የዛሬው የዘመን እንግዳችን በ1960ዎቹ በአገሪቱ በተካሄደው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ ናቸው። ኢሕአፓን ከመሰረቱና በውጭ ሆነው ወታደራዊ መንግሥቱን በመታገል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበራቸው ይነሳል። እኚህ ሰው ታዲያ ትውልዳቸውና እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ ነው። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በየነ መርዕድና ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥር በነበረው ሀረማያ እርሻ ኮሌጅ ገብተው ለሁለት ዓመታት ተምረዋል። ሆኖም የተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለግሉ ስለነበረና የንጉሡን ሥርዓት በመቃወም ይደረግ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ስለነበራቸው የፖለቲካውን ጫና በመሸሽ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ሆላንድ ተሰደዱ። በዚያም ሆነው በአገሪቱ እውነተኛ ዴሞክራሲ እንዲመጣ ሲሉ ትግላቸውን አላቆሙም። በውጭ ያለው የኢሕአፓን ክንፍም ከመሠረቱት መካከል አንዱ ነበሩ። የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የመጽሔት አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል።
እንግዳችን በሆላንድ አገር ሳሉም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ግንኙነት እንዲሁም በዲቨሎፕመንታል ስተዲስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በሶሾሎጂ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሰርተዋል። በተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ አገልግለዋል። ከእነዚህ መካከል ቱኒዚያ ውስጥ በሚገኝ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ለአራት ዓመታት ያበረከቱት አስተዋፅዖ የሚጠቀስ ነው።
የደርግ ሥርዓት መውደቅን ተከትሎ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መቀመጫውን ለንደን ያደረገ ፋኖስ ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅትን በዳይሬክተርነት እስከ 1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ ድረስ መርተዋል። ከዚሁ በተጓዳኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፖለቲካል ሳይንስ ክፍል ውስጥ ለአምስት አመታት አስተምረዋል። በተጨማሪ ዑጋንዳ በሚገኘው ናይል ቤዚን ዲስኮርስ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር ሆነው ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል።
ከተማሪው እንቅስቃሴ ጀምሮ በርካታ ጽሑፎችን በመፃፍ የሚታወቁት እንግዳችን በተለይም በመጽሐፍ ደረጃ ባሳተሟቸው ‹‹ከሰንጋተራ እስከ አምስተርዳም›› እና ‹‹states and civil socity in Ethiopia›› በተባሉት መጽሐፎቻቸው በስፋት ይታወቃሉ። በዋነትም ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ያሳተሙት ከሰንጋተራ እስከ አምስተርዳም በተባለው መጽሐፋቸው የተማሪውን አብዮትና ትክክለኛው የኢሕአፓን እንቅስቃሴ በመጻፍ መልክ ለትውልዱ በማድረስ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይገለፃል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ የኢኮኖሚ ምሑሩን ዶክተር መላኩ ተገኝን የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጓቸዋል። ከእንግዳችን ጋር በሕይወት ተሞክሯቸውና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በተማሪ እንቅስቃሴ ውስጥ ያደርጉት ስለነበረው እንቅስቃሴ እና ስለመጽሐፎችዎ ያንሱልንና ውይይታችንን እንጀምር?
