እያንዳንዱ ዘመን የራሱን የነበር ታሪክ አሻራዎች አትሞ ከሚያስተላልፍባቸው እጅግ በርካታ ብልሃቶችና መንገዶች መካከል ዜማዎችና መዝሙሮች ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው። ለምሳሌ፤ “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለውና በአራራይ የተቀናበረው የወቅቱ ብሔራዊ መዝሙር ሲደመጥ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን አሰስ ገሠሡን ጭኖ ወደ አእምሯችን ከተፍ ይላል። “ደሙን ያፈሰሰ” እና “ተጣማጅ አርበኛ” የሚሉት የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ መስቀያና ማውረጃ መዝሙሮችም ለዚያ ዘመን ትውልድና ወቅት ቋሚ ማስታወሻዎች ናቸው።
ዕድሜውን አድሏቸው በሕይወት የሚገኙ ዜጎች እነዚህን መዝሙሮች ሲሰሙ የሚሰማቸው ስሜት ምን እንደሆነ በአደባባይ ቢመሰክሩ ብዙ በተማርን ነበር። “ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ!” በማለት በጎ ምኞት የተመኙላት የዘመኗ አገራቸው በርግጥም እንደጓጉላት ደስታዋ ምልዑ ነበር ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር ያዳግታል። የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ክፉ ጠባሳዎች፣ የፊውዳል ሥርዓቱ መልከ ብዙ ግፎች፣ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች፣ የተማሪ መር አመጾችና እንቅስቃሴዎች፣ ርሃብና የድንበር ላይ ጦርነቶች ወዘተ. ዘመኑን ያጠለሹ ክስተቶች ነበሩ።
እንዲያም ቢሆን ግን ንጉሠ ነገሥቱ በጥበባቸውም ይሁን በኃይላቸው፤ የሚመሩት ሕዝብም በውዴታው አድርጎትም ይሁን ተገዶ ብቻ “አባባ ጃነሆይ!” እየተባሉ ሲወደሱ የኖሩት በብዙ ዜጎቻቸው አፍ ነበር። ያውም ከልብ። ቀን እስከጣላቸው ድረስም “በኃይለ ሥላሴ አምላክ!” እየተባለ በስማቸው የሙጥኝ ሲባል ኖሯል። ንጉሥ ነገሥቱ በየተገኙባቸው የዓለም አቀፍ መድረኮችና በየአገራቱ መሪዎች ዘንድም አንቱታ ሳይጓደልባቸው፣ የክብር አጀብና አቀባበል ሳይቀነስባቸው እንደ ተፈሩና እንደ ታፈሩ አራት ዐሠርት ዓመታትን ተንቀጥቅጠውም ይሁን አንቀጥቅጠው ብቻ ለረጅም ዘመናት ኢትዮጵያን ገዝተዋል።
የታሪካቸው ምዕራፍ እንዴት እንደተዘጋ ዝርዝሩን መተረኩ ቁርሾ መቀስቀስ ስለሚሆን በድርበቡ ብቻ አስታውሰን እናልፈዋለን። “ይኑሩልን ለክብራችን” ተብሎ እንዳልተዘመረላቸው የይሙት በቃ ዋንጫቸውን ተጎንጭተው ያለፉት ግፈኞች ባስተላለፉባቸው የግፍና የጭካኔ ውሳኔ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ይታወቃል። የመራሩ ታሪካችን አንዱ ገጽታ መሆኑም አይዘነጋም።
ይህ ጸሐፊ እኒህ የተከበሩ ንጉሠ ነገሥት በኖሩባቸው ዘመናት ምንም እንኳን በታዳጊነት ዕድሜ ላይ የነበረና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ ደጋግሞ አግኝቷቸው አበረታተውታል። ከእጃቸውም ለልጅ የሚገባውን የአንድ ብር ሽልማት እጅ ነስቶ ተቀብሏል። ከዘመነ አቻዎቹ ብጤዎች ጋርም “የነገ የአገሪቱ ተስፋ ስለሆናችሁ በርትታችሁ ተማሩ” የሚል ምክርና ምርቃታቸውን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት የአራት ኪሎው የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) በተገኙበት ጊዜ “አሜን!” ብሎ ተቀብሏል።
