ኢኮኖሚና ባንክ፤ ባንክና ኢኮኖሚ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው። ባንክ የኢኮኖሚ ማደሪያ ብቻ ሳይሆን ምንጭም ነው። ኢኮኖሚ የባንክ ምሰሶ ብቻ ሳይሆን ዋልታና ማገርም ነው። በመሆኑም፣ አይነጣጠሉም። ልማት ያለ ኢኮኖሚ፤ ኢኮኖሚ ያለ ባንክ (የፋይናንስ ተቋማት) አይታሰብምና፤ ስለ ልማት ሲነሳ ስለ ኢኮኖሚ ማንሳቱ የግድ እንደሆነው ሁሉ፤ ስለ ኢኮኖሚ ሲነሳም ስለ ባንክ መነሳቱ የግድ ነው። ባይሆን ኖሮማ እነ አለም ባንክ እና አይኤምኤፍ ተቋሞቻቸውን የደሀ መጨቆኛ መሳሪያቸው ባላደረጓቸውም ነበር።
የ80 ዓመት የእድሜ ባለጻጋው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በ1934 ዓ.ም (እአአ ኦገስት፣ 1942) ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ›› በሚል ስያሜ የንግድና የብሔራዊ ባንክነትን ጥምር ኃላፊነት ይዞ በንጉሥ አፄ ኃይለሥላሴ አማካኝነት ተመሰረተ። በ1963 ሥያሜው “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ” ወደሚል ተቀየረ። በ1974 በወቅቱ የግል ባንክ ከነበረው “አዲስ አበባ ባንክ” ጋር ተዋሀደ።
በዚህ መልኩ የምስረታና እድገት ጉዞው የሚወሳለት የዛሬው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢኮኖሚያችን እናት እና ቀዳሚ ባንክ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ፣ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ ሲያደርግ የነበረውና ሲጫወት የኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በርካታ መሰናክሎችን አልፎ እዚህ መድረሱና ለ80+ እድሜ መብቃቱም ምእተ አመቱን ሲያከብር ስለሚደርስበት እንድናስብ፤ አስበንም እንድንጓጓ የሚያደርግ ነውና ይበል ያሰኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሁን ይዞታው በአጭሩ ሲገለፅ፤ ከአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ገበያ አብላጫውን እጅ በመያዝ እስከ ጥር 2014 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ ከአንድ ነጥብ አንድ (1 ነጥብ 1) ትሪሊዮን ብር፤ ተቀማጩም ከ824 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ቅርንጫፎቹ (በውጪ አገራት ያሉትን ሳይጨምር) ከ1ሺህ 700 በላይ ሲሆኑ፣ የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም ከ31ነጥብ4 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። ከዚህ አኳያ የባንኩ ሀብት የአገር ሀብት ነውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያስመዘገበው ስኬት የሚያበረታታ ነው።
ይህ በደርግ ዘመን አንድ ሰው ከ500 ሺህ ብር በላይ በባንክ ማስቀመጥ አይችልም በተባለበት ዘመን ባይቆረቁዝ ኖሮ የት ይደርስ እንደ ነበር ሲታሰብ ደግሞ የባንኩ ጉዞና ስኬት የበለጠ እንደሚሆን መገመት ባያስቸግርም፤ በ2020 በተደረገ ውድድር አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ 100 ባንኮች መካከል 17ኛ ደረጃን መያዙ፤ በአገር ውስጥ ብቻ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በአፍሪካ ተወዳድሮ 17ኛ፤ ከምስራቅ አፍሪካ ከ267 በላይ ባንኮች በሚገኙበት ምድብ 1ኛ መውጣቱ ከ“አፍሪካ ቢዝነስ እና ዘ አፍሪካ ሪፖርት” ሲሰማ ደግሞ ባንኩ ጠንካራ መሰረት ላይ መቆሙን ያሳያልና መጪው ዘመን ለባንኩ ብሩህ ነው። ወደ ዛሬው እለት ሁነት (ምረቃው) እንሂድና ስለ ህንፃው አንዳንድ ነጥቦችን አንስተን እንመለስ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው ባንኩ የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት በዓል በርዝመቱ ከአፍሪካ ሦስተኛ ነው የተባለውን ባለ 53 (ወደታች አራት፣ ግራወንድ እና 48 የፎቅ) ወለሉን፤ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ዛሬ ያስመርቃል። በመግለጫው ወቅት እንደተመላከተው ይህ ግዙፍ ህንፃ በ165 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውን ዋና መሥሪያ ቤቱን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 303 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪን ጠይቋል።
በቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (CSCEC) የተገነባውና ከአራት ሺሕ በላይ የሚሆኑ የባንኩን የዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች አጠቃሎ የሚይዝ መሆኑ የተነገረለት ይህ ሕንፃ 48 ወለል፣ እንዲሁም አራት ወለል የምድር ቤትን (ቤዝመንቶች) የያዘ ሲሆን፣ 209ነጥብ15 ሜትር እርዝመት አለው።
በመግለጫው እለት ለየት ብሎ የተገኘ የባንኩ ሃላፊዎች ንግግር ቢኖር “የአፍሪካ አልማዝ ቅርፅ እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል” የተባለለት ይህ ሕንጻ፤ በዘመናዊ ጥበብ የታነፀው፤ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ የህንፃ ታሪክ ረዥሙ መሆኑ የተገለፀለት ይህ ግዙፍ ሕንፃ ከ11ኛ፣ 24ኛ እና 37ኛ ወለሎች በቀር ከሁለተኛ እስከ 46ተኛ ድረስ ያለው የሕንፃው ክፍል ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ነው። 47ተኛው የሕንፃው ወለል ለካፍቴሪያነት፣ 48ተኛው ደግሞ አዲስ አባባን ከሕንፃው የመጨረሻ ወለል ላይ ሆነው በአራቱም አቅጣጫ በግልፅ ለማየት ለሚፈልጉ ሰዎች ክፍት እንደሚሆንም ተነግሯል።
ይህም በበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ በደስታ የታጀበ ግርምታን ከመፍጠሩም በላይ፤ እውን ሆኖ ለማየት ጉጉትን ከወዲሁ አጭሯል። በአንደኛው ተደራቢ የሕንፃ ክፍልም ስድስት ያህል ሲኒማ ቤቶችን ያካተተ መሆኑ፤ እንዲሁም፣ ሁለት የሕንፃው ፎቆች የባንኩን ታሪክ የሚያመላክቱ የማሳያ ሥፍራዎች እንደሚኖሩት መታወቁም ለጥበብና ታሪክ ቤተሰቦች ሌላው ደስታን የፈጠረ የህንፃው አካል ነው። ይህ ሁሉ ተዳምሮም ከተማዋን በከፍተኛ ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ አቅም እንዳለው እየተነገረ መሆኑም ሌላው የህንፃው የጎንዮሽ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ነው።
የከተማዋን ገፅታ ከመገንባት አኳያ ሚናው ትልቅ መሆኑ ከወዲሁ እየተነገረለት ነው። ጥበባት ሁሉ የፈሰሱበትና ዘመናዊ መሆኑ እየተነገረለት፣ በዛሬው እለት ስለሚመረቀው ግዙፍ ህንፃ በጥቂቱ ይህንን ያህል ካልንና ጥቂት ገጽታዎቹን ካመለከትን ወደ ተነሳንበት፣ ባንኩና ስኬቱ እንመለስ።
ምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ባንኮች 1ኛ ደረጃ መያዙ የተነገረለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢኮኖሚው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን እንዳስመዘገበ በተደጋጋሚ ሲገለፅ የሚሰማ ሲሆን፤ ከእነዚህም አንዱ ባለፈው ሴፕቴምበር 2021 “በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱትና ከፍተኛ ሀብት ካላቸው ሁለት ባንኮች መካከል አንዱ፤ በአፍሪካ ደረጃም ከፍተኛ ሀብት ካላቸው ጥቂት ባንኮች መካከልም አንዱ፤ ከፍተኛ የሚባል ካፒታል ካላቸው ባንኮች መካከልም አንዱ መሆን” መቻሉም ታውቋል።
ይህም በአገር ውስጥ ካሉት ባንኮች የመሪነት ሚና እንዲይዝ ከማስቻል ባሻገር በቀጣናው ለሚደረገው የባንክ አገልግሎት መስፋፋት እንዲሁም ለደንበኞችና ለመላው ኅብረተሰብ የላቀ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት አቅም እንደሆነው ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
እንደ ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የ”ሪፖርተር” ማብራሪያ በ1934 ዓ.ም “በአንድ ሚሊዮን የማሪያትሬዛ ብር ካፒታል አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 80 ዓመታትን ባስቆጠረ አገልግሎቱ የትሪሊዮን ብር ሀብት ባለቤት ለመሆን የበቃው ሕዝቡን በማሳተፍ” ሲሆን፤ “ሁለተኛው ትሪሊዮን” በጥቂት ዓመታት እንደሚሳካ የሚያጠራጥር አይደለም።
ፕሬዚዳንቱ “በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ የገጠማትን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለመቋቋም ለሚደረጉ ጥሪዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት እጅግ የሚያኮራ ተሞክሮ ያለው” መሆኑንና “ከአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዞና ስኬት ጋር እጅጉን የተቆራኘ ታሪክ” እንዳለው የተናገሩትን ከግንዛቤ ካስገባን፤ የባንኩ ታሪክና ተግባሩ አካል አድርገን ከወሰድን ተቋሙ በአገሪቱ ልማትና እድገት ውስጥ የተጫወተውን ሚና በቀላሉ መረዳት እንችላለን።