ዶክተር መላኩ፡– እንዳልሽው ሀረማያ እርሻ ኮሌጅ ሳለሁ በተማሪ አብዮት ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጌያለሁ። ሆላንድ ከሄድኩም በኋላ ቢሆን ትግሉን አላቆምኩትም ነበር። በተለይም መጽሔት በማዘጋጀት ተማሪውን የማንቃትና እንቅስቃሴውን የማፋፋም ሥራ እንሠራ ነበር። የዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ፌዴሬሽን ተብሎ ሲቋቋም የመጽሔቱ አዘጋጅ እኔ ነበርኩኝ። በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ማኅበርም እንደዚሁ ፕሬዚዳንት ሆኜ ሠርቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪ ግን በአገሪቱ ፖለቲካና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እድሜ ልኬን ስጽፍ ኖሬያለሁ። በተለይም የተማሪዎች እንቅስቃሴ በርካታ ጽሑፎችን ጽፌያለሁ። በመጽሐፍ ደረጃ ከታተሙት ውስጥ ዶክትሬት ዲግሪዬ የሰራሁበትን ጽሑፍ ‹‹states and civil socity in Ethiopia›› በሚል ርዕስ አሜሪካ ታትሟል። ይህም መጽሐፍ ኢትዮጵያ እየተጋፈጠች ያለችውን የልማት ተግዳሮቶችን የሚያሳይ ነው።
ሁለተኛው መጽሐፌ ‹‹ከሰንጋተራ እስከ አምስ ተርዳም›› የሚል ነው። ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ በተማሪው እንቅስቃሴ፤ ከዚያም ደግሞ በኢሕአፓና እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ማንነት በአግባቡ ሲጠቀስ የማልሰማ በመሆኑ ይህንን ለማሳየት ስል ነው። በተለይም ለሚፈጠረው ነገር ሁሉ ‹‹ ያ ትውልድ›› እየተባለ ሲረገምና ሲወቀስ ስስማ ያመኝ ስለነበር እውነታውን ማሳየት አለብኝ በሚል መነሻ ነው የፃፍኩት።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ዶክተር መላኩ፡- ኢሕአፓን በሚመለከት አሁንም ድረስ ዝም ብሎ መሠረት በሌለው ሁኔታ ስም ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድ እስማ ነበር። እናም ከዚያ ቁጭት በመነሳት ‹‹ያ ትውልድ›› የወጣበትን ማኅበረሰብና የተቀረፀበትን ትክክለኛ ማንነት የሚያንፀባርቅ ጽሑፍ ለመፃፍ ሞከርኩ። በተለይም መስፍን ወልደማርያም ‹‹ያ ከይሲ ትውልድ›› ብሎ ስለፈረጀን ከይሲ እንዳልሆንን ለማሳየት በሚል ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በጎጥ ተከፋፍላ ወጣቱ በሚያሳፍር ሁኔታ እርስ በርሱ የመበላላቱ ምክንያት እኛ አለመሆናችንን ማስገንዘብ ስለወደድኩኝ ነው። በአጠቃላይ አሁን ላይ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉ ጣት የሚቀሰርብን ሳይሆን እውነተኛ ዲሞክራሲ ከመናፈቅ ሲደረግ የነበረ ትግል እንደነበር ትውልዱ እንዲገነዘብ እና በመሠረታዊነት ተጽዕኖ እንዲፈጥር አልሜ ነው የፃፍኩት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ኢሕአፓ ያደርግ የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምንም እንኳን የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ያስከፈለ ቢሆንም ውጤታማ መሆን ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው?
ዶክተር መላኩ፡– እንግዲህ በአንድ አገር ውስጥ የሚነሳ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲዳከም ወይም ሲሸነፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። እንዲያውም በዓለም ላይ የተደረጉ አብዮታዊ እንቅስቃሴዎችን ብናይ በአብዮቱ ተሸነፉ የተባሉት ከአሸነፉት በቁጥር በጣም ይበልጣሉ። እንዳውም አሸነፉ የተባሉት በጣም ጥቂት ናቸው። የሚደረጉ የፖለቲካ ትግሎች ሁሉ ጫፍ ይደርሳሉ ማለት አይደለም። በዓለም ላይ የታየውም ይኸው ነው። መንግሥት ምንም ይሉኝታ ሳይኖረው ትግል የሚያደርጉትን ሁሉ ሊጨፈጭፍ ይችላል። በብዙ አገራት የታየ ነው። ኢራን፤ ደቡብ አሜሪካ በስፋት የታየ ነው።
ለምሳሌ አርጀንቲና ውስጥ በፖለቲካ ትግል በጣም በርካታ ሕዝብ አልቋል። ቺሊ ውስጥ የሆነውን እናውቃለን። ለምሳሌ የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የመጥፋት አደጋ አጋጥሞት ነበር። ሁለት ጊዜ በጣም ከፍተኛ የሚባል የዘር ማጥፋት ተደርጎባቸዋል። እንደገና ተደራጅተው ከ 25 ዓመት በላይ የትጥቅ ትግል አድርገው አሸንፈዋል። እናም እንዲህ አይነት ነገር የተለመደ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያም ሁኔታ እነዚህ አብዮታዊ ድርጅቶች ለምን ተከፋፋሉ? ምን ከፋፈላቸው? የሚለውንም መለያየትና በአግባቡ ማጥናት ያስፈልጋል። ይሄ ደግሞ በእኔ ግምት በጣም ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሁሉ ያ ትውልድ ከጀመረው ሥራ ጋር የተያያዘ ነው።