ቤተሰቦቹ ሲያደንቋቸው እየሰማ እርሱም በታላቅ አክብሮት እያዳነቀ በልጅ አንደበቱ አሞግሷቸውል፤ አወድሷቸዋልም። ለአገርና ለዜጎቻቸው የሰሯቸው ተምሳሌዊ ተግባራት ሲተረኩም በየምሽቱ በምድጃ ዙሪያ ከቦ ይቀመጥ በነበረው የወታደር ፍሬ ቤተሰቦቹ መካከል እየተቁለጨለጨና የቁጢ ሻሂውን ፉት እያለ ገድላቸው ሲተረክ በማድመጥ አብሯቸው ለእኒሁ አባባ ጃነሆይ ረጅም ዕድሜን ተመኝቷል። ከእልፈታቸው በኋላም በንጉሡ ዘመን “ማዕዳችንና ጓዳችን የተትረፈረፈ ነበር” የሚለው የወላጅ እናቱ ትካዜ ዛሬም ድረስ ከትዝታው አልጠፋም። እንዲዚያም ቢሆን ግን የወቅቷ ኢትዮጵያ እንደ መዝሙሩ “ደስ ተሰኝታ ስለመኖሯ” ለመመስከር አፍ መያዙ አይቀርም። ቢሆንም… ቢሆንም ግን … ጅምሩን ሀረግ አንባቢው ሊሞላበት ይችላል።
“ተነሱ እናንት የርሃብ እስረኞች”፤
“ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ፤ በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ” – ከሚለው የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ይልቅ ገንኖ በዚያን ዘመን አብዮተኛ ትውልድ ይዘመር የነበረው፡-
“ተነሱ እናንት የርሃብ እስረኞች፤ ተነሱ የምድር ጎስቋሎች፣
ፍትህ በሚገባ ይበየናል፤ ሻል ያለ ዓለምም ይታያል።
ከእንግዲህ ባለፈ ይብቃ እስር፤ ተነሱ ባሮች ጣሉ ቀንበር፣
የዓለም መሠረት አዲስ ይሁን፤ ኢምንት ነን እልፍ እንሁን።”
ዝነኛ፣ “ትውልድ አንቀጥቅጥና” በውሰት ተበድረን ያመጣነው የባዕዳን መዝሙር ነበር። ዘመኑን በደም አበላ አጨቅይቶ ያለፈው የወታደራዊው አገዛዝ ያላቅሙ በጫንቃው ላይ ተሸክሞት የነበረው ለውጥና ነውጥ እንደምን አገሪቱን ወደለየለት መቀመቅ ጥሎ እንዳለፈ ያልመሸበት ታሪካችን ምስክር ነው። “ሀ ሁ ኢትዮጵያ ትቅደም!” በማለት የጀመረው አብዮት ዕድሜውን ያራዘመው የንጹሐን የደም ግብር እየተገበረለት እንደነበር ማን ሊዘነጋ ይችላል?
ውስብስቡን የደርግ ዘመን በምልዓት ገላልጦ ለማሳየት መሞከር እንኳን በጋዜጣ ጽሑፍ ቀርቶ ለመጽሐፍ ጥራዝ እንኳን ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን መገመቱ አይከብድም። የአብዮቱ ቋያ ሰደድ፣ የእርስ በእርስ መጠፋፋቱ ጭካኔ፣ በቀይና በነጭ ሽብር ቀለማት የሰከሩት የሞት መላዕክት አሰቃቂ ፍጅት፣ የውስጥና የውጭ ጠላት ወረራ፣ የድርቅና የርሃብ ትራዤዲ፣ በሰላም ውሎ መግባት ብርቅ መሆን፣ ሀብት አፍርቶ በአገር መኩራት የተነፈገበት፣ የአገሪቱ አየር በጦርነት የአረር ጭስ የታጠነበት፣ ወጣቱ ከብሔራዊ ውትድርና አፈሳ ጋር ድብብቆሽ የገጠመባቸው ክፉ ትዝታዎች ዘመኑን በሚገባ ይገልጹታል። አቤት! አቤት! አቤት! እያልን በማማተብ የዘመኑን ጥቁር “ደመና” በሆድ ይፍጀውና በታሪክ ይፍረደው ደምድሞ ማለፉ ይቀላል።
ቢሆንም፣ ቢሆንም ግን የዕለት ጉርስን ለማሟላት የሕዝቡን አቅም ያማከሉ ሸቀጣ ሸቀጦችን በአብዮት ጠባቂዎች ክላሽ ሰልፍ ተይዞም ቢሆን በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር። ከሻይ ቅጠል መጣያ ጋር ስኳር በአንድ ብር ከአስራ አምስት ሳንቲም፣ በቤተሰብ ቁጥር በአስር ሳንቲም ሂሳብ ዳቦ እየተገዛ፣ የሩዝ ቀለብ ቢሆንም የቤተሰባችሁን ኮታ አንሱ እየተባለ በግዳጅ ትዕዛዝ ሸመታው “መልካም” የሚሰኝ ነበር።
ሥርዓቱን የዘረኝትና የጎጠኝነት ደዌ እጅግም አልተጣባውም። እንደ ዛሬው “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” ልክፍትም ለዘመኑ ፈተና አልነበረም። እንደ ብሔራዊ መዝሙሩ ምኞት እንኳንስ “ኢትዮጵያ ልትቀድም” ቀርቶ በእንፉቅቅ እንኳን ለመራመድ በልምሻ የተጠቃችበት ዘመን መሆኑ ግን ደጋግሞ ሊሰመርበት ይገባል። “የርሃብ እስረኞች” የውሰት መዝሙር ይበልጥ ከሥርዓቱ ጋር ይገጥማል ቢባል አይስማማ ይሁን?