አቶ አቤ ሳኖ “በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ልማት ዕውን ለማድረግ ለሚደረጉ ጥረቶች የባንኩ የገንዘብ አቅራቢነት ሚና ከፍተኛ መሆኑን፣ በመላ አገሪቱ የሚከናወኑና ኢትዮጵያን ወደ’ሚገባት ከፍታ ለማድረስ እምነት የተጣለባቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድጋፍና ተሳትፎ ጉልህ” መሆኑን መናገራቸውን ስናስታውስ፤ የባንኩን የ80 አመት ጉዞና የልማት ተሳትፎ በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ይጠበቅበታልናም የተሻለ ነገ እንዲሆንለትም እንመኝለታለን። ስናበረታታውም ቢያንስ በ”ይቆጥቡ፤ ይሸለሙ!!!” መርህ መሰረት ይሆን ዘንድ በመሻት ነው።
የፋይናንስ ተቋሙ ሀላፊዎች “የውጭ ባንኮችን ልንወዳደር የምንችልበት በርካታ እውነታዎች አሉ። የውጭ ባንኮች ቢገቡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብዙ ላይፈተን ይችላል። ከእነሱ ጋር ሊያወዳድረን የሚያስችል ዝግጅት እናደርጋለን።” በማለት ከሰጡት ማብራሪያም የተቋሙን ዝግጅት ከወዲሁ መገንዘብ ይቻላልና አዲሱ ህንፃ ለዚህ ስኬት ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር አኳያ ሚናውን ይጫወታል ብለን እናምናለን።
የኢትትዮጵያ ንግድ ባንክ የአገሪቱን ሁሉን አቀፍ ልማት ከመደገፍ ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቶቹን ለመወጣት የሚያስችሉ ታላላቅ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ሀላፊዎቹ በሰጡት መግለጫ (ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም) ያስታወቁ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም ሕዝብ የሚያገለግሉ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዘጠኝ ክልሎች የጤና ጣቢያ ግንባታ፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስና ዩኒፎርም መግዣ የሚውል የገንዘብ ልገሳ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች የማልማት ዕቅዶችን ለማሳካት የተደረጉ ድጋፎች፤ ሸገርን ለማስዋብ የ500 ሚሊዮን ብር፣ ገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል ለሆኑት ለኮይሻ፣ ወንጪና ለጎርጎራ [እና ለመሳሰሉት] በአጠቃላይ የ1ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉ በፕሬዚዳንቱ መገለፁም የዚሁ የባንኩ የ80 አመት ጉዞ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋኦ ነው። ከዚህ አኳያ ባንኩ የምእተ አመቱን በአል (100ኛውን) ሲያከብር ከዚህ የበለጡ ስራዎችን በማከናወን፤ የተሻለ ስኬትና ውጤትን በማስመዝገብ እንደሚሆን ተስፋ አለ።
በ2025 አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ወደ ፊት ከበድ ያለ ፈተና ይሆንበታል ተብሎ የሚጠቀሰው እያደገ ከመጣው የባንክ ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ እየታየ የመሆኑ ጉዳይ ሲሆን፤ ለዚሁ የሚመጥን ቴክኖሎጂ መገንባት ከፍተኛ ሥራን የሚጠይቅ በመሆኑ አመራሩ ይህንን ችግር ለመቋቋም በከፍተኛ ሀላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት፤ ይህንንም በራሱ ጥናት የደረሰበት መሆኑን ከተቋሙ ከተገኘው መረጃ ታውቋል።
ከባንኩ ከተገኘው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከአራት ትሪሊዮን በላይ ገንዘብ ተንቀሳቅሷል። በቀን እስከ አራት ሚሊዮን ትራንዛክሽኖች (ግብይቶች) የተካሄዱበት ጊዜም አለ። ይህ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነና ለማቅለልና አገልግሎቱን ፈጣንና ተደራሽ ለማድረግ (ቴክኖሎጂን ከማሻሻል አኳያ) ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ መሆኑ ግንዛቤ ተይዟል።