ስለዚህ ስለዚያ ትውልድ ያለው አስተያየት ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሆነው ነገር ሁሉ ያ ትውልድ ከጀመረው ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ይሄ ጉዳይ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ተገንዝበው ኮንፈረንስ ጠርተው ዝም ብሎ በስሜት መጮህ ሳይሆን በደንብ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ተጋብዘው ጥናታቸውን አቅርበው ሰፊ ውይይትና ክርክር ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚያ ትምህርት ሊወሰድ ይችላል። እኛም ዳግመኛ እድሉን ብናገኝ በዚያ ትውልድ ላይ የሚነሳው አጓጉል ነገር መሠረት እንደሌለው ማሳየት እንደምንችል አምናለሁ።
ግን ይሄ አይጠቅምም። ከዚያ ይልቅ ወጥ የሆነ ጠንካራ ውይይት ማድረግና የታሪክ አካል ማድረግ ያስፈልጋል። ግን ደግሞ እስከዚያም ቢሆን አስተያየት መስጠት አይቻልም እያልኩኝ አይደለም። ለምሳሌ እኔ ራሴ ያ ትውልድ ምንም ጥፋት አላጠፋም ብዬ አላምንም። እንኳን አብዮትን ያህል ነገር በአንድ ተቋም ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ሲደረግ ጥፋት ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ያንን ጥፋቱን አጉልቶ ከማሳየት ይልቅ የድርጅቱ አጠቃላይ ዓላማ ምን እንደነበር ማየት ተገቢ ነው። እንዲህ አይነት እልቂት የደረሰበት ምን ቢሆን ነው? ብሎ መጠየቅ ይገባል። በእኔ እይታ እልቂቱ ዝም ብሎ በኢሕአፓ እንቅስቃሴ ብቻ የተፈፀመ አይደለም። ደርግም ትልቅ ሚና ነበረው፡ ይህንን መካድ አይቻልም። በአጠቃላይ ነገሩን እኔ የማየው እንደዚህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እናንተ ትታገሉለት ከነበረው ዓላማ አንፃር አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ የሚመለከቷት እንዴት ነው?
ዶክተር መላኩ፡– ከእኛ ትግል ዓላማ አንፃር ካየነው ባለፉት 27 ዓመታት ተሠራ የምለው ነገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ግን ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት አንፃር ካየነው የወያኔ መሄድን ተከትሎ የመጡት ለውጦች በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ በጣም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። እርግጥ የእኛ ፍላጎት የነበረው ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆ መሠረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ለውጦች እንዲመጡ ነው። ከሁሉ አስቀድሞ ደሃው ሕዝብ፤ አርብቶ አደሩና አርሶአደሩ ኑሮውን ከፍ የሚያደርግ እና የዕለት ከዕለት ችግሮችን የሚዳስስ ሥርዓት ሊኖር ይገባል የሚል እምነት ነበረን። ነገር ግን ይሄንን ለማድረግ ገና ብዙ ዓመታትን እንደሚያስፈልግ ግልፅ ነው።
አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ገና አልተመለሰም። ይህ ሲባል ግን ከዲሞክራሲ አንፃር አስቀድሜ እንዳልኩት አንዳንድ ለውጦች መደረጋቸው ታሪካዊ ነው። ለምሳሌ የመናገር ፤ የመፃፍ መብት በተጨባጭ መረጋገጡ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደልባቸው መቋቋም እና መሥራት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ትክክለኛ ዲሞክራሲ የሚፈለግ ከሆነ ደግሞ መጀመሪያ የፖለቲካ ነፃነት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ነፃነት ሲኖር ሰዎች በነፃነት እያሰቡ፣ እየተወያዩ፣ እየተከራከሩ የተሻሉ ፖሊሲዎች ሊመጡ ይችላሉ። የፖለቲካ ነፃነት ከሌለ ውይይት ሊኖር አይችልም። በደርግም ሆነ በወያኔ ጊዜ ምንም ነገር ሊሠራ አይችልም ነበር። አሁን ላይ ጥሩ መሻሻሎች ቢመጡም ወያኔ የሚባል ነቀርሳ አላፈናፍን አለ።
በሌላ በኩል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሕዝቡ ላይ የተዘራው ከፋፋይ አስተሳሰብ ዛሬም ወደፊት እንዳንራመድ አድርጎናል። አንዳንድ ሰዎች አሁን ያለውን ችግር ብሔርተኝነት የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ለእኔ ግን ከዘረኝነትም በላይ ነው። የብሔር ጥያቄ ሲጀመር እንደችግር አሁን ሊነሳ የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም የብሔር ጭቆና አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ከተወገደ 50 ዓመት አልፎታል። ደርግ የመሬት አዋጁን ባወጀበት ጊዜ የብሔር ጭቆና አልቆለታል። ምክንያቱም የብሔር ጭቆና የኢኮኖሚ መሠረት ይጠይቃል።