“እንዳያልፉት የለም”፤
ዘመነ ኢህአዴግን ዘመነ ፍዳ ብንለው ይቀላል። “እንዳያልፉት የለ ያ ሁሉ ታለፈ” የሚለው የጫካ መዝሙር ይበልጥ የዘመኑን ትዝታ የተሸከመ የጥበብ ጫንቃ ነው። ዘፍጥረቱ ላይ ለክልሉ ሕዝብና ጥቅም፣ እግሩ ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ ደግሞ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ስም እየማለና እየተገዘተ ከጠብመንጃውና ከዘር ልክፍቱ ጋር የሥልጣን መንበሩ ላይ የተቆናጠጠው ወያኔያዊው ሥርዓት እንደ ጫካ መዝሙሩ ይዘት ሁሉ ኖሮ ኖሮ የተቀበረው በቀል ጸንሶ፣ አርግዞና አቂሞ እንደነበር ከፍሬውም ከከናፍሩም ስንሰማ መኖራችን ግልጽ ነው።
“የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ጸንቶ፣
ታየ ሕዝባዊነት ዳር እስከ ዳር በርቶ።”
የሚለው ብሔራዊ መዝሙር የደራሲዎቹ የደረጀ መላኩ (ግጥሙን) እና የነፍሰ ሄር ሰሎሞን ሉሉ (ዜማውን) ምኞት ካልሆነ በስተቀር “የዜግነት ክብር” እንኳን የሕዝቡ ፍሬ ሊሆን ይቅርና ሽታውም ቢሆን ነበር ለማለት ያዳግታል። ከዚህ “ሕዝባዊ” ዝማሬ ይልቅ “እምበር ተጋዳላይ” ይበልጥ ለከበሮና ለዝላይ ምቹ ነበር። ጦርነት፣ ርሃብ፣ ዘረኝነት፣ ዘረፋና አጋባሽነት፣ ቂምና በቀል፣ እብሪትና ትምክህት የሥርዓቱ “ጌጦችና ፈርጦች (?)” ነበሩ ብሎ መጠቅለሉ ይበጃል።
የጦርነት ባሩድ ካላሸተተና በዜጎች መከራ ካልተደሰተ በጤና መኖር የተሳነው ይህ ሥርዓት፤ የቅዱስ መጽሐፍን ገላጭ አባባል እንጠቀምና፤ “በሞቱ የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ” (መጽሐፈ መሳፍንት ምዕ. 16፡30) ብሎ መደምደሙ ሳይሻል አይቀርም። ስለዚህ ጨካኝ ሥርዓትና የሥርዓቱ መሪዎች ብዙ ጽፈን ብዙም ስለተናገርን መልሰን መላልሰን መከለሱ ሳጥናኤላዊ ድርጊቶቹን ከማግዘፍ በስተቀር እጅግም ፋይዳ ላይኖረው ስለሚችል ከሕዝቡና ከፈጣሪ ዘንድ ፍርዱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀብሎ ፍጻሜው እስኪደመደም ድረስ በትዕግሥት መጠበቁ ሳይበጅ አይቀርም።
“ኩልና ከል”፤
ኩል የእህቶችና የእናቶች መዋቢያ፣ የሙሽራ ማቆንጃ የቅንድብ ማስዋቢያ ነው። “ ኧረ ኩሉን ማን ኳለሽ፤ ሙሽሪት ሲያምርብሽ” እየተባለ መዘፈኑም ስለዚሁ ነው። በአንጻሩ ከል ለመሪር ኀዘን የሚለበስ ጥቁር ጨርቅን ወይንም ማቅን ይወክላል። ሁለቱም የሚመሳሰሉት በጥቁረታቸው እንጂ በግብራቸው ተቃራኒዎች ናቸው።
