አንድነት ፓርክ /ፊት በር አካባቢ/ ቆሜ ቁልቁል አዲስ አበባን እየተመለከትኩ ነው። ከሁዋላዬ የአንድነት ፓርክ፣ ከፊትለፊቴ ወይም ከግርጌዬ የወዳጅነት ፓርክና ሸራተን አዲስና ተሻግሮ በርቀትና በቅርበት አረንጓዴ ስፍራና ሕንጻዎች ውበት ይታየኛል። የቆምኩበት አካባቢም እጅግ ማራኪ ቢሆንም አሻግሬ የተመለኩት ግን ለዛሬ ይበልጥ ስቦኛል።
በተለይ ለገሀገር፣ ስታዲየም፣ ብሄራዊ ፣ ሰንጋ ተራ አካባቢ ውብት የከተማዋ እንቁ ስፍራ መሆን ችሏል። በአካባቢዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዛታቸው እየጨመረ የመጣውን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች የተመለከተ ሕንጻዎቹ ቁመት የሚለካኩ ሊመስሉት ይችላሉ። ሕንጻዎቹ አዲስ አበባን አግድም ብቻ ሳይሆን ሽቅብም እንድትዋብ አርገዋታል። የአንድ ውብ ከተማ አንዱ መገለጫስ ይሄው አይደል።
እነዚህን አካባቢዎች በርቀት ብቻ አይደለም የማውቃቸው። በቀንም በምሽትም ሁሌም በአጠገባቸው አልፋለሁ፤ አብዛኞቹ ገና ስራ የሚጀመሩ በመሆናቸው በአካባቢው ላይ የመጣውን የትራፊክ ጫና ብዙም አላስተዋልኩም። ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ ግን ጫናው ሊመጣ እንደሚችል ከሕንጻ ባለሙያዎች መረጃው አለኝ። ምክንያቱ ደግሞ በሕንጻዎቹ ላይ መንደር ነዋ እየተፈጠረ ያለው።
ምሽት ላይ ደግሞ በሕንጻዎቹ ላይ ከተገጠሙት መብራቶችና ግዙፍ ስክሪኖች የሚወጣው ብርሃን ሕንጻዎቹን ራሳቸውንና አካባቢውን በልዩ ልዩ ህብረ ቀለም ያስውቡታል፤ በስራቸውና በአካባቢው የሚያልፈውን ሰው፣ ተሽከርካሪ ሌሎች አካላት ሁሉ ባለ ቀለም ያደርጓቸዋል።
በብሄራዊ እና አካባቢው ከተገነቡት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት የባንኮች ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻዎች ናቸው። የእነዚህ ሕንጻዎች መገንባት ባንኮቹ በተለያዩ አካባቢዎች ያሏቸውን ወሳኝ ክፍሎች እንድ ላይ አሰባስቦ ለመስራት ያስችላል። የተቀላጠፈ ሥራ አንዲኖርም ይጠቅማል።
ሕንጻዎቹ ግዙፍ እንደመሆናቸው የሚያከራዩዋቸው ወለሎችና ክፍሎች በብዛት ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል፤ ለአዳራሽነት፣ ሬስቶራንትነት እና ለመሳሰሉት የተገነቡ በቂ ወለሎችና ክፍሎች ያላቸው እንደመሆናቸው ሕንጻዎቹ ሁሉንም አገልግሎቶች በአንድ ስፍራ ሊሰጥ የሚችል መንደር ሊሆኑ እንደሚችሉም መገመት አይከብድም።
ዛሬ የሚመረቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻም በከተማዋ በከፍታ የሚወዳደረው የለም። አሁንም ሁሉንም ሕንጻ ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን የአዲስ አበባ ክፍል ቁልቁል ማየት የሚችል ሕንጻ በከተማ ተገንብቷል። እስከ አሁን በርካታ ከ30 በላይ ወለል ያላቸው ሕንጻዎች በከተማዋ የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ ሲሆን፣ የንግድ ባንክ ሕንጻ ከመሬት በታች አራት ወለሎች ከመሬት በላይ 48 ወለሎች እንዳሉት ነው የተጠቆመው። ይህ ሕንጻ ግን አሁን ላይ በከተማዋ ብቸኛው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ መሆን ችሏል። ልክ እንደ ምሰሶ የአዲስ አበባን ሰማይ ደግፎ የያዘም ይመስላል።
ግዝፈቱ ደግሞ ሽቅብ ከሁለት መቶ ሜትር በላይ መታየቱ ላይ ብቻ አይደለም የሚገለጸው። ከራሱም አልፎ ለሎሎች የተለያዩ አገልግሎቶች የሚተርፍ መሆኑ ነው። ለሬስቶራንት፣ ለሲኒማ ቤት፣ ለስብሰባ አደራሽና ለመሳሰሉት ሊውሉ የሚችሉ ወለሎችና ክፍሎች ያሉት መሆኑ ያመለክታል።
እናም በከተማዋ በባንኮች እየተገነቡ ያሉ ሕንጻዎች መቀመጫቸውን መሥሪያቸውን ብቻ ያመቻቹ አይመስለኝም። የህልውናቸው መሰረት የሆነውን የፋይናንስ ዘርፍ የተሻለ ደረጃ ላይ የማድረስ ግብ ያላቸውና አገልግሎት አሰጣጣቸውን ማሳለጥን ያለሙ ናቸው።
የእኔ ዋና ትኩረት የባንኮቹ ሕንጻዎች ለፋይናንሱ ዘርፍ በሚያደርጉት አስተዋጽኦ ላይ አይደለም። ለከተማ ልማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ነው። ባንኮቹ የገነቧቸው ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች በከተሞች ላይ ለሚስተዋል የመሥሪያና የመኖሪያ ቤት ችግር አንድ መፍትሄ ሊሆኑ ይችላል። ይህን ያህል ግዙፍ ሕንጻ ሲገነባ መቼም የባንኩን የቅርብ ጊዜ ችግር ታሳቢ በማድረግ አይሆንም። ባንኮቹ የንግድ ተቋማት እንደመሆናቸው ተሻጋሪ ኢንቨስትመንት የሚያስቡ ናቸውና ሕንጻዎቹ ሲታሰቡ ብዙ ነገሮች አብረው ታስበዋል ብዬ እገምታለሁ።