እንደእኔ እምነት ኢኮኖሚ መሠረቱ ደግሞ የመሬት ስሪቱ ነው። ነፍጠኛውና ሌላው ባላባት ተንሰራፍቶ የነበረው በመሬት ስሪቱ ምክንያት ነው። በዚያ ምክንያት የብሔር ጭቆና ያካሂድ ነበር። ያ አዋጅ ያንን የጭቆና ኢኮኖሚ መሠረቱን አጥፍቶታል። ከዚያ በኋላ ነፍጠኛ የሚባል ነገር የለም። ባለመሬት የሚባል ነገር የለም። መደቡ እንዳለ ጠፍቷል። ስለዚህ የብሔር ጭቆና ከተወገደ 50 ዓመት አልፎታል። የመሬት ጥያቄም ከተመለሰ ተመሳሳይ ጊዜ አሳልፏል። አሁን ጥያቄው ሌላ ነው።
እናም አንዳንድ ሰዎች አሁን ላይ ስለብሔር ጭቆና ሲያነሱ ይገርመኛል። ይህም ችግር ዞሮ ዞሮ እዚያ ትውልድ ላይ ይለጠፋል። በመሠረቱ የብሔር ጥያቄን ያነሳው ያ ትውልድ አይደለም። የብሔር ጥያቄ የተነሳው ጣሊያን ከኢትዮጵያ እንደወጣ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ እንቅቃሴዎች ነበሩ። ለምሳሌ ልክ ጣሊያን እንደወጣ በሁለተኛው ዓመት ላይ ትግራይ ውስጥ የወያኔ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ያኔ እንኳን የተማሪ እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲም አልነበረም።
ሁለተኛው በኦጋዴን የተነሳው ችግር ነው። እሱም እንደዚያው የኦጋዴን ችግር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንግሊዞች ከኬኒያ ጀምሮ ለጉዳዩ መፍትሔ እንሰጣለን ብለው የተነሱበት ጊዜ ነበር። ያኔ የሱማሌ ወጣቶች ‹‹ሱማሌ ዩዝ›› ብለው ሱማሊያን አንድ እናደርጋለን ብለው የተነሱበት ነው። ይህም ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን ኬኒያና ጅቡቲ ውስጥ ያለውን የሱማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን የማስተሳሰር ዓላማ የያዘ ነበር። ይህንን የተማሪው እንቅስቃሴ አይደለም ያነሳው። ከዚያ በኋላ በተለይም በኤርትራ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ‹‹ኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር›› ተብሎ የተቋቋመው ድርጅትም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። ችግሩ ጎልቶ የታየው እነሱ የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ነው።
በመቀጠል ባሌ ውስጥ የኦሮሞ አርሶአደሮች አመፅ አካሄዱ። ይሄ ሁሉ ሲሆን የተማሪ እንቅስቃሴ ከነመፈጠሩ አልነበረም። ግን ደግሞ ተማሪው ይህ ጉዳይ መልስ ያስፈልገዋል፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች እኩል መሆናቸው መታወቅ አለበት በሚል አቋም ነበረው። በተጨማሪ ትግሉ ሲካሄድ የነበረው መነሻ ሁሉንም ብሔሮች በእኩልነት የሚያስተዳድር ዲሞክራሲዊ መንግስት ያስፈልጋል የሚል ነበር። በመሠረቱ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድንድ ሰዎች ምንም አይነት ጥናት ሳያካሂዱና ሳያነቡ ተነስተው ባገኙት አጋጣሚ ያሻቸውን ቅጥያ ሥያሜ ይለጥፋሉ። ይህ ደግሞ በጋዜጠኞች ይራገብና የሐሰት ውንጀላው እውነት መስሎ ይቀርባል። በአጠቃላይ ነገሩን ጠለቅ ብሎ የሚያይ የለም። ብዙ ሰው የሚጋልበው በተነሳ ነጠላ ጉዳይ ላይ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለዘላቂ አገራዊ ሰላም በሚል መንግሥት የጀመረውን የምክክር ሂደት እንዴት ያዩታል?
ዶክተር መላኩ፡- በዚህ ጉዳይ ሃሳብ ለመስጠት ትክክለኛ የሆነ መረጃ ሊኖር ይገባል። ለምሳሌ መንግሥት እንመካከር ሲል የራሱ ምክንያቶች ይኖሩታል ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም የመንግሥትን መነሻ ሃሳብ ሳይታወቅ ከመሬት ተነስቶ ትክክል ነው፤ አይደለም ለማለት ይቸግረኛል። መንግሥትም ቢሆን እንመካከርም ሆነ እንደራደር ሲል በተወሰነ መረጃ ላይ ተነስቶ እንጂ ዝም ብሎ አይመስለኝም። ለእኔ ጄኔራል አበባው በቅርቡ የሰጠው ቃለምልልስ ትንሽ አይኔን የገለጠልኝ ነው። ያንን ከሰማሽ በኋላ የመንግሥት አማራጭ ሃሳብ ብዙ አያስደንቅም። ስለዚህ ይሄ ድርድር መኖሩና አለመኖሩ በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። በዚያ ላይ ተመሥርተን ለአገራችን የሚያስፈልገውን መፍትሄ መጠቆም እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ በእርስዎ እምነት ዘላቂ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?