ይህ አገላለጽ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ከመዝሙርና ከዜማ ይልቅ በሚገባ ይገልጽ ይመስለናል። “ዘመነ ብልጽግና” ሥርዓታዊ ርምጃውን የጀመረው በሰላም፣ በይቅርታና በፍቅር (‘ሰይፍ’ በሚል አጽርኦት ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስተዋወቃቸውን ልብ ይሏል) ኢትዮጵያን ለማሻገር አቅዶና አልሞ ነበር። ሦስቱ አማላይ ሃሳቦች (vertues) እንዲተገበሩ የተፈለገው መደመር በሚል የሥርዓቱ መርህ/ፍልስፍና ነበር።
እንደ ተባለውም እጅግ አማላይ ተግባራትና ስኬቶችን አይተን አጨብጭብንም አድንቀንም እስከ መገረም ደርሰን ነበር። ከኢህአዴግ ጋር የተቆራኘበትን እትብት በጣጥሶና ፈተናዎችን ተቋቁሞ የተወለደው የብልጽግና ፓርቲ መሩ ሥርዓት ገና ዳዴ ማለት ሳይጀምር ተግዳሮቶች እየተፈታተኑት የመጡት ገና “በእቅፍ” ላይ እያለ ነበር። አገሪቱ ልትዋብበት የቀረበላትን የልማትና የብልጽግና “ኩል” ገና ወደ ዐይኗ ከማቅረቧ ያልተጠበቀ “ከል” እንድትለብስ ተፈርዶባት መከራዋን ለማየት ተገዳለች።
ዛሬም ቀዳሚ ሥርዓቶችን የፈተነው ጦርነት አለቀቀንም። ምናልባትም አገራችንን በታሪኳ ውስጥ ገጥሟት የማያውቅ ፈተና የተጋረጠባት አሁን ነው ቢባል እውነትነት አያጣም። ወያኔ ይሉት የእርኩስ መንፈስ ውላጅ የፈጠረውን እልቂትና መከራ ዘርዝረን የምንዘልቀው ስላይደለ መንፈሳችን ሰከን ማለት ሲጀምርና መንፈሳችን ሲረጋጋ በወግ በወጉ እንተነትነው ይሆናል። ርሃብና ርዛቱም እንደ መዥገር ተጣብቆባት ልትላቀቀው አልቻለችም። መፈናቀልና የሕዝብ ጩኸት ዛሬም በአገሪቱ አየር ላይ እንደናኘ ነው። “ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሰው በጦርነት አለቀ፣ በመፈናቀል ተሰደደ፣ በግፈኞች ታረደ” የሚለውን መርዶ በነጋ በጠባ እየሰማን አእምሯችን ስለደነዘዘ እንደ ልማድ ቆጥረነዋል።
የኢኮኖሚው ድቀት፣ የማሕበራዊ ቀውሶች ምሬት የእለት ተእለት አፍ ማሟሻችን ከሆነ ሰነባብቷል። ሥርዓትና ሕግ ለጊዜው በክፋት ላይ ሙሉ ለሙሉ ሰልጥነው እፎይ ለማለት አልበቃንም። ግን እስከ መቼ? ለምንስ ማቅ ለብሰን ኖረን ማቅ እንደለበስን እናልፋለን? አገር እንዴት ትሁን ዜጎችስ ምን ያድርጉ? “ኢትዮጵያ ሆይ! ግራ ገብቶን ግራ አጋባንሽ!” ፤ “ፈጣሪ ሆይ! አንተስ ቢሆን ምን ብናደርግ የርህራሄ ፊትህን አዙረህ ይቅር ትለናለህ?” የኢትዮጵያንም የፈጣሪንም ምላሽ የምንጠብቀው “ነገም ሌላ ቀን ነው!” በሚል ተስፋ ነው። ለኢትዮጵያ ኩል እንጂ ከል አይገባትም። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014