አሁን ባለው አሰራርም ሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም መቀጠል እንደማይቻል፤ አሁን በሚሠራበት ሲስተም፣ ሥርዓተ ሒደት ቢዝነስ ኦፕሬሽን ሜካኒዝም የወደፊቱን ተግዳሮት መጋፈጥ እንደማይቻል ተረድቻለሁ የሚለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ የዲጂታል ባንኪንግ ተጠቃሚ ለሰከንድ አገልግሎቱ እንዳይቋረጥበት ለማድረግ ወደ ኮር ባንኪንግ ለመግባት እየተንደረደረ መሆኑንም ካሳወቀ ሰነባብቷል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት እንደሚሉትም፣ “ትልቁ የባንኩ ፈተና እና ትልቁ ችግር ተደርጐ ሊወሰድ የሚችለውም ከቴክኖሎጂው ጋር አብሮ የመፍጠን ጉዳይ ነው። ይህ ችግርና ፈተና በዚህ ዘመናዊ ህንፃ (ምቹ የስራ ስፍራ) ሁሉም ቀና ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። የብድርና የውጭ ምንዛሪ ስራውንም በሚፈልገው መንገድ ያሳልጣል ብለንም እናስባለን፤ ይሳካም ዘንድ ስንመኝለት ቆጥበን በመሸለም፤ የአገሪቱ የልማትና እድገት አካል በመሆን መሆኑን መግለፅ ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀደም ብሎ በውጭ አገሮች ቅርንጫፎች ኖረውት ኮርስፖንዲንግ ባንኪንግ ሪሌሽን (ባለሙያዎቹ “የአገናኝ ባንኪንግ ግንኙነቶች” የሚሉት)ን በራሱ የሚያስተዳድርበት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልሞ እየሰራ እንደ ሆነ ከተለያዩ የባንኩ ምንጮች መረዳት ይቻላል። ይህ ምኞቱ እንዲሳካለት ስንመኝም፣ በታታሪ ሰራተኞቹ አማካኝነት (የሀብትም የዕውቀትም ማዕከል ይሆናል በተባለለት በአዲሱ ህንፃ ውስጥ) ሁሉም ይሆናል ከሚል እምነት ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድንበር ተሻጋሪና የጠረፍ ንግድ ሥራው አካባቢ ላይ እና መድረሻው መቆሚያ ስለሌለው እንዲህ ባሉ ሥራዎች ላይ ለመግባት የያዘው ስትራቴጂክ እቅድም እድሜው 100 ሳይሞላ ከወዲሁ እንደሚያሳካው ህዝብ ይመኛል። (በነገራችን ላይ፣ ምንም ሳይሰሩ የ100 አመት እድሜያቸውን ያከበሩ አንዳንድ ተቋሞቻችን የገጠማቸውን አይነት ትዝብት ባንካችን እንዲገጥመው ካለ መፈለግ በመጣ ሀሳብና ስሜት ነው እዚህ ጽሑፍ ውስጥ አልፎ አልፎ ስለ 100ኛ አመት የተነሳው።)
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማራጭ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና በዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች አማካኝነት ተደራሽነቱን ለማስፋት እያደረገ ያለውን ጥረት 100 በ100 እውን የሚያደርግበት አመራር የሚሰጥበት፤ ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት፣ የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ (ተደራሸነት፣ የአገልግሎ ጥራትና ቅልጥፍና) ተግባሩን የሚያሳልጥበት፤ በፋይናንስ ዘርፍ ያለውን ውንብድና ለመቆጣጠር፣ የህገወጥ ገንዘብ ፍሰትን ለመከታተል እንዲሁም በተለያዩ የሽፋን ስሞችና የተጭበረበሩ ሰነዶች የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር እና የመሳሰሉትን፣ ችግሮች ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ብርቱ ጥረት ዳር የሚያደርስበት ይሆናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ምቹ የስራ ቦታ የሚሰጠው ይህ ግዙፍ ህንፃ ከአገልግሎቱ ባሻገርም በቱሪስት መስህብነቱም የአገር ኢኮኖሚን እንደሚደጉም አያጠራጥርም። ከዚህ አንጻር ይህ ባለ ግርማ ሞገስ ህንፃ ፋይዳው ብዙ መሆኑን እንገነዘባለን።
በመጨረሻም፣ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሉን የሚያከብረው እና ግዙፍ ሕንጻውን የሚያስመርቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከላይ የጠቃቀስናቸው መልካም ገጾቹ እና ክፍተቶቹን ለመሙላት የሚያደርጋቸው ተጋድሎዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አንድ ተቋም መቶ በመቶ ከችግር የነጻ አይደለምና ሊነቀሱ የሚችሉ ሕጸጾች ይኖሩታል። በመሆኑም ከሲስተም የለም ወይም “ኖ ሲስተም” ጀምሮ ሊጠቀሱ የሚችሉ ችግሮች አሉት። በመሆኑም በዓሉን ሲያከብርም ሆነ ሕንጻውን ሲያስመርቅ እነዚህንና ሌሎችም ሕጸጾችን አርሞ ለህብረተሰቡ የሚያረካ አገልግሎትን ለመስጠት ቃሉን በማደስ ጭምር ሊሆን ይገባል። እኔም ከወዲሁ መልካም የግዙፉና ዘመናዊው ሕንፃ ምረቃ በአል፤ መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንለት እመኛለሁ። ቺርስ ለባንካችን!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014