ዶክተር መላኩ፡- ዘላቂ መፍትሔ ለመጠቆም ነገሮችን ከመሠረቱ መፈተሽ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ለጊዜውም ቢሆን ሰላም ካልመጣ አሁን ያለው ኢኮኖሚም ሆነ አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታው አስጊ ነው። በዚያ ላይ ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ይዘን ኢኮኖሚው በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የሚፈጠረው ከባድ ነገር ነው። በአንድ ድርቅ እንኳን ቦረና ሱማሌ ክልል የሆነውን አይተናል። እንዲህ አይነት ችግሮች ያሉበት አገር ስለሆነ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት አጠያያቂ አይደለም። እናም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ሌሎች ነገሮች ላይ መሥራት ይቻላል። ለረጅም ጊዜ ጠቃሚ የሆኑ ችግሮችን መስጠት ይቻላል።
በሕወሓትና በመንግሥት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ብዙ ሰው ተጎድቷል፤ ንብረት ወድሟል። የትግራይ ሕዝብ ፈፅሞ ወያኔን እንደማይደግፍ ይታወቃል። እርግጥ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ የተወለዱና በወያኔ ስር ያደጉ ወጣቶች ሊደግፉት ይችላሉ። ነገር ግን ሌላው ኅብረተሰብ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ነው። ስለዚህ ይህንን ሕዝብ ማጣት በጣም ከባድ ነው። ከዚህ አንፃር ካየነው የትግራይን ሕዝብ የምንታደግበት መንገድ መታሰብ አለበት። እንግዲህ የሰላም አስፈላጊነት ወሳኝ የምንለው ለዚህ ነው። ሰላም ከሌለ የምንፈልገውንም ልማት ልናመጣ አንችልም።
ስለዚህ ድርድር ሲባል ሰጥቶ መቀበል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። አስተማማኝ ባልሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ሆነን የሰላሙ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን የሚል ስጋት አለኝ። ለምሳሌ የቤንዚን እጥረት ያስከተለው ችግር ትራንስፖርት ላይ ብቻ አይደለም። ሁሉም ነገር ላይ ነው። እናም ኢኮኖሚው ከሁሉም ነገር ጋር የተያያዘ በመሆኑ በጣም ምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ ሊከተን ስለሚችል ይህንን በአግባቡ ማጤን ያስፈልጋል። ደግሞም ፖለቲካ የእልህ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ ወጥቶ ምክንያታዊ መሆን ያስፈልጋል። ምክንያታዊ ለመሆን ደግሞ በጣም ትልቅ ወኔንና ጥንካሬን ይጠይቃል። ከዚህም በላይ ይህንን ውሳኔ ሕዝቡ እንዲቀበለው ማደረግ ይገባልም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረት በምን መልኩ መቀነስ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር መላኩ፡- በመጀመሪያ ደረጃ አስቀድመን ያነሳነው የአገሪቱ ፖለቲካ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለስ ያስፈልጋል። ሰላም ካልመጣ ስለሌላ ነገር ማሰብም ሆነ ማቀድ ይከብዳል። ሁለተኛው ጉዳይ አንቺ ካነሳሽው ከዋጋ ንረት መውጣት የሚቻለው በአጭር ጊዜ የሚከወን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራ ሲሠራ ነው። ለዚህ ደግሞ የችግሮቹን ሥረ-መሠረት ማጥራትና የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ያስፈልጋል። ሌላው ለረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ መሥራት ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ ለረዥም ጊዜ አቅደን መሥራት ባለመቻላችን ድንገታዊ ችግሮች ያጋጥሙናል። ስለዚህ በረጅም ጊዜ አቅደን አስተማማኝ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍና ወደ ሥራ መግባት ይገባል ባይ ነኝ።
