰድ አልቦዘነም። መሠረታዊ ፍጆታ የሚያቀርቡ ሸማቾች እንዲቋቋሙ ዕድሉን ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ህዝቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት አድርጓል።
ረጅም እድሜ ያስቆጠሩት እነዚህ መሰረታዊ ፍጆታ አቅራቢ ሸማቾች ሸማቹን በአክብሮት ከማገልገል ጀምሮ በአቅርቦት ማርካት አልቻሉም። ማህበራቱ በገንዘብ፣ በአደረጃጀትና በአመራር ጠንካራ አለመሆናቸው ለክፍተቱ እንደአንድ መንስኤ ይነሳል። በሌላው ዓለም እንደሚሰማው መሠረታዊ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የኑሮ ውድነትን የሚያስከትል የዋጋ ንረት ሲከሰት ማስተንፈሻ የሚሆኑት እነዚህ ማህበራት ናቸው።ትልቅ አቅምና ጉልበት አላቸው።በኢትዮጵያ ግን ማህበራቱ ሸማቹን ተጠቃሚ ከማድረጋቸው በላይ ጎልቶ የሚወጣው ክፍተታቸው ነው ለምን? በቸልታ መታለፍ ያለበት ጉዳይ መሆን የለበትም።
በሸማቾች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ዋጋን ለማርገብ በመንግሥት የተወሰደው እርምጃ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው የጎዳና ላይ ንግድ (የሰንበር ገበያ ) ነው። የህዝብ ፍሰቱ ወይንም የነዋሪው ብዛት ግምት ውስጥ ገብቶ በተመረጡ አካባቢዎች የተጀመረው የጎዳና ላይ ንግድ ጅምሩ በዋጋም በአቅርቦትም ብዙዎችን ያስደሰተ ነበር። ውሎ ሲያድር ግን እንደጅምሩ መሆኑ ቀርቶ ቅሬታን እያስከተለ ነው። በላተኛውን ማዕከል ማድረጉ ቀርቶ አትራፊ ነጋዴውን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ከጅምሩ ለሀሜት ተጋልጧል።
‹‹የወጡን እፍታ›› እንደሚባለው ገበያው ሲዘረጋ ቀድሞ የሚሰለፈው በዛ ያለ ኪሎ ወይንም በጅምላ የሚገዛው ነው። አንድ ሸማች በአቅሙ ሳይሆን በሻጮቹ ፍላጎት ነው እንዲገዛ የሚገደደው።አንድ ሰው ሽንኩርት ከአምስት ኪሎ በታች አይሸጥለትም። አትክልትና ፍራፍሬም እንዲሁ።ፍራፍሬ በልመና እንኳን ከሁለት ኪሎ በታች አይቻልም።እርሱም ቢሆን የበሰለና ያልበሰለ በዋጋ ይለያያል።አንድ ኪሎ ፈላጊ ቆሞ ይውላል እንጂ አያገኝም።እዛው በአንድ ስፍራም በተመሳሳይ አገልግሎት ላይ የአምስት ብር የዋጋ ልዩነት ያለው ሲሆን፣በዕቃው ላይ ግን የሚታይ ልዩነት አያስተውሉም።ለምን ሆነ? ብለው ቢጠይቁ እንኳን መልስ አያገኙም።
ግብይቱም ቢሆን ግፊያና ሽሚያ የበዛበት በመሆኑም ይመስላል የዋጋ ልዩነቱን የፈጠረው።የጎዳና ላይ ንግዱ ምንም እንኳን ከመደበኛው ገበያ በዋጋ የተሻለ ቢሆንም ወደ መደበኛው የተጠጋ የገበያ ይዘት እየተስተዋለበት በመሆኑ ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንደሚባለው ከዓላማው እንዳያፈነግጥ ከወዲሁ መታረም ይኖርበታል።የዚህ ገበያ ዓላማ ሸማቹን በዋጋና በጥራት ተጠቃሚ ማድረግና እንደአቅሙም እንዲገበያይ ከማድረግ በተጨማሪ የሥራ ዕድልንም በመፍጠር የሥራ አጥነት ችግርን መቅረፍ ነው።እንደተባለው በንግዱ ላይ ያሉት ዓላማውን ታሳቢ ባደረገ የሚሰሩ ናቸው።ይህንንም መለስ ብሎ ማየት ይጠበቃል።
ገበያውን ያረጋጋሉ። የህብረተሰቡንም የኑሮ ጫና ይቀንሳሉ ተብለው በመንግሥት የሚወሰዱት እርምጃዎች በክትትልና ቁጥጥር የሚፈለገው ውጤት ላይ እንዲደርሱ ማድረግ ካልተቻለ መንግሥትን መልሶ እጁን አመድ አፋሽ ያደርገዋል ። ከወቀሳ አይድንም።መደበኛ ነጋዴዎችስ ቢሆኑ ዋጋ እንደፈለጉ ማን ፈቀደላቸው። አገሪቱ የምትከተለውን የንግድ ሥርአት አክብረው ሸማቹን ማገልገል ነው ያለባቸው።
ለመሆኑ መንግሥት የመደበኛውን የንግድ ሥርአት ማሻሻል ለምን አልቻለም? መፍትሄ ብሎ የሚወስዳቸው እርምጃዎችስ ለምን ወደኋላ ተመልሰው የቅሬታ ምንጭ ይሆናሉ? እዚህ ላይ አገሪቱ ያቋቋመቻቸው ቁጥራቸው ወደ 50 የሚጠጉ ዩኒቨርሲቲዎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን በማፍራትም ሆነ በየተቋሞቻቸው የማህበረሰብ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረገ የምርምር፣ጥናትና ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት አላቸው። የኢኮኖሚክስ ማህበርም ተቋቁሞ በአባላቱ ብዙ ሥራዎችን እንደሚሰሩ ይታወቃል።እነዚህ ባለሙያዎችን የሚያፈሩ ተቋማትና ባለሙያዎች ከወዴት አሉ? እነርሱ ወደ መንግሥት፣መንግሥት ደግሞ ወደ ባለሙያዎቹ በመሄድ ተቀራርበው ችግሩን በጋራ ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሄ ለምን ማስገኘት ተሳናቸው።እነርሱም ቢሆኑ የማህበረሰብ ክፍል ናቸው።የእሳት ማጥፋት ሥራ እስከመቼ?
በጥናት የተደገፈ ባይሆንም ኢትዮጵያ አብዛኛው የምግብ ፍጆታዋ በአገር ውስጥ ምርት ነው የሚሸፈነው። ነገር ግን አንዳንዱ ለህፃናት የሚውል የታሸገ ምግብና ወተት ዋጋ ተወደደብን ብሎ ነው ድምጽ የሚያሰማው።ለምን ሆነ ሲባል እንደቀላል ነገር ሀብቱ እያለ መስራት ባለመቻላችን የተፈጠረ ስህተት ተደርጎ ይወሰዳል። ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ሆና ስሟ በትልቁ በሌላው ዓለም እየተጠራ ዜጎችዋ ቡና እየተወደደባቸው አንድ ኪሎ ቡና 300ብርና ከዚያ በላይ እንዲገዙ እየተገደዱ ነው። የዋጋው መናር ሰፊ ቁጥር የያዘውን የቡና ጠጡ የሥራ ዕድል እንዳያሳጣ ያሰጋል። በተለይ በአነስተኛ ምግብ ነክ ንግድ ላይ የተሰማሩት እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የመግዛት አቅም የሌለውን ዜጋ በመርዳት ፋይዳቸው ከፍ ያለ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2014