ከራሳቸውም አልፈው የሚያከራዩዋቸው ወለሎችና ክፍሎች እንደሚኖሯቸው ይጠበቃል። ይህን ተከትሎም በርካታ የንግድና የሥራ ተቋማት በሕንጻዎቹ ይገባሉ። ይህ ሲሆን የእነዚህ ተቋማት የመሥሪያ ቦታ ችግርም ተፈታ ማለት ነው። ይህ ተፈታ ማለት ደግሞ ከተማዋ ውስጥ የሚታየው የተቋማት የመሥሪያ ቦታ ችግር እየተፈታ ይመጣል። እናም ቱሩፋቱ ለከተማም ለአገርም ነው።
ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ብቻቸውን አይመጡም፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂንም ይዘው ይመጣሉና ከተማችን አገራችን ለከተማ ልማት የሚጠቅሙ ቴክኖሎጂዎችን ያገኛሉ ማለት ነው። ሊፍቶቻቸው ፈጣንና ብዙ ሰው የሚይዙ እንደሚሆኑ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮም አቅርቦታቸውም አስተማማኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የአገሮችና ከተሞቻቸው የኢኮኖሚ እድገት መገለጫ ተደርገውም ይታያሉ። የአንዳንዶቹ የበለጸጉ አገሮች ከተሞች ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች የከተሞቹ ወይም የአገሮቹ መገለጫ ተደርገው ይታያሉ። በአልቃይዳ ጥቃት እንዳልነበር የተደረጉት የዓለም ንግድ ድርጅት መስሪያ ቤት የነበሩት የኒዮርክ መንታ ሕንጻዎች በኒዮርክ የፋይናንሻል ማእክል አካባቢ የተገነቡና የግሎባላይዜሽንና የአሜሪካ ኢኮኖሚ ሃያልነት መገለጫ ተደርገው ይታዩ ነበር። ከእነዚያ ሕንጻዎች አንዱ 417 ሜትር ሌላው ደግሞ 415 ነጥብ 1 ሜትር ርዝመት ነበራቸው። በዓለም የሚወዳደራቸው ያልነበረ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ነበሩ። ሕንጻዎቹ ሲታዩ ኒውዮርክ ፣ ኒዮርክ ስትታሰብ ሕንጻዎቹ ይታሰቡ ነበር።
ወደ ዱባይ አንሂድ። የቡርጂ ከሊፋ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻም የዱባይ መገለጫ ነው። ሕንጻው ዱባይን ለማልማት ታስቦ ከተካሄዱ ግንባታዎች አንዱ ነው፤ 829 ነጥብ 8 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ሕንጻ አአአ በ2010 ተመርቆ ስራ የጀመረ ነው። ይህም ሕንጻ የዱባይ መገለጫ ተደርጎ ይታያል፤ የሕንጻው ምስል ሲታይ ዱባይ፣ ዱባይ ስትታሰብ ሕንጻው ይታሰባሉ።
ለእኛም ዛሬ የተመረቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ የሌሎች ባንኮቻችን ዋና መሥሪያ ቤት ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች እና ያሉበት የፋይናንስ ዞን የአዲስ አበባ እና የኢትዮጵያ መገለጫ ተደርገው ይወሰዳሉ። የአዲስ አበባን አልፎም ተርፎ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ከተማ ልማት እድገትና በቀጣይ ሊደርስ የሚችልበትን ሁኔታ ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ያስመረቀው ባለ53 ወለል ሕንጻም አንደ አገር ከዚህ አንጻር ሊጠቀስ ይችላል። የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ሰሞኑን እንዳሉት፤ የባንኩ አዲሱ ሕንጻ በአይነቱ ልዩ የሆነና የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተደረገበት ነው። በዘመናዊነቱ ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን፣ ከአፍሪካም በርዝመቱ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሕንጻው ከመሬት በላይ ከሁለት መቶ ዘጠኝ ሜትር በላይ ከፍታ አለው። የተለያዩ የንግድ ማእከላት ሕንጻዎችን አካቷል፤ ሶስት ሕንጻዎችን ያካተተና አንድ ሺ አምስት መቶ መኪኖችን ማቆም የሚያስችል ፓርኪንግ፣ ሁለት ሺ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ አዳራሾች ደረጃቸውን የጠበቁ ሬስቶራንቶችን ያካተተ ነው።
ይህ ሕንጻና ሌሎች የባንኮች ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ለአዲስ አበባ ከተማም ብዙ ፋይዳዎችን ይዘው መጥተዋል፤ የከተማዋ እድገትና ውበት መገለጫ መሆን ችለዋል፤ ከተማዋ ወደጎን እየሰፋች የቆየችበትን ሁኔታ ወደ ሽቅብ በማሳደግ የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ሕንጻ ስር መስጠት እንደሚቻልም ያመለከቱ መሆን ችለዋል። አዲስ አበባ ሌሎች ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን አሁንም ትፈልጋለች። በተቀደደው መንገድ በመሄድ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን በመገንባት የሕንጻ ላይ መንደሮችን በመመስራት የመኖሪያና መሥሪያ ቤቶችን እጥረት መፍታት የከተማ ልማቱን ማሳለጥ ይገባል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2014