በእኔ ግምት በደርግም ሆነ በወያኔና በብልጽግና ዘመን ያልተሰሩ ወሳኝ ሥራዎች አሉ። ስለልማት ያለው ምልከታ በራሱ ትክክል አይደለም። ኢትዮጵያ ባህላዊ አሠራር ተፅዕኖ ያሳደረባት አገር ናት። ኢኮኖሚዋ በኋላቀር የግብርና ሥርዓት ላይ የተመሠረተ ነው። ኢንደስታራላይዜሽን ገና አልተስፋፋም። ይህ ባህላዊ የኢኮኖሚ አሠራር የአርሶአደሩና የአርብቶ አደሩ ሕይወት ላይ የተመሠረተ ነው። የኢንዱስትሪ ሽግግሩ ገና አልመጣም። ዋናው ችግር ደግሞ ካፒታል አለመኖሩ ነው። እስካሁን ድረስ ካፒታል መፍጠር አልቻልንም።
ካፒታል መፍጠር ያልቻልንበት አንደኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ ባህላዊ አሠራር የሚከተሉ ዘርፎች የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ስላልሰጠናቸው ነው። ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የመሬት አዋጅ ቢታወጅም የአርሶአደሩን ሕይወት በመሠረታዊነት የሚቀይሩ ሥራዎች አልተሠሩም። በተመሳሳይ በወያኔ ዘመንም ‹‹በአርሶአደሩ ላይ የተመሠረተ የኢንዱስትሪ ልማት እናካሂዳለን›› ቢባልም ወሬ ሆኖ ቀርቷል። ምክንያቱም የአርሶአደሩ ልማት እንዴት ሊመጣ እንደሚችል ሃሳቡ አልነበራቸውም። ስለዚህ የተሳካ ነገር አልተገኘም።
በአጠቃላይ የሚያሰፈልገው አርሶአደሩ መሬት መያዝ ብቻ ነው፤ የመሬት ባለቤትነት በጣም ወሳኝ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ አርሶአደሩ ያለው መሬት የተበጣጠሰ ነው። በዚያች መሬት ላይ የሚያመርታት ምርት በጣም ትንሽ ነች። በዚህች ትንሽ ምርት ላይ ተመሥርቶ ኑሮውን ሊያሻሽል አይችልም። ስለዚህ መሬቱን ሽጦ ወደ ሌላ ንግድ ሊገባ የሚችልበት እድል ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱም ዝም ብሎ በተለመደ አካሄድ መቀጠል የለበትም። መሬት በተሸነሸ ቁጥር ደግሞ ለቤተሰብ ፍጆታ እንኳን አይበቃም። ስለዚህ እነዚህ መሠረታዊ ችግሮች ታይተው አርሶአደሩ የኑሮ መሠረቱን እንዴት ሊያሰፋ እንደሚችል መጠናት አለበት። እንደየአካባቢው ሁኔታና ችግር ተጠንቶ የአርሶደሩ ምርታማነትና ተጠቃሚነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ተጨባጭ የሆነ ምክረ ሃሳብ ይዞ መቅረብም ይገባል። አንድ አርሶአደር ብቻውን የማይችል ከሆነ በኅብረት ስራ ዩኒየን አማካኝነት ተደራጅተው ጠንካራ አቅም የሚፈጥሩበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት።
ሌላው ትልቁና እስካሁን ያልተፈታው ችግር የአርብቶ አደሩ ልማት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሕዝቡ ከድሮ ጀምሮ ‹‹ዘላን›› የሚባል ቅፅል ስም ተሰጥቷቸው ኖረዋል። ‹‹ዘላን›› ማለት ደግሞ እንደፈለገው የሚዋትት ማለት ነው። እውቀት የሌለው፤ ኋላቀር ተደርጎ ስለሚቆጠር የእነሱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በቀናነት ታይቶ አይታወቅም። ሁለተኛ እንደአገራዊ የኢኮኖሚ ምንጭ ታይቶ አይታወቅም። ግን መሬት ላይ ያለውን ነገር ብናይ ኢትዮጵያ እስከ 2004 ዓ.ም ድረስ በቀንድ ከብት ብዛት አንደኛ ነበረች።
ስለዚህ አሁን በሃብት ደረጃ ከመጣን ኢትዮጵያ ሃብት አላት የሚባለው በከብት ነው እንጂ በሰብል ምርት አይደለም። ነገር ግን የሚሳዝነው ነገር ይሄንን ያህል ሃብት ያላት አገር ሆና ሳለ የእንስሳት ሃብቱ እንደአገራዊ የገቢ ምንጭ ተደርጎ አልተቆጠረም። ይህ የሆነው ደግሞ አስቀድሜ እንዳልኩሽ በብዙዎች ዘንድ ባለው ባህላዊ አስተሳሰብ ምክንያት ነው። አሁንም አርብቶ አደሩን ለኢኮኖሚው ፋይዳ የሌለው አድርጎ የመቁጠር አስተሳሰብ በመኖሩ ይጠቅማል ተብሎ አይቆጠርም። ትልቁ ችግር ይሄ ነው። ስለዚህ ይህንን በጣም ትልቅ የኢኮኖሚ ሃብት በደንብ አይቶ አርብቶ አደሩ ራሱ ሕይወቱን እንዲለወጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም መንግሥት በጣም ሰፊ እድል ያለው በከብት እርባታ ዘርፍ ላይ መሥራት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም አርብቶ አደሩ ላለፉት 60 ዓመታት ገበያ እንዲፈጠርለት ሲማፀን ኖሯል። አሁንም ያ ጥያቄው ሳይመለስለት አራተኛ መንግሥት መጥቷል። ቀደም ባሉት ዓመታት ለወያኔ መንግሥት የሥራ ፕሮፖዛል አቅርበን ነበር። ግን ወያኔ የሚያዳምጥ መንግሥት ባለመሆኑ ሊቀበል አልቻለም። የአርብቶ አደሩም ችግር ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ መጥቷል።
ይህ ዘርፍ መንግሥት በጣም ትልቅ የኢንዱስትሪ ልማት ሊሰራበት የሚችልበት መሆኑን ተገንዝቦ ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ይህንን ስልም በመጀመሪያ ደረጃ ከብት ወደ ውጭ በስፋት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይቻላል። በተጨማሪም ስጋ በኢንዱስትሪ ደረጃ አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብም ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር ኢኮኖሚውን መደገፍ አለበት።
በነገራችን ላይ በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ሥጋ ፕሮሰስ የሚደረግበት ፋብሪካ ነበር። ሥጋ በቆርቆሮ እየታሸገ ለተለያዩ አገራት ይሸጥ ነበር። የት እንደደረሰ አይታወቅም። አሁንም ቢሆን ሃብቱ ስላለን በቆርቆሮ አሽገን ወደ ውጭ መላክ እንችላለን። ብዙ አገራት ከብት የላቸውም። ለምሳሌ አረብ አገራት ላይ ሰፊ የገበያ እድል አለን። እናም መንግሥት በዚህ ዘርፍ ውስጥ ጣልቃ ቢገባ አንደኛ ኢኮኖሚውን ያሳድጋል፤ ሁለተኛ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ስለዚህ እነዚህን ዋና ዋና ነገሮች በትኩረት ከሠራን የውጭ እርዳታና ብድር አያስፈልገንም።
የውጭ ብርድና እርዳታ የሚባል ነገር ኒዮኮሎናላይዜሽን እሳቤ ውስጣችን የሰነቀረው ነገር ነው። መሪዎቻችን ያለ ውጭ እርዳታና ብድር መኖር የምንችል አይመስላቸውም። ሁልጊዜ አበዳሪ አገራት ጋር የሚሮጡት ለዚህ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሃብት እኮ ይሄ ነው አይባልም። ለአብነት ያህልም የደን ሃብታችንን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነት ማሳደግ የምንችልበት እድል አለ። በአጠቃላይ የውጭ እርዳታ የመጠበቅን የማይረባውን ንድፈ ሃሳብ ከአዕምሯችን ውስጥ አውጥተን በእጃችን ያለው አማራጭ ላይ በትኩረት ልንሠራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ንረቱ እየተባባሰ የመጣው በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይ መሆኑ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ዶክተር መላኩ፡– በእኔ እምነት የእዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያቱ ምርታማነት ማነስ አይመስለኝም። ምክንያቱም የግብርና ውጤት የሆኑ ምርቶችን በሚካሄዱበት አካባቢ ድርቅ አልነበረም። እኔ እንደሚመስለኝ ለዋጋ ንረቱ መባባስ ዋነኛው ችግር ሙስናው የሚሰቀጥጥ ደረጃ ላይ መድረሱ ነው። አሁን ላይ እኮ ሙስና የሚጠየቀው በግላጭና ያለምንም እፍረት ነው ። እኔ በቅርቡ የቤት ካርታ ጉዳይን ይዤ ክፍለ ከተማ ሄጄ አምስት ሺ ብር አምጣና ቶሎ እንጨርስልህ ተብያለሁ። ይህ በጣም የሚያሳፍርና የሚያሳዝን ነው። ሙስና ደግሞ በዚህ ደረጃ ጨመረ ማለት የመንግሥት ሠራተኛው የአገልጋይነት ስነልቦና ምንያህል እንደዘቀጠ ያሳያል። የመንግሥት ሠራተኛው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር ምን ያህል ከሕሊናው እንደወጣችና ‹‹እኔ ብቻ›› የሚለው ነገር በዚያ ብቻ ተወስኖ እንዳለ ያሳያል።
አጠቃላይ በመንግሥት የሚደረገው የቁጥጥር ሂደት ጤናማ አይደለም። በየጊዜው ዝም ብሎ መግለጫ ይሰጣል፤ ግን ለውጥ የለም። ‹‹ይሄን ያህል ሱቆች ዘጋን ፤ ያንን ያህል ሰዎች አሰርን›› ይባላል። ግን ሥርዓቱ በጠቅላላው ስለተበላሸ መሻሻል አልቻለም። ስለዚህ በእኔ እይታ የቁጥጥር ስዓቱ መስተካከል አለበት። እናም ያንን ሥርዓት የሚዘውሩት አገልጋዮች ሐቀኛ ኢትዮጵያውያን፤ የአገር ፍቅር ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ሙስናው ደግሞ ጉቦ በመቀበል ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን ስነልቦናንም የተቆጣጠረ በመሆኑ ከዚህ አስተሳሰብ የምንወጣበት ሁነኛ መፍትሔ ማበጀት ለነገ የሚባል አይደለም። በአጠቃላይ የዋጋ ንረት የተፈጠረው ምርት በመቀነሱ ሳይሆን ብልሹ አሠራሮች በመስፋፋታቸው እና ገበያውን የመቆጣጠር አቅም ባለመፈጠሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከውጭ የሚገቡ መሠረታዊ ምርቶች ላይ ገደብ መጣል እንዳለበት ያነሳሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ዶክተር መላኩ፡– ከውጭ የሚመጣውን የመተካት ሂደት እንደስትራቴጂ ብዙ ጊዜ የታሰበበት ነገር ነው። ግን ስለፈለገን ብቻ ከውጭ የሚመጣውን ማስቀረት አንችልም። በተጨባጭ በምንወስደው እርምጃ ላይ የሚመሠረት ነው። እንደተባለው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉና ጭራሽም በውጭ ምንዛሪ ልናስመጣቸው የማይገባቸው ብዙ ሸቀጦች አሉ። ብዙ ጊዜ እኛ ራሳችን ማምረት የምንችለውን ነገር ከውጭ እናስመጣለን። ስለዚህ የውጭውን ምርት የምንተካበትን ስትራቴጂ በደንብ ማጤን ይጠይቃል። የማያስፈልጉትን ማቆም ይገባል። ራሳችን ማምረት የምንችላቸው ወሳኝ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን።
የመድኃኒትና ኮስሞቲክስ አስፈላጊነቱ እኩል አይደለም። መሽቀርቀርና ጤንነት መጠበቅ አንድ አይደለም። ነገር ግን እዚህ አገር ሁሉም የሚገቡት በእኩል ደረጃ ነው። ስለዚህ መንግሥት ለመድኃኒት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል። መድኃኒትም ቢሆን ዝም ብሎ ሁልጊዜ ከውጭ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በስፋት የሚፈልጉ መድኃኒቶችን በውስጥ አቅም ማምረት መቻል አለብን።
የአገሪቱን ፋይናንስ ሥርዓት የሚከታተሉ መንግ ሥታዊ ተቋማት በተደራጀ አግባብ ስትራቴጂ ነድፈው ወሳኝ የሚባል ለውጥ ማምጣት አለባቸው። አሁን እኛ ስላወራን ብቻ የሚመጣ ነገር የለም። የውጭውን በአገር ውስጥ የመተካቱ ወሬ ሲወራ ብቻ 70 ዓመት አልፏል። ስለዚህ በተጨባጭ መሠራት አለበት። ለምሳሌ የዘይት ችግር ብዙ ጊዜ ይነሳል። በአንድ በኩል ጎጃም ላይ በጣም ግዙፍ ኢንደስትሪ ተቋቋመ ተባለ፤ ይህ በተባለ ሶስትና አራት ወር ውስጥ ዘይት ከውጭ መግባት ጀመረ። ይሄ የሚያሳየው አለመቀናጀትን ነው። በመሆኑም በመንግሥትም ሆነ በግል ባለሃብቱ የሚሠራው ሥራ መቀናጀት አለበት። በተጨባጭ አሁን ዘይት ከውጭ ማስመጣት አለብን ወይ? የሚለው ነገር ልናጤነው ይገባል። ለምን ማምረት እንዳልቻለም መሬት ላይ ያለውን ተግዳሮት አጥንቶ መፈተሽ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር መላኩ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2014